የአንድ ቤተሰብ ወግ፤
ቤተሰብ የማሕበረሰብ፣ ማሕበረሰብም የኅብረተሰብ መሠረት መሆን ብቻም ሳይሆን ታላቅ የምትሰኝን ሀገር እንደ ድርና ማግ የሸመኑ ተቋማትም ጭምር ናቸው። የሀገር ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ ወግና ልማዶች፣ ሃይማኖቶችና እምነቶች “ሸማው” የተዋበባቸው የጥበቡ ኅብረ ቀለማት ሲሆኑ፤ ዜጎች ደምቀው የሚጎናጸፉት የእነዚህን እሴቶች የመስተጋብር ጸጋ ነው። ይህንን እውነታ ይበልጥ አድምቆ ለማሳየት ያግዝ ዘንድም ለዚህ ጽሑፍ መንደርደሪያነት “አስኳል” የተሰኘውን ቀዳሚ ተቋም ሊወክል የሚችል የአንድ ቤተሰብ ታሪክ እንደሚከተለው እናስታውስ፡፡
ይህንን ቤተሰብ የሚያውቁት የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ አብሮ አደጎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ስለየትኛው ቤተሰብ እንደሚዘከር በሚገባ ይረዱ ይመስለኛል። የቤቱ አባወራ ለሀገራቸው ክብር ሕይወታቸውን በግዳጅ ቀጣና ለመስዋዕትነት የገበሩ ማዕረግተኛ ወታደር ሲሆኑ እናት ደግሞ ደርባባ የቤት እመቤት ነበሩ። ይህ ቤተሰብ ልጆቹን በሙሉ ያሳደገው በታላቅ የሥነ ምግባር መደላድልና በመንፈሳዊ ሕይወት ጭምር አርቆና አንጾ ነው፡፡
የወላጆቻቸው ጥረት ሰምሮም ከአንዱ የሀገር ውስጥ ነዋሪ ልጅ በስተቀር የተቀሩት ልጆች በሙሉ ነዋሪነታቸው በተለያዩ የውጭ ሀገራት ነው። በዕውቀት የዳበሩትና በሀብት የተባረኩት የዚህ ቤተሰብ ፍሬዎች ታሪካቸው ተጠቃሽ፣ ግብራቸውም አስመስጋኝ የሆኑባቸውን አንዳንድ ጉዳዮች በመጠቃቀስ ወደ ዋናው ጉዳይ እንንደረደራለን፡፡
ስለራሳቸው ማውራትም ሆነ እንዲወራላቸው የማይፈልጉት የዚህ ቤተሰብ ልጆች ለረጅም ዓመታት የኖሩት በውጭ ሀገራት ይሁን እንጂ ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ሀገራቸው እየተመላለሱ እናታቸውን የመክበብ ልማድ አላቸው። እናት ግን ከኖሩበት ማሕበረሰብ፣ ከጎረቤቶቻቸውና በአቅራቢያቸው ካለው የእምነታቸው ደጀ ሰላም መለየቱ አልሆን ስለሚላቸው በደርሶ መልስ ጉዞ ካልሆነ በስተቀር ከልጆቻቸው አንዳቸው ዘንድ ጠቅልለው በመሄድ ኑሯቸውን ባዕድ ምድር ላለማድረግ የወሰኑት ገና ከማለዳው ነበር። ስለዚህም ልጆቹ ዓመታዊውን ቤተሰባዊ መሰባሰቢያ የሚያደርጉት በሀገራቸውና በነባሩ የእናታቸው ቤት ውስጥ ነው፡፡
ብዙ የአካባቢው ነዋሪዎች በምሳሌነት የሚጠቅሱትንና ታሪካቸውን በሩቁ የሚሰማ ሁሉ የሚገረምባቸውን አንዳንድ “ልቦለድ አከል” እና ፈገግ የሚያስደርጉትን የቤተሰቡን ነባር ወግና ባህል እንደሚከተለው ለመዘከር እንሞክር፡፡
ልጆቹ መኖሪያቸውን ከሀገር እርቀው በባዕድ ምድር ያድርጉ እንጂ ቀደም ሲል በልጅነታቸው እድሜ ይተኙበት የነበረው ሰፊ አረግራጊ የሽቦ አልጋ ከእናታቸው ቤት ውስጥ አልወጣም ነበር። ከዓመት ዓመት ሁሌም ማዕረጉን ጠብቆ እንደተነጠፈ ነው። ነባሩ ካሊምም ወዙ አልነጠፈም፤ በዕድሜ ብዛትም አልነተበም። ካሊም ምን እንደሆነ የማያውቁ አንባቢያን ግር እንዳይላቸው እንደ አንሶላ አንዳንዴም እንደ አልጋ ልብስ የሚያገለግል በዝንጉርጉር ቀለማት የተዋበ የአረብ ሀገራት ስሪት የሆነ ቀደምት የሌሊት ልብስ መሆኑን አስታውሶ ማለፉ ግድ ይላል። ሁሉም ልጆች ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ የሚሽቀዳደሙት በዚያ አልጋ ላይ ቀድሞ ለመተኛት ነው። ለምን ይህንን እንደሚያደርጉ ሲጠየቁም “አስተዳደጋችንንና ልጅነታችንን በሚገባ ያስታውስልናል” ምክንያታቸውና መልሳቸው ነው፡፡
አልጋው ላይ ለመተኛት ብቻም ሳይሆን ልክ በልጅነታቸው ይደረግላቸው እንደነበረው ተወዳጇ እናታቸው በአልጋው ዳር ቁጭ ብለው የተኛውን ልጅ ፀጉር ዛሬም እንደ ትናንቱ ስለሚደባብሱ የልጆቹ የእሽቅድድም ሩጫ አንዱ ምሥጢር ይህ ነበር፤ ስስት የሌለበትን የእናትን የፍቅር ጠረን ለማሽተት ጭምር፡፡
ሌላውና እጅግ የሚያስገርመው ልማዳቸው አንዱ ወንድና ተከታዩ ታናሽ እህቱ ታዝለው ያደጉበት ባለ ዛጎል አንቀልባ ሁሌም በላስቲክ እንደተሸፈነ ከተሰቀለበት ግድግዳ ላይ አይወርድም። እነዚህ ሁለት የአንቀልባው ባለታሪክ የቤቱ ልጆች ወደ እናታቸው ጓዳ በመጡ ቁጥር መጀመሪያ የሚያደርጉት ያንን ያሳደጋቸውን አንቀልባ ጠረን ማሽተት ነው። ለምን? የሚለውን ጥያቄ በብዙ አቅጣጫ ስለሚተነትኑት አስደናቂውን ክስተት ብቻ አስታውሶ ማለፉ ይመረጣል። የእናታቸው ቤት መብልና መስተንግዶ የሚካሄደውም ልጆቹ በሕይወታቸው ማለዳ ላይ ይገለገሉባቸው በነበሩት አሮጌ ሣህኖች፣ ኩባያዎችና መሶብ ነው። ይህንን መሰሉን በርካታ የቤተሰቡን አስደማሚ ልማዶች መዘርዘር ቢቻልም ለጊዜው ግን የተጠቀሱት ለማሳያነት ይበቁ ይመስለኛል፡፡
ቀጣዩ ጉዳይ ልጆቹ በሙሉ በእናታቸው ዙሪያ ተኮልኩለው ከሠፈርተኛውና ከቤተዘመድ መካከል ማን ሀዘን እንደገጠመው፣ በጋብቻ ጎጆ እንደወጣ ወይንም የልጅ በረከት እንዳገኘ አለያም የኑሮ እክል እንደገጠመው በዝርዝር በሚሰጣቸው መረጃ መሠረት እየተከፋፈሉ በመጎብኘት ድጋፍ ማድረግ ነው። በእነርሱ የልጅነት ዘመን ታላላቆቻቸው ያደርጉላቸው እንደነበረውም ለአካባቢው ልጆችና ወጣቶች የመማሪያ ቁሳቁሶችና የመጫወቻ ኳሶችንና መለያዎችን በማበርከትም ያበረታቷቸዋል፡፡
እነርሱ ቦርቀውና ፈንጥዘው ባደጉበትና ከቤታቸው ፊት ለፊት ከሚገኘው የሜዳ ጠርዝ ላይ ወደ ማምሻ ግድም ሰብሰብ ብለው በመቀመጥም የልጅነታቸውን ትዝታ እያጠነጠኑ ናፍቆታቸውን ይወጣሉ፡ በየተማሩባቸው ትምህርት ቤቶች እየተገኙም መደገፍ ሌላው ልማዳቸው ነው። የዚህን ቤተሰብ ታሪክ መከታተል ካቆምኩ በርከት ያሉ ዓመታት ተቆጥረዋል። ዛሬ ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ያለማጣራቴ የእኔ ደካማነት ነው። በእርግጠኝነት መመስከር የምፈልገው ግን እኔው ራሴ ብሆን ቢያንስ በዓመት አንዴ ወይንም ሁለቴ አቅጄና ተዘጋጅቼ ባደኩበት በዚያ የተባረከ ሠፈር የእግረ መንገድ ጉብኝት ማድረጌን ያለማቋረጤ ነው፡፡
ከዕለታት በአንዱ ቀን እንደለመድኩት በዚያ ተወዳጅ ሠፈሬ በኩል ሳልፍ ታላላቆቻችንና የእኔው ዘመነ አቻዎች ፈንድቀን ያደግንበት የኳስ መጫወቻ ሜዳችን የአካባቢው አስተዳደር ለምን እንደሆነ ባልገባኝ ምክንያት ያንን ታሪካዊ ሜዳ እየቆፈረ ለግንባታ ሲያመቻች ተመልክቼ በውስጤ ኡኡ እያልኩኝ በመጮኽ ስሜቴን በእንባዬ ገልጬ ማለፌን አስታውሳለሁ። ትርፍ ቦታ ሳይጠፋ ቆፍረው ያበላሹት ሜዳችንን ብቻም ሳይሆን የሺህ ምንተ ሺህ ነባርና የወርተረኛውን ወጣት ስሜት ጭምር እንደሆነ አልገባቸውም ወይንም ለታሪክና ለትውልድ ደንታ አልነበራቸውም። የሚመለከተው ክፍል ትብብር የሚጠይቅ ከሆነ ዝርዝሩንና አካባቢውን ከዚህ ጸሐፊ ጋር አብሮ በመጎብኘት እውነቱን ማረጋገጥ ይቻላል።
የበርካታ ሠፈር ወጣቶች እየተቀጡ ያሉት በጋራ የኳስ መጫወቻ ቦታዎች ያለመኖር ጭምር መሆኑን በእግረ መንገድ ጥቆማ አቤቱታችን ይድረስ እንላለን። እርግጥ ነው ተመርቀው ሥራ ባይጀምሩም በአንዳንድ ክፍለ ከተሞች “የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች” ተመረቁ የመባሉን ዜና ደጋግመን አድምጠናል። በበዓላትና በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ዋና ዋና ጎዳናዎችን በሥልጣናቸው እየዘጉ ሲጫወቱ የሚውሉትን ታዳጊዎችና ነፍስ አወቆች አይቶ የሚራራ የሕዝብ መሪ እንዲፈጠርልን በጸሎትም ሆነ በጉትጎታ መትጋታችንን አናቋርጥም፡፡
ወደ ማጠንጠኛችን እንመለስና ለካስ የሀገር ፍቅር የሚባለው “ቅዱስ መንፈስ” ነፍሳችንንና ሥጋችንን ሰንጎ እንዳሻው ደማችንን የሚያንተከትከው በየግላችን ባደግንበት ቤተሰባዊ ወግና ሥርዓት ውስጥ እየተዘራብን ያደገው ዘር ጎምርቶ ለመከር ሲደርስ ነው። ለካስ ከማሕበረሰቡ እየቀዳን ስንጎነጭ የኖርነው ፍቅርም ህልው ሆኖ ዳር ድንበር ሳይገድበው በውስጣችን እየተላወሰ የሚኖረው የተደበቀ ምሥጢር ስላለው ነው። ለካስ የታነጽንበት ባህልና ታሪክ እያደር ኃይሉ እየበረታ በትዝታ የሚያስቀዝፈን ኢትዮጵያዊነት የሚሉትን ክብር ስለደረብን ኖሯል።
እንጂማ፡- ከቤተሰብ የወረስነው ዘር መች ከደማችን ውስጥ ይጠፋል? የማሕበረሰብ ፍቅርስ መች ከውስጣችን ይደበዝዛል? ባህልና ታሪካችንስ በምን ተዓምር ጠውልጎ ይወይባል? ልብ ብለን ካስተዋልነው “ልጅነቴ፣ ልጅነቴ ማርና ወተቴ!” የሚለው ዝማሬ የለጋ ዕድሜያችን አፍ ማሟሻ፣ የታዳጊነት ዘመናችን ማስታወሻ ብቻ ሳይሆን የእርጅናና የሽበት ማምሻ መተከዣ መዝሙራችን የሆነውም ስለዚሁ ምክንያት ነው፡፡
የእናት ሀገር ቤት፤
ሰሞኑን በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የጠቅላይ ሚኒስትራችንን ጥሪ ተቀብለው የሀገራቸውን አፈረ እየረገጡ ጠረኑን በመማግ “በእናት ዓለም ጓዳ” ውስጥ መሰባሰብ ጀምረዋል። “የጥሪው ደውል የምጽአተ ኢትዮጵያዊያን መሰባሰቢያ ብቻ ሳይሆን ምጽአተ ኢትዮጵያም ጭምር አንደሆነ” ታምኖበት ቢሞካሽ አያንስበትም። እየፈለሱ ወደ ሀገራቸው በመግባት ላይ ያሉት ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ የተሰደደችው ኢትዮጵያም አብራቸው እየገባች ነው።
ይህንን ጠንካራ አገላለጽ ጥቂት እናፍታታው፡- ወደ ሀገር ከተመለሱት ወንድም እህቶቻችን መካከል ብዙዎቹ ለስደት የተዳረጉት ወቅት ወለድ መከራ ከብዶባቸው፣ ሥርዓተ መንግሥታቱ እያሳዳዷቸው መሆኑን ደጋግመው ሲመሰክሩ አድምጠናል። እንባቸውን እያዘሩ በተሰደዱበት ወቅትም “ኢትዮጵያ የምትባልን ሀገር ዳግም ተመልሰው እንደማያዩዋት” ምለውም ይሁን ተገዝተው ቃል በመግባት እንደነበርም በይፋ ሲናገሩ ሰምተናል። ይህ ማለት “ከአፈሯ ኢትዮጵያ” ተኳርፈው ቢርቁም እናታቸው ኢትዮጵያን በመንፈሳቸው አዝለው ወጥተዋል ማለትም ሊሆን ይችላል። ለዚህም ነው ይህ የተለየ ባህርይ ያለው ጥሪ (Historical Homecoming) የኢትዮጵያዊያን ብቻም ሳይሆን የኢትዮጵያዊነት መንፈስም አብሮ እየተመለሰ ነው የምንለው፡፡
እርግጥ ነው ብዙዎች የመጡት “የቁስ ሥልጡን” ከሆኑ ሀገራት እንደሆነ ይገባናል። በዚህም ምክንያት ጓጉተው የሚገቡበት የእናት ሀገራቸው ጓዳ ጎድጓዳ እነርሱ እንደጠበቁት ላይመች ይችል ይሆናል። በተለይም በዚህ ወቅት ከወዳጆች አንደበትና ከሚዲያ ሞገዶች የሚያደምጡት አብዛኛው ዜና ለልብ ስብራት የሚዳርግ ዜናም ሊሆን ይችላል። በአማራ፣ በአፋርና በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች በጨካኞቹና በአረመኔዎቹ ሕወሓትና ሸኔ በተሰኙት “ጠብመንጃ ነካሾች” የፈሰሰው የንፁሐን ደምና እንደ ቅዱስ መጽሐፏ ራሄል ወደላይ ያረገው የሕዝብ እምባ በሰማዩ ላይ አቆርዝዞና ደመናው ከብዶ ሊያስተውሉም ይችሉ ይሆናል። የወደመውን የሀገርና የሕዝብ ሀብት ቀረብ ብለው ሲያስተውሉም ህሊና ባላቸው ሰብዓዊያን ፍጡሮች ስለመፈጸሙ ለማመን ይቸገሩ ይሆናል።
በመንግሥታዊም ሆነ በግል ተቋማት ለሚጠይቁት አገልግሎትም የተቀላጠፈ ምላሽ ላያገኙ እንደሚችሉ ይገመታል። የቢሮክራሲው ጥልፍልፍ ገመዶችም ሊያባሰጯቸው መቻላቸው አይቀርም። ቅንነት በጎደለው መስተንግዶም የስሜት ጉዳት ሊገጥማቸው ስለመቻሉ መከራከር አይቻልም። ለሚፈጽሟቸው ዘላቂ በጎ ተግባራትም ሆነ በዕለት ጉዳዮች ለሚያበረክቱት መልካም ተግባር “አመሰግናለሁ!” የሚል ምላሽም ሊነፈጉ ይችላሉ። እንደሚኖሩባቸው ሀገራት “ሕዝባዊ ባህል” ምናልባትም “በአርቴፊሻል ፈገግታ – እኝ” እያለ ሰላም የሚላቸው ሰውም ውድ ሊሆንባቸው ይችል ይሆናል። እንደነዚህ ዓይነቶቹ ማሕበራዊ ህፀፆች እንደ ቅንቅን ቢኮሰኩሳቸውም የመጡት የእናታቸውን ጠረን፣ የሕዝባቸውን መከራና ርዕይ ለመጋራት ስለሆነ የትዕግሥታቸውን ስንቅ በሚገባ ሊሸክፉ እንደሚገባ ማሳሰቡ አይከፋም፡፡
የረገበው የእናት አረግራጊ የሽቦ አልጋ ባይመችም በአጠገቡ እናት ስላለች እረፍታቸው የሚቆረቁር አይሆንም። መከራና ችግር የማይበግረው የወገናቸው ጠረን የኢትዮጵያም ጠረን ስለሆነ ያጀግናል እንጂ ለቁዘማ አይዳርግም። ከላይ የዘከርነው ያ ቤተሰብ በአንድ ጣራ ሥር የተሰባሰበን ቤተኛ የሚወክል ብቻም ሳይሆን የኢትዮጵያና የልጆቿ አሁናዊ ምሳሌም ጭምር ነው። “ሰው በሀገሩ ሰው በወንዙ . . .” ያለው ሕዝባዊ አንጎራጓሪ እውነት ብሏል። ባለ ሀገሮች ሆይ እንኳን ደህና መጣችሁ። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 23/2014