ውትድርና ራስን ለመስዋዕትነት በማዘጋጀት ሀገርንና ሕዝብን ከማናቸውም ጥቃት ለመከላከል ብቁ የሚኮንበት ሙያ ነው። ከራስ በፊት ለሕዝብና ለሀገር የመሰለፍ ክብርን መቀዳጃም እንደሆነ ብዙዎች ምስክርነታቸውን ይሰጡበታል። ምክንያቱም ይህ ሙያ እንደሌሎቹ የሙያ መስኮች ፍላጎትና ተሰጥኦ ብቻ አለያም እውቀትና ጉልበት ብቻ ሳይሆን የሚጠይቀው ጥልቅ የሆነ የሀገር ፍቅር ስሜትን ነው። እናም ለሀገርና ለሕዝብ ሲባል ደምና አጥንትን ለመገበር ዝግጁ መሆን ቅድሚያ የሚሰጠው ሙያ እንደሆነ ማስቀመጥ ይቻላል።
ደከመኝ፤ ታከተኝ ሳይሉ ሀገርን ማገልገል፣ ሳይሰስቱ በፍቅር ሕይወትን መስጠት፣ በመርህ ኖሮ በመርህ መሰዋት መሆንም ነው ውትድርና። በዚህም ብዙዎች ቁርጠኛ ሆነው ተቀላቅለውት ዛሬ ድረስ ሀገርንና ሕዝብን ከወራሪ እየታደጉበት ያለ የተከበረ ሙያ ነው። ራሳቸውንም ቢሆን ባለሀገር አድርገዋል። ከእነዚህ እንቁ የቁርጥ ቀን ልጆች መካከል ኮማንደር ይበልጣል ባህሩ አንዱ ናቸው። እኚህ ሰው ዛሬ ላይ የወገናችንን ደማቅ የጀግንነት ታሪክና የጠላቶቻችንን የውርደት ጉዞ በብዕር ከትበን ለትውልድ እንድናስተላልፍ እድሉን ሰጥተውናልና በ‹‹ሕይወት ገጽታ›› አምዳችን ላይ እንግዳችን አድርገናቸዋል።
ውትድርናን ከልጅነታቸው ጀምሮ የናፈቁት ብቻ ሳይሆኑ የኖሩበት በመሆኑም የሙያውን ልዕልና በሚገባ በሕይወታቸው ውስጥ ያሳዩናል። ዛሬ ድረስ ስለሙያው ጥልቅ ፍቅር እንዳላቸውና ለሀገራቸው የሚዋደቁ እንደሆኑም ይነግሩናል። በተለይም በጋሸና ግንባር ብቻ ያደረጉት ተጋድሎ ብዙዎችን ያስገረመ ስለነበር ልምዳቸውን ያጋሩናል። ብዙ ቁም ነገሮችንም ያስጨብጡናልና ተማሩባቸው ስንል ጋበዝናችሁ።
ልጅም ባለታሪክ ነው
ኮማንደር ይበልጣል ሁልጊዜ ውትድርናን ሲያስቡት ታሪክ እየሰሩ መሄድ እንደሆነ ያምናሉ። ለዚህም በቤታቸው ውስጥ በየቀኑ ያዳምጧት የነበረችው ሬዲዮ ትልቁን ስፍራ ትይዛለች። ከሁሉም በላይ ግን አባታቸው የሚነግሯቸው ታሪክ እርሳቸውን ወታደር አንዲሆኑ ይገፋፋቸው ነበር። አባታቸው ባለታሪክ እንዲሆኑ አድርገውም አስተምረዋቸዋል። ምክንያቱም የዛሬው እንግዳችን አባታቸው ዘማችም ሀገር ወዳድም ነበሩ። እናም የልጃቸውን የተረዱት አባት ልጃቸው በሚፈልጉት ሙያ ላይ እንዲሰማሩ የማያደርጉላቸው ድጋፍ ነገር አልነበረም። ይህ ደግሞ እንግዳችንን በውትድርናው ቤት በሙዚቃው ዘርፍ ለመሰማራት እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። ገና የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ እያሉም በአካባቢው ይህንን ተግባር በሚፈጽሙ ታዳጊ ኪነቶች ውስጥ የመሳተፋቸው ምስጢርም ይህ ነበር።
እንግዳችን የተወለዱት ቀደም ሲል በወሎ ጠቅላይ ግዛት በሚባለው በአሁኑ ደግሞ ሰሜን ወሎ ውስጥ ኮን ወረዳ፣ በቋና ቀበሌ፣ በጁሃ ማርያም በሚባል ቦታ በ1959 ዓ.ም ነው። እናም በዚያ አካባቢ ባሉ የሙዚቃ ክበባትና ታዳጊ ኪነቶች ውስጥ በመሳተፍ ፍላጎታቸውን አርክተዋል። በዚያ ላይ በክበባቱ ውስጥ ልማትና ራስን መፈለግም አለና ዛሬ ያሉበትን የውትድርና ሕይወት ከአባታቸው በመቀጠል መንገድ የጠረገላቸው ይኸው ተግባራቸው ነው።
አባታቸው በአካባቢው የታወቁ አርሶ አደርም ናቸው። ስለዚህም ከመንሽ ቀጥሎ ጦር ሰብቀው ሀገራቸውን ከጠላቶቿ ታድገዋል። ልጆቻቸውም ይህንኑ አቋማቸውን እንዲከተሉ ይፈልጋሉ። ስለሆነም በቀን ጉዟቸው ውስጥ ሀገራዊ ሁኔታን ሳያካትቱና ሳይናገሩ አንድም ቀን አልፈው አያውቁም። ይህ ደግሞ ለኮማንደር ትልቅ አቅም ነበር። ሀገራቸውን ከመውደድም በላይ ታሪክ ሰሪነታቸውን እንዲያጠነክሩ አግዟቸዋልም። ለሀገር መታገል ምን አይነት ስሜት እንዳለው እንዲረዱም አድርጓቸዋል። በተለይም ውትድርናውን በደንብ እንዲያውቁት በብዙ መልኩ አሳይተዋቸዋል።
ተተኪዎቹ እነርሱ እንደሆኑና በሥራቸው ሁሉ ለሀገራቸው እንዲኖሩ የሚያግዛቸው ደግሞ የሀገር ፍቅር እንደሆነና ያንን ለመረዳት ሀገር በምትፈልጋቸው ሁሉ ቀድመው መገኘት እንዳለባቸውም ይመክሯቸው ነበር። ለዚህ ደግሞ ዋነኛ መንገድ ቀያሹ ውትድርናውን መቀላቀል እንደሆነ ከእርሳቸው ተምረዋል። እናም ኮማንደር የሙያ ሁሉ ታላቅ ውትድርና ነው እንዲሉና አምነውበትም እንዲቀላቀሉት ሆነዋል። ሁሉም ሙያ የራሱ የሆነ ባህልና ስርዓት ያለው ቢሆንም በውትድርና ሕይወት ውስጥ እንዳለው ሀገር ወዳድነት የትም አለ ብለውም አያስቡም። በዚህም ለሀገር መሰዋት ለቤተሰብ መኖር እንደሆነ የምንማርበት ትምህርት ቤት ነው ይሉታል ውትድርናን። ኖሬ ሳየውም እውነትነት አለው፤ ደስተኛ ሆኜበታለሁም ይላሉ።
ከፍላጎታቸው ስንወጣ ኮማንደር ቤተሰባቸውን በማገዝ ዙሪያም ወሰን የማያውቁ ታዛዥ ልጅ ናቸው። በሥራ የሴት የወንድ አይሉም። በእርግጥ ይህ ክፍፍል በአካባቢው አለ። ለእርሳቸው ግን ይህ አይሰራም። ዛሬም ድረስ መንኩሰው እንኳን እታተይ የሚሏቸውን እናታቸውን በጣም ስለሚወዱ የሴት ሥራ ሳይሉ ያግዟቸዋል። እንጨት ለቀማና ውሃ መቅዳት እንዲሁም የቤት ውስጥ ሥራ መስራትም ለእርሳቸው ብርቅ አይደሉም። በአባታቸው በኩልም ቢሆን የግብርና ሥራውን ቀጥ አድርገው ይሠራሉ። ከብት ማገድ ላይም ጎበዝ ናቸው። በዚህም በሁሉም ዘንድ ይወደዳሉ።
በባህሪያቸው ጭምት አይነት ልጅ ሲሆኑ፤ ጨዋታ ወዳድና መታዘዝ የሚያስደስታቸው ናቸው። ይህ የሚሆነው ደግሞ ለቤተሰብ ብቻ አይደለም። ለአካባቢው ማህበረሰብ መታዘዝ ግዴታዬ ነው ብለው ያስባሉና ያደርጉታል። ምክንያቱም ቤተሰብ የአካባቢው ማህበረሰብም ነው ብለው ያስባሉ። ለእድገታችን ጡብ እየደረደረን ማገልገል ውዴታ ሳይሆን ግዴታ ነው ብለው ያምናሉ። በዚህም የታዘዙትን ብቻ ሳይሆን መሆን ያለበትን ያደርጋሉ። ምርቃትንም ይቀበላሉ።
መማርና ዋጋው
የኮማንደር የትምህርት ጅማሮ ‹‹ሀ›› ያለው በቄስ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ ከዳዊት አልፈው የቅዳሴና ሌሎች ትምህርቶችን በአካባቢው አሉ ተብለው በሚጠሩ የኔታዎች ዘንድ ተምረዋል። ብዙ ትምህርቶችን ከአብነቱ ከቀሰሙ በኋላም መሰረታቸውን አጽንተው የአስኳላውን ትምህርት ተቀላቅለዋል። መነሻቸው አብነቱ መሆኑ ደግሞ ለዘመናዊው ትምህርት ትልቅ አቅም ፈጥሮላቸው ነበር። ለዚህም ማሳያው ከአንደኛ እስከ አስረኛ ክፍል ሲማሩ አንድም ቀን ከደረጃ ተማሪነታቸው አለቀቁም። ለአካባቢው ልጅ ተምሳሌትም ነበሩ።
እርሳቸው ዘመናዊ ትምህርቱን ሲቀላቀሉ ከአጎታቸው ልጅ በስተቀር በአካባቢው ላይ የተማረ ሰው አልነበረም። ተምረው ከአካባቢው የወጡትም ሁለቱ ብቻ ናቸው። ይህ ደግሞ ዛሬ ድረስ የሚኮሩበት እንደሆነ አጫውተውናል።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን ሲጀምሩ በእግራቸው 10 ኪሎሜትር እየሄዱ እንደነበር የሚያስታውሱት ኮማንደር ይበልጣል፤ ትምህርትቤታቸው የተሰራው በስዊዲኖች አማካኝነት ሲሆን፤ ቋና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይባላል። እናም በዚህ ትምህርት ቤት እስከ ስድስተኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።
ሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውን የተከታተሉት ደግሞ መጀመሪያ ይማሩበት ከነበረው ትምህርት ቤት የእግር ጉዟቸውን በእጥፍ ጨምረው ነው። ምክንያቱም በአቅራቢያቸው ትምህርት ቤት ስላልነበረ ነው። ሰባት እና ስምንት ወደተማሩበት ኮን ትምህርት ቤት ለመድረስ ብቻ 20 ኪሎሜትር ይጓዛሉ። ሲመለሱም እንዲሁ። በዚህ ሁኔታ ሁለት ዓመታትን አሳልፈዋል። ግን አንድም ቀን ተበሳጭተው አያውቁም። ምክንያቱም መማር ከዚያ በላይ ዋጋ እንዳለው ይረዳሉ። ብዙ ደክሟቸውም ቢሆን ማድረግ ያለባቸውን ከማድረግ አይቆጠቡም።
በድካም ውስጥ ሥራ፣ በሥራ ውስጥ ደግሞ ማጥናትና ትምህርታቸውን በሚገባ መከታተል ውስጥ ያሉት ባለታሪካችን፤ ይህ ሁሉ ጫና ቢኖርባቸውም በትምህርታቸው የቀነሱበት አንድም ሁኔታ የለም። እንዲያውም በየጊዜው በፈተናቸው ውስጥ ብርታታቸውን ያያሉ። የወደፊት ህልማቸውንም ያስባሉ። በእርግጥ ከዚህም በኋላ ቢሆን ለመማር ርቀት መጓዝ ግዴታቸው እንደሆነ ያውቃሉ። ምክንያቱም ከዘጠነኛ ክፍል በኋላ ያለውን ትምህርት ለመከታተል በቀን ቢያንስ ከ50 ኪሎ ሜትር በላይ መጓዝ አለባቸው። ስለዚህም ይህንን ሁኔታ ለመቀነስ ከአጎታቸው ልጅ ጋር ተከራይተው ቅዳሜና እሁድ ወደ ቤተሰብ እየተመላለሱ አይበገሬነታቸውን አሳይተዋል። በንፋስ መውጫ ጋይንት ከተማ ላይ ዘጠኝና አስረኛ ክፍልን ተምረዋልም። ከዚህ በኋላ ግን ትምህርቱን አልቀጠሉም። ለዚህ መንስኤው ደግሞ ጉዞው ሳይሆን ፍላጎታቸው ነው።
የልጅነት ህልማቸው ወታደር መሆን ነው። እናም ያንን የሚያሳኩበት አጋጣሚ ደግሞ አስረኛ ክፍል ላይ የገጠማቸው እድል ነው። እናም ያንን መተው ስላልፈለጉ ከአስረኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጠው ውትድርናውን ተቀላቅለዋል። ፍላጎታቸው እውን እንዲሆን የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ ተመኝተው ነበር። ሆኖም ገና ልጅ በመሆናቸውና የወረዳው አስተዳዳሪ ስላስቆማቸው አልተሳካላቸውም። ስለዚህም ዳግም ያገኙትን እድል መተው አልፈለጉም። ለዚህም ነው የዛሬውን የፖሊስ ሙያን ገና በ18 ዓመታቸው የተቀላቀሉት።
እንግዳችን ውትድርና ውስጥም የተለየ ትምህርት እንዳለ ያውቃሉ። ሳይንሱ በተከታታይነት ከምንማረውም የሚያንስ እንደማይሆን ይረዳሉ። እንደውም የውትድርና ሳይንስ ከዚያም እንደሚልቅ ያስባሉ። ይህንን ደግሞ ከገቡ በኋላ እንዳረጋገጡ ይናገራሉ። በዚህም ነው በ1976 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፖሊስ ሰራዊት ከአስረኛ ክፍል ወታደሮችን መልምሎ ማሰልጠን እንደሚፈልግ ሲገልጽ ሳያቅማሙ ሙያውን የገቡበት። ይህ ደግሞ ሰፊ እድልን እንደሰጣቸው ያምናሉ።
በውትድርናው መስክ የመጀመሪያ ትምህርታቸው በለገዳዲ የፖሊስ ማሰልጠኛ የወሰዱት ስልጠና ሲሆን፤ ዓመት ከሁለት ወር ፈጅቷል። አራተኛ ኮርስ ይባላልም። በከፍተኛ ውጤትም ተመርቀውበታል። ከዚያ የምርመራ ኮርስ ትምህርትን ተማሩ። በብላቴ ኮማንዶ የፖሊስ ማሰልጠኛም ተመላልሰው የተለያዩ ኮርሶችን ወስደዋል። ለምሳሌ የአድማ ብተና፣ የቤት ውስጥ ውጊያ፣ የፎቅ ላይ ውጊያ፣ የመረጃ አሰባሰብ ስልትና ምርመራ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። የኮምፒውተርና መሰል ስልጠናዎችንም እንዲሁ በፖሊስ ኮሌጆች ውስጥ ወስደዋል። አሁንም ውትድርናውን በሚመለከት ማወቅ ያለባቸውን ነገር ከመማር አልቦዘኑም፤ ይቀጥላሉም።
የተማሩትን መሥራት
የመጀመሪያ ሥራቸው አዲስ አበባ ላይ የከተሙበት ነው። በጉልበትም በእውቀትም ብርቱ ነበሩና ጥሩ መርማሪ ፖሊስ ሆነው በአራት ኪሎ ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ እንዲሁም ወደ ካሳንቺስ ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተዛውረው አገልግለዋል። ሁለት ዓመት ያህልም በቦታው ላይ ቆይተዋል። ከዚያ ከዛሬው የሀገር ነቀርሳ ከሆነው ሕወሓት ጋር ጦርነት መግጠም ነበረባቸውና ወደ ትግራይ ክፍለ ሀገር ሄዱ። ከሁለት ዓመት በላይም ተዋጉ። ግን መኪናው ላይ በተጠመደ ፈንጅ አማካኝነት ብዙዎች ሲጎዱ እርሳቸውም ተመተዋልና ተመለሱ።
ወደነበረ ማንነታቸው ሲመለሱ በቀድሞው ምስራቅ ሸዋ ፈንታሌ ወረዳ በአሁኑ አፋር ክልል እንዲሰሩ የተመደቡት ኮማንደር ይበልጣል፤ 1983 ዓ.ም ላይ ከፍተኛ ውጊያ ውስጥ ገብተው እንደነበር ያስታውሳሉ። በውጊያው ከ27 ሰዎች ውስጥ ሰባት ያህሉ ሲሞቱ ሌሎቹ ቦታውን ለቀው ወጡ። አለቃቸውና እርሳቸው ብቻም ቀሩ። አለቃቸው እርሳቸውን እንዲወጡ
ጎትጉተዋቸው ነበር። ሆኖም እርሳቸውን ትተው መሄድ እንደማይፈልጉ ገለጹ። በዚህም አለቃቸው ተመትተው ሞቱ። ብቻቸውንም ቀሩ። ግን ብዙ ቦታ ላይ ያውም ፊት ደረታቸውን ተመተው ከመፋለም ማንም አላገዳቸውም። ከጻድቃን ገብረ ተንሰይ ጋር ፊት ለፊት እንደተጋጠሙም አይረሱትም። ሲያስታውሱት ሦስት ጥይት በደረታቸው ማለትም በግራ ጎናቸው በቀኝ በኩል ደግሞ በቦንብ ፍንጣሪ ቆሳስለው ነበር። እጃቸውም እንዲሁ ተመትቷል። ነገር ግን ሳይማረኩ፤ የነበረውን ንብረታቸውንም ሳያስነኩ ታግለው ተርፈዋል። ለዚህ ደግሞ የአፋር ሕዝብ በተለይ የአዋሽ ነዋሪ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል ብለውናል።
እርሳቸው በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ የተቀበላቸውና ወደ ሕክምና የወሰዳቸው የአፋር ሕዝብ ነበር። ወደ አዲስ አበባ እስኪመለሱ ድረስ ተንከባክበዋቸዋል። ሁኔታው የገረማቸው እርሳቸው ብቻ ሳይሆኑ የወያኔ አመራሮች ጭምር ናቸው። ምክንያቱም በወቅቱ ‹‹የዚህ ሀገር ልጅ ነህ፤ ወልደሃል አግብተሃል›› ብለዋቸው ነበር። ሁኔታውን ሲረዱም ‹‹ምንም እንኳን እርስ በእርስ ለዓላማችን ብንዋጋም የሕዝብ ልጅ መሆንህን በሚሆነው ነገር ተረድተናልም›› እንዳሏቸው አይረሱትም።
ኮማንደር ይበልጣል በአፋር ክልል ቆይታቸው በምርመራና በጣቢያ ኃላፊነት ሥራ ላይ አገልግለዋል። በሱማሌ ክልል ደዋሌ ውስጥም እንዲሁ። ይህ ደግሞ የሁለቱን ክልሎች ልዩ የኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዲያዩ እንዳስቻላቸው ይናገራሉ። ዛሬ ድረስም የእነርሱን የሀገር ልጅነት ከእኔ ውጪ የሚመሰክር የለም ይላሉ። ምክንያቱም አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ጠላት ሲያንዣብብባቸው ድባቅ መምታትን የሚያውቁ ፣ ለሀገራቸው ልዩ ክብርን የሚሰጡና ቅድሚያ ለሀገር የሚሉ ናቸው። ወደፊትም ይህ መለያቸው እንደሚቀጥል አምንባቸዋለሁም ብለውናል።
ቀጣዩ የሥራ ቦታቸው የሥራ ጅማሮዋቸውን ያደረጉበት አዲስ አበባ ፌደራል ፖሊስ ሲሆን፤ በጸጥታና ሕግ ማስከበር ውስጥ የሻለቃ አመራር ሆነው ከ2002 ዓ.ም ጀምረው ዘመቻውን እስከተቀላቀሉበት ድረስ ያሉበት ነው። በዚህ ደግሞ ብዙ ተግባራትን እንደፈጸሙ ይናገራሉ። ከሁሉም የማይረሳቸው ግን የሰኔ 16ቱ የግድያ ሙከራ እንደሆነ አጫውተውናል። የድጋፍ ሰልፉ ከመካሄዱ በፊት በአዲስ አበባ የፌደራል ፖሊስ ስብሰባ ተካሂዶ ነበር። እናም በዚያ ስብሰባ ላይ መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች ሲነጋገሩ የግድያ ሙከራ እንደሚኖር አሳስበዋል። በዚህም ሰራዊቱ ልዩ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ሆኖ የተቃጣውን ጥቃት ከአከሸፉት መካከል አንዱ እንዲሆኑ አግዟቸዋል። ሕዝቡ እንዲረጋጋ መንገድ የጠረጉም ናቸው። ምክንያቱም ጠላት ምን ያህል እንደሚጓዝ በሴራው ያውቁታልና ይህ እንዳይሆን መደረግ ያለበትን ሁሉ አድርገዋል።
እንግዳችን አሁን እየተደረገ ባለው ዘመቻ ውስጥ በማስተባበርና ያላቸውን ልምድ በማካፈል ከበላይ አመራሮች ጋር በመሆን እየሠሩ ይገኛሉ። በአብዛኛው ተግባራቸውም ፊት መሪ በመሆን ላይ የተመሰረተ ነው። በሰሜን ዕዝ ውስጥ በ51ኛና 34ተኛ ክፍለ ጦር ውስጥ ሆነው ከጓዶቻቸው ጋር ብዙ ምሽጎችን ሰብረው ድሉን ለሀገራቸው ልጆች አብስረዋል። ወደ ፊትም ይህንኑ ተግባራቸውን እንደሚቀጥሉበት አውግተውናል። በተለይ አካባቢውን በደንብ ስለሚያውቁት ብዙ ተሞክሮን ያካፍላሉና እድሉን መጠቀም እፈልጋለሁም ነው ያሉን። ምክንያቱም ጠላት እስካልጠፋ ድረስ ሀገር ሰላም አትሆንምና ለብቻ የሚከፈል መስዋዕትነት መኖር የለበትም የሚለው አቋማቸው ነው።
ወታደር መሆንና እይታው
በውትድርና ሙያ ውስጥ ውድ ሕይወትን መስጠት እንጂ መቀበል የለም። ለራሴ ብለህ የምትቀንሰው ቀን የለም፤ ትልቁ ሀብቱ ሀገርንና ሕዝብን መጠበቅ ብቻ ነው። በሕይወት አለመኖር እንኳን ቢመጣ በውትድርና ሙያ ውስጥ ለሀገርና ለሕዝብ ተብሎ የተከፈለ ዋጋ ስለሆነ ጥቅም አለው። ዋጋውም ልዩ ነው። ምክንያቱም መስኩ የሚፈልገውም ይህንኑ ስለሆነ። በእርግጥ ዛሬ የእናት ጡት ነካሾች ይህንን ነገር ዋጋ ሊያሳጡት ጥረዋል። በብዙ መንገድም ዓላማውን አስተውት ነበር። ያው ጀግና መስመሩን አይስትምና አስመለሰው እንጂ። እናም ውትድርና ልዩ ነው ይላሉ።
እንደእርሳቸው ገለጻ፤ በየትኛውም ዓለም ከውትድርና ሙያ ውጪ ለሌላው መኖር የለም። ታላቅ መስዋዕትነት የሚከፈልበትም እንዲሁ። በደማቸው መፍሰስ፣ በአካላቸው መጉደል፣ በአጥንታቸው መከስከስ፤ በውድና መተኪያ በማይገኝለት ሕይወታችሁ መስዋዕትነት ጭምር ሀገርን የሚያቆም ሙያ ይህ ብቻ ነው። አሁን እየመጣ ያለው ድልም የእርሱ የመስዋዕትነት ውጤት ነው። ጎጥ፣ ብሔር፣ ቀለም አለያም ሀይማኖት አይገድበውም። አንድና አንድ ገደቡ ሀገር ብቻ ነው። በሀገር ተወልዶ በሀገር ይሞታልና በተግባሩ እኮራለሁ ይላሉ ስለ ሙያው ሲናገሩ።
በጋሸና ግንባር ላይ የነበረውን የፊት መሪነታቸውን እያነሱም ወታደር መሆን ምንኛ እንደሚያስደስት ይቀጥላሉ አሁንም በማብራራት። በተለይ ግንባሮች ላይ የነበረውን ሁኔታ ሲያነሱ የደስታ ሲቃ ይይዛቸው ነበርም። ምክንያቱም የወታደሩ ጥንካሬን በብዙ መልኩ አይተዋል። አንዱ ጠላት ከወረረበት እስከ በረገገበት ድረስ ያለው ፍጥነት ሲሆን፤ ከዚህ በኋላ ማንም ቢመጣ አይችለንም አረጋግጧል ባይ ናቸው። ወደ ፊትም ቢሆን ሁሉም ከኢትዮጵያ የሚቀድም ምንም አጀንዳ እና ሕይወት የለውም እንዲል አስችሎታል ይላሉ።
በነበረው ውጊያ አይዞህ እየተባሉ የተፋለሙበት አጋጣሚ እንደነበርና በእርሳቸው አገላለጽ «ልበላሽ ነበር» ያሉበት ጊዜ እንደነበር የሚያነሱት ኮማንደሩ፤ ብቻቸውን መሃል ገብተው ሊያዙ እንደነበርና ከመማረክ ራስን ማጥፋት ብለው ሽጉጥ ራሳቸው ላይ ደቅነው ኮሎኔል ኪሮስና ሌሎች ጓዶች በመድረሳቸው ነገሮች ስለተስተካከሉ እንደተውትም አይረሱትም። እናም ውትድርና አለመማረክም ነው። ስለአገር ራስን አሳልፎ መስጠትም ነውና ብዙዎች አሁን ባለንበት ሁኔታ ይህንን እያረጋገጡ ይገኛሉም ብለውናል።
አሁን በሁሉም አይዞህ ባይነት ድሉን አብረን ተቀዳጅተናል። እኛም ተርፈን ሀገራችንን ታድገናል የሚሉት ኮማንደር ይበልጣል፤ ዛሬን ሲያስቡት ዳግም ወጣት መሆን ቢቻል ብለው ያስባሉ። ምክንያታቸውም ጉልበቱና አቅሙ በብዙ መንገድ ይኖረኝና ሀገሬን ቶሎ ከችግሯ ማውጣት እችል ነበር። ይሁን እንጂ አሁንም ባለሁበት ሁኔታ ይህንን እንደነፈኳት አይሰማኝም። ግን አንድ ነገር አደራ ማለት እፈልጋለሁ። ከሽማግሌው ይልቅ ወጣቱ ለድሉ ፍጥነት ይበጃልና መከላከያን ይቀላቀል። ሀገሩን ከአለችበት ፈተና ይታደግ ሲሉ ያስገነዝባሉ።
ውትድርና ግልፅ ያለና የነጠረ ተልዕኮ አለው። የሀገርን ሉዓላዊነት መጠበቅና ሕገመንግሥታዊ ስርዓቱን መጠበቅ ደግሞ አንዱ ተልዕኮው ነው። ስለዚህም ዋነኛ ሥራው አሸባሪዎችን ድባቅ መምታትና መቅበር፤ በዚህም የሕዝብን ሰላም ማረጋገጥ ነው። መስዋዕትነቱ ቅኝ ገዢዎችን ተላላኪዎቻቸውን በማንበርከክ፤ ለትውልድ ለሚተርፍ ታሪክ ማስቀመጥ ነው። እናም ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ነፃነትንም የሚያደርገው በመሆኑ ተግባሩን በብዙ መልኩ እያስመሰከረ መቀጠል አለበትም ባይ ናቸው።
አሸባሪዎቹ በውርደት የሚመክቱት፣ በክህደት ቅጥፈት ለግፍ ለብተና፣ በጥላቻ፣ በከፋፋይነት ሕዝብን ለማተራመስ የማያደርጉት ነገር የለም። በዚህም የመጨረሻ አቅማቸውን አሟጥጠው፤ ለጥፋት ያስቀመጧቸውን የመጨረሻ ካርታዎች በመምዘዝ ብዙ ግፍ አድርሰዋል። ነገር ግን አወዳደቃቸው ምን እንደመሰለ አይተነዋል። ለትውልዳቸው እንኳን የቀረ ነገር የላቸውም። የእናት ጡት ነካሽነታቸው ካልሆነ በቀር። ይሁን እንጂ ሞራልና ኃፍረት ስለሌላቸው ነገም ያደርጉታል። እናም እንደ ፌንጣ እንዳይዘሉ ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህም ወታደሩ ቁርጠኛ መሆኑን ከእኔ ጭምር ማረጋገጥ ይቻላል ብለውናል።
ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ተፈትናለች። ነገር ግን የአድዋ ጀግኖች፤ በየዘመናቱ የተፈጠሩ አርበኞች በመስዋዕትነታቸው ህያው አድርገዋታል። ለዚህ ደግሞ የጸጥታ ኃይሉ ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ማንም አይክደውም። ለዚህም ነው ወታደር ማለት ራሱን የማይሰስት፣ ልማት፤ ሕብረተሰብ፣ ሕዝብ፣ መምህርና ሀገር ነው የምንለው። ስለዚህም እርሱን ማመንና ከእርሱ ጎን መቆም፤ ከዚያም አለፍ ብሎ እርሱን መምሰል ያስፈልጋል። ሕብረተሰቡም ይህንን ተገንዝቦ ከጎኑ መቆም ይገባዋል ይላሉ።
ወታደር የሚከፈለው ደሞወዝ ዝቅተኛ ቢሆንም ለሀገሩ የማይሰስት ነው። ለዚህም ማሳያው ለምሳሌ ፌደራል ፖሊስ ካለው ደሞወዝ ላይ አዋጥቶ ሰቆጣ ላይ ጥሙጋ ውስጥ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አሰርቷል። ለሀገር ነው ከተባለም ደሞወዝ የሚባል እንኳን ሳይተርፈው ያዋጣል። ግን በራሱ ዜጎች እንዲህ ሲበላ ማየት እጅጉን ያማል። በተለይም ለወታደሩ ይህ ከሕመም በላይ ነው። ምክንያቱም ኑሮውን ያውቀዋልና ብለውናልም።
‹‹አሁን ያ ያረዱትን ሰራዊት ተቀላቅዬ ከሰሜን እዝ ሰራዊት ጋር ሆኜ ጁንታውን ድባቅ ለመምታት መታደሌ በትንሹም ቢሆን ጥሜን እያረካሁ እንዳለሁ ይሰማኛል›› የሚሉት ኮማንደር ይበልጣል፤ ከአሉበት ቦታ አስር ኪሎሜትር ብቻ የሚርቅ ቢሆንም እናታቸውን እንኳን ለማየት ሳይጓጉ ነው ለወራት ያህል ሲፋለሙ የቆዩት። ምክንያቱም ለእርሳቸው መጀመሪያ ሀገር ነጻ መውጣት አለባት። እናም በዓመት ሦስቴና አራት ጊዜ ሄደው የሚያዩዋቸውን እናታቸውን በዓይነ ስጋ መገናኘት አልቻሉም። ከድል በኋላ ግን ከሌሎች ጓዶቻቸው ጋር አድርገውታል። ይህ ደግሞ ዛሬ ድረስ እንደሚያስደስታቸው ይናገራሉ።
‹‹እንደአሁኑ ጦርነት እስኪጀምር የጓጓሁበት አለ ለማለት እቸገራለሁ›› የሚሉት ኮማንደሩ፤ የተዋጋነው ኃይል በሀሽሽ የሰከረና የደነዘዘ ነበር። ተማርኮ እንኳን እጅ ስጥ የሚልም እንደነበር አይተነዋል። ምክንያቱም በሰውኛ አስተሳሰብ እንዲህ አይነት ጭካኔ አይታሰብምም አይሆንምም። ግን ሕወሓት በመደንዘዙ ምክንያት አድርጎታል። ነገር ግን የዚህን ጨካኝ አስከሬን ምሽጉ ውስጥ ከ51ኛና 34ተኛ ክፍለ ጦር ጋር በመሆን ከፊት በመቅደም መቀበሪያውን በማድረጌ ደስተኛ ነኝ ሲሉም አጫውተውናል።
እንግዳችን ሁለተኛ ታናሻቸውን ጭምር በመያዝ ዘመቻውን የተቀላቀሉ ሲሆን፤ ከዚያ በተጨማሪ የአጎቶቻቸው ልጆችንና ሌላውን ቤተሰባቸውንም ቢሆን ከአሉበት ቦታ እንዳይለቁና ዘመቻውን እንዲቀላቀሉ አበርትተዋል። ይህ ደግሞ ብዙዎችን አነሳስቷል። በተለይ በቤተሰባቸው አካባቢ ያሉ ወጣቶችንም ጭምር፤ በዚህም ደስተኛ ናቸው። አሁንም ቢሆን ይህንን እንደሚያደርጉት ይናገራሉ። ምክንያቱም ሀገሩ ከእርሱ ውጪ የምትፈልገው ነገር የለም። እናም መከላከያን ተቀላቅሎ ለሀገሩ ብሔራዊ ወታደር መሆን አለበት። በችግር ጊዜም አለሁልሽ ማለትን ከዛሬ ጀምሮ መልመድ ይገባዋል። ሀገር እኛን ስትፈልግ እኛ ደግሞ አንችልም ካልናት ከአሸባሪዎችና ከጠላቶቻችን በምንም አንለይም። ስለሆነም ጊዜው አሁን ነውና ሀገራችንን ካለችበት ችግር በቻልነው ሁሉ እንታደጋት ሲሉ ይመክራሉ።
መልእክት
አሸባሪው ሕወሓትና መሰሎቹ መጥፋት አለባቸው ሲባል ሰዎቹ ብቻ አይደሉም። ጭካኔው አራስን ካልደፈርኩ ብሎ ባሏን የሚገል ነውና መንፈሳቸው ጭምር አብሮ ሊወገድ ይገባል። የተበረዘ ብዙ ነገር ማህበረሰቡ ላይ አስቀምጠዋል። ስለሆነም ያንንም አብሮ መቅበር ያስፈልጋል። የአስተሳሰብ ልኬታቸው ሰውኛ ባህሪን የተላበሰ አይደለምና እርሱንም ማስወገድ ላይ መረባረብ ለነገ የሚባል መሆን የለበትም የሚለው የመጀመሪያ ምክራቸው ነው።
ጣሊያን ቢወር በሀገር ልጅ ተመክቷል። የዜጋችንን ያህልም አልጨከነብንም። ይልቁንም ብዙ የልማት ሥራ ከውኖ ነው የወጣው የሚሉት ኮማንደር ይበልጣል፤ የጁንታው መንፈስ በቀላሉ የሚሰበር አይደለም። ብዙ ከሰይጣናዊ ባህሪያት ተጣብቷል። እናም መተካከሙ ላይ መሥራት ግድ ነው። ብዙ ነገሮችን በመጥፎ ስብዕናቸው ተመርዟልና የቀረው መልካምነታችን ለማቆየት ይህንን ማጥፋቱን ቅድሚያ ልንሰጠው ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን በሕዝባዊ ክንዳችን ያለማቋረጥ እያሸነፍን ቀጥለናል። እናሸንፋለን፤ የቀሩት ጥቂት ቦታዎች በጣት በሚቆጠሩ ቀናት ነፃ ይወጣሉ። ከዚያ በጠላት የፈረሰውን እንገነባለን። በወራሪው ኃይል እና ተላላኪዎቻቸው የግፍ በትር ሳቢያ ያዘኑትን እናፅናናለንም። የተሰው ጀግኖችን ልጆችም እንከባከባለን። ምክንያቱም ከብርቱ ሀዘን በኋላ ብርሃናማው ተራራ አለ። እዚያ ላይ ቆመን የድል ብስራትን ለሁሉም እንናገራለን። እያንዳንዱን የተወረወረብንን ድንጋይ በመደርደር በጠንካራ አለት ላይ ኢትዮጵያንም እናፀናለን። ህልማችን ይህ ነውና እናደርገዋለንም። ለዚህ ግን ሁሉም የበኩሉን ማበርከት አለበት ሲሉ ይመክራሉ።
በመጨረሻ የሚመክሩት አሁን ከእያንዳንዱ ፈተና ትምህርት የምንቀስምበት፣ ለችግሮች ደግሞ መላ የምንዘይድበት ጊዜ ላይ ነን። ከተደጋገፍን አንወድቅም። መተሳሰባችን ከበረታ አንደናቀፍም። በሕብረታችን አብበን ለልጆቻችን ነገን እንሰጣለን። ፍቅርን እናወርሳለን። ለዚህ ደግሞ የዛሬው ጉዟችን መሰረት ይሆነናልና አጥብቀን እንያዘው የሚል ነው። እኛም ምክራቸውን በልባችን እናኑረው ስንል አበቃን። ሰላም!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24 ቀን 2014 ዓ.ም