የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የ‹‹ወደ ሀገር ቤት እንግባ›› ጥሪን እንዲቀላቀሉ ግብዣ ማቅረባቸውን ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል፤ እየገቡም ነው፡፡ የኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በዚህ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ትርጉሙና ፋይዳው ብዙ ነው፡፡ አሜሪካና ጥቂት አጋሮቿ ‹‹የኢትዮጵያ የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ አስጊ ስለሆነ ዜጎቻችን ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ እንመክራለን …›› እያሉ የማስጠንቀቂያ ጋጋታ በሚያሰራጩበት ወቅት ኢትዮጵያውያን ግን ‹‹ሀገራችን ሰላም ናት … ስለፀጥታዋ ለመናገርም የባዕድ ምስክርነትና ምክር አያሻንም … ›› በማለት ወደ እናታቸው ዘንድ እየጎረፉ ነው፡፡
አሸባሪው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕ.ወ.ሓ.ት) ወደ አዲስ አበባ ያደርግ የነበረውን ጉዞውን ስትደግፍ የቆየችውና በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በምትቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙኃን በኩል ‹‹አዲስ አበባ በአማፂያኑ ተዋጊዎች ተከባለች …›› ዓይነት የውሸት መረጃዎችን ስታሰራጭ የቆየችው አሜሪካ፣ ያቀደችው ሁሉ ሳይሳካ ሲቀር ነገረ ስራዋ ሁሉ ‹‹ካፈርኩ አይመልሰኝ›› ዓይነት ሆኗል፡፡ አሁንም ዜጎቿ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ እያሳሰበች ነው፤ የሰሞኑ ማሳሰቢያዋ ለ17ኛ ጊዜ የተላለፈ መልዕክት ነው፡፡ በቀጣይ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ በእያንዳንዱ ዜጎቿ ቤት እየዞረች ‹‹ከኢትዮጵያ ውጡ›› ብላ ትለምን እንደሆነም በቀጣይ የምናየው ይሆናል ፡፡
ዛሬ ላይ ኢትዮጵያውያንና ትወልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እየመጡ ያሉት ይህ ሁሉ የምዕራባውያን መንግሥታትና የመገናኛ ብዙኃኑ ዘመቻና ጫና ባለበት ወቅት ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መግባት ‹‹በአንድ ድንጋይ ብዙ ወፍ የሚያሰኝ›› ተግባር እንደሆነም ይታመናል፡ ፡ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ ሰላም እንደሆነች ለቀሪው ዓለም ሲያሳውቅ፤ በሌላ በኩል ደግሞ መጪዎቹን የገናና የጥምቀት በዓላት በሀገሩ ከወገኑ ጋር በማሳለፍ በአሸባሪዎች ጉዳይ ለየደረሰባቸው ወገኖቹ ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን ያደርጋል፡፡
ዳያስፖራው በተለያዩ አጋጣሚዎች ለሀገሩ ያበረከተው አስተዋፅዖ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ የዘንድሮው ደግሞ ከዚህ ቀደም ካደረጋቸው አስተዋፅዖዎች ሁሉ የተለየ ሆኖ ታይቷል፡፡ አሸባሪው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ካወጀ ጊዜ ጀምሮ የቡድኑ ደጋፊና ተንከባካቢ ሆነው የዘለቁት ምዕራባውያን መንግሥታትና ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ መጠነ ሰፊ ዘመቻና ጫና እያሳደሩ ዘልቀዋል፡፡ ከስም ማጥፋት ዘመቻና ውንጀላ ጀምሮ አሸባሪውን ቡድን እስከመደገፍና በኢትዮጵያ ላይማዕቀቦችን እስከመጣል የዘለቁ እርምጃዎችን ወስደዋል፡፡
ሀገሩ በዓለም አደባባይ ፍትሕ መነፈጓና መከዳቷ ያስቆጣው ዳያስፖራው የሀገሩን እውነት ሊገልጥና የተከፈቱባትን ክሶች ውድቅ ውሸት መሆናቸውን ለመመስከር ‹‹በቃ›› ብሎ የአሜሪካንና የአውሮፓ ጎዳናዎችን አጥለቅልቋቸዋል፡፡ አሜሪካና ሸሪኮቿ እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ እንዲያነሱ ጠይቋል፤ የአሸባሪውን ነውረኛነት ለዓለም ገልጿል፡፡ የውሸት መረጃ የሚያሰራጩ መገናኛ ብዙኃን ቢሮ ድረስ በመሄድ የኢትዮጵያን እውነት እያስረዳ ተቋማቱ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና የሙያቸውን መርህ ተከትለው እንዲሰሩ ጠይቋል፡፡
ለሹማምንት ደብዳቤ በመፃፍ መንግሥቶቻቸውና ሀገሮቻቸው ‹‹የሰብዓዊ መብትና የዴሞክራሲ ጠበቃ ነን›› ማለታቸው ከእውነት የራቀ እንደሆነ በማስረጃ አስደግፎ አስረድቷል፡፡ በእነዚህ ጥረቶቹም ምክንያት በኢትዮጵያ ላይ ይደረጉ የነበሩ ጫናዎች እንዲረግቡ አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያውያን በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ቢኖራቸውም በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ግን ልዩነት እንደሌላቸውና በሕልውናዋ ላይ እንደማይደራደሩ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዐሳይቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ዳያስፖራው በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ዓይነት ብዙ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል፡፡ ጊዜውን፣ ገንዘቡን፣ ጉልበቱንና እውቀቱን በማስተባበር የተቸገሩ ወገኖቹን እያገዘ ነው፡፡ ባለሙያዎች ተሰባስበው በሙያቸው የሚያስፈልጉ እገዛዎችን ለማድረግ እየታተሩ ነው፡፡ ‹‹እኔ በሕይወት እያለሁማ ወገኔ አይራብም›› ያሉ አገርና ሕዝብ ወዳድ ኢትዮጵያውያን የአንገት ሀብላቸውን ጭምር ሲሰጡ ተመልክተናል፡፡ የተለያዩ የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮችን በመቅረፅ ገንዘብ እያሰባሰበ ነው፡፡ ‹‹አይዞን (Eyezone)›› የተሰኘውና በአጭር ጊዜ ውስጥ እስካሁን ድረስ ከአምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ የተሰበሰበበት መርሃ ግብር የዚሁ ማሳያ ነው፡፡
ዳያስፖራው ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት ቀን ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚቆይባቸው ቀጣይ ሳምንታት የሚሳተፍባቸው ልዩ ልዩ መርሃ ግብሮችም ተዘጋጅተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የግብይት፣ የጉብኝት፣ የደም ልገሳና የውይይት መርሃ ግብሮች ይጠቀሳሉ፡፡ ዳያስፖራው በእነዚህ መርሃ ግብሮች በቀጣይ ጊዜያት ለሀገሩ ስለሚያከናውናቸው ተግባራት ይመክራል፤ በጦርነቱ ምክንያት የተጎዱ ወገኖቹን ይጎበኛል፤ በሀገሩ ልጆች የተሰሩ የምርት ውጤቶችን ይሸምታል፤ ለሚወዳት ሀገሩ ደሙን እያፈሰሰ ላለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ደም ይለግሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ በበርካታ ችግሮች ውስጥ ስትሆን ‹‹አይዞሽ እናታችን፤ አለንልሽ›› ብሎ የመልካም ልጅነት ባህርይን በተግባር ያሳየውን የዳያስፖራውን ማኅበረሰብ ተሳትፎ በማጠናከር እስካሁን ያስመዘገባቸውን ድሎች የበለጠ ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ በቀጣዮቹ ጊዜያት ዳያስፖራው በጦርነቱ ሰበብ ለከፋ ጉዳት የተዳረጉ ወገኖችን በተቀናጀ ሁኔታ መደገፍ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ትኩረት ሰጥ መስራት ይገባል፡፡ ዳያስፖራው ጊዜውን፣ ገንዘቡን፣ ጉልበቱንና እውቀቱን አስተባብሮ ‹‹ወገኔን ልደግፍ፤ ሀገሬን ላልማ›› ብሎ ሲነሳ መንግሥት በበኩሉ ይህን የዳያስፖራውን የተቀደሰ ዓላማ ሊያሳኩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይጠበቅበታል፡፡
ለተጎዱ ወገኖች ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ የሚደረገው ድጋፍ በትክክል ለተጎጂዎች መድረሱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ ዳያስፖራው እነዚህን አካባቢዎች እንዲጎበኝና በአካባቢዎቹ የመልሶ ማልማትና ማቋቋም ተግባራት ላይ እንዲሳተፍ ማበረታታት ይገባል፡፡ ሀብቱን አቀናጅቶ በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ እንዲሰማራ ቢሮክራሲያዊ መሰናክሎች ተስፋ እንዳያስቆርጡት መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
ዳያስፖራው ኢትዮጵያን ከሚጠቅምባቸው መንገዶች መካከል አንዱ የውጭ ምንዛሬ በመላክ የሚያበረክተው አስተዋፅዖ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ገንዘባቸውን በሕጋዊ መንገድ (በባንክ) ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ረገድ አሁንም ብዙ ውስንነቶች
አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው መረጃ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት ከሚላከው ገንዘብ 30 በመቶ ብቻ የሚሆነው በህጋዊ መንገድ እንደሚላክ አስታውቋል፡፡
70 በመቶው ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ አይላክም ማለት እጅግ አስደንጋጭ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ ግዙፍ ገንዘብ ምን ያህል ጥቅም እንደምታጣ ማሰብ ቀላል ነው፡፡ ስለሆነም ዳያስፖራው ገንዘቡን በሕጋዊ መንገድ በመላክ ሀገሩንና ወገኑን ተጠቃሚ እንዲያደርግ መንግሥትም ሆነ ራሱ ዳያስፖራው ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡
ዳያስፖራውም በጦርነቱ የተጎዱትን ወገኖችንና አካባቢዎችን ተመልክቶ አካባቢዎቹን በዘላቂነት ለማልማት በሚያስችሉ ተግባራት ላይ ለመሰማራትና በዚህ በኩልም ለሀገሩ አስተዋፅዖ ለማበርከት መዘጋጀት አለበት፡፡ ዳያስፖራው ማኅበረሰብ በቀጣይ ቀናት በኢትዮጵያ በሚኖረው ቆይታ በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችንና የደረሰውን ውድመት ተዘዋውሮ በመጎብኘት አካባቢዎቹን በዘላቂነት ማቋቋም ስለሚቻልበት ሁኔታ እንዲሁም ሀገሩን ከዚህ በበለጠ ማገልገል ስለሚያስችለው አሰራር ቢያስብና ቢመክር የተሻለ ይሆናል፡፡
በአጠቃላይ ዳያስፖራው የኢትዮጵያን እውነት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስረዳት ያደረገውን ዲፕሎማሲያዊ ተጋድሎና ያስመዘገበውን ድል የበለጠ ለማጠንከር፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በመወጣት የዳያስፖራውን ድል እንዲቀጥል ማድረግ ይገባቸዋል!
ፒያንኪ ዘኢትዮጵያ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 23/2014