ኢትዮጵያ በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ከዓመት በፊት በተከፈተባት ወረራ ሉኣላዊነቷን ለማስከበር ተገዳ ወደ ጦርነት ገብታለች። በዚህም የተቃጣባትን ወረራ በፍጥነት በመቀልበስ ከሃዲ ቡድኑን ከመቀሌ ወደ ተምቤን ዋሻ ሸኝታለች።
የጥሞና ግዜ ለትግራይ አርሶ አደር ብላ የተኩስ አቁም አድርጋ መቀሌን ለቃ ብትወጣም ይህን አጋጣሚ ለእኩይ አላማው ለመጠቀም ሲያሴር የቆየው አሸባሪ ቡድን በአማራና በአፋር ክልል መጠነ ሰፊ ወረራ ጀመረ።
ቡድኑ ካደረገው ወረራ በተጨማሪም ንፁሃን ዜጎችን በመጨፍጨፍ እጅግ አሰቃቂ ግፎችን ፈፅሟል። ሴቶችንና እናቶችን በመድፈርም ጥግ የሌለው አረመኔነቱን አሳይቷል።
ዜጎች ለዓመታት ያፈሯቸውን ንብረቶች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን፣ የመሰረተ ልማት አውታሮችንና ሌሎች ህብረተሰቡ የሚገለገልባቸውን ንብረቶችንም አውድሟል። የቻለውንም ዘርፏል።
ንብረትን እያወደመና እየዘረፈ፣ ሴቶች እየደረፈረና ንፁሃንን እየጨፈጨፈ እስከ ደብረ ብርሃን ድረስ የተጠጋው የሕወሓት አሸባሪ ቡድን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጦሩን ለመምራት ግምባር ከዘመቱበት ግዜ አንስቶ በጥምር ሃይሉ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ እንዲሞት፣ እንዲቆስልና እንዲፈረጥጥ ተደርጓል። ሃያ ቀን ባልሞላ ግዜ ውስጥም አከርካሪው ተሰብሮ ከአፋርና ከአማራ ክልል ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተጠራርጎ ለመውጣት ተገዷል።
አሸባሪ ቡድኑ በአፋርና በአማራ ክልል በቆየባቸው ግዜያቶች ውስጥ ህብረተሰቡ ያፈራው ንብረት፣ አርሶ አደሩ ያመረተው ምርት፣ ህብረተሰቡ የሚጠቀምባቸውን መሰረተ ልማቶች ሙሉ በሙሉ በሚያስችል ደረጃ አውድማል። ይህንንም ተከትሎ በርካታ ህዝብ ለተለያዩ ችግሮች ተጋልጧል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም በተለይ የተፈናቀለውን ህብረተሰብ መልሶ ማቋቋምና የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ መገንባቱ ከባድ ፈተና እንደሚሆን ይጠበቃል። የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ስራው ለመንግስት ብቻ የሚተው ተግባር ባለመሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንና የሁሉንም ዜጎች ርብርብ እንደሚያስፈልገው አያጠያይቅም። በዚህ ግዜ የሁሉም ዜጋ ትኩረት ሊሆን የሚገባውም በዚህ አሸባሪ ሃይል ወረራ ምክንያት በብዛት ተፈናቅለው የሚገኙ ዜጎችን መልሶ ማቋቋም ሊሆን ይገባል።
በእርግጥ በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸውን ለማገዝና የተዘረፉና የወደሙ ንብረቶችንና የመሰረተ ልማት አውታሮችን መልሶ ለመገንባት ብሎም ተፈናቃዮችንም መልሶ ለማቋቋም ሰፊ ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ።
ይሑንና ኢትዮጵያ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉና ንብረታቸው የወደሙ ዜጎቿን መልሳ ለማቋቋምና ንብረታቸውን ለመተካት ያለ የሌለ ሀብቷን አውጥታ ጥረት እያደረገች በምትገኝበት በዚህ ጊዜ አንዳንድ ለሆዳቸው ያደሩና ከአሸባሪ ቡድኑ ያልተናነሰ ወንጀል የሚፈፀሙ ባንዳዎች እያስተዋልን እንገኛለን።
በችግር ውስጥ ካለችው እናት ሀገራቸው መቀነት ፈተው የሚዘርፉት እነዚህ ባንዳዎ፣ ነፃ በወጡ አካባቢዎች ከሽብር ቡድኑ የተራረፉ ንብረቶችን ለመዝረፍ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል።
ይሕን ህገ ወጥ እና አሳፋሪ ተግባር ለማስቆም በየአካባቢው ያለው የፖሊስ ሃይል ብርቱ ቁጥጥር እንዲያደርግና ይህን በሚፈፅሙት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ እዝ ከሰሞኑ ትእዛዝ ማስተላለፉ ይታወሳል።
አገር በውስጥና በውጪ ጠላቶች ተወጥራ ባለችበት በዚህ ግዜ ግርግሩን ተጠቅመው የራሳቸውን ከርስ ለመሙላት ሌብነትን እንደዋና አማራጭ የወሰዱም እየታዩ መጥተዋል። ይህ ታዲያ በተለይ አሸባሪው ሕወሓት በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያደረሰው አሉታዊ ተፅእኖ ሳያንስ ከዚቹ ሀብት ላይ መዝረፍ የሀጢያቶች ሁሉ ሀጢያት መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል።
ለአብነት እንኳን ከሰሞኑ በህገ ወጥ የመሬት ወረራ በተሳተፉ 88 አመራሮችና ሰራተኞች ላይ ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስታውቋል። ከ260 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ ስፋት ያላቸው እና በህገ ወጥ የመሬት ወረራ የተያዙ 671 ይዞታዎች ካርታቸው እንዲመክን በማድረግ ወደ መሬት ባንክ መመለሳቸውንም አስተዳደሩ ገልጿል።
ህገወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ በስፋት የታየባቸው የለሚኩራ፣ የቦሌ፤ የአቃቂ፣ የንፋስስልክና የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለከተሞች መሆናቸውንም በመግለጫው አስቀምጧል። ይሄ የሚያሳየው እነዚህ ሰዎች አገር ምንም ውስጥ ትግባ ያላትን ከማራቆትና የራሳቸውን ከርስ ከመሙላት ወደኋላ እንደማይሉ ነው። ድርጊታቸውም አሸባሪ ቡድኑ ከፈፀማቸው የውንብድና ወንጀለኞች ተለይቶ የሚታይ አይደለም።
አገር በዚህ ሰዓት ከዜጎቿ ብዙ ነገር በምትጠብቅብት በአሁኑ ወቅት ጭራሽ ይመሩኛል ያስተዳድሩኛል ብላ የሾመቻቸው ሲቦጠቡጧት መመልከትና መስማት እጅግ ያሳዝናል። ከሀገር ላይ መዝረፍ በተለይ ደግሞ በዚህ ግዜ የአስክሬን ከፈን እንደመስረቅም ይቆጠራል።
በዚህ ሰዓት አገር እንዲህ በውጪና በአገር ውስጥ ጠላት ተወጥራ ይህን ግርርግር በመጠቀም ለመዝረፍ ማለምም ሆነ መሞከር ያስተዛዝባል፤ ከባንዳነትም ተነጥሎ የሚታይ አይደለም። አገር ከመሸጥ ጋርም በምንም አይለይም።
በመሆኑም ሀገራችን ኢትዮጵያ ከገባችበት ፈተና ተላቃ በተቃና የልማት ጎዳና እንድትዘልቅ በተለይ በእንዲህ ያለ ሰዓት ዜጎች ዘራፊና ወረበሎችን በማጋለጥ የዜግነት ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል።
አገር ስትዘረፍ እያዩ ዝም ማለትም መብት ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው። በአሁን ወቅት ሌባን የማጋለጥ ተግባር የኢትዮጵያን ዳር ድምበር ለማስከበር ግምባር ተሰልፎ መስዋዕትነት እየከፈለ ካለው የመከላከያ ሰራዊታችን ጀብድ የሚተናነስ አይሆንም።
መንግስትም ቢሆን በጉያው ተሰግስገው የለውጡ አንድ አካል ነን በሚል የለውጥ መዝሙር እየዘመሩ ከኋላ ሀገሪቱን የሚዘርፉ አመራሮችንና በየደረጃው ያሉ ፈፃሚ አካላትን መታገስ የለበትም። ሌቦችን ፈልፍሎ በማውጣት ለህግ በማቅረብና ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ ይኖርበታል።
በተለይ በዚህ ወቅት ዜጎችም ሆኑ መንግስት በሌብነት ላይ የማያወላዳ አቋም አስከወሰዱ ድረስ በነብስ በላና አረመኔው የሽብር ቡድን የወደሙ ንብረቶችን መልሶ መተካት ይብዛም ይነስም እዳው ገብስ ነው።የተፈናቀሉ ዜጎቻችንንም በዘላቂነት ማቋቋም ቢሆን ዓመታትን የሚወስድ አይሆንም።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 25 ቀን 2014 ዓ.ም