የአሁን ዘመን ወጣቶች የተፈጠርነው ለወሬ እስኪመስል ድረስ አይቶ ማለፍ አይሆንልንም። ‹‹የጉንጬን ወሬ ከሚቀማኝ ገንዘቤን ቢቀማኝ ይሻላል›› ያለኝን ወጣት አልረሳውም፡፡ ፍቅራችንም ሆነ ትዳራችን በማነብነብ የተወጠነ በመሆኑ መሰረቱ ሸክምን የሚችል ጥንካሬ የለውም።
አስተሳሰባችንን የሰላ አድርገን ከምንገናኝ ይልቅ ሒሳባችንን አስልተን መገናኘት ምርጫችን ነው፡፡ የእውቀታችን ጥግ ማጣቀሻችንም ከፌስ ቡክ አይዘል፡፡ መካሪያችንም፣ ነጋሪያችንም እሱኑ ያደረግን የዋሆች፡፡ መጠጋታችን ባልከፋ ዳሩ የወሬ ጥማታችንን አለማርካቱ እንጂ፡፡ ሐሳባችንን፣ ኑሯችንን፣ ለውጣችንን፣ አጠቃላይ አደራችንን ለፌስቡክ ቤተሰቦች ሰጥተን ትራሳችንን ከፍ አድርገን የተኛነውን ወጣቶች ‹‹ሲነጋ ቀስቅሱን›› ማለቱን ቤት ይቁጠረው፡፡ እህ! ምን እያልኩ ነው?፡፡
የተነሳሁበትን ሐሳብ ትቼ ለፌስ ቡከኞች የነገርናቸውን ሚስጥር ዘከዘኩት እንዴ? ቀልብህን እሱ ይመልስልህ በሉኝ። ዘባረቅኩባችሁ፡፡ ከሰሞኑ አንድ የቀድሞ የሥራ ባልደረባዬ ጋር ተገናኝተን የልብ የልባችንን እያወጋን በደስታ ፍንክንክ ብለናል፡፡ ‹‹በዘመነ ነውጥ የተለያየን በዘመነ ለውጥ ተገናኘን አይደል?›› አለና አይኑን አይኔ ላይ ተከለ፤ ተያየን፡፡ ለአፍታ ፈገግ ያልን ያህል ጥርሳችን ቢታይም በሐሳብ ጭልጥ ብለን መኳተን ይዘናል ፡፡ ሐሳቡን ገታ አድርጎ ‹‹የፌስ ቡክ የይለፍ ቃሌን በመርሳቴ ከጎበኘሁት ረዥም ጊዜ ሆነኝ›› እንካ እስኪ እየው ብሎ ስልክ የያዘ ቀኝ እጁን ዘረጋልኝ፡፡
እኔም እንኳን ተገላገልክ እንደማለት ተቀብዬ ላስተካክልለት ሞከርኩ፤ተሳካልኝ፡፡ ‹‹ከፈትከው?….ከፈትከው?… እንዴት አድርገህ?›› እያለ በደስታ ፈነጠዘ፡፡ ከዚያም ቀበል ብሎ የስልኩን ቁልፎች ነካክቶ ቀና ብሎ ሲመለስ ተበርግዶ ጠበቀው፡፡ ደስታው እንደገና ናረ፣በሳቅ ተንከተከተ፣መረቀ፡፡ በተከፈተው የፌስ ቡክ ገጽ ከተለጠፈ ቆየት ያለ ‹‹ጀግኒት ትችላለች›› የሚል ደማቅ ጽሁፍ ተመለከተና ቀና አድርጎ አሳየኝ፡፡ ቀጥሎም ‹‹ምን የማትችለው አላት?፣ ለመቻል የተፈጠረች አይደለች እንዴ? ፣ እሱ ላያስችል አይሰጥም።›› አለ ቀና ብሎ በሰማዩ ፋንታ ጣሪያውን እያየ። ያኔ እንሰራበት በነበረው ተቋም አገልግሎት ፈላጊው ሥፍር ቁጥር የለውም፡፡
በሰዓት ገብቶ በሰዓት መውጣት አይታሰብም፡፡ ምሽቱ ለዓይን ያዝ እስኪያደርግ ድረስ የተጋጩ ቤተሰቦችን ለማስማማት ላንቃችን እስኪነቃ እንሰራለን፡፡ ደስታም፣ሐዘንም፣ለቅሶም ሁል ጊዜ በሽ በሽ የሆኑበትመስሪያ ቤት፡፡ ንገረን ካላችሁ ቡናም ባይፈላ መቦጨቅ አያቅተኝ፡፡ አስመራቂው ተቋም ባይታወቅም ሁሉም በሚያስብል ደረጃ የእኛ አገር ሰዎች የሀሜት ምሩቅ ናቸው፡፡ የት አጠናኸው እንዳትሉኝ፤ የእሱም ተቋም አይታወቅምና፡፡
የአገራችን ሴቶች በሰው ሀገር የሚሆኑትን ለጊዜው እንተወው፡፡ በሀገራችን ወንዶችም ተነግሮ የማያልቅ ግፍ ይፈጸምባቸዋል። መንግሥት ጭምር እንባቸውን የሚያብስላቸው ሳይሆን ተሰብስበው የሚያለቅሱበት መስሪያ ቤት ለይምሰል ያቋቁምላቸዋል፡፡ ለእነዚህ ቅርብ የሆነው የወረዳ ሴቶችና ሕጻናት ጽህፈት ቤት አብሮ ከማልቀስ በዘለለ ጠንከር ያለ እርምጃ የመውሰድ፣ለአሁን ችግር ፈጣን መፍትሄ መስጠት የሚያስችል ቁመና የለውም።
ክፍለ ከተማም ነጻ ጠበቃ አቆምኩላችሁ በሚል ለማፍያ ሌባ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፡፡ ጠበቃ ተብየሁ ከበዳያቸው ጋር በገንዘብ ይደራደራል፡፡ እሱም የቻለውን ያህል ያስለቅሳል፡፡ ‹‹ተዘርዝሮ የሚያልቅ ይመስል ትተረትራለህ እንዴ በል በቃህ›› ብሎ ከሐሳቤ መለሰኝ፡፡ እየውልህ ‹‹ፖለቲከኞች በፖለቲካ ንግድ ውስጥ ትርፍ እስካገኙ ድረስ እንኳን ከአይኗ ቀርቶ ከሰራ አካሏ ብታነባ ግድ የላቸውም፡፡
አሁን ነው የገባኝ፣ የምትነታረክበት አንድ ሃሳብ ይፈጥሩልህና እነሱ ሥራቸውን ያጧጡፋሉ፡፡›› ታስታውሳለህ አይደል ተጋጭተው የመጡ ባለትዳሮች የሚሉትን፡፡ ‹‹ቀበሌ ስብሰባ የሚባል በ50 ብር አበል መሄድ ከጀመረች ወዲህ፣ በአንድ ለአምስት እንዲህ ተብለናል ማለት ካመጣች ወዲህ ባለቤቴ(ሚስቴ) አልታዘዝ አለችኝ…..ሌላም ሌላም›› በሚል መዘርዘሩን ቀጠለ፡፡ ‹‹ፈጣሪ አልክ አይበለኝ እንጂ፣ ወንዶችም ባል የማይመስሉ ደባሎች በርካታ ናቸው፡፡›› ፈጣሪ ይቅር ይበለኝ ብሎ ከት ከት ብሎ ሳቀና መዘርዘሩን ቀጠለ፡፡
‹‹የፈሰሰ ውሀየማያቃና፣ለልጆቹ ጎሮሮ ወጪ የሚከለክል፣አረብ አገር ልኮ የሚጦር፣ ሚስቴ ዱላ ትወዳለች የሚል፣ አፉ እንዳመጣለት የሚለጥፍ፣በመጠጥና በጫት ሱስ የተንዘላዘለ….. ወዘተ›› አይነሳ ይቅር፡፡ የፖለቲካውን ሰበብ ትተነው የወንዶቹም ዓመል ሺ ነው፣እሾህ ነው፡፡ ተጠፋፍተን መኖራችን ሳያንስ አሁንም ያን ጭቅጭቅ እናነሳለን አይደል? ጨዋታ ቀየርኩ አለኝ፡፡ ደመቅ ባለ ሳቅ ታጅበን ጥሩና የማይረሳ ጊዜ አሳልፈን ተሰነባበትን፡፡
አሁንስ ቢሆን የሴት እህቶቻችን፣እናቶቻችን እና ሚስቶቻችን ሥቃይ እፎይታ አግኝቶ ይሆን? ከራሳችን ጀምሮ ክብር እንሰጣቸዋለን? እናግዛቸዋለን? እነሱስ ለባሎቻቸው እንዴት ናቸው? እኔ እንጃ! የራሴን እወጣለሁ፤የራሳችሁን ተወጡ፡፡ እህት አሳዝኖ ደስታ የለም፡፡ እናት አሳዝኖ ጽድቅ የለም፡፡ ሚስትን አስቀይሞ ሰላም ማደር የለም፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 28/2011
በሙሀመድ ሁሴን