የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን እንደሚያስረዱት፣ ‹‹ፖለቲካ የአስተሳሰብም ልዩነት ፣ፉክክርና የሚጋጭ ፍላጎት (Conficting Interest) ባለባቸው አገራት ውስጥ ችግሮች በአንድ ፓርቲ ፣በአንድ ቡድን ወይንም በጥቂት ሰዎች አይፈቱም።ጥቂቶች በር ዘግተው ቢጨነቁና ቢጠበቡም መፍትሄ ሊሆኑና ሊያመጡም ፈፅሞ አይቻላቸውም::
በመሆኑም ልዩነቶችን ለማጥበብም ሆነ ለማስታረቅ፣ ከተናጥል ይልቅ የጋራ ውይይት ባህልና ልምድ የግድ ነው››ይላሉ:: በተለይ በግሎባላይዜሽን ዘመን ከአግላይ Exclusive Policy ይልቅ አሳታፊ Inclusive policy የግድ እንደሚልና አንደኛው ሌላውን ከሚያገል ጠባብ አስተሳሰብ ነፃ ወጥተን‹‹የጋራ ውሳኔያችን ትክክል ነው፣Divided, we Fail; United, we Stand›› በሚል መርህ ወደ 3ኛው አስተሳሰብ /Third Alternatives/ መምጣት እንደሚያስፈልግ ያሰምሩበታል::
ኢትዮጵያ በየዘመኑ የተፈጠሩና ከዘመን ዘመን እየተሸጋገሩ የመጡ ያልተጋጩ ሃሳቦች፣በይደር የቆዩ አለመግባባቶች እንዲሁም አገር ትቀጥል ዘንድ ቅድሚያ ተነፍጓቸው የቆዩ የማያግባቡ አጀንዳዎች የተሸከመች አገር ናት።
የአገሪቱ መሪዎችና የአገዛዝ ባህርይ የህዝብ መስተጋብር ደግሞ በውይይት በመቻቻል ሳይሆን፣በገዢናበተገዥነት፣በበላይናበበታችነት፣ትእዛዝ በመስጠትና መመሪያ በመቀበል፣ በአለቃና-በምንዝር፣በጌታና-በሎሌ አይነት ግንኙነት ላይ የተመሰረተ መሆኑም በርካቶችን የሚያስማማ ሃቅ ነው::
ውይይት የሞት ያህል የሚከብድበት፣በአመለካከት የሚለዩ በጠላትነት የሚፈረጁበት አገር ሆናም አመታትን አስቆጥራለች::‹‹እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ ሞቼ እገኛለሁ››እኔ የማስበው ሁሌም ትክልል ነው››የሚል የአመለካከትና የባህሪ ችግር ኢትዮጵያን ረጅም ጊዜ ሲያደማት ከርሟል:: ‹‹ችግር ካለም እኛው የስርአቱ ባለቤቶች እንናገር እንጂ ሌላው ምን ቆርጦትና ምንስ አግብቶት ነው በስርአቱ ላይ ትችት የሚሰነዝረዉ?››የሚለው ከእኔ እና ከእኛ ውጭ ላሳር አመለካከትና ተግባርም ኢትዮጵያና ህዝቦችን በሁሉ ረገድ ሊቀይሩ የሚችሉ የተለያዩ ገንቢ አስተያየቶችንና መፍትሄዎች ከስመው እንዲቀሩ አድርጓል::
አገሪቱ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት የአሳታፊነት ባህልና ልምድ የሌለባት መሆኑ ደግሞ ችግሮች በቀላሉ ፈጣን ምላሽ እንዳያገኙ፣ውስጥ ውስጡን እንዲብላሉና ከትናንት እስከ ዛሬ እንዲከተላት ምክንያት መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል::ይሁንና ከህልውና ባሻገር ስለ መፅናትና መቀጠል እንዲሁም ስለ ሁለንተናዊ እድገት ሲታሰብ ለእነዚህ ልዩነቶችና አጀንዳዎች መፍትሄ መስጠት የግድ ያስፈልጋል::
ኢትዮጵያ አንድነቷ ተረጋግጦ፣ሰላምና መረጋጋት ሰፍኖ የህዝቧን ቁሳዊና መንፈሳዊ ፍላጎት ማርካት የምትችለው በአንድ በኩል ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ሲኖራት ነው::በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ምን አይነት ቅርጽ መያዝ አለበት? ምን አይነት የዲሞክራሲ፣የፖለቲካ፣ የህግ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተቋሞች ያስፈልጉናል የሚሉ ትልልቅ አገራዊ ጥያቄዎችን ኢትዮጵያውያን ቁጭ ብለው በመወያየት በጋራ ሲመልሱ ብቻ መሆኑ እርግጥ ነው::
በተለይ ባለፉት አራት አስርት አመታት የውይይት እሳቤ በኢትዮጵያ ምድር እውን ይሆን ዘንድ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ከተለያዩ አካላት ሲነሳ ቆይቷል::‹‹ይሁን›› የሚል መልስ የሰጠ መንግሥት ግን አልነበረም::በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው መንግሥትም በአንጻሩ ይህን ታሪክ ለመለወጥ በተለይ ስለ ኢትዮጵያ ቁጭ ብሎ ለመምከር በሩን ክፍት አድርጓል::
ውይይቱ እውን ይሆን ዘንድ በሁሉ ረገድ ፈቃደኛ መሆኑን የሚያመላከቱ እርምጃዎች እየተራመዱ ይገኛሉ:: የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከቀናት በፊት ባካሄደው 2ኛ ልዩ ስብሰባው አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በአብላጫ ድምጽ አፅድቆታል::የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጅ 1265/2014 በ13 ተቃውሞ፣በአንድ ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል::የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሠ ጫፎ፣ ተጠሪነቱ ለምክር ቤቱ የሆነው ይህ ኮሚሽን ሥራውን ገለልተኛ እና ተዓማኒ እንዲሁም አካታች በሆነ መልኩ መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል።
በአገራዊ ጉዳዮች አገራዊና ተቀራራቢ አመለካከት ለመያዝ ከሚያበቁ ተቋማት አንዱ ይህ ኮሚሽን መሆኑንም አስገንዝበዋል።የሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እፀገነት መንግስቱ፣ ረቂቅ አዋጁ ለዝርዝር እይታ ከተመራበት ጊዜ አንስቶ የአዋጁን ክብደት ከግምት በማስገባት ይፋዊ የህዝብ ውይይት ሲደረግበት እንደቆየ ገልጸዋል።
የአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች በህዝብ እንደሚመረጡና ሹመታቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚጸድቅ በሰጡት መግለጫ አሳውቀዋል::‹‹የኮሚሽነሮች ጥቆማ መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያሳትፍ ሲሆን ፤ ከተጠቆሙት 14 እጩዎች መካከል 11 ተመልምለው በአፈ ጉባኤው አቅራቢነት በምክር ቤቱ የሚሾሙበት አሰራር ተዘርግቷል›› ብለዋል።
ኮሚሽነሮቹ በምክር ቤቱ ከተሰየሙበት እለት ጀምሮ ለ3 ዓመታት የሚቆይ የስራ ጊዜ እንደሚኖራቸው ተጠቁሞ፤ እንደ አስፈላጊነቱ ቆይታቸው ሊራዘም እንደሚችልም ታውቋል:: አዲስ ዘመን ጋዜጣም አገራዊ ምክክር ምን ማለት ነው?
ለአንድ አገር ሁለንተናዊ እድገትስ ምን ትርጉም ይኖረዋል?፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አገራዊ የምክክር ባህል የሌለው ለምን ይሆን፣አሁን ላይ ለማካሄድ የመታሰቡን ፋይዳስ እንዴት ታዩታላችሁ? መሰል መድረኮችንስ እንዴት መቃኘት ይገባል፣ የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ምሁራንን አነጋግሯል:: በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ሰለሞን ተፈራ፣ በአንድ አገር ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ላይ ውይይት በሳል ውሳኔን በማመንጨት፤መተማመንን በማዳበር፣ህብረትን አንድነትን ለማጠናከር እንዲሁም አሰራርን ለማሻሻል እጅግ ወሳኝ ስለመሆኑ አፅንኦት ይሰጡታል:: እንደ አቶ ሰለሞን ገለፃ፣በአንዳንድ አገራት የታዩ ሁነቶች እንደሚያሳዩት ፈፅሞ ሊቀራረቡና ሊታረቁ አይችሉም የተባሉ ሃሳቦችና ከግለሰብ አንስቶ እስከ አገራት የተቀራረቡት ከልዩነት ይልቅ በአንድነት ለጋራ አላማ የተሰለፉት በምክክር ነው::
የውይይት የመጀመሪያም፣ የመጨረሻም ግብ ሰላም አንድነትና እድገት እውን ማድረግ ነው:: ደቡብ ኮሪያ አይነት አገራት ዛሬ ላይ በብልፅግና ጎዳና የመራመዳቸው ዋነኛው ምክንያት ከአምስት አስርት አመታት በፊት ከሁሉ በላይ ለውይይት ቅድሚያ መስጠታቸው እንደሆነ የሚጠቁሙት ምሁሩ፣ከሌሎች አገራት አንፃር ሲታይም የኢትዮጵያ አብዛኞቹ ችግሮች በውይይት ፈር ሊይዙ የሚችሉ ናቸው››ይላሉ:: ምሁራን ኢትዮጵያ ውስጥ የውይይት ባህልና ልምድ ያልዳበረበትን ምክንያት ሲያስረዱ የተለያዩ አመክንዮዎችን ያስቀምጣሉ::
ይህን ጥያቄ በሚመለከት አቶ ሰለሞን በሚሰጡት ምላሽ ደግሞ ችግሩን በዋነኛነት ከስጋትና ከፍራቻ ጋር ያቆራኙታል::ለእዚህ እሳቤአቸውም ሩቅ መሄድ ሳይስፈልግ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በስልጣን በቆየባቸው አመታት የፈፀማቸው ተግባራትን ዋቢ ያደርጋሉ:: እንደ አቶ ሰለሞን ገለፃ፣ አሸባሪው ቡድን አስቀድሞ ከበረሃ ይዞት የተነሳው አጀንዳና ግብ ራሷን የቻለች ትግራይ መገንባት ነው::
ኢትዮጵያ የምትባል አገር በቡድኑ እሳቤ ውስጥ ፈፅሞ የለችም::ለቡድኑ አመራሮችም የትግራይ እንጂ የኢትዮጵያ እድገትና ልማትና ብልፅግና ግድ አይሰጣቸውም:: ይህ እንደመሆኑም በአገረ መንግሥት ግንባታውም ሆነ በአስተዳደር መዋቅር ውስጥ ለኢትዮጵያ የልዩነት ችግሮችም ሆነ ሁለንተናዊ እድገት የሚጠቅሙ ሃሳቦችን በጠረጴዛ ዙሪያ ማስቀመጥና ለውይይት ክፍት ማድረግ አይፈልግም:: በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ለይስሙላ ካልሆነ በስተቀርም ለእውነትና ስለ እውነት ምሁራንን ማሳተፍም ሆነ ሃሳብ መቀበል ፈፅሞ አይዋጥለትም::
በሁሉ ረገድ አማራጭ ሃሳቦች ዝግ መደረጋቸውም ማስተካከያና መፍትሄ ሊሰጥባቸው የሚችሉ በርካታ ጉዳዮች ተድበስብሰው እንዲቀሩ ከማድረግ ባለፈ ቡድኑ 27 አመታት ህዝብ ዘንድ ያሰረፃቸው የተሳሳቱ ትርክቶች ካለከልካይ ይበልጥ እንዲጎለምሱና እንዲሰርፅ እድል መፍጠሩን የሚያስረዱት አቶ ሰለሞን፣ችግሩም ለቡድኑ እድሜ መራዘም ከመሆን ባሻገር የንትርክና የግጭት መንስኤ እስከመሆን መድረሱንም ይጠቁማሉ::
በአሁኑ ወቅት መንግሥት ለውይይት በሩን ክፍት ማድረጉም እጅግ በጣም የሚበረታታ ስለመሆኑ አፅእኖት የሚሰጡት አቶ ሰለሞን፣አካታች አገራዊ የምክክር መድረክ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ለዘላቂ ሰላም፣ ለተሻለ የፖለቲካ ባህል ግንባታና ለሁለንተናዊ እድገት እጅግ ወሳኝ ስለመሆኑም ያሰምሩበታል::‹‹የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን መምሰል አለባት የሚለው ላይ ትልቅ አቅጣጫን ያስቀምጣል::የተረጋጋችና በኢኮኖሚ የዳበረች ዲሞክራሲያዊት አገር ለመፍጠር እጅግ ወሳኝ ነው››ይላሉ::
የተለያዩ የፖለቲካ ምሁራን አንድን ምክክር ውጤታማ ለማድረግ፣ከወገናዊነት ነፃ በመሆን ሚዛናዊ አስተሳሰብን ማራመድ፣ሁሉም እኩል የሚያሸንፍበት/ Win-Win Resolution/መንገድ መከተል፣ግልጸኝነት፣ ትእግስት፣ መደማመጥ እና የሌሎችን ሃሳብ ማክበር የግድ እንደሚል አፅንኦት ይሰጡታል:: አቶ ሰለሞን እንደሚያስረዱት ከሆነም፣በውይይት በምክክር ወቅት በሰዎች መካከል የአመለካከት ልዩነት ሊፈጠር ይችላል:: የሃሳብ ልዩነቶች ደግሞ አላማንና ግብን የማያስቱ እስከሆነ ድረስ ተፈጥሮአዊና ሰውኛ /Humanistic/ ናቸው::
የሃሳብ ልዩነቶን አቻችሎ ለመቀጠል ከሁሉም በላይ ውይይትን ውጤታማ ለማድረግ ግን በተለይ የሰጥቶ መቀበል መርህ እጅግ ወሳኝ ነው:: አገራዊ የውይይት መድረኮች ሲካሄዱ የሁሉም ጥያቄ ፈጣን መልስ ይኖረዋል ብሎ ማሰብም አግባብ እንዳልሆነና የእያንዳንዱ ውይይት መልስም የሂደት ውጤት መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ አፅንኦት የሚሰጡት አቶ ሰለሞን፣አንድን ብሄራዊ የውይይት መድረክ መገናኛ ብዙሃን የሚዘግቡበት መንገድ በራሱ በጥንቃቄና በአግባቡ ሊቃኝ ተገቢው ዝግጅት ሊደረግበት የሚገባ ስለመሆኑም ያሰምሩበታል::
አሁን ላይ ለሁሉም ችግር ነጋ ጠባ ከመነቃቀፍና ጣት ከመቀሳሰር ተላቀን ለመፍትሄው ቁጭ ብለን መወያየት መጀመር አለብን የሚሉት አቶ ሰለሞን፣ከራስ ጥቅም ይልቅ ቅድሚያውን ለአገር ማድረግ ከተቻለ መፍትሄ የሚጠፋለት አንድም ችግር እንደማይኖርና ለዚህ እጅግ ወሳኝ ታሪካዊ ሁነት ሁለንተናዊ መሳካትም ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበት አፅእኖት ሰጥተውታል::
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋዬ ዳባም፣ ሁሉን አቀፍ አገራዊ ምክክሩ እንደ ህዝብ ሳንወያይባቸው የፀደቁ የተለያዩ ሕገመንግሥታዊ ጉዳዮችን ለማሻሻል ይረዳል ነው ያሉት:: በምክክሩ በአገራዊ ጉዳዮች በተለይም በሕገመንግሥቱ፣በሉዓላዊነት ጉዳይ፣ በሰላም ጉዳይ፣ በዴሞክራሲ ስርዓት ዙሪያ ፣ በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ የማይነቃነቁ አገራዊ ምሰሶዎችን ለመትከል የሚያስችል ውይይት ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው ያመላከቱት:: ‹‹የምክክር መድረኩ ምሁራንን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ህብረተሰብ የሚያሳትፍ መድረክ እንደሚሆን ይታመናል ›› ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ አካታች አገራዊ ምክክሩም በመሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያግዝ ስለመሆኑም አስረድተዋል:: ኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ የቀድሞ የብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና አሁን የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሻዶ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ባንተይገኝ ታምራት፣ በአካታች አገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያ አትራፊ እንደምትሆን ያስረዳሉ፡‹‹ዘላቂ ሰላም በሌለበት ሁኔታ ምንም ያህል ሀብት ንብረት ማፍራት ቢቻል ዞሮ ዞሮ የሚፈየድ ነገር አይኖርም:: ስለዚህ ከብሔራዊ መግባባት አገራችን የምታተርፈው ትልቁ ነገር ሰላም ነውም››ይላሉ:: ይህንን አገራዊ ምክክር እንደሌሎች የውይይት መድረኮች ተድበስብሶ የሚቀር ሳይሆን የሚዳሰስ ውጤት ማምጣት የሚቻልበት መልክ ሊቃኝ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ::ከምንም በላይ ለብዙ ዓመታት ስንጠይቅ የመጣን ከመሆናችን አንፃር በጣም በጥንቃቄና በጥሩ ዝግጅት መካሔድ አለበት ይላሉ::ለዚህ ደግሞ እንደ አንድ ፓርቲ የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ ዝግጁ ስለመሆናቸው ያስገነዛባሉ:: በዚህ የምክክር መድረክ ላይ እነማን ሊሳተፉ ይገባል?በተለይ በሽብርተኝት የተከሰሱ ቡድኖች ሁኔታስ እንዴት ይታያል ?የሚለው የበርካቶች ጥያቄ ነው::
ይህን ጥያቄ በሚመለከት ዶክተር ባንተይገኝ ሲመልሱም፣‹‹ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀ አካል ለህግ እንጂ ለድርድር መቅረብ አለበት ብዬ አላምንም፡›› ይላሉ:: ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያዊነታቸውን መንፈግ እንዳልሆነም ይጠቁማሉ::
በሕግ አግባብ ሕጉ በሚፈቅደው የቅጣት ውሳኔ ከተወጡ በኋላ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ በሚደረጉ ምክክሮች መሳተፍ አለባቸው የሚል እምነት ያላቸው ዶክተሩ፣አሁን ባለው ሁኔታ ግን በአንድ በኩል ሽብርተኛ ተብሎ ተፈርጆ በሌላ በኩል ከሽብርተኛ ጋር ቁጭ ብለን እንደራደራለን ማለት ተገቢነት የለውም›ይላሉ:: ማን ይሳተፍ ከሚለው ባሻገርም አንዳንዶች ይህን አገራዊ ምክክር ከአሸባሪ ጋር ድርድር ለማድረግ የታሰበ አድርገው የመመልከት አዝማሚያ ይታይባቸዋል::
መንግሥት በአንፃሩ አገራዊ ምክክሩ ከአሸባሪዎች ጋር ድርድር ለማድረግ እንዳልሆነ ‹‹ይታወቅልኝ›› ብሏል:: የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ ከቀናት በፊት ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፤ አገራዊ የምክክር መድረኩ ሪፎርም ከተጀመረ ወዲህ ዘላቂ የሠላም ግንባታ ለማምጣት የታሰበ መሆኑን ጠቁመው፣በአሁኑ ወቅት አንዳንድ ግለሰቦች ጉዳዩን በደንብ ባለመረዳታቸው ከአሸባሪው ቡድን ጋር የሚደረግ ድርድር አድርገው ማሰባቸው ስህተት ነው››ብለዋል:: ምክክሩም የአገረ መንግሥት ግንባታውን ለማጠናከር እንዲሁም አገራዊ መግባባትን ለማምጣት እንደሚረዳም ነው ያስገነዘቡት::
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 26/2014