በመላው አለም ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አንድ ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑት ሰሞኑን ወደ ሀገራቸው እየገቡ ነው።በዚህም የተነሳ ለወትሮውም ቢሆን በሀይማኖታዊ በዓላት (ገና እና ጥምቀት) እንዲሁም በማህበራዊ በዓላት (ሰርግ፣ ልደት፣ ድግስ ወዘተ) የተነሳ የሚደምቀው ወርሀ ጥር ዘንድሮ ከከርሞውም በባሰ ሁኔታ ውብ እንደሚሆን ከአሁኑ መገመት ይቻላል።ታዲያ በነዚህ ውብ ቀናት እና ሳምንታት ‹‹ምን ይለበስ›› የሚለው የብዙዎች ጭንቀት ነው።እርግጥ በዚህ ወቅት ላይ ስለሚለበሰው ነገር የፋሽን ባለሙያዎች ተገቢውን ዝግጅት ያደረጉበት ቢሆንም አንድ ሁለት ጥቆማዎችን እንሰጥ ዘንድ ወደድን።
አንደኛ፤ በተቻለ መጠን የሀገር ውስጥ ምርቶችን መጠቀም
እንደሚታወቀው ብዙኃኑ ዲያስፖራ ወደ ሀገር ቤት ሲመጣ የሚለብሰውን ልብስ ከዚያው ይዞ ነው የሚመጣው።እንዲያውም ከእሱ አልፎ ለዘመድ አዝማድ ሁሉ የሚሆን ልብስ ይዞ ነው የሚመጣው።ይህ መልካም ተግባር ነው።ነገር ግን እዚህ በሚኖረው ቆይታ ላይ ልብስ የመግዛት ፍላጎት ካለው መልካም የሚሆነው እሱ ከመጣበት የአለም ክፍል ልብስ እያስመጡ ከሚሸጡ ሱቆች ይልቅ፤ እዚሁ ሀገር ውስጥ በሀገር ልጆች የሚሰሩ አልባሳትን እንዲገዛ ይመከራል።የዶልቼ እና ጋባና ወይም የካልቪን ክሌይንን አልያም የሉዊስ ቪቶንን ምርቶች ለመግዛት ከሆነ እዚያው በሚኖረበት አገር በአንጻራዊ ዋጋ ያገኘዋል።ነገር ግን በአገር ውስጥ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች እና በኢትዮጵያውያን ዲዛይነሮች የተሰራን ልብስ መግዛት ለገዢውም ከዋጋ አንጻር ለአምራቹም ከገበያ አንጻር ጠቃሚ ነው፡፡
ሁለተኛ፤ ወቅታዊ መልዕክት ያላቸው አልባሳት መጠቀም
ዲያስፖራው ባለበት አገር እያደረገ ያለው ትግል አገርን ከመፍረስ እየታደገ ነው።በተለይም በ ‹‹#ኖ ሞር›› እንቅስቃሴ በኩል ያደረገው ተግባር ታሪክ ሲዘክረው የሚኖር ነው።ወደ አገር ቤት በተመለሰበት በዚህ ወቅትም ዲያስፖራው ይህን ተግባሩን ማቆም የለበትም።እንዲያውም በአሜሪካ እና አውሮፓ ጎዳናዎች ላይ አጊጦባቸው የነበሩ አልባሳትን እዚህም መልበስ አለበት።የ‹‹ኖ ሞር›› ቲሸርት አዲስ አበባም ላይ መለበስ አለበት።ኮፍያዎቹ፣ ጃኬቶቹ ወዘተ ወቅታዊውን መልዕክት የሚያስተላልፉ መሆን አለባቸው።ከዚህም በተጨማሪ አንድነትን የሚሰብኩ መሆን አለባቸው፡፡
ሶስተኛ፤ አዳዲስ የፋሽን እይታዎችን ማስተዋወቅ
ዲያስፖራው የሚኖርበት የዓለም ክፍል የፋሽን ኢንደስትሪው ብዙ ርቀት የተጓዘበት ነው።ዲያስፖራውም በሚኖርበት አገር በቆይታው አለባበስን በተመለከተ ብዙ ልምድ እንደቀሰመ መገመት ይቻላል።ይህንን ልምድ ለአገር ቤት ዲዛይነሮች ሊያካፍል ይችላል።የጆርጂዮ አርማኒን ወይም የዛራን ዲዛይን በአገር ውስጥ በቀላል መልኩ እንዴት መስራት ይቻላል ለሚለው ዲያስፖራው መላ ሊኖረው ይችላል።እዚያ ያየውን ዲዛይን እዚህ ካለው አለባበስ እና ጨርቅ ጋር እንዴት አድርጎ መስራት እንደሚቻል፤ ዲያስፖራው ልምድ ማካፈል ይችላል፡፡
አራተኛ ፤ ለአገር ውስጥ ልብሶች በሞዴልነት ማገልገል
ዲያስፖራው በአገር ቤት በሚኖረው ቆይታ የባህል አልባሳትን በመልበስ በሞዴልነት አገሩን እና ባህሏን ብሎም የፋሽን ስልታችንን ሊያስተዋውቅ ይችላል።በተለይም በዚህ ዘመን ማህበራዊ ሚዲያ ይህን ተግባር ቀላል አድርጎታል። እያንዳንዱ ዲያስፖራ በሚለብሰው ልብስ እና በማህበራዊ ሚዲያ በሚያጋራቸው ምስሎች ብዙ ምዕራባውያን ወዳጆቹን ተደራሽ ሊያደርግ ይችላል።ብዙ ወደ አገር ቤት ላልመጡ ኢትዮጵያውያንም እንዲሁ ተደራሽ ሊሆን እና ለልብሱ ያለ ፍላጎት ሊጨምር ይችላል።ስለዚህም ዲያስፖራው በቀጣይ አንድ ወር በሚኖረው አለባበስ ለብዙ የፋሽን ዲዛይነሮች ሞዴል መሆን የሚችልበት እድል ሰፊ ነው፡፡
አምስተኛ ፤ ለምዕራባውያን አልባሳት ያለው የተጋነነ አመለካከትን ማስቀየር
በአገር ደረጃ ከውጭ ለሚመጡ አልባሳት ያለው አመለካከት ከፍተኛ ነው።‘ጫማዬ የመጣው ከጣልያን ነው’፤ ‘ልብሴ የመጣው ከአሜሪካ ነው’፤ ‘ቀሚሴ የእንግሊዝ ነው’፤ ‘ሽቶዬ የፈረንሳይ ነው’ ማለት ለብዙዎች የኩራት ምንጭ ነው።እርግጥ ምርቶቹ ካላቸው የተሻለ ጥራት እና እነሱን ለመግዛት ከሚወጣው ወጪ ከፍተኝነት አንጻር ለነሱ ያለው አመለካከት ከፍተኛ መሆኑ የሚጠበቅ ቢሆንም አለቅጥ የተጋነነ አመለካከት ግን የባርነት አስተሳሰብን ይወልዳል።ስለዚህም ዲያስፖራው ይህን አመለካከት ለመቀየር መትጋት አለበት።ለዚህም መፍትሄው ከላይ በተደጋጋሚ የተጠቀሱትን ተግባራት በመፈጸም ነው።ማለትም የአገር ውስጥ ምርቶችን በመግዛት እና በመጠቀም ማለት ነው።ጥራት ያለው ልብስ መልበስ የሚጠላ ነገር ባይሆንም የራስን፤ የአገርን የመሰለ ነገር እንደሌለ ዲያስፖራው ማሳየት አለበት፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቀጣይ የጥር ወር በርካታ የአደባባይ በዓላት የሚከበሩበት ወቅት ነው።በዋነኝነት የጥምቀት በዓል በከፍተኛ ደረጃ የሚጠበቅ ነው።በዓሉ የአደባባይ እንደመሆኑ መጠን ብዙዎች አለን የሚሉትን ልብስ ለበሰው ወደ አደባባይ ይወጣሉ።በዚህ ሂደት ዲያስፖራውም ሆነ መላው የበዓሉ አክባሪ የሚለብሳቸው አልባሳት የፋሽን ይዘታቸው ከፍተኛ እንደሚሆን ባለፉት አመታት አከባበር ላይ የነበረው ሂደት አመላካች ነው።ይህ የሚያስደስት የጎዳና ላይ የፋሽን ትርዒትን ፈጥሯል።በቀጣይ ግን ይህ ወቅት ምናልባትም አመታዊ የኢትዮጵያ የፋሽን ሳምንት እንዲታሰብም እድል የሚፈጥር ነው፡፡
እንደሚታወቀው በሌሎች ሀገራት ከበጋ ወቅት መምጣት ጋር በተያያዘ የፋሽን ትርዒቶች ይበራከታሉ።እኛም በተመሳሳይ የኢትዮጵያ የፋሽን ሳምንት በዚህ ወቅት ልናዘጋጅ እንችላለን።በተለይም ይህን የዲያስፖራውን ወደ ሀገሩ መመለስ ልማድ ቋሚ በማድረግ ከዚህ ጋር በተመሳሳይ ወቅት ላይ የፋሽን ሳምንቱ ቢዘጋጅ ለአዘጋጆቹም ሆነ ለተሳታፊዎች ጠቃሚ ወቅት ይሆናል።በዚህ ወቅት የሰሜኑም፣ የደቡቡም፣ የምስራቁም፣ የምዕራቡም አልባሳት በዲዛይነሮቻችን ዘመኑን በዋጀ መልኩ ይቀርባሉ።ዲያስፖራውም ራሱ ከመምጣቱ ባለፈ ሌሎች በፋሽን ዘርፍ ያሉ ምዕራባውያንን መጋበዝ ይችላል።ምናልባትም አዳዲስ የኢንቨስትመንት እድሎችንም ሊፈጥሩ ይችላሉ።ስለዚህም ነገሩ በቅጡ ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡
አቤል ገብረኪዳን
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 25 ቀን 2014 ዓ.ም