የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በተለይም የድርጅቱ የፀጥታው ምክር ቤት ከምክር ቤቱ አባላት የኃፅያት ተፈጥሮን ወርሶ የተወለደ ተቋም ነው። ድርጅቱ የዓለምን ሠላም፣ ደህንነት እንዲሁም ልማት ለማረጋገጥ የተመሰረተ ከሚለው አስተሳሰብ በተቃራኒው ከምክር ቤቱ አባላት የተወረሰ የኃፅያት ተፈጥሮ ይዞ የተወለደ ነው። ድርጅት ሲመሰረት አብዛኞቹ አፍሪካ ሀገራት ዛሬ ድርጅቱን በተለይም የፀጥታ ምክር ቤቱን በተቆጣጠሩት ኃይሎች ቅኝ ግዛት ስር በነበሩበት ወቅት ነው።
ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አብዛኞቹ የአህጉሪቱን መቅኔ እየመጠጡ በነበሩበት ዘመን፣ አፍሪካ በሁለት እግሯ ባልቆመችበት ዘመን የተመሰረተው። ድርጅቱ ከመስራቾቹ ኃፅያተኛ ተፈጥሮን ወርሷል። በውርስ ኃፅያት ምክንያት፣ ምክር ቤቱ በባህሪውና በተግባሩ ኃፅያተኛ ነው። ድርጅቱ እስካሁን ድረስ አፍሪካን የማግለል እና የመግፋት ተፈጥሮ ይዞ በመወለዱ ነው።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በአሸናፊዎቹ ኃያላን የተገነባ ነው። ድርጅቱ የተለያዩ ተግባራትን የሚከውኑ የተለያዩ አካላት አሉት። ድርጅቱ እና የድርጅቱ ተቋማት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሸናፊ የነበሩ ሀገራት ጥቅም ለማስጠበቅ የሚሰራ ሆኖ ቀጥሏል። በጦርነቱ አሸናፊ ሆነው የወጡት ሀገራት ከጦርነቱ በኋላ የመሰረቷቸው ድርጅቶች የአሸናፊዎቹን ጥቅም እና ፍላጎት እንዲወክሉ ተደርገው መመስረታቸው የሚደንቅ አይደለም። በሂደት ግን የሌሎችን ጥቅሞችን እና ፍላጎቶችን በተለይም የአፍሪካን ፍላጎቶችን እና ጥቅሞችን በሚወክል መልኩ እየተስተካከለ አለመሄዱ እንደ አፍሪካ ያሉ አህጉራትን ክፉኛ እየጎዳ ይገኛል።
ድርጅቱ የተለያዩ ተግባራትን የሚከውኑ የተለያዩ አካላት አሉት። አንዱ አካል የሆነው የፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካን ባገለለ መልኩ ከተመሰረቱት የድርጅቱ አካላት አንዱ ነው። የጸጥታው ምክር ቤት ሲመሰረት አምስት አባላት የነበሩት ሲሆን ከድርጅቱ ምስረታ ከ20 ዓመታት በኋላ አስር ሀገራት በድርጅቱ ውስጥ ቋሚ ያልሆኑ መቀመጫዎች እንዲመደብላቸው ተደርጓል። ሆኖም ቋሚ መቀመጫ ያላቸው ሀገራት ዛሬም አምስት ብቻ ሆነው ቀጥለዋል።
አምስቱ ቋሚ አባላት አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ ናቸው። አፍሪካ በምክር ቤቱ ውስጥ ቋሚ መቀመጫ የላትም። ከ1ነጥብ3 ቢሊዮን በላይ ህዝብ ያላት አህጉር ሦስት ቋሚ ያልሆኑ መቀመጫዎች ተመድበውላታል። 60 ሚሊየን ህዝብ ያላቸው ሀገራት ቋሚ መቀመጫ ይዘው ከአንድ ነጥብ ሦስት ቢሊየን በላይ ህዝብ ያላት አህጉር ቋሚ መቀመጫ አለመኖር በሁሉም ረገድ ተቀባይነት የሌለው ነው።
የጸጥታው ምክር ቤት የዓለማችን ከፍተኛ ስልጣን የተሰጠው የፖለቲካ እና የዓለም ደህንነት የሚያስጠብቅ አካል ነው። የዚህ አካል አለመሆን ብሎም ይህ አካል በሚወስናቸው የፖለቲካና የደህንነት ውሳኔዎች ላይ ከዚህ አካል ጋር አብሮ መወሰን አለመቻል አፍሪካን ትልቅ ዋጋ ሲያስከፍላት ኖሯል። ለፕላኔታችን የጋራ ሠላምና ብልጽግና አስፈላጊ ከሆኑት ዓለም አቀፍ የደህንነት እና የልማት ማዕቀፎች ተገልላ በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ ሳትሆን ኖራለች። ከዚያ በተጨማሪም አፍሪካዊያን በሌሉበት በአፍሪካዊያን ላይ ሲወሰንባቸው ኖረዋል።
የአፍሪካ አህጉር እንደ አህጉር ቋሚ ወንበሮች የማግኘት መብት በዓለም የጋራ ፍትህ ጉዳይ እና በውሳኔ አሰጣጥ ጉዳዮች ላይ እኩል ውሳኔ የማስተላለፍ መብት የማግኘት ጥያቄ እንጂ ማንም የመጉዳት ጥያቄ አይደለም። ወይም የማንንም ጥቅም የማሳጣት ጉዳይ አይደለም። ይህ ለረጅም ጊዜ የዘለቀው ኢ-ፍትሃዊነት ለነገ ሳይባል መታረም አለበት። የበርካታ ህዝቦች መኖሪያ የሆነችው አፍሪካ ወሳኝ ጉዳዮች ከሚወሰኑበት ከዓለም አስተዳደር ድርጅት ልትገለል አይገባም።
አፍሪካዊያን ይህንን ዕድል ለረጅም ዘመናት ሲጠብቁ ኖረዋል። ለብዙ ዓሥርት ዓመታት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት አባላትን ቁጥር መጨመር እንደሚያስፈልግ ከተለያዩ አካላት ጥሪዎች ሲተላለፉ ቆይቷል። ሆኖም በምክር ቤቱ ዓማካኝነት የፖለቲካ ጥቅማቸውን ሲያስጠብቁ የኖሩት አብዛኞቹ የምዕራብ ዓለም ሀገራት አፍሪካን ከጸጥታው ምክር ቤት በማግለል ሀገራዊና ቀጣናዊ ጥቅሞች ሲያግበሰብሱ የኖሩ ሀገራት ምክር ቤቱ ሪፎርም እንዳይደረግ የተቻላቸውን ሲያደርጉ ኖረዋል።
አሁን ግን ድርጅቱ በዚህ መልኩ መቀጠል የሚችል አይመስልም። ድርጅቱ ለአፍሪካ ቋሚ ውክልና በመስጠት ራሱን ማስተካከል ይገባዋል። አህጉሪቱ ለረጅም ዘመናት ይህንን ስትጠብቅ ኖራለች። አሁን ግን አህጉሪቱ በዚህ መልኩ መቀጠል የምትችል አይመስለኝም። ትዕግስቷ ተሟጧል። ትዕግስቷ እንደተሟጠጠ በቅርቡ በኢትዮጵያዊያን አነሳሽነት በተጀመረው ‹‹NO MORE›› ወይንም ‹በቃ› ንቅናቄ ዓማካኝነት በግልጽ እየታየ ነው።
የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችም እንደ ከዚህ ቀደሙ መሽኮርመም አቁመው ድፍረት በተሞላበት መልኩ መብታቸውን ሊጠይቁ ይገባል። እንደ ቀደሙት የአፍሪካ የነጻነት አባቶች ቋሚ መቀመጫቸውን ለማግኘት እጅ ለእጅ ተያይዘው ሊታገሉ ይገባል። በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ያስተላለፉትን ዓይነት ቆፍጠን እና ጠንከር ያለ መልዕክት ሊያስተላልፉ ይገባል።
አፍሪካን በእጅ አዙር ለመግዛት የሚፈልጉ ኒዮ- ኮሎኒያልስ ኃይሎች ዛሬም አፍሪካ ከምክር ቤቱ ለማግለል እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ለአፍሪካ አህጉር በምክር ቤቱ ቋሚ ውክልና እንደሚያስፈልግ በብዙዎች ዘንድ እየታመነ የመጣ ይመስላል። ስለ አፍሪካ መቀመጫ የሚናገሩ አካላት ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ከአህጉሪቱ ውጪ ያሉ ሀገራት ጭምር አፍሪካ ቋሚ መቀመጫ እንደሚያስፈልጋት እየተናገሩ ነው።
የፀጥታ ምክር ቤቱን አፍሪካን አካታች የማድረግ ጉዳይ ለአፍሪካ ሀገራት ብቻም ሳይሆን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጭምር ከፍ ያለ ፋይዳ አለው። በምክር ቤቱ ለአፍሪካ ቋሚ መቀመጫ የማይሰጥ ከሆነ የምክር ቤት ውሳኔዎች ህጋዊነት እና ውጤታማነት እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ ሆኖ ይቀጥላል።
ድርጅቱ ለዲሞክራሲያዊ ዓለም አቀፍ አስተዳደር መዋቅሮችን እስካልዘረጋ ድረስ፣ ለዚች ፕላኔት የጋራ ሠላምና ብልጽግና አስፈላጊ የሆኑት ፍትሃዊ ዓለም አቀፍ የደህንነት እና የልማት ማዕቀፎች የማሳካት ጉዳይ የሚታሰብ አይደለም። በመሆኑም ምክር ቤቱን አካታች የማድረግ ጉዳይ ‹‹ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ አለበለዚያ ግን ድንጋይ ተብለህ ትወረወራለህ›› ነው።
የአፍሪካ ሀገራት የምክር ቤቱ አባል እንዳይሆኑ የሚጥሩ አካላትም ተግባራቸውን ቆም ብለው ሊመለከቱ ይገባል። አፍሪካ በራሷ የልማት እና የጸጥታ ጉዳዮች ላይ ከሌሎች ጋር አብራ የምትወስንበት ሁኔታ የማይፈጠር ከሆነ የልማትም ሆነ የጸጥታ ችግር ሊቀረፍ አይችልም። ይህ ደግሞ የበለጸጉ ሀገራትንም በተዘዋዋሪ ይጎዳል። ከእንግዲህ በኋላ ሰፊው እና የብዙ ህዝቦች መኖሪያ የሆነው የአፍሪካ አህጉር የልማት እና የፀጥታ ችግሮች የማይፈቱ ከሆነ ጥቂት ሀገራት የብልጽግና ኪሶች ሆነው ሊቀጥሉ አይችሉም። ወላፈኑ እየለበለባቸው ይቀጥላል።
የፀጥታው ምክር ቤት አቋም ምንም ይሁን ምን የፀጥታው ምክር ቤት ተወካይ፣ ዲሞክራሲያዊ እና ተጠያቂነት ያለው ለሁሉም አባል ሀገራት የሚሆንበት ጊዜ አሁን ነው። የፀጥታ ምክር ቤቱን ለማሻሻል የሚደረገው እንቅስቃሴ ደግሞ የአፍሪካን ጥሪ ያስቀደመ ሊሆን ይገባል። ድርጅቱም ራሱን ከውርስ ኃፅያት ሊያነጻ የሚችልበት አንድ መፍትሄ አለው። አፍሪካን እና ሌሎች የተገፉ ህዝቦችን የሚያካትት ማሻሻያ ማድረግ ድርጅቱ ከውርስ ኃፅያት የሚያነፃ ብቸኛ መፍትሄ ነው።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24 ቀን 2014 ዓ.ም