ታዲያስ ልጆች፣ እንደምን ሰነበታችሁ? መቸም የዛሬ ርእሴን ስታዩ በጣም እንደተደሰታችሁ እርግጠኛ ነኝ። ለምን እርግጠኛ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ? አዎ፣ እርግጠኛ የሆንኩት ልጆችና መጻሕፍት ያላቸውን ግንኙነት በሚገባ ስለማውቅ ነው። በመሆኑም ዛሬ ስለ መጻሕፍት እናወራለን።
ከዛ በፊት ግን አንድ ነገር ልንገራችሁ። ትናንትና ቴሌቪዥን ተመልክታችኋል? ወይም ሬዲዮ አድምጣችኋል? ወይም ጋዜጣ አንብባችኋል? ከእነዚህ አንዱን ወይም ሁለቱን ወይም ሁሉንም ተከታትላችሁ ከሆነ በመሀል አዲስ አበባ፣ 4 ኪሎ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተገኙበት አንድ ትልቅ ሥነ-ስርአት ተካሂዷል። አዎ፣ በጣም ደስ የሚል ሥነስርአት ነበር። በጣም ደስ የሚለው ደግሞ ዛሬ ከምናወራው ጉዳይ ጋር የተያያዘ መሆኑ ነው።
አዎ ልጆች፣ በትናንትናው እለት በመሀል አዲስ አበባ፣ 4 ኪሎ አንድ ግዙፍ፣ እጅግ ዘመናዊና በአገራችን እስከ ዛሬ ያልታየ ቤተ መጻሕፍት (“አብርኈት ቤተ መጻሕፍት” የሚባል) ተመርቋል። ታዲያ ይሄ ደስ አይልም ልጆች? በጣም ደስ ይላል። በጣም … ለምን መሰላችሁ ደስ የሚለው? በቃ እናንተ (አባባ ተስፋዬ “የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች” የሚሏችሁ) ትልቅ እየሆናችሁ ስትሄዱ፣ እያወቃችሁና በትምህርታችሁ ጎበዝ እየሆናችሁ ስትሄዱ፤ ሳይንቲስት፣ ፈላስፋ፣ መሀንዲስ፣ ሀኪም ስትሆኑ የምትፈልጉትን ሁሉ የምታገኙበትና የምታነቡበት፤ ቁጭ ብላችሁ የምታጠኑበትና የምትመራመሩበት፤ መዝናናት ስትፈልጉ ሁሉ የምትዝናኑበት (ልጆች የሰው ልጅ በሌሎች ነገሮች እንደሚዝናናው ሁሉ በንባብም እንደሚዝናና ታውቃላችሁ አይደል? አዎ፣ ሰው በሌሎች ነገሮች ብቻም ሳይሆን በንባብም በጣም ይዝናናል እሺ ልጆች። እንደውም ጥቅሙ ከመጻሕፍት የሚደረገው መዝናናት ይበልጣል።) ቤተ መጻሕፍት አላችሁ፤ ወይም ተዘጋጅቶላችኋል። ደስ አይልም ልጆች፣ በጣም ደስ ይላል።
በተለይ ቤተ መጻሕፍቱን ጠጋ ብላችሁ፣ ውስጡ ገብታችሁ … ስታዩት ደግሞ በጣም ትደሰታላችሁ። እንዴት እንደሚያምር ስታዩት አገራችሁ ውስጥ እንደዚህ አይነት ቤተ መጻሕፍት በመኖሩ ትኮራላችሁ። ስለዚህ ወደ ፊት በየአካባቢያችሁ የተለያዩ ቤተ መጻሕፍቶች ይሰራሉ ብለን ነው የምንጠብቀው፤ አይደል? አዎ፣ ይሰራሉ። ከእናንተ የሚጠበቀው ጎበዝ ተማሪ፣ ጎበዝ አንባቢ፣ ጎበዝ ጸሐፊ … መሆን በቻ ነው።
ልጆች አሁን ስለ ቤተ መጻሕፍት ማውራታችንን እናቁምና እናንተና መጻሕፍት ስላላችሁ ግንኙነት እናውራ።
ልጆች እስኪ አጠገባችሁ ላሉ ሰዎች የምትወዷቸውን መጻሕፍት ንገሯቸው፤ እነዚህ መጻሕፍት ምን አይነት መጻሕፍት (የተረት፣ ልቦለድ፣ ስነ ልቦና፣ ፍልስፍና ወዘተ) እንደሆኑ ንገሯቸው። ከቻላችሁ በይዘታቸው (መልእክታቸው)፤ ካልቻላችሁ በርእሳቸው ንገሯቸው። ነገራችኋቸው አይደል፣ በጣም ጥሩ!!!
አሁን ደግሞ አንድ ቤተሰቦቻችሁ እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ልጠይቃችሁ። ቤተሰቦቻችሁ ምን ምን አይነት መጻሕፍትን ልግዛልህ/ሽ ቢሏችሁ ምን አይነት ብላችሁ ነው የምትነግሯቸው? አዎ፣ ይህንን ጉዳይ በሚገባ ማወቅ አለባችሁ።
ልጆች በይዘት ብዙ አይነት መጻሕፍት አሉ። ከላይ እንዳልኳችሁ የሳይንስ፣ ስለ ተፈጥሮ የሚያስረዱ፣ ስለ ሰው ልጅ አመጣጥ፣ ስለ እንስሳት የሚያስገነዝቡ ወዘተ መጻሕፍት አሉ። ስለዚህ ከእነዚህ ውስጥ የእናንተ ፍላጎት የትኛው እንደሆነ በሚገባ ማወቅ አለባችሁ።
እነዚህን ካወቃችሁ ምን እንዲገዛላችሁ ስትጠየቁ ወዲያውኑ፣ በቀላሉ ትናገራላችሁ ማለት ነው። እኔ ልጅ ሆኜ “ምን አይነት መጽሐፍ ይገዛልህ?” ተብዬ ስጠየቅ ቶሎ ብዬ “ልቦለድ” ነበር የምለው። በቃ፣ ከዛ በኋላ እረፍት ሲሆን የማነባቸው ልቦለድ መጻሕፍት ይገዙልኛል።
ልጆች የእኛን አገር አላውቅም እንጂ ሌሎች አገራት በልጆች የተነበቡ፣ በልጆች የተወደዱ፣ በልጆች ተዘወትረው በተደጋጋሚ የተነበቡ መጻሕፍት ይታወቃሉ። ለምን መሰላችሁ በቀላሉ የሚታወቁት፣ ምሁራን በየጊዜው ጥናትና ምርምር ስለሚያደርጉና በየቤተ-መጻሕፍቱ ስለሚያስቀምጡ ነው። በቃ፣ ከዛ ሁሉም ሰው እንዲያውቀው ይደረጋል። ለዛ ነው የእነሱን የጠቀስኩላችሁ። እኛም አገር ወደ ፊት እንደዚህ የሚሆን አይመስላችሁም? አዎ ይሆናል።
ልጆች አንድ ምሳሌ ብቻ ልንገራችሁ። ባለፈው የፈረንጆች ዓመት (በ2020 ማለቴ ነው) በዓለም ዙሪያ ከተፃፉት የልጆች መጻሕፍት መካከል በጣም የተነበበው የቱ እንደሆነ ታውቃላችሁ? አዎ፣ በጣም የተወደደውና የተነበበው መጽሐፍ አንቶኔ ዲ ሴንተ (Antoine de Saint-Exupry) የተባሉ ጎበዝ ደራሲ የፃፉት (እ.አ.አ በ1943) Le Petit Prince (በእንግሊዝኛ The Little Prince ተብሎ ተተርጉሟል) መጽሐፍ ሲሆን ሌሎችም እንደዚሁ በጣም ተወዳጅ የሆኑ መጻሕፍት አሉ። ልጆች እስኪ ይህ መጽሐፍ ስለ ምን እንደሚተርክ ፈልጋችሁ፣ ጠይቃችሁና አጠያይቃችሁ፤ ወይም የተለያዩ መጻሕፍትን አገላብጣችሁ መልሱን ለጓደኞቻችሁ ንግሩ።
ልጆች፣ የዛሬውን ስለመጻሕፍት ያደረግነውን ጭውውታችንን ከማጠቃለላችን በፊት እስኪ አንድ ጥያቄ እናንሳና ስለመልሱ እናስብ።
ልጆች ለመሆኑ የመጻሕፍት ጥቅም ምንድን ነው? ትምህርት ቤት እያላችሁ መምህራንን ጠይቃችሁ ታውቃላችሁ? ወይም ነግረዋችሁ ያውቃሉ? ነግረዋችሁ ከሆነ በጣም ጥሩ። ካልሆነ ግን ምንም አይነት ጊዜ ሳትሰጡ ከነገ ጀምሮ ጠይቁ። በጣም ብዙ የሆኑ የመጻሕፍት ጥቅሞችን ይነግሯችኋል። በጣም ብዙ ….
በሉ እንግዲህ ልጆች፣ የዛሬውን ርእሰ ጉዳያችንን በዚሁ እናጠናቅቃለን። ይህን ስንል ስለ መጻሕፍት መነጋገሩ አልቋል ማለታችን አይደለም። በፍፁም አያልቅም። ስለዚህ በሌላ ጊዜ ደግሞ በደንብ እናወራለን፣ እሺ ልጆች። በደህና ሰንብቱ! ቻው!
በሉ እንግዲህ ሳምንት በሌላ ርእስ እስክንገናኝ ድረስ መልካም ሳምንት። ደህና ሁኑ ልጆች፤ ደህና ሁኑ።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 24/2014