አሸባሪው ሕወሓት በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ ባደረገበት ወቅት በርካታ አሰቃቂና ዘግናኝ ግፎች ሲፈፀሙ እንደነበር በተለያዩ ሚዲያዎች ሲዘግቡ ቆይተዋል። ከጤና ተቋማት ጀምሮ የንብረት መውደም፣ ዘረፋ፣ የጅምላ ግድያና አስገድዶ መድፈር ከዘገቧቸው ውስጥ ይጠቀሳሉ።
አፈፃፀማቸው ምንም ያህል የከፋ ቢሆንም ሰፊ ሽፋን አግኝተው በመዘገባቸውና ለዓለም ህዝብ ግልፅ መውጣታቸው ጥሩ እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል።
የሴቶች ጉዳይ በመገናኛ ብዙሃን ጉልህ ሽፋን የማግኘቱ ሁኔታ በተቋማቱ የተሻለ አሰራር መኖሩንም ያመላከተ ነው። የስነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚሉት እንደ አገር አሸባሪው ቡድን በሴቶች ላይ ያደረሰውን ጥቃት ለማሳየትና የአሸባሪውን ቡድን ማንነትም ለዓለም ሕዝብ ለማሳወቅ ረድቷል።
የችግሩ ሰለባዎችም ጉዳታቸውን ለሌሎች በማካፈላቸው እንዲረጋጉና እፎይታን እንዲያገኙ አስችሏል። በተጎጂዎች በኩል ጥቃቱን ለመግለጽ የነበራቸውን ስጋት ቀርፏል። በወሲባዊ ጥቃቱ ለሚያጋጥማቸው የአንጎል ውስጥ የደም ዝውውር ችግር፤ በዚያም ሳቢያ ለሚገጥማቸው የመርሳት «ዲሜንሲያ» በሽታና የስነ ልቦና ችግሮች ፈጥነው ሕክምና እንዲያገኙ፤ ከማድረግ አንፃር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንዲሰሩ አስችሏል።
በቅርቡ የኢትዮጵያ ሴት ጋዜጠኞች ማህበር ለ10ኛ ጊዜ ያዘጋጀው የውይይት መድረክም በዚሁ ዙሪያ ያተኮረ ነበር።
በመድረኩ ጥቃቶቹ መዘገባቸው ከስነ ልቦናና ከሌሎች የጤና ችግሮች ፈጥነው እንዲወጡ ያለው ፋይዳ፣ አሁን ላይ እየተዘገቡ ያሉበት ሂደት፣ እንዴት መዘገብ እንዳለባቸው፣ በዘገባ ወቅት ለተጠቂዎቹ መቅረብ ስለሚገባቸው ጥያቄዎች፣ የዘጋቢዋ/ው አቀራረብ ምን መምሰል እንዳለበት፣ በተጎጂዋ ማህበራዊ ግንኙነትና ስነ ልቦና ላይ ሊያሳድር የሚችለው አወንታዊና ይሁንታዊ ተፅዕኖዎች ተነስተው ነበር።
ውይይቱን የቃኘንበትንና በውይይቱ የተሳተፉ የማህበሩ አባላትና ሌሎች ተሳታፊ ሴቶችን ያነጋገርንበትን ጽሑፍ ለዛሬ ልናስነብባችሁ ወድደናል። አስቀድመን ያነጋገርናት ጋዜጠኛ የሸዋ ማስረሻ ትባላለች።
በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የዜናና ፕሮግራም አርታይ ክፍል ረዳት አዘጋጅ ነች። የሴት ጋዜጠኞች ማህበር አባል ስትሆን በዕለቱ የተሳተፈችው የውይይት መድረኩን በመምራት ጭምር ነበር። ውይይቱ በሴቶች ጥቃት አዘጋገብ ላይ ማተኮሩን እንደወደደችው ገልፃ በጦርነት ግጭት ወቅት በተለየ መልኩ ተጠቂ የሚሆኑት ሴቶችና ህፃናት ከመሆናቸው አንፃር ወቅታዊና አስፈላጊም ነው ብላለች።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የስነ ልቦና የሰብዓዊ መብትን ጨምሮ የተለያዩ ባለሙያዎችን ማካተቱ አንድም በዘገባው ዙሪያ ተጨማሪ ዕውቀት እንድታገኝ አድርጓታል። በተጎጂዎቹ የወደፊት ሕይወት ላይ የሚያመጣውን አሉታዊ ተፅዕኖም ከወዲሁ ማስቀረት ያስችላል ብላ ታስባለች።
የሸዋ አሁን ላይ በየመገናኛ ብዙኃኑ ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ወሲባዊም ሆነ አካላዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችን የተመለከተ ዘገባ የሚዘገብበትንም ሆነ ለተደራሲያኑ የሚቀርብበትን ሂደት ታዝባለች። ብዙዎቹ ጥንቃቄ የተሞላባቸው ናቸው። የተጎጂዎቹን ማንነት የመደበቁ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶታል። ሙያዊ ስነምግባር ያሟሉም ቢሆን የሚቀር መኖሩን ታዝባለች። ተጎጂዎቹ የሚናገሩትን በሙሉ ማቅረብ ይታያል። አሁን ላይ ተጎጂዎቹ ጥቃቱ ስላቆሰላቸው፣ መናገር ግድ ስለሚመስላቸውና መተንፈሱ ለጊዜውም ቢሆን ስለሚያረጋጋቸው ስሜታዊ ሆነው ነው የሚናገሩት። የሆኑትን ሁሉ አይደብቁም። በጦርነቱ የደረሰባቸውን ጥቃት፣ የወደመባቸው ንብረት ማውራታቸው፣ ወንዶች ከሚያወሩት የተለየ ባለመሆኑ ችግር የለውም። ከጾታዊ ጥቃት ጋር ተያይዞ የሚያወሩት ግን ይለያል። ነገ በፍቅር ግንኙነታቸው፣ በማህበራዊ ሕይወታቸው፣ በቤተሰባቸው ላይ የሚያሳድርባቸው ተፅዕኖ ይኖራል። ጦርነቱ ጋብ ሲል ሁኔታዎች ሲረጋጉ በዙሪያቸው ያለው ማህበረሰብ እንዲህ የሆነችው በማለት መጠቋቋሚያ እንደሚያደርጋቸው ጥርጥር የለውም። ሆኖም አንዳንዶቹ ዘገባዎቻችን ይሄን ያገናዘቡ አይደሉም።
ትኩረት ያደረጉት ጥቃቱን ማሳየት ላይ ብቻ ነው። ማንነት መደበቁን ዘንግተውታል ትላለች። ጋዜጠኛዋ በዚህ ጊዜ ውስጥ ተጎጂዎቹ ቆም ብለው ስለደረሰባቸው ጥቃት፣ ከጥቃቱ በኋላ በማህበረሰብ ውስጥ ስለሚኖራቸው ሚና፣ ስለ ፍቅርና ሌሎች ግንኙነቶቻቸው ሊያስቡ ይችላሉ። ይሄኔ ማንነታቸው መታወቁ ሊጎዳቸው ይችላል። ተጎጂዎቹ ላይ ጥቃቱ ካመጣባቸው በተጨማሪ ሳናስበው አዘጋገባችን የሚያቀጣጥለው ነገር ሊኖር እንደሚችል ትጠቅሳለች።
‹‹እንኳን ጦርነት ውስጥ ያለና ጥቃት የደረሰበት ሰው ወሬውን የሰማ እንኳን ይጨነቃል›› የምትለው የሸዋ ይሄን ጭንቀት የሚያባብሱ ጥያቄዎችን ለተጎጂዋ ማቅረብ ከሙያም ሆነ ከሰብዓዊነት አኳያ አግባብ አለመሆኑንም ትመክራለች።
ጉዳቱ የሚያደርሰውን የስነ ልቦና ጫና እንደሚያከብደውም ትናገራለች። የደረሰባቸውን ችግር ማሳየቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ተጎጂዎቹን በሚያግዙ፣ በሚያፅናኑና ጥንካሬና ብርታት በማግኘት ቀጣይ ሕይወታቸውን መኖር እንዳለባቸው የሚያመላክቱ አቀራረቦችን መጠቀምና ዘገባቸውን መሥራት ይመረጣል ትላለች። በአዲስ ማለዳ መጽሔት ዋና አዘጋጅ የሆነችው ሌላዋ የውይይቱ ተሳታፊ ሊዲያ ተስፋዬም ሃሳቡን ትጋራዋለች።
በብዙ መገናኛ ብዙኃኖች ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ታሪክ ምስላቸው እንዳይታይ፣ ግማሽ ፊታቸው እየተሸፈነ፣ ስማቸውም ሳይገለጽ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ እየተዘገበ መሆን እንዳለበት ትስማማለች።
እሷ ያለችበትን መገናኛ ብዙኃን አብነት አድርጋም እንደገለፀችው በአዲስ ማለዳ ታሪካቸውን ከተናገሩ በኋላ ስማችን ይገለፅ፣ ፎቷችን ይውጣ በሚለው ጉዳይ ፈቃደኛ ሆነው በእርግጠኝነት መስማማታቸው አስፈላጊ ቢሆንም የሚያስከትለው ማህበራዊ ተፅዕኖ በተደጋጋሚ ጥያቄ ውስጥ ይጥላል።
ማንነትን በመደበቁም ሆነ ስም በመለወጥ መስራት ይቻላል ነገር ግን በምን መልኩ ታሪካቸው ይነገር የሚለው ላይ በህትመት ዘርፉ የሚቀር እንዳለም ጋዜጠኛ ሊዲያ አልሸሸገችም። ‹‹ዘገባዎች እንዴት መሰራት አለባቸው፣ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ታሪክ በምን መንገድ መቅረብ አለበት የሚለው ጥንቃቄ ይፈልጋል›› የምትለው ሊዲያ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች መደረግ የሚገባውን ጥንቃቄ በወንጀል ሕጉ በአስገድዶ መድፈር ለተሳተፉ እስረኞች ከተሰጠውና ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ ወንጀለኛ ከማያስብለው የሕግ ከለላ ጋር ታመሳስለዋለች። ፍርድ ጨርሰው ሲወጡም ወንጀለኛ ብሎ መጥራት ሕብረተሰቡን በሚቀላቀሉበት ጊዜ መገለል ስለሚያደርስባቸው መከልከሉንም ትጠቅሳለች።
ወሲባዊና አካላዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ታሪክ በዚህ መልክ ተቃኝቶ መዘገብ እንደሚገባው በመጥቀስ ሃሳቧን ታሳርጋለች። ‹‹ተጎጂ ሴቶችም አሁን ላይ ከገቡበት ቀውስ አንፃር ሳይደብቁ የደረሰባቸውን ጥቃት ለጋዜጠኞች ሊነግሩ ይችላሉ›› ስትል አስተያየቷን የጀመረችልን የሰብዓዊ መብቶች ላይ የምትሰራውና የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት አክሊል ሰለሞን ነች።
አክሊል ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ያለባለሙያ ድጋፍ ታሪካቸውን እየደጋገሙ እንዲናገሩ የማድረግ፣ ሲያለቅሱ አይናቸውን አቅርቦ የማሳየትና ሀዘኔታን እንዲያገኙ የማድረግ ዓይነት አዘጋገብ በአንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ማየቷን በትዝብት ትጠቅሳለች። ይህ ጉዳትን ማሳየት ቢያስችልም ምን አልባት ሴቶቹ ላይ መልሶ ጥቃት እንዳይደርስባቸው ትሰጋለች፤ በመሆኑም ዘገባዎች ሴቶችን ድጋሚ ለጥቃት የሚጋለጡበት ሁኔታ እንዳያስከትልም ትመክራለች። ‹‹የተጎጂዎቹን ታሪክ መዘገቡና የሆኑትን ማሳወቁ አስፈላጊ ነው›› የምትለው የህግ ባለሙያዋ የሚዘገብበትና ታሪካቸው የሚቀርብበት መንገድ ከጥቃቱ በኋላ ዋጋ እንደሌላቸው አድርጎ የማቅረብ ዕድምታ ዓይነት ስላለው ወደፊት ለሚኖራቸው ማህበራዊ ግንኙነቶችም ሆነ ለቆሰለው ስነ ልቦናቸው መልካም ባለመሆኑ ሊስተካከል እንደሚገባው ታወሳለች። በውይይቱ ወቅት ሙያዊ ተሞክሮውን ለተሳታፊዎች ያካፈለው የእርቅ ማዕድ ኮሚኒኬሽንና ሚዲያ አዘጋጅና አቅራቢ ዓለምሰገድ ታደሰ በሴቶች ጥቃት ዙሪያ የሚሰሩ ዘገባዎች የተጎጂዋን ቀጣይ ማሕበራዊ ሕይወት ታሳቢ ማድረግ እንዳለባቸው ይመክራል። በሥራው የገጠመውን ተሞክሮ ዋቢ በማድረግም አንዳንዴ የሆኑትን ለጋዜጠኛ ካወሩ በኋላ “ምን ሆኜ ነው የተናገርኩት?” የሚሉበት ሁኔታም እንዳጋጠመው አጫውቶናል። ተጎጂዎች እንዲህ ታሪካቸውን የሚነግሩን የደረሰባቸውን ችግር በአስጨነቃቸውና ገፋፍቶ ስሜታዊ ባደረጋቸው ወቅትና ሁኔታ ውስጥ ሆነው ሊሆን ስለሚችል የተጎጂዎቹን ታሪክ ከመዘገባችን በፊት የግድ እስኪረጋጉ መጠበቅ እንደሚያስፈልግም አስገንዝቧል። ዘገባው የባለሙያ እገዛ ካገኙ በኋላ ቢሆን የተሻለ እንደሚሆንም ይጠቁማል። ባለሙያው የሆኑትን ነገር እንዲያምኑና ስለሆኑት ነገር በመናገራቸው በመፀፀት መልሰው እራሳቸውን እንዳይወቅሱም በቂ እገዛ ስለሚያደርግላቸው ዘገባውን የተሳካ ያደርገዋል ይላል። በዚሁ በሴቶች ላይ በሚደርስ ወሲባዊና አካላዊ ጥቃት ዙሪያ ያነጋገርናቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአእምሮ ሕክምና ትምህርት ክፍል ውስጥ የካወንስሊንግ ሳይኮሎጂ ባለሙያና የስነ ልቦና ሕክምና ባለሙያ ሄኖክ ኃይሉ ሙያዊ ሃሳባቸው መነሻ ከጋዜጠኛ ዓለምሰገድ ጋር ተመሳሳይነት አለው። እንደ ባለሙያው ከዘገባው በፊት ተጎጂዎቹ ከደረሰባቸው የስነ ልቦና ጫና መውጣትና ሙሉ በሙሉ በራሳቸው በመተማመን ታሪካቸውን መናገር የሚያስችላቸው መሆኑን ለመረዳት የስነልቦና ባለሙያ ቢያገኛቸው ይመክራል። ‹‹ያም ሆነ ይህ እንዲህ ዓይነት ጥቃት ደርሶብኛል እንዲህ ተደርጌያለሁ ብለው ለዘጋቢው ማውራታቸው በተወሰነ መልኩም ቢሆን ለስነ ልቦና የሚጠቅመው አለ›› ሄኖክ ይላል። የስነልቦና ባለሙያው እንዳከሉት ስለደረሰባቸው ጉዳይ ማውራትና ለሌላ ሰው ማጋራት በራሱ የሚፈጥረው የስነ ልቦና መረጋጋት አለ። በዚሁ ልክ ደግሞ ሴቶቹ ታሪካቸውን ለዘጋቢው የሚነግሩት ባልተዘጋጁበትና ከደረሰባቸው የስነ ልቦና ጫና በፍጥነት ሊወጡ ባልቻሉበትና ራሳቸውን ባላወቁበት ሁኔታ ሊሆን ስለሚችል የተወሰነ ጥንቃቄ ሊፈልግ እንደሚችልም ሄኖክ ይጠቁማል። ‹‹መገናኛ ብዙኃን ላይ የተጎጂዎቹ ታሪክ በሚዘገብበት ወቅት ከስምና ከአለባበስ ጀምሮ የተጎጂዎቹን ማንነት ለመደበቅ የሚደረገውን ጥረት አይቻለሁ›› የሚለው ሄኖክ ነገር ግን ይህ በቂ ነው ብለው እንደማያምኑ ይገልፃል። ምክንያቱም በኤሌክትሮኒክስም ሆነ በህትመት ዘርፍ የሰዎቹ ድምፅ፣ የሰዎቹን ሁኔታና አለባበሳቸውን የሚያውቁ የአካባቢው ሰዎች ማንነታቸውን በቀላሉ ሊለዩ የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩን ይጠቁማል። ይሄ ክፍተት ወደፊት ለመገለል፣ መጠቋቆሚያ ለመሆንና ለሌሎች ሰለባዎች በመዳረግ በማህበራዊ ግንኙነታቸው ላይ ጫና እንዳይፈጥርባቸው መገናኛ ብዙኃኖች መጠንቀቅ እንደሚገባቸውም ይመክራል። በተለይ እንዲህ ተደርጌያለሁ እያሏቸው ላሉ ሴቶች የት ነበርሽ፣ ለመከላከል ምን እርምጃ ወሰድሽ፣ ለምን ለመጮህ አትሞክሪም ነበር የሚሉ ጥያቄዎችን በማቅረብ ስነ ልቦናቸው የበለጠ እንዲጎዳ ማድረግና ታሪካቸውን በመናገራቸው የበለጠ እንዲፀፀቱ ማድረግ እንደማይገባቸውም ያስጠነቅቃል። ‹‹የስነ ልቦና ችግር መገለጫዎች ቀስ በቀስ እንጂ በአንድ ጊዜ የሚመጡ አይደሉም›› የሚለው ሄኖክ ምንም ዓይነት የማረጋጋት ሥራ በማይሰራበት ሁኔታ መረጃ ለማግኘት በሚል ሰበብ ጥያቄዎችን ማጅጎድጎድና በጉትጎታና በስሜት ከተናገሩ በኋላ የሚፀፀቱበት ሁኔታ እንዲኖር ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ ያሳስባሉ። እንደ ሄኖክ ገለፃ ከሆነ የሴቷ ጥቃት ችግር አንዴ የስነ ልቦና ባለሙያ አይቷታል ተብሎ ተዘግቶ የሚኬድ አይደለም። መጠኑም ሰፊ ነው። በቅርብ እንደወጣው ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት መረጃ በዓለም ዙሪያ ከ736 ሚሊዮን በላይ ሴቶች በማያውቁት ወይም በቅርብ ሰው በሕይወታቸው ውስጥ ቢያንስ አንድ ጊዜ ወሲባዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል። ይሄ ማለት 30 በመቶ የሚሆኑት ከ15 ዓመት ዕድሜ በላይ የሆኑ ሴቶች የዚህ ጥቃት ሰለባ ይሆናሉ ማለት ነው። ያም ሆኖ 40 በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው ሙያዊ ምክርና እርዳታ የሚያገኙት። ወሲባዊ ጥቃቶች ሴቶችን ለመርሳት በሽታ፣ ለሀፍረት፣ ለመሸማቀቅ፣ ለስሜት መረበሽ፣ ለድብርትና ሌሎች የስነ-ልቦና ቀውሶች ይዳርጓቸዋል። በመሆኑም በሴቶችና ልጃገረዶች ላይ ወሲባዊና አካላዊ ጥቃቶች የሚያደርሱትን ጫና ለመቀነስ ለረጅም ጊዜ ተከታትሎ ሕክምና መስጠት ሙያዊ ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል። በጥቃቱ የደረሰውን ጫና ለመቀነስ የስነ አእምሮና ስነ ልቦና ባለሙያዎች ከሐይማኖቸት አባቶች ጋር በመቀናጀት መሥራት ይኖርባቸዋል። የሚዲያ ባለሙያዎችም በዘገባ ስራቸው ወሲባዊና አካላዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች የመርዳትና የማረጋጋት ሥራም ጭምር መሥራት ይኖርባቸዋል በማለት ጽሑፋችንን ደመደምን።
ሠላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 26/2014