ኢትዮጵያውያን መመረቅ ይችሉበታል፤ ለሚወዱት መልፋት መሰዋት ግብራቸው ነው። ስሞና አቅፎ ፣መርቆና አወድሶ በመሸኘት የሚያህላቸው የለም። እጆቻቸውን ከፍ አርገው ፣ ሲጠጓቸውም እቅፋቸውን ወለል አርገው ከፍተው ተንደርድረው እጅ ነስተው እቅፍ አርገው የሚወዱትን መቀበል ልማዳቸውም ነው።
በዛው ልክም አትንኩኝ ባይነታቸውና ቁጡነታቸው ከደግነታቸው እኩል አብሮ የሚነሳ ማንነታቸው ነው። በዚህ የማንነት መልክ ትላንት ከትናንት በስቲያቸውን ከታሪክ ድርሳት ቃኝተናል፤ ከአባቶች ትረካ አድምጠናል። ዛሬን ደግሞ ራሳችን እየሠራን ነው። ነገም በዚሁ ይቀጥላል።
ሰሞነኛው ሽር ጉዳችንም ይሄን ኢትዮጵያዊ ማንነት እያሰየ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ጥሪ ተቀብለው በዚህ የገና ወቅት አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወደ አገራቸው በመግባት ላይ ይገኛሉ። ኢትዮጵያውያንም በእናት በአባት ምረቃና ጸሎት ደህና ግቡ ብለው እንደሸኙዋቸው እንኳን ደህና መጣችሁ ብለው እየተቀበሏቸው ነው።
ገና ለክርስትና እምነት ተከታዮች የእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ነው፤ በልደት ውስጥ ደግሞ ትንሳኤ አለ። ልደት ከሌለ ትንሳኤ የለም። ለኛ ለኢትዮጵያውያን የዘንድሮው የገና በዓል ካለፉት ሁሉ ይለያል እላለሁ። የጌታችንን የእየሱስ ክርስቶስ ልደት እና የኢትዮጵያን ትንሳኤ እያሰብን የምናከብረው በዓል በመሆኑ ለየት ያደርገዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ልጆች ከያሉበት ተጠራርተው በእናታቸው ጉያ ስር መሰባሰባቸው የዘንድሮውን ገና ለየት ከሚያደርጉት ምክንያቶች ይጠቀሳል። ስለ ኢትዮጵያ የጮሁ፣ ስለ ጥቁርነት የተጉ መልካም ነፍሶች በዚያም በዚም ተደምጠዋል። ስለ አገራቸው ሉአላዊነት፣ ስለ ሕዝባቸው የመከራ ቀንበር ድምጽ ሆነው ዓለምን በአንድ እግሯ ያቆሙ ኢትዮጵያውያን ሞልተዋል። የኢትዮጵያን ክብርና ነጻነት ለባዕድ አሳልፈን አንሰጥም ሲሉ የአንድነት ንቅናቄ የፈጠሩ መልካም ልቦች በስፋት ታይተዋል፤ እነዚህ ሁሉ .ጊዜው ደርሶ በመሪያችን ጥሪ የእናት አገራቸውን መሬት ረገጡ። እኛም እንኳን ደህና መጣችሁ ስንል አጎነበስን ነው።
እኛ ኢትዮጵያውያን የራሳችን ወግና ስርዐት ያለን ሕዝቦች ነን። ወግ እና ስርዐታችን ዓለምን ያስቀና ገድለ ብዙ ነው። በዚህ የአንድነት ውበታችን ከትላንት ዛሬን አይተናል። በሐዘንና በደስታ ሰዓት አብሮ መሆን ከጥንት አባቶቻችን የወረስነው ሐበሻዊ መልክ ነው። አብሮ መብላት ብርቃችን አይደለም። አንድነትና ሕብረት ድሮም ያለ ነው። የአብሮነትን ጣዕም ለተረዳነው ለእኛ መሰባሰባችን አዲስ ነገር አይደለም።
የዘንድሮው አዲሱ ነገር በኢትዮጵያ የምጥ ሰዓት ከአገሬ በፊት እኔን ብለው ሁሉ ነገራቸውን ጥለው ወደ አገራቸው የመጡት ወገኖቻችን ናቸው። ትንሳኤዋን ሊያዋልዷት፣ ድልና ብስራቷን አጠገቧ ሆነው ሊያዩ፣ ስለ ነጻነቷ እልል ሊሉ የቋመጡ ቀና ነፍሶች መበርከታቸው ነው። ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ መታዘዝ በሚያውቁ ቅን ነፍሶች፣ ጉልበትና ገንዘባቸውን ባልሰሰቱ የቁርጥ ቀን ልጆች መሀል ኢትዮጵያን ማየት እንዴት ደስ ይላል መሰላችሁ።
ኢትዮጵያውያኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሸባሪው ትህነግና ተባባሪዎቹ ላይ ኢትዮጵያውያን የከፈቱት የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ድልን አብሮ ለማክበር ያቀረቡትን ጥሪ አክብረው ነው የመጡት። አንዳንዶቹ መሪ ሲጠራ ይመጣል ብለው መጥተዋል፤ በእርግጥም ትክክል ናቸው። አንዳንዶቹ በእዚህ ወቅት ወደ አገር ቤት ካልተመጣ መቼም አይመጣም ብለው ነው የመጡት። አንዳንዶቹ ምዕራባውያን የሐሰት መረጃ እየረጩ ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ እያስፈራሩ እያስገደዱ ባለበት፣ ዓለም አቀፍ የሚባሉ መገናኛ ብዙሃንም ይህንኑ ሥራ አርገው በሚያሰራጩበት ሁኔታ አገራቸው ሰላም መሆኗን ለመላ ዓለም ለማሳየት አስበውበት ነው የመጡት። ሁሉም ትክክል ናቸው።
እኛ ሰላም ነን..አገራችንም ሰላም ናት። ጠላቶቻችን እንደሚሉት የሆነ አንድም ነገር በእኛ ሰፈር የለም። ይሄን ሰላማችንን መላው ዓለም እንዲረዳው ደግሞ የኢትዮጵያ የክፉ ቀን አምባሳደር የሆኑት ዲያስፖራዎቻችን ያስፈልጉናል። የእነሱ እዚህ መምጣት ገናን ከማክበር በላይ፣ ወዳጆቻቸውን ከማግኘት በላይ ትርጉሙ ብዙ ነው።
ዓለም በነሱ እዚህ መገኘት ውስጥ የሚረዳው እውነት አለ። በእነሱ መምጣት ውስጥ ኢትዮጵያ አገራችን የምትመልሰው ብዙ ጥያቄ አለ። እናም እናት የአገር ባለውለታ ዲያስፖራዎች የአገራችሁ ደቀ መዝሙር ናችሁና የኢትዮጵያን ሰላምና መረጋጋት ለቀረው ዓለም እንድታሳዩ ከፍተኛ አደራ ተጥሎባችኋል።
ሙሴን ሆናችሁ አገራችሁን እንደምታሻግሩ እናምናለን። ኢትዮጵያ በደስታዋ ጊዜ ከሚያሸረግዱላት እኩል በመከራዋ ሰዓትም አለንልሽ የሚሏት ብዙ ልጆች አሏት። ለዚህ ደግሞ እናንተ ምስክር ናችሁ። ለዚህ ደግሞ በዚህ ክፉ ጊዜ አጋር ሆነው ከጎኗ የቆሙት እማኝ ናቸው።
በእናት አገር ጥሪ በገና ሰሞን አገራችንን አርነት እናወጣታለን። ዓለም ከመቼውም ጊዜ በላይ የአንድነታችንን የሐይል ክንድ የሚያደምጥበት ጊዜ ይህ ይሆናል እላለሁ። ጠላቶቻችን ከትላንት እስከ ዛሬ በአንድነታችን በትር ሲደቆሱ ነው የኖሩት። ኢትዮጵያን ለሚወድ ሁሉ ጊዜው የበረከት ነው።
ባለን ነገር ሁሉ ሕዝባችንን ለመጥቀም አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ ምቹ ነው። ያለንን መልካም ነገር ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ የምንዘረጋበት፣ ወደ ሕዝባችን የምንልበት ነው በአንድነት የምንነሳበት ጊዜ ነው። አገር ለመልካም ልቦች ውለታ አላት።
ሕዝብ ለበጎ ነፍሶች ምንዳ አለው። የአገር ውለታ ተራ ጉዳይ አይደለም ። የአገር ውለታ በምንም አይለካም፣ ሕዝብ ብድር ቆጥሮ ሲከፍል እንዲህም አይደል። ኢትዮጵያ አገራችን በመከራዋ ሰዓት አለንልሽ ላሏት መልካም ልቦች ሁሉ በትንሳኤዋ ማግስት ስጦታ አላት። በምንም የማይተካ ስጦታ። የአገር ስጦታ ነጻነት ነው። የአገር ስጦታ ሉአላዊነት ነው። ክብርና መታፈር ነው። የሕዝብ ምንዳ ያልተበረዘ ማንነት ነው።
ዛሬ ላይ እንደ አገርም ሆነ እንደ ሕዝብ የምንከፍለው ዋጋ ነገ ላይ እኛንና በእኛ በኩል የሚመጣውን ትውልድ ቀና የሚያደርግ ነው። ዛሬ ላይ እየሄድንበት ያለው የውጣ ውረድ ጎዳና ነገ ላይ እኛንና ትውልዱን በነጻነት እንደልብ ያራምዳል።
የዛሬ ዝቅታችን በከሀዲው ሕወሓትና በወንበዴ ወዳጆቹ የጎረበጠውን ኢትዮጵያዊነት የተደላደለ ያደርጋል። የጠላቶቻችንን የክፋት መረብ ይበጣጥሳል። ራሳችሁን ለአገራችሁ በመስጠታችሁ ልትኮሩ ይገባል። ጊዜአችሁን ጉልበታቸሁን ለወገናችሁ በመስጠታችሁ እናንተ ብሩካን ናችሁ። በእውቀታችሁ፣ በገንዘባችሁ ባላችሁ ነገር ሁሉ ኢትዮጵያን በማገልገል ላይ ላላችሁ ቀና ትውልዶች የራሳችሁን የማይፈርስ ቤት እየገነባችሁ ነውና ልትኮሩ ይገባል እላለሁ።
ፍጻሜአችን የአገራችን ትንሳኤ ነው። ግባችን የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነት ነው፤ እኚህ ጣምራ ድሎች እውን እስኪሆኑ ድረስ የመስዋዕት በግ ለመሆን ዝግጁ ነን። ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ በአለት ላይ ጠንክረው እስኪቆሙ ድረስ ትግላችን የሚቀጥል ይሆናል። ይሄ በሁላችንም ነፍስ ውስጥ ያለ የጋራ ድምጽ ነው።
አገር በልጆቿ ነው የምትጠበቀው። ሕወሓት ያቆሸሸን ኢትዮጵያዊነት፣ አሜሪካና ምዕራባውያን ያዛቡትን ሐበሻነት ጥጉን እናሳያቸዋለን። ማንነታችንን ዳግም እንዳይደርሱብን አድርገን እናሳያቸዋለን። በመጨረሻም ከጊዜአችሁና ከሐብታችሁ ላይ ቀንሳችሁ ከክፉዎች ሴራ አገራችሁን ልትታደጉ ስትንገላቱ ለነበራችሁ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራዎች እናንተ የእውነት ዜጋ ናችሁ፤አገራችሁ በእናንተ ኮርታለች። እኛም በእናተ ኮርተናል፤ እናመሰግናለን። አሁንም ስለአገራችሁና ስለ ድሀ ሕዝባችሁ እያደረጋችሁት ያለውን የህልውና ትግል በበረታ መልኩ ትቀጥሉበት ዘንድ ኢትዮጵያ አደራ ትላችኋለች።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵያ)
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 23/2014