ዓለም በስሜት ሳይሆን በስሌት የሚጓዙባት መድረክ ናት። ኢትዮጵያም በስሌት መጓዝ ግድ የሚላት ወቅት ላይ ናት። በእርግጥም የጠቢባን አገር የሆነችው ይህቺ ታላቅ አገር የቀረቡዋትን መሰክሎች ሁሉ በጥበብ እያለፈች ዛሬ ላይ ተገኝታለች። በተለይ ዛሬ ላይ ከፍትዋ የተደቀኑ መሰናክሎች በጣጥሶ ለማለፍ ህልውናዋ የሚገዳደሩ አደጋዎችን ለማራቅ ከፍተኛ ትግል እያደረገች ያለችበት ወቅት ነው። የገጠማትን ፈተና ለማለፍ ብልሀት ጠላቶችዋን ለመርታት ማስላት ይጠበቅባታል።
ከምንጊዜውም በተለይ የምዕራባዊያን አይን ኢትዮጵያ ላይ አርፏል። አይኖቻቸው ወደኛ የሚያማትሩት የአገሪቱን መልካም ተመኝተው አይደለም። ያነጣጠሩት የኢትዮጵያዊያንን ለውጥና ዕድገት ተመኝተውም አይደለም። ይልቁንም እኛ እንደፈለግን በምናሾራት ዓለም ውስጥ ሉዓላዊነቴን አሳልፌ ለእናንተ አልሰጥም እንቢኝ ማለትዋ አስቆጭቷቸው እንጂ። በእብሪት በሚመርዋት ዓለም እኛን ተዳፍሮማ ሰላም መሆን የለም የሚል እልህ ውስጥ ገብተው ሊያተራምሱን በማሴር ላይ ይገኛሉ።
ይሄኔ ነው ከበፊቱ በተለየ ጥበብ የሚያሻን፤ በዚህ ወቅት ነው ከፊታችን ያዘጋጁልንን ወጥመድ ሁሉ በጥበብ በጣጥሰን የምንግዜም አሸናፊነታችን ለዓለም ማወጅ የሚገባን። በዚህ ወቅት ነው ከስሜት የነፃ ውሳኔ ላይ መድረስ፤ በስሌት የተቀመረ እርምጃ መውሰድ የሚገባን። ረጋ ብሎ አዋጭ የሆነን ዘላቂ መፍትሄ አስቀምጦ በእቅድ መመራት ለስኬት ያቃርባልና።
እኛ ብቻ አዛዥ እንሁን ከኛ ወዲ ለዓለም የሚበጅ ማንም ሊመክር አይገባም ባዮቹ ምዕራባዊያን የኢትዮጵያ ህዝብ አልበገር ባይነት አብሽቆዋቸዋል። አንድ ሆኖ ለአገሩ መቆሙ አስቆጭቷቸዋል። ዓለም ሁሉንም የዓለም ህዝብ የሚወክል መድረክ መሆኑን ሆን ብለው የዘነጉትና እብሪት የወረሳቸው እነዚህ አካላት ዓለም ማለት ምዕራብም፣ ምስራቅም፣ ሰሜንና ደቡብ እንጂ ምዕራብ ብቻ አይደለም መባሉ ያስኮርፋቸዋል። ኢትዮጵያ ያኮርፍዋት ስለራሴ እኔው አውቃለሁ ማለትዋ ነው። ኢትዮጵያን የሚዘምቱባት ሉዓላዊነቴ ላይ አልደራደርም ማለትዋ ነው።
በእኛ ላይ የተቆጡት በክብራችን ባለመደራደራችን፤ ለትዕዛዛቸው ባለመገዛታችን መሆኑ እውነት ነው። እንደ ኢራን፣ ሶሪያና ሊቢያ በቀላሉ እናፈራርሳቸዋለን ብለው የሰሩት ስራ መምከኑ ማመን አይፈልጉም። ሲነኩን እንደ አለት መጠንከራችን ሊበትኑን ሲሰሩ መሰባሰባችን ሲያዩ እልህ ውስጥ ከቷቸዋል። እጅ መጠምዘዝ እንችላለን ያሉት ሳይሳካላቸው መምከኑ አብግኗቸዋል።
የእነሱ ፈረስ የሆነው አሸባሪው ቡድን ከእኩይ ዓላማው ተላቆ አያውቅምና የተቀዳጀንበት ታላቁ ድላችን እሱና አጋሮቹ በወጠኑት ሴራ ሰተት ብለን እዳንገባ ማስላት ይገባናል። የምንለው ለዚህ ነው። ትግራይ ላይ ያለው ሰቆቃ በእዚያ ህዝብ ላይ የሆነው ሁሉ ዋንኛ ባለቤት አሸባሪው ሕወሓት ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያ ጀግና ሰራዊት ማጠልሸት ኢትዮጵያዊያን ለማንተብ ያጠመዱት ወጥመድ ውስጥ መውደቅ ፈፅሞ አይገባምና የወደፊት ጉዟችንን ቆም ብለን በማሰብ ሊሆን ይገባል መባሉ ትክክለኛነት ነው።
ሰሞኑን መንግስት የኢትዮጵያን ሰራዊት ከሰሜን ወሎ ዞን ጠራርጎ ካባረረ በኋላ ሰራዊቱ አሸባሪው ቡድን ደግሞ ጥቃት አንዳይከፍት መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ ባለበት እንዲፀና ትዕዛዝ መተላፉን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ ከርመዋል። በእርግጥ በጀግናው ሰራዊታችን አከርካሪው የተሰበረው ሕወሓት ድል አድርጎ ዛሬ ላይ በእጁ ያሉ የትግራይ ክልል አካባቢዎች መቆጣጠር የሚችል አስተማማኝ አቅምም ሞራልም እንዳለው ባይካድም ባለበት ቦታ ፀንቶ ለዚጌው እንዲቆይ መወሰኑ ሁለንተናዊ አሸናፊነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ውሳኔ አድርጌ ወስጄዋለሁ።
መንግስት በሰጠው መግለጫ ለዚህ ውሳኔ ያበቃው ምንያቶችን አስቀምጦ የኢትዮጵያ አሸናፊነት ለማረጋገጥ የሚያስችለውን ውሳኔ መሆኑን ገልፃል። በተለይም እኔ የፅሁፌ ዋንኛ ነጥብ የሆነው የጠላት ሴራን ለማክሸፍ የሚያስችል ውሳኔ መሆኑ ላይ ነው። ነገር ግን አንዳንድ ወገኖች የመንግስት ውሳኔን አላስደሰታቸውም። አሸባሪው ቡድን በወረራቸው አካባቢዎች በህዝብ ላይ ያደረሰው ግፍ በደልና ሰቆቃ አስቆጭቷቸው የእርሱ ኢትዮጵያ ምድር ላይ መቆየት አስቆጭቷቸው ነው።
በእርግጥም የወያኔ መክሰም እርግጥ ነው። እርሱን ለማክሰም ግን የሚከፈለው መስዋዕትነት መቀንስና በተጠና መልክ ማድረግ እርምጃዎች ሁሉ በተሰላ መልክ መከወን ግድ ይላል። ስራ ግብሩ ተንኮል ልማዱ የሆነው ወያኔ ለእኛ የሚወጥናቸው ሴራዎች ቀድሞ ተረድቶ እነዚያን ሴራዎች በጣጥሶ እርሱን ወደተመኘው ሲዖል የመላኩ ተግባር ጥበብ በተሞላበት መንገድ መከወን ይገባል።
ወያኔ ከደቡብ ወሎና ከሰሜን ወሎ እንዲሁም አፋር አካባቢዎች በጀግኖች ኢትዮጵያውያን ተቀጥቅጦ ሲወጣ ሰብስቦ የወሰዳቸው አስክሬኖች የጅምላ ጭፍጨፋ ተደርጓል የሚል ድራማ ሰርቶ በድጋሚ ይህችን አገር ለማሳጣት ማሴሩ አንዱ ወጥመድ ነው። ለዚህ ደግ የምዕራባውያን ጋሻ ጃግሬነት ለእሱ እገዛ ያደርግለታል። ወትሮም ሲረዱት የነበሩት እሱና በእነሱ ምክር የተሸረበው ሴራ እኛ ዘው ብለን ስንገባ ጥሩ መሸፈኛ ያደርጉና ተባብረው ይረባረቡብን ዘንድ መንገድ ያገኛሉ።
ወያኔ አንዴ እራሱ የቀበራቸው የጅምላ መቃብሮች እያሳየ ጅምላ ጭፍጨፋ ተካሄደ ማለቱ በቂያቸው ነው። እነሱም የሚፈልጉት ትንሽ እውነት የሚመስል ማታለያ ብቻ ነውና ለጩኸታቸው መነሻ ያገኛሉ። ድራማው የእውነት ያህል ተደርሶ ይተወንና ጩኸት በተጠና መልክ ይቀልጣል። በእነሱ ስለነሱ ጥቅም የሚሰሩት አጋዥ የሆኑ ሚዲያዎቻቸው ያስተጋቡታል። ተከፋይ የሆኑ አክቲቪስትና ጥቅመኛ የሆኑ ድጅቶች ያጓሩለታል።
ከዚያም እንዚህ ቀደሙ ኢትዮጵያ እውነትዋ ይቀበራል። ያለ ፍትህ ትብጠለጠላለች። በታላቅ መስዋዕትነት የተጎናፀፈቸው አሸናፊነት በረከሰ ምግባራቸው ያለዝቡታል። አሸባሪው ቡድን በጦር ሜዳ ያጣውን ድል በደጋፊዎቹ ጩኸት ሀሰትን እውነት በሚያስመስለው ትርክታቸው መልሶ ነፍስ ይዘራል። ምዕራባዊያን ሰብዓዊ መብት በሚል ሽፋን እጃቸውን ለመስደድ ይቃጣሉ። የሚፈለልጉት ሰበብ ተሳክቷልና በማታለያ ሽፋናቸው ተከልለው ሰብዓዊነት ተገረሰሰ ወንጀል በረከተ የሚል ጩኸታቸው ይበረታል።
ለዚህ ነው ከሴራቸው መጠበቅ የሚያስፈልገው፤ ለዚህም ነው የተጠና አካሄድ መሄድ የሚያሻው። ዘርፈ ብዙ ዘመቻ ተከፍቶብናል። በተለያየ መልኩ እኛን ለማዳከም አሸባሪዎቹን በግልፅ እስከመርዳት ድረስ ደርሰዋል። ምክንያቶችን አጥፍተን ካላስቆምናቸው በስተቀር ቀድመናቸው እየተገኘን የሚያሴሩትን ማክሸፍ ይገባል።
ጦሩ ወደ ትግራይ መግባቱን ገታ እንዲያደርግ መንግስት መወሰኑን የሰሙት አሸባሪው ሕወሓትና ጋሻ ጃግሬዎቹ ቀድመው በተሸናፊነት ስሜት የወጠኑት እየከሸፈባቸው መሆኑን ሲያውቁ ያሉትና ያደረጉት ብቻ በማየት መረዳት ይቻላል። ምን አስበውል እንደነበር ከሁኔታቸው ማወቅ ቀላል ነው። ቀድማ ጠላቶችዋ ያዘጋጁላትን ወጥመድ የገባት አይጥ የጠላቶችዋን ስራ አልጠፋትምና ማምለጫ አዘጋጅታ ሲጠግዋት “እኛ አውቀናል ጉድጓድ ምሰናል” እንዳለችው አይነት ነው ነገሩ።
የመንግስት ውሳኔ አገር ላይ የሚጋረጠውን ትልቅ አደጋን መከላከልም ያስችላል። በእርግጥ ኢትዮጵያ በሉዓላዊ ግዛትዋ ውስጥ በፈለገችው ጊዜና ቦታ ጦር ኃይልዋን በማሰማራት የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ሙሉ የሆነ መብት አላት። አሸባሪው የሚፈነጭበት የትግራይ ክልልም የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት እንደመሆኑ ይህን ማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት ሙሉ መብት ነው። ነገር ግን መቼ? እንዴትና? በምን ሁኔታዎች? የሚሉ ጥያቄዎች በደንብ መመለስ ይገባቸዋል።
ምዕራባዊያንና በፈረስነት የሚጋልቡት አሸባሪው ወያኔ በደገሱት ሴራ መጠለፍ በሸረቡት የድራማ ድግስ መታደም አይገባምና አስተውሎ መራመድ የሚያስፈልግበት ወቅት ነው። እየተዋጋን ያለነው አሸባሪው ሕወሓትን አይደለምና። እሱን የሚደግፉ ከእርሱ ጋር በግልፅ መቆማቸውን ደግመው ያሳወቁን ያላግባብ እኛ ላይ የዘመቱት የእኛ ተጠልፎ መውደቅ የኢትዮጵያን መሸነፍ እጅጉን ይፈልጉታል። ምዕራባወያን እነሱ ያልፈለጉት መሪ ምድር ላይ መቆየቱን አይፈቅዱም። ለእነሱ ጥቅም ያልቆመ ተላላኪ አስተዳደር ካልመሰረቱ እረፍት የላቸውም።
ለእነሱ ስለነሱ አገልጋይ ሆኖ ማንነቱና ሉዓላዊነቱን አላስደፍር ያለ ምድር ላይ ፈተና ያበዙበታል። የጫናዎች መዓት በእርሱ ላይ ያዘንባሉ። ከታላላቅ ሚዲያዎቻቸው እስከ ተራ ተቋሞቻቸው አብረው በዚያች በክብርና በሉዓላዊነቴ አትምጡ እጃችሁን ሰብስቡ ባለች አገር ላይ ይዘምታሉ። ሰላም እናስከብር ብለው የአገራት ሉዓላዊነት ንደዋል ሰብዓዊነት ብለው የሰው ልጆች ሰብዓዊ ክብር አርክሰዋል። ስለፍትህ እንጮሀለን እያሉ ከፍትህ እጅጉን የራቁ ጨቋኝና በደለኞች መሆናቸውን ዓለም በስራቸው መመልከት ጀምሯል።
የሚጮሁት መርጠው ነውና በሕወሓት የተፈፀመው ግፍ አይታያቸውም። ወሎ ላይ ስለተፈፀመው አስነዋሪ ተግባር አልገደዳቸውም። ሰብዓዊነት መፈፀም ለሚያስቡት ጣልቃ ገብነት መሸፈኛ ለቃዱት እቅድ መወጠኛ መንገድ ነውና ስለሰብዓዊነትና ፍትሀዊነት የሚጮሁት በሚፈልጉት ቦታ ላይ ብቻ ነው። ለእነሱ የሚገደው ሰብዓዊ ክብርና ፍትህ መንገስ ሳይሆን የራሳቸው ጥቅም ማስጠበቅና ፍላጎታቸውን ማሳካት ነው።
የእኛን በእነሱ ወጥመድ መውደቅ አጥብቀው ይፈልጉታል። በየትኛውም መንገድ እጃችን መጠምዘዙ አጥብቀው ይናፍቁታል። ለዚህም ነው ብዙ አስልተን መራመድ ይገባናል የምንለው። ለዚህ ነው እኛ በራሳችን መንገድ ያገኘነው ታላቅ ድል በተሸረበብን ሴራ ማሳጣት የለብንም የምንለው። አስፈላጊ በሆነ ጊዜና ሁናቴ የምንፈልገውን የአገራችን አሸናፊነት የሚያረጋግጥና የአሸባሪው መክሰም የሚያረጋግጥ እርምጃ መውሰድ ይቻላል።
ይህ በእኛ እቅድና ባሰብነው ጊዜ እንጂ እነሱ በፈለጉት መልኩ መቼም ሊሆን አይገባውም። ለዚህም ነው የመንግስት ውሳኔ ትክክለኝነት እዚህ ላይ ማንሳት የምፈልገው። አስልቶ መራመድ ብዙ ርቀት ያስጉዛልና ከጉዟችን የሚገቱን እንቅፋቶች በጥበብ እየነቀልን ዘላቂ የሆነ አሸናፊነት እንቀዳጃለን። በእርግጥ ኢትዮጵያ ጠላቶችዋን ሁሉ በአሸናፊነት መርታት ልማድዋ ነውና ወደፊትም አሸናፊነትዋ ይቀጥላል። አበቃሁ ስለ አገሬ ኢትዮጵያ ቸር ያሰማን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 25 ቀን 2014 ዓ.ም