የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተመሠረተው ከጣልያን ወረራ በኋላ ነበር። የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ተዋናይ የነበረችው የሙሶሊኒዋ ፋሽስት ጣልያን በ1933 ከኢትዮጵያ የአምስት ዓመት ወረራ ተሸንፋ ከወጣች ከአምስት ዓመት በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተቋቋመ።ይህም የዛሬ 76 ዓመት ታኅሳስ 21 ቀን 1938 ዓ.ም ነው።
በአሜሪካ ሠራሽ አውሮፕላኖች የበረራ ሥራ የጀመረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጊዜው ዐፄ ኃይለሥላሴ ጋር በተደረገ ስምምነት አየር መንገዱን ያቋቋመው ዛሬ ላይ ገበያ ላይ የሌለው የአሜሪካኑ ትራንስ ወርልድ አቪየሽን TWA (Trans World Aviation) ነበር።የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስተዳዳሩም በአሜሪካዊያን እጅ ነበር ።ዓለም አቀፍ ጉዞውንም አሀዱ ብሎ የጀመረውም ወደ ግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ ሳምንታዊ በረራ በማድረግ ነው። ይህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተመሠረተ በሦስተኛው ወሩ መጋቢት 30 ቀን 1938 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ተነሥቶ ካይሮ ድረስ ያካሄደው ዓለም አቀፍ በረራ ነው፡
አየር መንገዱ ሲመሠረት ከአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል የተገዙና በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ያገለገሉ አምስት ዲ.ሲ. 3 (DC 3-C47) አውሮፕላኖች ነበሩት። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራውን ሲጀመር ይገለገልበት የነበረው የአዲስ አበባ አውሮፕላን ማረፊያ በጦር ኃይሎች በሚባል በሚጠራው ቦታ ሥር የሚገኘውን ማኮብኮቢያ ሜዳ ነበር። ሜዳው ለአውሮፕላን ለመንደርደሪያ በቂ ስላልነበር ቀስ በቀስ ዋና ማረፊያ ጣቢያው ቦሌ ወደ ሚገኘው ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ አዘዋወረ። የጦር ኃይሎችን አንዳንድ ሰዎች አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ በሚል ይጠሩታል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተመሠረተ አምና 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓሉን አክብሯል። አየር መንገዱ በዓለም ላይ እጅግ ተወዳዳሪ ከሆኑ ግዙፋ ገናና ስምና ዝና ካላቸው ተርታ የሚጠቀስ ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ 76 ዓመቱ በተቆጠረበት በያዝነው ታኅሳስ ወር የ2014 ዓ.ም የአፍሪካ ምርጡና ቀዳሚ አየር መንገድነት ሽልማትን በድጋሚ ማሸነፉም ስምና ዝናው ገናና እንደሆነ ማሳያ ነው።ሽልማቱን የሰጠው በብሪታኒያ የሚገኝ እና በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ አገልግሎት ጥራት፥ የሚሸልመው ስካይ ትራክስ የተሰኘው ተቋም መሆኑን መረጃዎች ያስረዳሉ።በአሁኑ ወቅት በዓለማችን በሚበርባቸው በረራዎች ብዛት የዓለማችን አራተኛው አየር መንገድ ነው።
አየር መንገዱ የራሱ የአውሮፕላን አብራሪዎች የበረራ አስተናጋጅ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ያለው ሲሆን ዓለም አቀፍ ደረጃው ያሟላና ለአፍሪካ አገሮችና ለሌሎችም ጭምር ሥልጠና በመስጠት በማስመረቅ ይታወቃል።ለግል አብራሪና ለንግድ አውሮፕላን አብራሪ ፈቃድ በመስጠት የአገርና የውጪ ዜጎችን በማሠልጠን ከአርባ ዓመታት የቆየ ልምድ አለው።ለብዙ የአፍሪካ አገሮች ብሔራዊ አየር መንገዶች እና ለግል አውሮፕላን ባለንብረቶች የአውሮፕላን ጥገና በማካሄድም የሚሠራ ተቋም ነው።
ከቦይንግ አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ጋር ከ60 ዓመታት በላይ የዘለቀ የንግድ ግንኙነት ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመንገደኞች አገልግሎት ቦይንግ 787 ( Boeing 787 Dreamliner) አውሮፕላኖች በማዘዝና በአፍሪካ አገልግሎት ላይ በማዋል የመጀመሪያው ነው።ይህንንም የተረከበው ድሪምላይነር አውሮፕላን በነሐሴ ወር 2012 ዓ.ም ነበር።አየር መንገዱ ቦይንግ 777 ቦይንግ 787 ቦይንግ 737 በአጠቃላይ 68 እጅግ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን ይጠቀም እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።
በአውሮፓውያኑ በ1960ዎቹ D720 የመጀመሪያው ጀት ኤንጅን ያለው አውሮፕላን ወደ አፍሪካ ያመጣው አየር መንገዱ ፤ከዚያም ቦይንግ 707፣ 727፣737፣ 757፣ 767ን በማስመጣት ሲገለገል ቆይቷል። ይህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ አንድ ምርት ውጭ ሁሉንም የቦይንግ አውሮፕላኖች እንደተጠቀመ ነው ሰነዶች የሚያስረዱት።በአምስት አህጉሮች ከ110 በሚበልጡ መዳረሻዎች ይበራል።
በኮረና ወረርሽን ተጠቂ ኢንዱስትሪዎች መካከል ቀዳሚው ዓለም አቀፍ የአየር መንገድ ኢንዱስትሪ ሲሆኑ ከዚህ ውስጥ የአፍሪካ አየር መንገዶች 4.2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያጡ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ በመሆኑ ትልቅ ድርሻ ስለነበረው ቀውሱ ይጎላል በሚል ተገምቶ ነበር።
በወረርሽኙ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጥር ወር 2012 ዓ.ም 550 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ። በወቅቱ 110 የመንገደኛና 17 የጭነት በድምሩ 127 መዳረሻዎች ያሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ 91 መዳረሻዎች መዘጋታቸው የወረርሽኙን ተፅዕኖ ያሳያል ፣ በዚህም 19 የመንገደኞች መዳረሻዎች ብቻ ቀርተው ነበር። በየቀኑ 350 በረራዎች የነበሩት አየር መንገዱ በወቅቱ በቀን በአገር ውስጥ 14፣ በዓለም አቀፍ አሥርና ከዚያ በታች በረራ ነበረው።በዚህም የአየር መንገዱ እንቅስቃሴ 90 በመቶ ቀንሶ፣ በአሥር በመቶ ብቻ አቅም እየበረረ ነበር።ይህም የአየር መንገዱን ህልውና የሚፈታተንና በታሪኩ የመጀመሪያ ከሆነው ዓለም አቀፋዊ ቀውስ ደርሶበት ነበር ።
ይህም የኮሮና ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ቀውስ ማስከተሉን ገልጸው የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ቀዳሚ ተጠቂ እንደነበር ማሳያ ነው። በወቅቱ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከዓለም ሕዝብ ሲሦው ከቤቱ እንዳይወጣ በመገደዱ ነው።
በወቅቱ ወረርሽኙ ባመጣው ተፅዕኖ አየር መንገዱ ካሉት 120 አውሮፕላኖች 91 ያህሉ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት እንዲቆሙ ተገደዋል፣ ይህም የቦታ ጥበት ፈጥሮ ነበር። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኮሮና ወረርሽኝ ቀውስ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ቢሆንም በጭነት በረራዎች፣ በቻርተር በረራዎች፣ የካርጎ ዘርፍ በአውሮፕላን ጥገና ጥሩ ሥራ በመከናወኑ ቀውሱን ለመቋቋም ብርቱ አቅም ፈጥሮለታል።
የኮሮና ቫይረስ (COVID-19) እንደዓለም አቀፍ የአየር መንገድ ኢንዱስትሪውን ሁሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የመንገደኛ በረራዎቹን ከ90 በመቶ በላይ እንዲቆሙ በመደረጋቸው ይህንን ቀውስ ለመውጣት ሙሉ በሙሉ የስራቴጂክ እቅድ ለውጥ በማድረግ የትኩረት አቅጣጫውን ወደ እቃ ጭነት ቢዝነስ አዞረ። በዚህም የኮቪድ ወረርሽኝን ተከትሎ በዓለም እየጨመረ ለመጣው የጭነት አገልግሎት ፍላጎት በነበሩት የጭነት ማመላለሻ አውሮፕላኖች አጠናክሮ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።
ይህንን አዲስ ስትራቴጂ በመጠቀም የጭነት ማጓጓዝ አቅሙን ለማሳደግ ተጨማሪ 22 የመንገደኛ አውሮፕላኖችን የጭነት አገልግሎት እንዲሰጡ በውስጥ አቅም የምህንድስና ማስተካኪያ (Conversion) ተደርጎባቸው በጭነት አገልግሎት እንዲሠሩ ተደረገ።በወቅቱ 12 የዕቃ ጭነት እና 22 የመንገደኞች አውሮፕላኖችን ለጭነት በማዘጋጀት ሠርቷል። ከአገር ውስጥ አበባና እና የፍራፍሬ ምርቶች ከውጪ ደግሞ የህክምና መሣሪያዎች መድኃኒቶችና የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች በማመላለስ ይሠራል።
አየር መንገዱ በመንገደኛ አውሮፕላኖቹ ውስጥ የሚገኙ መቀመጫዎችን ከቦታቸው በማንሳት ለጭነት አገልግሎት እንዲውል ያደረገው ዓለማቀፍ የአቪየሽንና የቴክኒክ ተቆጣጣሪ አካላት ያስቀመጧቸውን መስፈርቶች በመከተልና በማሟላት ነው። አየር መንገዱ የኮሮናን ቫይረስ ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ህይወት አድን የሆኑ የህክምና ቁሳቁሶችን በመላው አፍሪካ በማጓጓዝም ሠርቷል።በወቅቱ ከቻይና ወደ ብራዚል ቺሊና ኮሎምቢያ ጭምር የኮቪድ መድኃኒት በማመላለስ ሲሠራ ቆይቷል። የአገልግሎት ተልእኮውን በብቃት ለመወጣትም በመንገደኛ አውሮፕላን የእቃ ማስቀመጫ ቦታ፣ እንዲሁም የአውሮፕላኖቹ ወንበሮች ሳይነሱ ጭነት በመጫን አገልግሎቱን በማቀላጠፍ ሠርቷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፈታኝ በሆነበት ወቅት የዓለምን ማህበረሰብ ለማገልገል ባደረገው ጥረት ሕይወት አድን የሆኑ የህክምና መሣሪያዎችን በበርካታ መጠንና ፍጥነት ያጓጓዘ ሲሆን፣ በዚህም አጠቃላይ የአገልግሎት ብቃቱን በማስመስከሩ ምስጋናና አድናቆት ተችሮታል።
በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ የሕክምና መሣሪያዎችና መድኃኒቶች ፍላጎት በመናሩና ከፍተኛ የጭነት በረራ ፍላጎት በመፈጠሩ፣ የኢትዮጵያ ካርጎና ሎጂስቲክስ ክፍል ጥሩ በመሥራት ላይ ቢሆንም አየር መንገዱ ያጣውን ገቢ ለማካካስ ረድቶታል።
በአፍሪካ ትልቁ የሆነውን የአየር መንገዱን የዕቃ ማራገፊያ እና መጫኛ ጣቢያ ወይንም ካርጎ ተርሚናል ሁለት በሰኔ በ2009 የተመረቀ ነው። የመጀመሪያው የተገነባው በ2007 ዓ.ም 600 ሺህ ቶን ማስተናገድ የሚችልና የአውሮፕላን መቆሚያ፣ የጭነት መኪኖች ጭነት ማራገፊያ ሥፍራ፣ ቢሮዎችና የመኪና ማቆሚያ አለው ።የካርጎ ተርሚናሉ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ሥጋ፣ መድኃኒትና ደረቅ ጭነትን ጨምሮ፣ በአጠቃላይ በዓመት አንድ ሚሊዮን ቶን ጭነት የማስተናገድ አቅም አለው።
በ2012 ዓ.ም የካርጎና ሎጂስቲክስ አገልግሎትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በአፍሪካ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ ዕርዳታ ማከፋፈያ ማዕከል እንዲሆን ተመርጦ ሠርቷል። ይህም አየር መንገዱ ባሉት ዘመናዊ አውሮፕላኖችና ግዙፍ የካርጎ ተርሚናል ለአፍሪካ የሚመጡ የሕክምና ቁሳቁሶችን ለማከፋፈል ብቁ ሆኖ በመገኘቱ ነው።አየር መንገዱ በረጅም አገልግሎቱ በኮሞሮስ በጠላፊዎች የደረሰው እና መጋቢት 1 ቀን 20011 ዓ.ም በቢሾፍቱ አቅራቢያ በምትገኘው አድአ ወረዳ የደረሱት ይታወሳሉ ።
በታኅሳስ አጋማሽ 2012 አየር መንገዱ በአዲስ አበባ በሥሩ ደረጃውን የጠበቀ ስካይ ላይት ሆቴል በመዲናዋ አስገንብቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት አስመርቋል።አየር መንገዱ ከስኬት ወደ ስኬት የሚሄድ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካውያንም የሚኮሩበት ነው።ባለንበት ወቅት #no more በቃ ንቅናቄ ለሀገሩ የቆመውንና በዓለም ከ40 ከተሞች በላይ ምዕራባውያን እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ እንዲያነሱ በሰላማዊ ሰልፍ ሲታገል ለነበረውና አገሩ ለሚገባው ዲያስፖራ እንዲመጡ በማመላላስም እየሠራ ይገኛል።
ኃለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 24/2014