አሸባሪው የሕወሓት ቡድን እየወሰደ ባለው ሀገር የማፍረስ እንቅስቃሴ ጫና ከተፈጠረባቸው ዘርፎች መካከል ቱሪዝም አንዱ ነው። ባለፉት ዓመታት የተወሰነ መነቃቃት እየታየበት መጥቶ የነበረው ቱሪዝም የኮሮና ወረርሽኝ እንቅስቃሴው አስተጓጉሎት ቆይቷል። የኮሮና ወረርሽኝ ዓለም አቀፍ ክስተት በመሆኑ ተጽእኖ የፈጠረው በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፉ አጠቃላይ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ ነበር። ሆኖም ከእልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ በኋላ በሀገሪቱ የተሰራጨው የኮሮና ቫይረስ ስጋት የመሆኑ ጉዳይ እየተቀዛቀዘ በመዲናዋ የቱሪዝም መዳረሻ አማራጭ ሆኖ ቢመጣም የሕወሓት የሽብርና አገር የማፍረስ እንቅስቃሴ ለዘርፉ ሌላ እንቅፋት ሆኖ ተደቀነ ።
አሸባሪው ሕወሓት በምድር ከሚያደርገው አገር አፍራሽ ጦርነት ባለፈ በአውሮፓውያንና በአሜሪካውያን ጋሻ ጃግሬነት በሀሰት ፕሮፓጋንዳውም ማስፋፋቱ ደግሞ ዘርፉን የበለጠ እግር ከወርች ሊያስረው በቅቷል። ይህም ሆኖ በቅርቡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ በመቀበል ወደ ሀገራቸው የመጡና የሚመጡ ኢትዮጵያውያን ዘርፉን ለማነቃቃት ብዙ ስራ እንደሚጠበቅ በማሳሰብ እነሱም የድርሻቸውን ለመወጣት ከመላው ዓለም ተነቃንቀዋል። ‹‹በኢትዮጵያ የሰላሙ ሁኔታ አስጊ ነው፤ በአስቸኳይ ውጡ›› የሚል የሽብር ወሬ ከሚነዙት፣ ማሳሰቢያና ማስጠንቀቂያ ከሚሰጡት የውጪ ሀይሎች መልዕክት ይልቅ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ የተቀበሉት ብዙዎች ናቸው። መቀበል ብቻ ሳይሆን የታሰበውን ቱሪዝሙን የማሳደግ ተግባሩንም በተግባር እያሳዩ ናቸው።
አቶ ሬድዋን ከድር ለሐያ ዓመታት የኖሩት በእንግሊዝ ሀገር ለንደን ከተማ ነው። አቶ ሬድዋን በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተደረገውን ጥሪ ተቀብለው ወደሀገራቸው የመጡ ሲሆን በሌሎች የማህበራዊ ድጋፍ ተሳትፎዎች እንደሚያደርጉ ሁሉ ለቱሪዝም ዘርፉም ትኩረት እንደሚያደርጉ ይናገራሉ። በሀገሪቱ ያለውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በቅርበት ሲከታተሉት እንደነበር የሚናገሩት አቶ ሬድዋን ያላቸውንም አስተያየት እንደሚከተለው ተናግረዋል። አሸባሪው ሕወሓት በከፈተው ጦርነት ምክንያት በሁሉም መስክ የሚታይ ኢኮኖሚያዊ ድቀት አለ። ስለ ቱሪዝም ስናነሳ ደግሞ ሆቴል ቀዳሚ መዳረሻችን ነው።
በርካታ ሆቴሎች ቱሪዝሙ በመቀዛቀዙ ገቢያቸው ቀንሷል። ከሳምንት በፊት በነበረን አንድ ስብሰባ ላይ ዳያስፖራውን ለመቀበል ሆቴሎች ከሐያ እስከ ሰላሳ በመቶ ቅናሽ ሊያደርጉ እንደሚገባ ምክረ ሀሳብ ቀርቦ ነበር። እኔ ይህንን ሀሳብ በመቃወም እንዲያውም የሆቴሉ ዘርፍ ድጋፍ ሊደረግለት የሚገባ መሆኑን አሳስቢያለሁ። አሁንም ቢሆን ዳያስፖራው ወደ ሀገር ቤት ሲገባ በሌሎች ጉዳዮች ላይ እንደሚያደርገው ተሳትፎና ርብርብ ሁሉ የቱሪዝም ዘርፉንም ለማነቃቃት የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይገባል የሚል እምነት አለኝ ።
ለዚህ ደግሞ ያለንበት ወቅት የፈጠረልን አጋጣሚዎች አሉ። ከቀናት በኋላ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የገና እና የጥምቀት በአላት በተከታታይ ይከበራሉ። የገና በአል የአደባባይ በአል ባይሆንም በላልይበላ በመገኘት በአሉንም ማክበር በአካባቢው በአሸባሪው ቡድን የደረሰውን ጉዳትና ህዝቡ ያለበትንም ሁኔታ ማየት ከዳያስፖራው ይጠበቃል። የጥምቀት በአልም በዓለም የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበ ትልቅ በዓል ነው። አንዱ የቱሪስት መስህብ መሆኑ ይታወቃል። ምንም እንኳን ይህንን በአል ለማክበር እንደ ከዚህ ቀደሙ በርካታ የውጪ ዜጎች ይገኛሉ ተብሎ ባይገመትም ወደአገር ውስጥ እየገባ ያለው ዳያስፖራ መገኘት ከቻለ ትልቅ ለውጥ ማስመዝገብ ይቻላል። ኢኮኖሚውን ማነቃቃት ይቻላል።
በተጨማሪ ዳያስፖራው በቀጥታ የቱሪዝሙን ዘርፍ ለመደገፍ ከሚያደርገው አስተዋጽኦ ባለፈ ያለውን ሰላም ለቀሪው ዓለም የማሳወቅም ሃላፊነት አለበት። እስካሁን ባለው እኔን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን በውጪ ስለ ኢትዮጵያ ይወራ የነበረው ነገር ትክክል አለመሆኑን በአይናችን አይተን ለማረጋገጥ ችለናል።
ነገር ግን ይሄ ብቻውን በቂ አይደለም። ሁላችንም ተመልሰን ወደመጣንበት ስንሄድ ለትውልደ ኢትዮጵያውያንም ሆነ ለሌላው ህዝብ በያለንበት የኢትዮጵያ የሰላም አምባሳደር በመሆን ያለውን እውነታ ልናስተዋውቅ ይገባናል። በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ብቻ በርካታ ሊጎበኙ የሚገባቸው የቱሪስት መዳረሻዎች ስፍራዎች አሉ። እነዚህን ማየት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም መጥተው እንዲጎበኙ ማስተዋወቅ ለዳያስፖራው ትልቅ የቤት ስራ ነው ሲሉ ይናገራሉ።
‹‹ይህን ያህል ከባድ ወደ እናት ሀገራችሁ ኑ የሚልን ሀገራዊ ጥሪ ተቀብሎ የመጣ ሁሉ ለጥቂት ሽርፍራፊ ትርፍ ብሎ የውጪ ምንዛሬን በጥቁር ገበያ መቀየር የለበትም። ማንኛውንም የሚያደርገውን ግብይት በህጋዊ መንገድ በባንክ መሆን ይኖርበታል። የቱሪዝም ቁሳቁሶችን በመግዛት ጭምር ዘርፉን መደገፍ አለበት።›› ያሉት ደግሞ ላለፉት አስራ ሰባት ዓመታት ነዋሪነታቸውን በእንግሊዝ ሀገር ለንደን ከተማ አድርገው የቆዩት አቶ በቀለ ወዬቻ ናቸው።
አቶ በቀለ እንደሚናገሩት፤ አሜሪካም ሆነ አውሮፓውያን ሊያንበረክኩን የሚፈልጉት በአጎዋ ላይ እንዳሳዩን ሁሉ በተለያየ የኢኮኖሚ አሻጥር ነው። ለዚህ ደግሞ ትኩረት አድርገው የሚሰሩት እንደ ቱሪዝም ዘርፍ ባሉ የውጪ ምንዛሬ በምናገኝባቸው እንቅስቃሴዎች ላይ ነው።
ይህንን አሻጥር የማክሸፍ አቅም ያለው ከሀገሩ ውጪ የሚኖረው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ነው። ይህንንም ለማድረግ ከዳያስፖራው ሁለት ነገሮች ይጠበቃሉ። የመጀመሪያው አሸባሪው የሕወሓት ቡድን እያከናወነ ያለውን ሀገር የማፍረስ ተልእኮ አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት ድጋፍ እየሰጡት እንደሆነ ይታወቃል። ከእነዚህም መካከል እንግሊዝ አንዷ ናት። እኔ በዚህ ወቅት ቤተሰቦቼን ይዤ ወደሀገሬ የመጣሁትም ይህንን እኩይ ሴራ ለማፍረስና በውጪው ዓለም በአንዳንድ ሚዲያዎች ተዛብቶ እንደተቀመጠው ኢትዮጵያ በጥልቅ ችግር ውስጥ አለመሆኗን ለማሳየት ነው። በመሆኑም ልክ እንደኔ ሁሉም ከያለበት ለጥቂት ግዜም ቢሆን አገሩ እየመጣ ያለውን ነገር ከሶስተኛ ወገን ወሬ ለዚያውም ቀና ከማያስቡልን ሀይሎች ከመስማት በአይኑ ሊመለከት ይገባል። ይህን በማድረጉ በኢኮኖሚ ዘርፍ ከሚያደርገው አስተዋጽኦ ባለፈ የሚያስከትለው ፖለቲካዊ ፋይዳ ከፍተኛ ይሆናል።
በሁለተኛ ደረጃ ሀገራችን የውጪ ምንዛሬ እንደምትፈልግ እኛ በውጪ የምንኖር ኢትዮጵያውያን ደግሞ ይህንን ማድረግ እንደምንችል ይታወቃል። በዚህ ረገድ ሁላችንም በህጋዊ መንገድ በባንኮች ገንዘባችንን ማስተላለፍ አለብን። ይህንን ማድረጋችንንም በማሳወቅ ለሌሎች አርአያ ልንሆን ይገባል። ለምሳሌ እኔ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በህጋዊ መንገድ ገንዘብ መንዝሬ ነበር። ይህንን ሂደት በቪዲዮ ቀርጬ በቲውተር ገጼ ላይ በማስፈር ለማውቃቸውና ለሚከታተሉኝ በሙሉ እንዲዳረስ ማድረግ ችያለሁ። የአጎዋ ችግርና ሌላውንም ለመፍታት ዳያስፖራው በዚህ ረገድ ያለው ትልቅ አቅም አሟጦ ሊጠቀም ይገባል ሲሉ ይናገራል።
በተመሳሳይ ሰላሳ ሶስት ዓመት በጀርመን ሀገር ኑሯቸውን ያደረጉት ወይዘሮ አሳየች ታምሩ ይባላሉ። ከውጪ እየተደረገ ያለውን ጫና ለመቀነስ የዳያስፖራው ተሳትፎ ወሳኝ እንደሆነ ይናገራሉ። እርሳቸው በሁሉም መስክ ለሀገራቸው ጠበቃ ሆነው እያገለገሉ ናቸው። ለአገራቸው ጠበቃ ሆነው የዓለምን የተንሻፈፈ አመለካከት ለመቀልበስ በፖለቲካው መስክ ጭምር ሽንጣቸውን ይዘው ይሟገታሉ።
ወይዘሮ አሳየች እንደተናገሩት ለዳያስፖራው የተደረገውን ጥሪ እኛ ከመቀበል አልፈን ባገኘነው ሚዲያ በሙሉ ለሌሎችም እያስተላለፍን እንገኛለን። ኢትዮጵያ ሀገራችን ነች። ከሀገራችን ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም፤ የፖለቲካ ልዩነት አሁን ካለው ችግር በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው አይገባም። አሁንም እዚህ የተገኘነው አጠቃላይ የህዝባችንንና የሀገራችንን ችግር ለመካፈል ነው። አውሮፓውያን በተለይ አሜሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን የውጪ ዜጎች ከኢትዮጵያ ውጡ፤ ውጪ ያለውንም ማህበረሰብ እንዳትሄዱ እያለች ስታሸብር ነበር። በተለይ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑትን እንዲወጡ በጣም ጫና ሲፈጥሩ ቆይተዋል።
የዚህ ስራቸው መጨረሻ ግብ ህዝቡ ላይ ሽብር በመንዛትና ፍርሃት በመፍጠር የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በማሽመድመድ መንግስትን ለራሳቸው አላማ ተገዢ ማድረግ ነበር። የእኛ እዚህ መገኘት እንድምታው ብዙ ነው። አንድም ለእናንተ የኢኮኖሚ ጫና የሚንበረከክ ህዝብ አይኖርም። የሀገራችንንም ኢኮኖሚ በአየር መንገዱም ሆነ በቱሪዝሙ እኛው እንደግፋለን። የእናንተም እርዳታ ቢቀር አንንበረከክም የሚለውን ለአውሮፓውያንና ለአሜሪካውያን ለማስተላለፍ ነው።
ሁለተኛው ከሁሉም በላይ ደግሞ ወደ ሀገራችን በመምጣታችን የሚኖረው ፋይዳ በአሸባሪው ቡድን እኩይ ስራ የተጎዳውን ኢኮኖሚ ለማስተካከል እየተሰራ ያለው ስራ በውጪ ምንዛሬ እጥረት እንዳይጎዳ የአቅማችንን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነው። ለዚህም የተለያዩ በአላትን በሀገራችን እያከበርን፤ የምንገዛቸውን የእለት መጠቀሚያም ሆነ የስጦታና ሌሎች ቁሳቁሶችን ከአገር ውስጥ በመጠቀም የአገር ውስጥን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማስፋፋት እንዲሁም ራሳችን አገልግሎት ይዘን የምንመጣውንም ሆነ ለቤተሰቦቻቻን የምንልከውን የውጪ ገንዘቦች በህጋዊ መንገድ እየላክን የተደቀነብንን ችግር ለመቅረፍ የምንሰራ ይሆናል።
በሌላ በኩል የቱሪዝም ዘርፍ ከሰላም ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለው መሆኑ ይታወቃል። በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሀገራትም ሰላም ከሌለ የቱሪዝም ዘርፉ መቀዛቀዙ አልያም ለተደራራቢ ችግር መዳረጉ የማይቀር ነው። በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ የሚለየው ግን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተዳከመው የቱሪዝሙ ዘርፍ በጦርነቱም እግር ከወርች መታሰሩ ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው ችግር በቀጥታ ለቱሪዝም እንቅስቃሴ መሰናክል መፍጠሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ከዛ በባሰ አውሮፓውያንና አሜሪካውያን በፈጠራ ያስወሩት የሰላም መደፍረስ ዜና ቱሪዝሙን በከባዱ እየጎዳው ይገኛል።
አሁን እኛ በአካል በመገኘት እንዳረጋገጥነው በኢትዮጵያ ጦርነት ያለው በጣም በተወሰኑ ቦታዎች ነው። ዛሬም በርካታ የቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች ሰላም ናቸው። ማንኛውም ጎብኚ ሄዶ ሊጎበኛቸው ይችላል። ጥቂት የማይባል ዳያስፖራ በተለያዩ ሀገራት ጉብኝት እንደሚያደርግ ይታወቃል። ይህንን ወደ ሀገር ውስጥ ማዞር ይጠበቃል። ከዚህ በፊት ልምዱ የሌለን እንኳን ብንሆን ሀገራችንን ከገጠማት ችግር ለመታደግ መረጃ በማሰባሰብ የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎችን መጎብኘትና በአላትን ከህዝባችን ጋር የማክበር ልምድን ልንጀምር ይገባናል።
ዛሬ ላለንበት ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ለሌላም ነገር መሰረቱ የሰላማችን መረጋገጥ ነው። ለዚህ ደግሞ እንኳን መንግስትን በኢኮኖሚ መደገፍ ይቅርና መክፈል ያለብንን መስዋእትነት ከፍለን ነጻ መውጣት አለብን። ይህን ሳናደርግ ቀርተን ለግዜያዊ ጥቅም ለውጪ ሀይሎች ጣልቃ ገብነት በራችንን የምንከፍትና የምንበረከክ ከሆነ የሚገጥመን የሶርያና የሊቢያ እጣ ይሆናል። ስለዚህ አሁን ያለውን የአሜሪካና የአውሮፓውያን ጫና በመጋፈጥ ጠንካራ የማትንበረከክ ሀገር ለመፍጠር በሚደረገው ሂደት ዳያስፖራው ቀዳሚ ተሳታፊ ሊሆን ይገባል ሲሉ ምክረ ሀሳባቸውን አካፍለውናል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 24/2014