የአዲስ አበባ የተማሪዎችና መምህራን ውድድር ነገ ይጠናቀቃል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ከከተማዋ ትምህርት ቢሮ ጋር በመሆን ሲያካሂድ የቆየው ከተማ አቀፍ የመምህራንእና የተማሪዎች ስፖርታዊ ውድድር ነገ ይጠናቀቃል።በተማሪዎች መካከል ያለውን የእርስ በእርስ ግንኙነት ማጠናከር እንዲሁም በተለያዩ ውድድሮች ላይ ከተማዋን ሊወክሉ የሚችሉ ስፖርተኞችን ማፍራት ዓላማው በማድረግ ሲከናወን የቆየው ውድድር ዘንድሮ ለ10ኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን፤ በደማቅ መርሃ ግብር እንደሚጠናቀቅ ተጠቁሟል።

የውጤታማ ስፖርተኞች መፍለቂያ በሆኑት ትምህርት ቤቶች ሥልጠናዎችን መስጠትና መሰል ውድድሮችን በማጠናከር ወደፊት ሀገርን ሊያስጠሩ የሚችሉ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት ያስችላል ተብሎ ይታመናል።ተማሪዎች ለስፖርት ያላቸውን ዝንባሌ ከታዳጊነታቸው አንስቶ በማጎልበት ለትልቅ ደረጃ መድረስ እንዲችሉ በመላው ዓለም በትምህርት ቤቶች ውስጥ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ የተለመደ ነው።የኢትዮጵያ የስፖርት ፖሊሲም ህብረተሰቡ በሚኖርበት፣ በሚሠራበት እና በሚማርበት ሥፍራ በስፖርት ተሳታፊ እንዲሆን የሚያበረታታ እንደመሆኑ ተማሪዎች በትምህርት ቤት መምህራንም በሥራ ቦታቸው በስፖርት አካላዊ ጤናቸውን እንዲጠብቁ ጥረቶች ይደረጋሉ።

ትምህርት ቤቶች የህጻናትና ታዳጊዎች ምንጭ እንደመሆናቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን በቀላሉ ማግኘት በመቻሉ እንዲሁም የስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎች በመኖራቸው ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ በተለያየ እድሜ እርከን ምርጥ ስፖርተኞችን ለማፍራት፤ ክለቦች፣ የስፖርት ማሠልጠኛ አካዳሚዎችና ብሄራዊ ቡድኖች ስፖርተኞችን ለመመልመልም ወሳኝ ሥፍራ ነው።መምህራኑ በሚሠሩበት ሥፍራ የውድድር ዕድል እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ የተለየ ተሰጥኦ ያላቸው ደግሞ ከተማ አስተዳደሩን በተለያዩ ውድድሮች የመወከል እድልም ያገኛሉ።በመሆኑም ከተማ አስተዳደሩ ለውድድሩ ትኩረት በመስጠት እንዲከናወን እያደረገ ይገኛል።

‹‹የትምህርት ቤቶች ስፖርት ሊግ ውድድርን ባህል በማድረግ ጤናማ፣ ንቁና ብቁ ትውልድ እንፈጥራለን›› በሚል መሪ ሃሳብ ሲካሄድ የቆየው ውድድርም በየዓመቱ የሚቀጥልም ይሆናል።በአዲስ አበባ ስታዲየም በድምቀት የተጀመረው ውድድር በከተማዋ በሚገኙ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች በ4 ኪሎ፣ ራስ ኃይሉ እና ጃንሜዳን በመሳሰሉ የትምህርትና ሥልጠና ማዕከላት እንዲሁም በመደመር ትውልድ የመጽሃፍ ሽያጭ በየሥፍራው የተገነቡ ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ከ 9 ሰዓት በኋላ ሲከናወን ቆይቷል።አብዛኛዎቹ ውድድሮች ፍጻሜያቸውን ያገኙ ሲሆን፤ አሸናፊዎችም ተለይተዋል።

ፍጻሜ ካገኙ ስፖርቶች መካከል አንዱ አትሌቲክስ ሲሆን፤ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአጠቃላይ ውጤት ቦሌ ክፍለ ከተማ ውድድርሩን በአሸናፊነት ሊያጠናቅቅ ችሏል።ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ እና አራዳ ክፍለ ከተማ ደግሞ ሁለተኛና ሶስተኛ በመሆን ይከተላሉ።በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል በተካሄደው ፉክክር ደግሞ የካ ክፍለ ከተማ በአጠቃላይ ባስመዘገበው ውጤት የውድድሩን የበላይነት ሲይዝ፤ ኮልፌ ቀራንዮ እና አራዳ ክፍለ ከተማ ቀጣዮቹን ደረጃዎች አግኝተዋል።

በጠረጴዛ ቴኒስ ስፖርት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወንዶች ቦሌ እና አራዳ ክፍለ ከተማ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ሲያጠናቅቁ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ እና ልደታ ክፍለ ከተሞች ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። በተመሳሳይ ሴቶች ቦሌ ክፍለ ከተማ፣ ንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ እንዲሁም ልደታ እና አራዳ ክፍለ ከተማ ከአንድ እስከ ሶስተኛ ባለው ደረጃ ተከታትለው ተቀምጠዋል።በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር ደግሞ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በወንድና በሴቶች ውድድሩን በአንደኝነት ሲያጠናቅቅ፤ ጉለሌ ክፍለ ከተማ በወንዶች ሁለተኛ በሴቶች ሶስተኛ፤ ኮልፌ ክፍለ ከተማ በሴቶች ሁለተኛ የካ ክፍለ ከተማ በወንዶች ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

በውሃ ዋና ውድድር ቦሌ ክፍለ ከተማ በ 4 የወርቅ፣ 7 የብር እና በ 2 የሃነስ ሜዳሊያዎች ውድድሩን በአንደኝነት ሲያጠናቅቅ፤ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ 4 የወርቅ እና በ 1 የነሃስ ሜዳሊያ ሁለተኛ እንዲሁም ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በ 1 የብር እና 1 የነሀስ ሜዳሊያ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል። ዛሬ የሚካሄዱ የቅርጫት ኳስ የእግር ኳስ እና ገመድ ጉተታ ውድድሮችም ፍጻሜ የሚያገኙ ይሆናል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You