ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሮተርዳም ማራቶን ለድል ይጠበቃሉ

ትልቅ ስም ካላቸው የማራቶን ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው የሮተርዳም ማራቶን ለ44ኛ ጊዜ የፊታችን የረፍት ቀናት ይካሄዳል፡፡ ፈጣን ሰዓት ከሚመዘገብባቸው የማራቶን ውድድሮች አንዱ ሆኖ በሚጠቀሰው በዚህ ውድድር ላይ ዘንድሮም እንዳለፉት ዓመታት ከመላው ዓለም የተውጣጡ ምርጥ የርቀቱ አትሌቶች እንዲሁም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች ይካፈሉበታል፡፡

ለሁለት ቀናት በሚኖረው ውድድር የፊታችን ቅዳሜ ወጣቶችና አዋቂዎችን የሚያሳትፉ በተለያየዩ ርቀቶች ፉክክሮች የሚከናወኑ ሲሆን፤ እሁድ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ጨምሮ ስመ ጥር የማራቶን አትሌቶች ፈጣን ሰዓት ለማስመዝገብ የሚፋለሙበት ዋናው ውድድር ይካሄዳል።

“ፍላት ኮርስ” ወይም ዳገትና ቁልቁለት እንደሌለው በሚነገርለት የሮተርዳም ማራቶን አትሌቶች በርቀቱ ፈጣን ሰዓት ለማስመዝገብ የሚፎካከሩበት ነው። ማራቶንን የሚቀላቀሉ አዳዲስ አትሌቶችም ከባድ የማራቶን ፉክክሮችን ከመጋፈጣቸው በፊት ሮተርዳምን ምርጫቸው ያደርጋሉ፡፡ ይሁን እንጂ ውድድሩ እንደሚነገርለት አዳዲስ ፈጣን ሰዓቶች በየጊዜው ሲመዘገቡበት አይስተዋልም።

የቦታው ክብረወሰን በወንዶች ለቤልጂየም በሚሮጠው ትውልደ ሶማሊያዊው አትሌት በሽር አብዲ የተያዘ ሲሆን፤ አትሌቱ እአአ በ2021 የገባበት 2:03.36 ሰዓት በሮተርዳም ማራቶን ፈጣኑ ነው፡፡ በሴቶች ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ቲኪ ገላና እአአ በ2012 የገባችበት 2:18:58 አሁንም ድረስ ያልተደፈረ የውድድሩ ክብረወሰን ነው፡፡

በዘንድሮው ውድድር አዲስ ሰዓት ሊያስመዘግቡ የሚችሉ ጠንካራ አትሌቶች ተሳታፊ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ምርጥ የማራቶን ሯጭ የሆኑ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይገኙበታል፡፡

በሴቶች መካከል በሚካሄደው ውድድር የሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አስቀድሞ የአሸናፊነት ግምት ማግኘት ችለዋል፡፡ ጥሩዬ መስፍን እና አሚነት አህመድ ደግሞ የውድድሩ አሸናፊዎች ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁ አትሌቶች ናቸው፡፡ በግማሽ ማራቶን ውድድሮች የምትታወቀው ጥሩዬ እአአ በ2022 የቫሌንሲያ ማራቶን ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፋ ስድስተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቋ ይታወቃል። ይህም ዘንድሮ ሮተርዳም ላይ በአርባ ሁለት ኪሎ ሜትሩ ፉክክር ጠንካራ ተወዳዳሪ እንደምትሆን ፍንጭ የሰጠ ነው። አትሌቷ በቀጣዩ ዓመትም በሃምበርግ ማራቶን ተሳትፋ 2:20:18 የሆነ ሰዓት በማስመዝገብ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ነበር የፈጸመችው፡፡ በዚያ ውድድር አሸናፊ ለመሆን ተቃርባ የመጨረሻ ሜትሮች ላይ በመውደቋ ቀዳሚ መሆን እንዳልቻለች ይታወሳል።

ይህች ተስፈኛ አትሌት በድጋሚ የተካፈለችበት የቫሌንሲያ ማራቶን ላይ ሶስተኛ ሆና ማጠናቀቅ ችላለች። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ክለብ አትሌት የሆነችው ጥሩዬ በቅርቡ በተከናወነው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል ሀገር አቋራጭ ቻምፒዮና ላይ በአዋቂ ሴቶች በአሸናፊነት ማጠናቀቋም የሚታወስ ነው፡፡ ይህም ልምዷ ከቀናት በኋላ በሚካሄደው የሮተርዳም ማራቶን ለአሸናፊነት እንድትጠበቅ አድርጓታል።

ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት አሚነት በሃምበርግ፣ አምስተርዳም እና ዶሃ ማራቶኖች በመሳተፍ አስከ ስድስት ያሉትን ደረጃዎች ይዛ በማጠናቀቅ በርቀቱ ጥሩ ልምድ ያላት ሲሆን፣ በዘንድሮው የሮተርዳም ማራቶን ቀላል ተፎካካሪ እንደማትሆን ይጠበቃል። በርቀቱ 2:21:24 የሆነ የግሏ ፈጣን ሰዓት ያላት የ25 ዓመቷ አትሌት በሮተርዳም አሸናፊ ለመሆን ጠንካራ ፉክክር ለማድረግ ተዘጋጅታለች።

ባለፈው ዓመት የሮተርዳም ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አሸቴ በከሪ ኬንያውያን ተፎካካሪዎቿን በሰፊ ልዩነት አስከትላ በመግባት አሸናፊ መሆኗ ይታወሳል፡፡

በወንዶች መካከል በሚካሄደው ውድድር ኬንያዊው የሶስት የዓለም ግማሽ ማራቶን እንዲሁም ሁለት የዓለም ሀገር አቋራጭ ውድድሮች ቻምፒዮን መሆን የቻለው ጄኦፈሪ ማምዎረር ከባድ ሚዛን ተፋላሚ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ቀደም ባሉት ዓመታት በለንደን፣ ኒውዮርክ እና ሮተርዳም ማራቶኖች ተሳትፎ ጠንካራ ተፎካካሪ መሆኑን ያሳየው ይህ ኬንያዊ አትሌት የግሉን ፈጣን ሰዓት ለማስመዝገብ በዘንድሮው የሮተርዳም ማራቶን እንደሚሳተፍ አሳውቋል። ባለፈው ዓመት በዚህ ውድድር አሸናፊ የሆነው የኔዘርላንድስ ዜግነት ያለው ትውልደ ሶማሌያዊው አብዲ ናጌዬ ሲሆን፤ ኢትዮጵያውያኑ አምደወርቅ ዋለልኝ እና ብርሃኑ ለገሰ ደግሞ በአስደናቂ ፉክክር በሰከንዶች ብቻ ተበልጠው ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ነበር ያጠናቀቁት፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You