ሀገራዊ ምክክር በትውልዶችና በዘመናት መካከል አንድ ጊዜ የሚያጋጥም የወሳኝ መታጠፊያዎች ሁሉ ወሳኝ መታጠፊያ ከመሆን ባሻገር ራስና ጉልላት መሆኑ በአጽንኦት ሊሰመርበት ይገባል። የነገዋን ኢትዮጵያ በጽኑ መሠረት ለመገንባት የሚያግዝ ፍኖተ ካርታ ተደርጎም ሊወሰድ ይችላል። ባለፈው እሮብ እኩል ቀን ላይ ከወዳጅነት ፓርክ በኢቲቪ ቀጥታ ስርጭት የኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፓራዎችን የአቀባበል ስርዓት እየተከታተልሁ እያለ “ሰበር” ማስታወቂያው ሲመጣ ተገደን ከገባንበት ጦርነት ጋር የተያያዘ ብስራት ወይም መርዶ ነበር የጠበቅሁት። በአንድ ጊዜ ሆዴን ያመኝ ጀመር።
ሆኖም ግምቴ ስህተት ነበር ። “ሰበሩ” ያልተለመደ አይነት ነበር ። “ሰበሩ” የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ልዩ ስብሰባ በአብላጫ ድምጽ መጽደቁን የሚያበስር ነው። ይህን ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያዎች “ሰበር”ነቱ ምኑ ላይ ነው ከሚሉት አንስቶ፤ በኢቲቪ ላይ የሚሳለቁ በአራዶች ቋንቋ ሙድ የሚይዙ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ ጹሑፎችንና አስተያየቶችን ስመለከት የግንዛቤ ክፍተት እንዳለ ተረዳሁ። እነዚህ ወገኖች ቢረዱት ለዚች አገርና ሕዝብ ከአገራዊ ምክክር በላይ በሰበር የሚበሰር ምን ዜና አለ በሚል ይቺን መጣጥፍ ለመሞነጫጨር ተነሳሁ።
በአገራችን ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው፤ በትውልዶች ጅረት አንድ ጊዜ የሚያጋጥመውን አገራዊ ምክክር በባለቤትነትና በበላይነት የሚመራ ገለልተኛ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ መጽደቅ አይደለም አንድና ሁለት ጊዜ አስር ጊዜ በ”ሰበር”ቢታወጅ ያንስበታል እንጅ አይበዛበትም። አካታች አገራዊ ምክክሩ በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያስችል ነው። በማንነት በልዩነትና በጥላቻ የተጎነቆለውን ፖለቲካችንን እልባት የሚሰጥ ነው። አገረ መንግስቱን ከተቀለሰበት ድቡሽት አንስቶ በጽኑ መሠረት ላይ የሚያንጽ ነው። ትውልዶች ለዘመናት ሲያነሷቸው ሲታገሉላቸውና መስዋዕት ሲከፍሉላቸው የኖሩ ጥያቄዎችን የሚመልስ ነው። አገራዊ ምክክሩ የጋራ አገር፣ የጋራ ሕልም ፣ የጋራ ራዕይ ፣ የጋራ ሰንደቅ አላማ ፣ የጋራ ጀግና ፣ የጋራ ታሪክ ፣ ወዘተረፈ እንዲኖረን የሚያግዝ ነው።
ምክክሩ አገራችን በጀግኖች ልጆቿ ነጻነቷንና ሉዓላዊነቷን አስከብራ የኖረች ጥንታዊት አገር መሆኗን ተቋማዊ ያደርጋል። በታሪኳ አይታው ሰምታውና ገጥሟት የማታውቀውን ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ የተደቀነባትን የህልውና አደጋ በጀግኖች ልጆቿ የገፈፈችው ቢሆንም አገራዊ ምክክሩ እንዲህ ያሉ አደጋዎች ዳግም እንዳያገረሹ ያግዛል። በታሪክ አጋጣሚ የተከሰቱ ቁርሾዎችን ጠባሳዎችንና ሕመሞችን በእርቅና በመግባባት ለመፍታት አስተዋጾ ይኖረዋል።
ለመጭው ትውልድም አገራዊ ዕዳ ማለትም ተሰርቶ ያላለቀ ሀገረ መንግስት፤ ጥላቻ፣ የተዳፈነ ግጭት/ጦርነት/፣ ልዩነትና መጠራጠር በይደር እንዳናቆየው ያግዛል። በአጠቃላይ በሀገራችን ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ክስተት ስለሆነ ነው የሰበርም ሰበር ነው ያልሁት። ሚዲያዎች የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጁን የማይተካ ሚና እንዲሁም ያለውን አገራዊ አንድምታ ለሕዝቡ ከተለያየ ማዕዘን አንጻር ማብራራት መተርጎምና ማስረዳ ይጠበቅባቸዋል። በአገራችን ታሪክ የወሳኝ መታጠፊያዎች/critical junctures/ወሳኝ መታጠፊያ መሆኑን የማሳየት ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው በልኩ ተረድተው ሊሰሩ ይገባል። ተገደን የገባንበት ጦርነት በድል አድራጊነት መቋጨት ብንችል እንኳ ለጦርነት የዳረጉንን ችግሮች በዘላቂነት መፍታት የምንችለው በእውነተኛ ሀገራዊ ምክክር ነው።
እንደ የሰላም፣ የእርቅ አለማቀፍ ረቡኒው (መምህሩ)፣ አሸማጋዩ፣ አደራዳሪው፣ ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ አሰፋ አስተምህሮ፤ “…ሰላም ጦርነትንና ሁከትን ማስቆም ሳይሆን ለግጭቶች ዘላቂ መፍትሔዎችን መሻት ነው። ግጭት ወደድንም ጠላንም በሰው ልጆች መካከል ሁል ጊዜ የሚኖር መርገምም፣ በረከትም ነው። አጋጣሚውን ተጠቅሞ በጊዜ ግጭቱን ለፈታ ተፈጥሮአዊ በረከት ሲሆን በአንፃሩ ላልተጠቀመበት ደግሞ መርገም ነው። የሚያስከትለውን መጥፎ ቀውስ፣ ዳፋ፣ መዘዝ በመፍራት ብንሸሸውም እንደጥላችን ሲከተለን ይኖራል። ግጭት በሕይወታችንም ሆነ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት በሚገባ ትኩረት ሰጠን ያልፈተሽነው ጉዳይ መኖሩን ይጠቁማል። በበጎ ከተረዳነው ለሁሉ የሚበጅ መፍትሔ ለመሻት ወደ ሚያግዝ መልካም አጋጣሚ ልንቀይረው እንችላለን። …” አዎ አገራዊ ምክክሩ ቢያንስ ባለፉት 50 አመታት ያጋጠሙንን ፈተናዎች ወደ መልካም አጋጣሚነት የምንቀይርበት ቁልፍ ነው። በአገራችን ባለፉት ሶስት ሺህ አመታትም ሆነ ከዚያ በቀደም ወደ ኋላ በሚሳበው ታሪካችን በሺዎች በሚቆጠሩ ግጭቶች፣ መንቆራቆሶች፣ ጦርነቶች ያለፍን ቢሆንም፤ እነዚህን የታሪክ ወሳኝ መታጠፊያዎች ዘላቂ ሰላም፣ እርቅ ለማስፈን በሚያግዝ መልኩ አልተጠቀምንባቸውም። ይሁንና ግጭት የአርባ ቀን እድላችን ሆኖ በእኛ ላይ ብቻ የተጫነ የታሪክ መርገም ተደርጎም መወሰድ የለበትም። ግጭት የሰው ልጅ በኃጢያቱ ከገነት ከተባረረበት ከዚያ ሩቅ ዘመን ጀምሮ ኖሯል። ወደፊትም ይኖራል። የሰውን ልጅ ከብሉያት ዘመን አንስቶ እስከዚች ሽርፍራፊ ሰከንድ nano second ጦርነት ተለይቶት አያውቅም። በፋርስ፣ በባቢሎን፣ በቤዛንታይን፣ በሮማውያን፣ በኦቶማን ዘመን፤ በ፩ኛው፣ በ፪ኛው የአለም ጦርነት፤ ወዘተረፈ የተካሄዱ ግጭቶችን የቀሰቀሱ ምክንያቶችን በዘላቂነት መፍታት ባለመቻሉ ባህሪያቸውን፣ አይነታቸውን፣ አውዳሚነታቸውን እየቀያየሩ ለዛሬው ትውልድ በዕዳ ቢተላለፉም ዛሬም ሙሉ በሙሉ አለመወገዳቸው፤ የግጭትንና የሰውን ልጅ ያደረ ቁርኝት ያሳያል።
የዩጎዝላቪያ፣ የእኛ የእርስ በዕርስ ጦርነት፣ የኢትዮ ሶማሊያ፣ የኢራቅ ኢራን፣ የአፍጋኒስታን፣ የሶማሊያ፣ የኢራቅ፣ የሶሪያ፣ የሊቢያ፣ የኢትዮ ኤርትራ ዘግናኝ ጦርነቶች፤ የአልቃይዳ፣ የታሊባን፣ የአይሲስ፣ የቦኮ ሀራም፣ የአልሻባብ፣ ወዘተ. አማፅያን መነሳት፤ የሰው ልጅ ዛሬም ያልፈታቸው፣ ያልተሻገራቸው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፈተናዎች ከፊቱ መኖራቸውን ያሳያል። ለዚህ ነው ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ ግጭት እንደጥላችን በምንሄድበት ሁሉ ይከተለናል ያሉት፤ ዛሬ በሀገራችን ባለፉት ሶስት ዓመታት፤ በተለይ ደግሞ ከአንድ ዓመት ወዲህ ብቻ እንኳ ብንመለከት ሁለት ታላላቅ ጦርነቶችን እያካሄድን ነው።
በጦርነት ቀለበስነው ያልነው አደጋ ሌላ ጦርነት ቀስቅሶ በዜጎች መካከል በቀላሉ የማይሽር ጠባሳ ከመተው ባሻገር በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሙትና ቁስለኛ ከመሆናቸው ባሻገር በአማራና በአፋር ክልሎች ወደ ግማሽ ትሪሊዮን የሚጠጋ ሀብት መዘረፉንና መውደሙን አንዳንድ ይፋ ያልሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ። ከዚህ ጦርነት በፊት በነበሩ ሁለት ዓመታትም ሆነ ባለፈው ዓመት በኦሮሚያና በሶማሊያ ክልሎች፣ በደቡብና በኦሮሚያ፣ በጅግጅጋ፣ በድሬዳዋ፣ በአማራ፣ ክልሎች ግጭቶች፣ ውጥረቶች፣ መፈናቀሎች ተከስተዋል። ዛሬ መፈናቀሎች፣ ግጭቶች በአንፃራዊነት ቢረግቡም፤ የግጭቶችን መነሻ ምክንያቶች ግን አልተፈቱም። ተዳፈኑ እንጅ አልጠፉም። ነገ ገላልጦ የሚሞቃቸው ጦር አውርድ የሚል ኃይል ከተነሳ መልሶ ሊያቀጣጥላቸው ይችላል። ይህ ሀገራዊ ምክክር ከዚህ የግጭትና የጦርነት አዙሪት ያወጣናል ተብሎ ስለሚታመን ነው ከፍ ያለ ቦታ የተሰጠው። በኢትዮጵያ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት አገራዊ ምክክር መድረክ እንዲመራና እንዲያሳልጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በመቋቋም ላይ የሚገኘው አገራዊ ምክክር ኮሚሽንን፤ 11 ያለ መከሰስ መብት ያላቸው ኮሚሽነሮች ይመሩታል። ከፖለቲካ ወገንተኝነት፣ ከማንኛውም የመንግሥት ወይም ሌላ አካል ተፅዕኖ ነፃ የሆነ ራሱን የቻለ ሕጋዊ ሰውነት ያለው አካል ሆኖ ይቋቋማል ። በአዋጁ እንደተገለጸው ለኮሚሽኖቹ የተሰጠው ያለ መከሰስ መብት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካልተነሳ፣ ወይም ወንጀል ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ ካልተያዙ በስተቀር በኮሚሽነርነት በሚያገለግሉበት ወቅት በወንጀል ያለ መከሰስ መብት አላቸው።
በቅርቡ ይቋቋማል ተብሎ ለሚጠበቀው ኮሚሽን ከሕዝብ፣ ከፖለቲካ ድርጅቶችና ከሲቪል ማኅበራት ኮሚሽነር ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦች ተጠቁመው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የሚሾሙ ስለመሆናቸው ተደንግጓል። የኮሚሽኑ የሥራ ዘመን ለሦስት ዓመታት ሲሆን፤ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤ ት ሊራዘም ይችላል። ከፍ ብሎ ለመግለጽ እንደሞከርሁት የኮሚሽኑ መቋቋም አስፈላጊነት በዋነኝነት የተለያዩ የፖለቲካና የሐሳብ መሪዎች እንዲሁም የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ የሆነ የሐሳብ ልዩነት፤ አለመግባባትና ተቃርኖ የሚታይ በመሆኑና አለመግባባቱንና ተቃርኖውን ለማርገብና ለመፍታት ሰፋፊ አገራዊ የሕዝብ ምክክሮችን አካታች በሆነ መንገድ በማካሄድ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ነው።
በአገራዊ ምክክሩ ተወያዮችንና የውይይት አጀንዳዎችን ከመምረጥ ጀምሮ በውይይቶቹ የሚገኙ ምክረ ሐሳቦችን በተግባር ላይ ለማዋል የሚያስችል ግልጽና ተጨባጭ የሆነ ዕቅድ መዘጋጀቱን ማረጋገጥና አስፈላጊውን ዕገዛ የማድረግ ኃላፊነቶች ለኮሚሽኑ ተሰጥተውታል። በሌላ በኩል ለኮሚሽኑ ከተሰጡት ኃላፊነቶች ውስጥ በልሒቃን መካከል አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያሉትን ልዩነቶች በጥናት፤ በሕዝባዊ ውይይቶች ወይም በሌሎች አግባብነት ባላቸው መንገዶች በመጠቀም፤ በአገራዊ የምክክር ጉባዔ ላይ የሚሳተፉ አካላትን ግልጽ በሆኑ መሥፈርቶችና የአሠራር ሥርዓት መሠረት ይለያል። በምክክሮች ላይ እንዲሳተፉም ያደርጋል።
የአገራዊ ምክክር ጉባዔ አጀንዳዎችን፣ የምክክሮቹን ሒደት፣ በምክክሮቹ የተገኙ ምክረ ሐሳቦችን፤ እንዲሁም ምክረ ሐሳቦቹ በተግባር ላይ ሊውሉ የሚችሉበትን ሥልት የሚጠቁም ዝርዝር ሪፖርት በማዘጋጀት ለመንግሥት ያቀርባል። ኮሚሽኑ እንደሚካሄዱ የታቀዱትን አገራዊ ምክክሮች አካታች፤ ብቃት ባለውና ገለልተኛ በሆነ አካል የሚመሩ፤ ላለመግባባት መንስዔዎችን በትክክል በሚዳስስ አጀንዳ የሚያተኩሩ ግልጽ በሆነ የአሠራር ሥርዓት የሚመሩና የምክክሮቹን ውጤቶችን ለማስፈጸም የሚያስችል ዕቅድ ያላቸው እንዲሆኑ የሚሠራ ስለመሆኑ ተመልክቷል። እናሸንፋለን ! አንጠራጠርም !
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24 ቀን 2014 ዓ.ም