ሽሮ ሜዳ ሁሌም በአገር ባህል አልባሳት ደምቃና አሸብርቃ ትታያለች። በተለይ የጠዋቷ ጮራ ፍንትው ብላ ወጥታ በመሸጫ ሱቆች(መደብሮች) በተዘረጉ ቁሳቁሶች ላይ ብርሃኗን ስትፈነጥቅ ላየው ሰው፤ ጻዳ የተጎናጸፈች ሙሽራ ትመስላለች። በህብረቀለም የደመቁት የባህላዊ ልብሶች ጥለት ከፀሐይዋ ብርሃን ጋር ሲዋሃድ ከአዕምሮ የማይጠፋ ልዩ ትዕይንት ይፈጥራል። መጤ (ዘመናዊ) አልባሳት ገሸሽ ተደርገው የአገር ባህል አልባሳት በነገሰባት ሽሮ ሜዳ ከመንግሥት ሰራተኛው የስራ መግቢያ ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ ሁለትና ሶስት ሰዓት ድረስ ወደ ስፍራው ላቀና ሰው በአስፓልቱ ግራና ቀኝ በተደረደሩ መሸጫ ሱቆች ለበዓላት፣ ለሰርግ፣ ለልደት፣ለቀለበት፣ ለተለያየ ፕሮግራም አልያም ለመዘነጫ በሚሆኑ የአገር ባህል አልባሳት ተሞልተው ይታያሉ። እርሶም የአገር ባህል ልብሶችን ለመሸመት ወደ ስፍራው ካቀኑ “ከየትኛው መደብር ገብቼ ብመርጥ ይሻለኛል” ብለው አይን አዋጅ እንደሚሆንብዎት አልጠራጠርም። እኔም ዛሬ ፀሃይዋ ፍንትው ስትል እግሬ በስፍራው ደርሶ የታዘብሁት ይህንኑ ሃቅ ነው። በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አንድ ሚሊዮን ዲያስፖራዎች ለገና እና ለጥምቀት በዓል ወደ አገራቸው ገብተው በዲፕሎማሲው ያስመዘገቡትን ድል በአገራቸው ከወገኖቻቸው ጋር በደስታ እንዲያከብሩ ጥሪ ማስተላለፋቸውን ተከትሎ፤ ወደ እናት አገራቸው እየተመሙ ያሉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች በዓሉን ደምቀውና ተውበው የሚውሉበት ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የአገር ባህል አልባሳት በስፋት መዘጋጀቱን በሽሮ ሜዳ የሚገኙ የባህል አልባሳት ነጋዴዎች ይናገራሉ። እኔም በአካል ተገኝቼ ይሄንኑ እውነት ታዝቤያለሁ። ሽሮሜዳ የመሲ ዲዛይን የባህል አልባሳት መሸጫ ሱቅ ባለቤት ወጣት ምህረት ባልቻ እንዳለችው፤ በኮቪድ 19 ወረርሽኝና በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ሳቢያ የባህል አልባሳት ገበያ ተቀዛቅዞ ቆይቷል። የአገር ሉአላዊነትና የህዝብ ህልውና ጥያቄ ምልክት ውስጥ በመግባቱ ህብረተሰቡ ማህበራዊ ግንኙነቱ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ስለነበር ትኩረቱ ሁሉ ሌላ ነበር። ኢኮኖሚውም ፈታኝ ነበር። በዚህም ህብረተሰቡ ፕሮግራሞችን ለማድረግ እና የቅንጦት እቃዎችን ለመግዛት ደስተኛ አልነበረም። ደስታና ፌሽታ ከሌለ ደግሞ የአገር ባህል አልባሳት ገበያ ዜሮ ነው የሚገባው። በዚህም የአገር ባህል አልባሳት ገበያው በመቀዛቀዙ ሰርቶ የቤት ኪራይና የልጆች የትምህርት ቤት ለመክፈል እንዲሁም የቤት ወጪዎችን ለመሸፈን አዳጋች አድርጎታል። እንደ ቤተሰብ አስተዳዳሪ በጣም ችግሮች ነበሩ። ነገር ግን አሁን ላይ አገሪቱ በተለያዩ ግንባሮች ባስመዘገበቻቸው ድል በተፈጠረው አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት ገበያው እየተነቃቃ ነው። በተለይ ዲያስፖራው ማህበረሰብ ወደ አገሩ ገብቶ በአገሩ ልማትና ኢኮኖሚ የበኩሉን ድርሻ እንዲጫወት እንዲሁም የአገሪቱ ችግር ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ እንዳልሆነ ለአለም ማህበረሰብ በማሳየት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አንድ ሚሊዮን ዲያስፖራዎች ለገና በዓል ወደ አገራቸው ገብተው በጦር ግንባር የተገኘውን ድል በአገራቸው ከወገኖቻቸው ጋር በደስታ እንዲያከብሩ ጥሪ አስተላልፈዋል። በዚህም ዲያስፖራው ማህበረሰብ የእናት አገሩን ጥሪ ተቀብሎ ወደ አገሩ እየተመመ በመሆኑ የገበያ አየሩ እየተነቃቃ ይገኛል። የገበያ ድባቡ ሞቅ ሞቅ ብሏል። የገበያ እድሉም እየሰፋ መምጣቱን ትናገራለች። ዲያስፖራው ማህበረሰብ ወደ እናት አገሩ እየገባ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የባህል አልባሳት ገበያው እየተነቃቃ ከመምጣቱ ባለፈ”የሚመጣ እንግዳ አለ” በሚል ተስፋ የአገር ባህል አልባሳትን በስፋት አዘጋጅተን ሰርተን እናገኛለን የሚል ተስፋ እንዳደረባት ወጣቷ ትገልጻለች። ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዲያስፖራው ማህበረሰብ ባደረጉት ጥሪ መሰረት ዲያስፖራውን በቅንነት ለማገልገል ሞራል አድሮብናል። ስለዚህ እህት ወንድሞቻችን ወደ አገራቸው ሲመጡ ይበልጥ ባህላቸውን ወጋቸውን አውቀው፣ በአገር ባህል ልብስ ደምቀውና ተውበው ለዓለም እንዲታዩና ኢትዮጵያ ሰላም መሆኗን እንዲያበስሩ ደረጃውን
የጠበቀና ጥራት ያለው የአገር ባህል ልብሶችን በስፋት አዘጋጅተናል።››ትላለች። ኢትዮጵያዊነት ማለት “አንቺ ትብሽ አንተ” ተብሎ መተሳሰብና መከባበር እንደመሆኑ መጠን ምዕራባዊያን አገራት ወይም የውጭ ዓለም በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን የተዛባ አመለካከት እንዲቀይሩና ኢትዮጵያ ሰላም መሆኗን ለዓለም ለማህበረሰብ ለማሳወቅ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ወደ አገራቸው ሲመጡ፤ አክብሮ እንኳን ደህና መጣቹህ ብሎ ከመቀበል ባሻገር እኛም በአቅማችን በፊት ይሸጥበት ከነበረው ዋጋ ቀንሰን በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶችን ከመሸጥ ባለፈ የባህል አልባሳትን ሲገዙ እንደ ስካርፕ አይነት ቀለል ያሉ እቃዎችን ስጦታ ለመስጠት ጭምር ተዘጋጅተናል።
ቅናሽ በምናደርግላቸው ገንዘብ ለተፈናቀሉና ለተቸገሩ ወገኖች እርዳታ እንዲያውሉ ከመርዳቱ ባሻገር የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል ።
ስለዚህ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እህት ወንድሞቻችን ወደ አገራቸው ሲመጡ የሁሉንም አቅምና ኪስ ባገናዘበና የሁሉንም ብሄር ብሄረሰቦች ባህልና ወግ የሚያንጸባርቁ አልባሳትን በስፋት አዘጋጅተናል ብላለች ወጣቷ። ወጣት ምህረት ዲያስፖራው ወደ አገሩ ሲመጣ በስፋት የሚገዟቸውን የአልባሳት አይነቶች ተለይተው መዘጋጀቱን ገልጻ፤ ብዙውን ጊዜ ከውጭ የሚመጡ እህትና ወንድሞቻችን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ጥለት ያለበት የባህል አልባሳትን ይወዳሉ። ስለዚህ የባህል አልባሳትን ተወዳጅ ቀለም ባላቸው ጥለቶች በማስዋብ በስፋት አዘጋጅተናል።
በተለይ ጀግኖቻችን ከውጩ አለምም እንደመምጣታቸው መጠን እነርሱን የሚመጥንና ነገ ላይ ወደ መጡበት አለም ሂደው አልባሳቱን ሲለብሱት ይበልጥ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ የሚገነቡ፣ ባህልና ወግ በደንብ የሚያንጸባርቁ፣ ልዩነታችን ውበታችን ሆኖ በአንድነት ደምቀን የምንታይበትና እነርሱን በመጡበት አገር አጉልቶ የሚያሳይ ባህላዊ አልባሳት ተዘጋጅተዋል።
ስለዚህ ዲያስፖራው ከዘመድና ከወገኑ ተለይቶ ለእንጀራ በሚንከራተትበት አገር ሁሉም ደልቶት አይኖርም። ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡትን ጥሪ ተቀብሎ እናት አገሩንና ወገኑን ብሎ የሚመጣ በመሆኑ ጥራት ያለው እቃ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ዝግጅት ተደርጓል ።
በዚህ መልኩ ሁሉም ነጋዴ ተነጋግሮ ተስማምቷል። ከዚህ ቀደም የባህል አልባሳት ከጥለት ስፋትና ከልፋቱ አንጻር ውድ ነበር። አንድ ቆንጆና ትልቅ የሚባል ጥለት ያለው የባህል ቀሚስ ከ5 እስከ 6ሺህ ብር ነው። አሁን ግን ከ4ሺህ እስከ 4 ሺህ 500 ብር ድረስ እየሸጥን ነው። እስከ 1ሺህ 500 ብር ድረስ ቅናሽ አድርገናል። ወገኖቻችን ስለመጡ ዋጋ የምንጨምርሳይሆን ይበልጥ በባህላቸው ደምቀው የሚታዩበትን አልባሳት በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብ ስራ እየተሰራ ነው። እንዲሁም መምጣት ላልቻሉ ወዳጅ ዘመዶቻቸው አልባሳቱን ገዝተው በስጦታ እንዲያበረክቱና የአገራቸውን ባህል በአለም አደባባይ ለማስተዋወቅ ይረዳቸው ዘንድ ምርቱን በተመጣጣኝ ዋጋ አቅርበናል።
ወጉን ባህሉን የሚያውቁበት ባህላዊ አልባሳት ተዘጋጅተዋል። በሌላ በኩል የአገር ባህል አልባሳትን ሊገዙ ወደ ሽሮ ሜዳ ጎራ የሚሉ ዲያስፖራዎችን ሁሉም በየባህል አልባሳት መሸጫ ሱቆች ቡና ጠጡ በማለት የምናስተናግድ ይሆናል።
በአገር ባህልና ወጉ በደንብ ለማስተናገድ ተዘጋጅተናል። ሽሮ ሜዳ ገብይተው የሚመለሱበት ብቻ ሳይሆን ከወገናቸው ጋር የሚጨዋወቱበትና የሚጠያየቁበት ነው። ወደ አገራቸው ደግመው ደጋግመው ለመምጣት እንዲጓጉና አገራቸውን እንዲናፍቁ የሚያደርግ መስተንግዶ ለማቅረብ የተቻለንን እናደርጋለን።
እንዲሁም ሁሉም አይነት ባህላዊ አልባሳት ስለሚዘጋጁ አልባሳቱ እንዴት እንደሚዘጋጁ አገር በቀል እውቀት የሚቀስሙበትና ለወደፊት በዘርፉ ኢንቨስት ለማድረግ ቢፈልጉ ወደ ስፍራው መጥተው ትምህርት መቅሰም የሚችሉበትን ልምድ ያገኛሉ ብላለች።
ከንአን የባህል አልባሳት መሸጫ ሱቅ ሲሸጡ ያገኝናቸው አቶ ፍቃዱ ክፍሌ በበኩላቸው፤ አሁን ካለው አገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ አኳያ በአገሪቱ ያለው ገበያ ተቀዛቅዟል።
አገሪቷ ላይ የተከሰተውን ችግር ተቀብለን እርስ በእርስ እየተደጋገፍን እየተጋፈጥን ነው ያለነው። ወደ ገበያው ለመመለስ ሊደረግ የሚገባውን ጥረት ሁሉ እያደረግን ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ጥሪ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው መምጣታቸው ለዘርፉ ይዞት የሚመጣው የገበያ እድል እንደተጠበቀ ሆኖ በአካል መጥተው ሽሮ ሜዳን ጎብኝተው የአገራቸውን ባህልና ወግ ማየታቸው በቂ ነው። በአካል መጥተው አይተው የወደዱትን ስለሚገዙ ወገናቸውን ይጠቅማሉ። እኛም ያለንን ነገር አዘጋጅተን እጃችንን ዘርግተን እንቀበላቸዋለን። ስለዚህ ወደ አገራቸው ሲመጡ የገበያ እድል እናገኛለን በሚል እየጠበቅን ነው። የገበያ መነቃቃቱም ጀምሯል። በኛ በኩል ዝግጅት አድርገናል።
ዲያስፖራው ወጉን ባህሉን እንዲወድ የሚያደርገውን አልባሳት አዘጋጅተን እየጠበቅን ነው። ሁሉም አይነት አልባሳት አለ። ሽሮሜዳ ብዙ አማራጭ ቀርቧል ፤ መጥተው የሚያጡት ነገር የለም። የቱን ገዝቼ የቱን ልተው በሚል አይን አዋጅ እስኪሆንባቸው ድረስ አማራጮች ተዘጋጅተዋል። የሁሉንም ማህበረሰብ ኪስ ታሳቢ ያደረገ የባህል አልባሳት በሰፊው ተዘጋጅቷል።
ወደ አገራቸው የሚመጡ ዲያስፖራ ማህበረሰብ ከየትኛውም ቦታ በተመጣጣኝ ዋጋ የባህል አልባሳትን በፈለጉት አይነት አማራጭ የሚያገኙበትን ሽሮ ሜዳን እግራቸው ሳይረግጥ እና አይናቸው ሳያይ ለመግዛት እንዳይወስኑ ላሳስብ እወዳለሁ ያሉት አቶ ፍቃዱ፤ ሁሉም ነጋዴ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቱን ለማቅረብ ተነጋግሯል። ስለዚህ ቦታው ላይ ተገኝተው ጥራቱን፣ የዋጋ ተመጣጣኝነቱንና ያሉትን አማራጮችን ማየትና ማግኘት ይችላሉ።
በጥቅሉ የዲያስፖራው መምጣት የባህል አልባሳት ገበያውን ያነቃቃል በሚል በሰፊው ዝግጅት አድርገን እንግዶቻችንን እየጠበቅን ነው ብለዋል። ሄራ ጥበብ የባህል አልባሳት መሸጫ ስትሸጥ ያገኘናት ወጣት ሔለን ብርሃኑ፤ የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ በሁሉም የገበያ ዘርፍ ጫና አሳድሯል። ነገር ግን ከሁሉም በላይ ሰላም ይቀድማል።
ችግሩ በአገር ሉአላዊነት የመጣ ስለሆነ ችግሩን ተባብሮ ለማለፍ የበኩላችን ድጋፍ ለህልውና ዘመቻው ስናደርግ ነበር። ለወደፊትም የሚጠበቅብንን ለማድረግ ወደ ኋላ አንልም። “ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ወይም ልትፈርስ ነው” በሚል ሲያሟርቱ ለነበሩ ሟርተኞች እና ኢትዮጵያ እንድትበጠበጥ ሳይታክቱ ለሚሰሩ ታሪካዊ ጠላቶቿን ሴራ ለማክሸፍና አገሪቱ የገጠማት ፈተና ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ አለመሆኑን ለአለም ማህበረሰብ ለማሳወቅ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለገና በዓል ወደ አገራቸው መግባታቸው ሰፊ የገበያ እድል ይዞልን ይመጣል የሚል ተስፋ ሰንቀን እየሰራን ነው።
ይህም ሽጠን ከምናተርፈው በላይ ነገ ልብሱን ለብሰው በዓለም አደባባይ ስለሚታዩ የአገሪቱን ባህል ከማስተዋወቅና ገጽታ ከመገንባት አኳያ የምናተርፈው ያስደስተናል ።
ይህን ታሳቢ በማድረግ ለሁሉም የእድሜ ክልልና ጾታ የሚሆኑ እና የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችን ባህልና ወግ የሚያንጸባርቁ እንዲሁም አገራዊ አንድነትን የሚያጎሉ የባህል አልባሳት በስፋት አዘጋጅተናል ።
ከውጭ የሚመጡ ወገኖቻችንን የሚመጥን፣ ባህልና እሴታቸውን የሚያንጸባርቁ ጥሩ የባህል አልባሳት አዘጋጅተን እንግዶቻችን በጉጉት እየጠበቅን ነው። የአገራቸውን ጥሪ ተቀብለው ያለ ፕሮግራም ብድግ ብለው የሚመጡ ዲያስፖራዎች ስለሚኖሩ እነዚህን ወገኖች ታሳቢ ያደረገ ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ አስቀድሞ ዝግጅት ተደርጓል።
ስለዚህ ከነበረው ዋጋ በመቀነስ እንጂ እነርሱ ይመጣሉ የሚደረግ የዋጋ ጭማሪ እንደማይኖር ይናገራሉ። ስለዚህ በአገር ባህል አልባሳት አምረው የገናንና የጥምቀት በዓላትን ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲያሳልፉ እንጋብዛለን ስትል መልዕክቷን አስተላልፋለች።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 27/2014