እንጉዳይን ከነደም ግባቷ በአይኑ በብረቱ አይቶ የማያውቅ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ ከእነ አካቴው በወጥ ብቻ የሚያውቃትም አይጠፋም፡፡ ይሁን እንጂ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች በአስራ አንድ ቁጥር /በእግሩ ማለቴ ነው/ ለተንሸራሸረ ‹‹እንጉዳይን በቤትዎ ጉልቻ ሥር በቀላሉ ማምረት እንዲችሉ እናደርግዎታለን›› የሚለውን የማስታወቂያ ጥሪ ባያይ ባይሰማም ‹‹በቀላሉ ከ20 ሺህ ብር በላይ በወር የሚያፍሱበት የፈጠራ ሥራ ባለቤት እናደርግዎታለን›› የሚሉ የግድግዳ፣ የመብራት እና የስልክ ፖል ማስታወቂያዎች አለማየት አይቻልም፡፡ መቼም ሰው ራሱን ለመታዘብ እድል አይሰጥም እንጂ ለማዳዋን እንጉዳይስ እኔም አላውቃት፡፡
አንድ ሥራ ፈላጊ ባልንጀራዬ ‹‹በአጭር ጊዜ ራስዎን የሚችሉበት የፈጠራ ሥራና የከፍተኛ ደመወዝ ባለቤት መሆን ይፈልጋሉ?›› የሚል ማስታወቂያ ተመልክቶ ‹‹ማንን እፈልጋለሁ›› ሲል ገስግሶ ከተጠቆመበት ቦታ ይደርሳል፡፡ ከዚያም ‹‹በወሬ ናላየን አዙሮ በልጅነታችን የምንጫወትበት እና በተለያዩ ብስባሾች ላይ በቅሎ የምናገኘውን የውሸት እንጉዳይ›› አሳይቶ 50 ብር ቀብድ ክፈል አለኝ፡፡ ‹‹እኔም እንጀራዬ ቀብድ ከማይለው ከፈጣሪዬ እጅ እንጂ ከአንተ እጅ ከቶም አልሻም ብዬ መጣሁ፡፡›› ብሎ ያሳቀኝን መቼም አረሳውም፡፡ አይ የኔ ነገር! ‹‹በቀደዱል ቦይ አትፍሰስ›› አለ የፌስ ቡክ አርበኛ፤ ቁም ነገሬን ረስቼው በሌላ ቦይ ፈሰስኩ፡፡ አሁን አሁን ከሆነ የከተሞቻችን ሕንጻዎች ለምልክት የሚበቁ አልሆኑም፡፡
እነሱን ምልክት ከማድረግ የሄደበትን መንገድ ማስታወስ ላልቻለ የኔ ቢጤ ‹‹ልብ የለሽ›› ባደግንበት በእጁ መዳፍ ላይ ምራቁን ለጉዶ በሌላኛው እጁ ቷ! በማድረግ የበዛውን የምራቅ አካፋይ ተከትሎ መንጎድ ይሻለዋል፡፡ አስተዋይ ጠፍቶ እንጂ በአብላጫ መመራት ከዚህ ይሆን እንዴ የመጣው? የዛሬውን አያድርገውና ‹‹በአድርባይነት፣ እውቅናን አሳልፎ ሰጥቷል›› በሚል ሂስ ታስውጠኝ ነበር፡፡ እስኪ ይሁን፡፡ ስታልፍ ያልተመለከትከው ሕንጻ ስትመለስ ተገጥግጦ ሊቋጭ ደርሶ አለያም ተቋጭቶ ልታገኘው ትችላለህ፡፡ አይንህም አስተውሎትህም ከራስህ ጋር መሆናቸውን ተጠራጥረህ ጠዋት እንዴት ይሄን አላየሁትም በሚል ታዝንባቸዋለህ፤ ትወቅሳቸዋለህ፡፡ ግን ከእነሱ ሳይሆን ከእነዚያ ነው ጥፋቱ፡፡
በሌላኛው ቀን ደግሞ ‹‹አፈር ነህና……እንዳለው ታላቁ መጽሐፍ›› ትቢያ ቅመው ልታያቸው ትችላለህ። በተለይም የአዲስ አበባ ሕንጻዎች መልካቸውም፣ሥሪታቸውም፣ እድሜያቸውም ‹‹የእንጉዳይ›› የሆነ ይመስላል፡፡ ‹‹ፈጥኖ የደረሰ እሸት ወፍ ይበዛበታል›› እንዳሉት አበው ፈጥነው በመድረሳቸው አይን አርፎባቸው ይሆን? ደግሞም እኮ ደመ ግቡ አይደሉም፡፡ ከአይን ያውጣቸው እንጂ ሌላ ምን ይባላል፡፡ እኔ ምለው በግንባታው ጥበብ እውቀቱ ያለው ሰው እንዴት አስችሎት እያያችሁ ያልፍ ይሆን? መልከ ጥፉዎች እኮ ናቸው፡፡ የሙያው ሰዎችም እንደ እኛ በጅምላ ከማወደስ እና በጅምላ ከመንቀፍ በዘለለ የሚያዩበት አይን ከተማሩባቸው ዩኒቨርሲቲዎች አልተቀበሉ ይሆን፡፡ ሌላ ምን ይባላል፡፡ በአገራችን ውብ የሥነ ጥበብ እጆች ያረፉባቸው ሕንጻዎች ነበሩ ነበሩ…ነበሩ…ነበሩ…ነበሩ…ነበሩ የትኛው ትውልድ እነሱን ሊተካ ወኔ ሰንቆ፣ እጅጌውን ሰብስቦ ይሰማራ ይሆን? እድሜ ይስጠን እና ለማየት ያብቃን፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት28/2011
በሙሀመድ ሁሴን