እንዴት ነበር ታላቅ ሀገርና ህዝብ የሆነው? እንዴት ነበር የነጮችን አገዛዝ አሸንፈን የነጻነት ምድር የፈጠርነው? እንዴት ነበር ከራሳችን አልፈን ለመላው ጥቁር ህዝብ የብርሀን ቀንዲል የሆነው ? የስልጣኔ ፋና ወጊ የሆንነው ? ለማያውቁን መልስ አለን…. እንሆ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት
መልስ አንድ
እንዴት ነበር ታላቅ ሀገርና ህዝብ የሆነው? በኢትዮጵያዊነት የስነ ልቦና ውቅር ውስጥ ከየትኛውም የሰው ልጅ የራቀ አንድ በኩረ ማንነት ያለ ይመስለኛል። ደግሞም አለ። አሁን ላይ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ገናና ህዝብ እንደ ባለታሪክም የቆምንው በዛ በኩረ ማንነት ነው እላለው።
ይህ በኩረ ማንነት አጽናፍ..ምኩራብ የሌለው የሀገር ፍቅር ነው። የሰው ልጅ ሁሉ ሞትን ይፈራል። ነፍሶች ሁሉ ከየትኛውም ስጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ጉስቁልና በላይ ከዓለም መለየትን ይፈራሉ። የትኛውም ትውልድ፣ የትኛውም ህላዊ የመጨረሻዋን የሞት ቀን የሚሸሽ ነው። ኢትዮጵያዊነት ላይ ግን ይሄ እውነት አይሰራም።
ኢትዮጵያውያን ስለ ሀገራቸው፣ ስለ ክብራቸው እየሞቱ የመጡ ህዝቦች ናቸው። ስለ ሀገራቸው ብዙ ጊዜ ሞተዋል፣ ብዙ ጊዜ ተጎሳቁለዋል። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ስለ ሀገርና ስለ ህልውና የተከፈሉ በርካታ ሞቶች፣ በርካታ ጉስቁልናዎች አሉ። ሞት ለኢትዮጵያውያን ምንም ነው። ዓለም ላይ ስለ ሀገራቸው ስለ እርስታቸውም ሞትን የማይፈሩ ሀበሾች ብቻ ናቸው። ለዚህ ደግሞ ብዙ ጊዜ እየሞቱ አሳይተውናል። ዛሬም በሕወሓትና በማዕራባውያኑ የጋራ ሴራ ስለ ሀገራችን እየሞትን ነው።
ትውልድ ከአባቶቹ ጥሪት ይወርሳል፣ ትውልድ ከታላላቆቹ እውቀት ስልጣኔ ይቃርማል። ሀገር ካለፈው ታሪክ ይወስዳል። የኢትዮጵያ የታሪክ ትውፊት ለክብር ሲባል መሞትንም ያካተተ ነው። አድዋ በሳቅና በእልልታ አልመጣም። አድዋ በደስታና በፈንጠዝያ አልተገኘም።. አድዋ የሞትና የጉስቁልና ውጤት ነው።
በሀበሻ ምድር ለሀገር ከሆነ ሞት የክብር ጥግ ነው። እናም እላችኋለው እንዴት ነበር ታላቅ ሀገርና ህዝብ የሆናችሁት ብለው ሲጠይቋችሁ ከአባቶቻችን በተማርንው የሀገር ፍቅር ነው በሏቸው። ታላላቆቻችን ባስቀመጡልን የነጻነት አውድ ነው በሏቸው። ለክብራችን እየሞትንና እየተጎሳቆልን ነው በሏቸው።
መልስ ሁለት
እንዴት ነበር የነጮችን አገዛዝ ተቃውመን የነጻነት ምድር የፈጠርነው?
ኢትዮጵያዊነት የፍቅርና የርህራሄ፣ የፍትህና የእውነት ምልክት ነው። በዚያው ልክ የሚሞትለት፣ አይሆኑ የሚሆንለት ሀገርና ህዝብ ያለው ማንነት ነው። ኢትዮጵያ ፍትህ የማታጓድል ሌሎችም ፍትህ እንዲያጓድሉባት የማትሻ ሀገር ናት። በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ያለፉ አብዛኞቹ እንከኖች ፍትህ በማጉደል ሰበብ የመጡ ናቸው።
በበርሊን ጉባኤ ላይ አውሮፓውያን በአፍሪካውያን ላይ አንድ ደባ ሸረቡ። ሁሉም የአውሮፓ ሀገራት አፍሪካውያንን ሊቀራመቱ ተነሱ። በዚህም ኢትዮጵያ ለጣሊያን ደረሰች። አላዋቂ ሳሚ ንፍጥ ይለቀልቃል የሚባለው እሄኔ ነው።.ጣሊያን የኢትዮጵያን ማንነት ሳታውቅና ሳትረዳ ለዘላለም ምናለ ባላደረኩት የምትለውን መጥፎ ታሪክ በራሷ ላይ አተመች።
በወታደሮቿና በዘመናዊ የጦር መሳሪያዋ ተማምና ባህር አቋርጣ ስትመጣ ኢትዮጵያዊነትን በድህነታቸውና በኋላ ቀርነታቸው ብቻ ነበር የመዘነቻቸው። ግን እኛ ስለ ሀገራችን ሞትን የናቅን፣ ስለ ሉአላዊነታችንና ስለአባቶቻችን አደራ ጉስቁልናን የደፈርን ነበርንና ከጣሊያን ስልጣኔ የእኛ ድህነት በለጠ። ከጣሊያን ዘመናዊ መሳሪያ የእኛ ህብረትና አንድነት ላቀ። ከነጮቹ ታንክና መድፍ የእኛ ጦርና ጎራዴ በለጠ…እንሆም አሸነፍን። የነጮችን አገዛዝ በመቃወም የነጻነት ምድርንም ፈጠርን።
ይሄ ትላንት ነው ዛሬም በተመሳሳይ አላማና ተልዕኮ ኢትዮጵያዊነትን ሊያቆሽሹ የሚንቀሳቀሱ የውጪ ሀገራት እየመጡብን ነው። አሸባሪን ደግፈው፣ የመቶ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብን እውነትና ፍትህ ገፍተው ከሕወሓት ጋራ የግፍ እንጀራ ሊቆርሱ ሉአላዊነታችንን የሚጋፉ ሀገራት እየተፈጠሩ ነው።
እንደ ትላንቱ ለክብራችንና ለእውነታችን እንሞታለን። እንደ ትላንቱ በአንድነታችንና በህብረታችን የሀያላኑን ጩኸት ዝም እናሰኛለን። እንደ ትላንቱ አፍሪካ የምትተማመንባትን ኢትዮጵያ ለመፍጠር ዝግጁ ነን። በኢትዮጵያውያን አንድነት የጣሊያን ውርደት የመላው ነጭ ውርደት ሆኖ ዛሬም ድረስ አለ።
በህዝቦቿ ህብረት የኢትዮጵያ አሸናፊነት የመላው ጥቁር ህዝብ አሸናፊነት ሆኖ ዛሬም ድረስ ይወሳል። እንዴት ብለን የነጮቹን አገዛዝ በመቃወም የነጻነት ምድር እንደፈጠርን እኛ እናውቃለን። የመጣን ሁሉ እንዴት መመለስ እንዳለብን የምናውቅ ህዝቦች ነን። አላርፍ ያለች ጣት እንደሚባለው አሁንም ግን አልተውንም። ጭቆናና ጣልቃ ገብነት ታሪክ በሆኑበት፣ ስልጣኔና ዘመናዊነት በቀደሙበት 21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ የአፍሪካ ሁሉ ኩረት የሆነችውን ኢትዮጵያ በመነካካት ላይ ናቸው።
ዝም ባልንበት ለዳግም ድል እየቀሰቀሱን ነው። ኢትዮጵያዊነት ዝም ሲል እንጂ ከተነሳ የሚያቆመው የለም። ዝምታችን ፍርሀት መስሏቸው፣ ትዕግስታችን አቅም ማነስ መስሏቸው ነካኩን…እነሆም በአንድነት ተነሳን። የሕወሓትን አሸባሪ ቡድን አከርካሪ ሰብረን አለምን ስለ ኢትዮጵያ በድምጻችን እየቀሰቀስን ነው።
ወቅቱ ዳግማዊ አድዋ ነው እላለው። የኢትዮጵያ ጠላቶች የሚያፍሩበት፣ ኢትዮጵያዊነት ላይከስም የሚፍምበት ጊዜ። ነጮቹ ለዳግም ውርደት እኛም ለዳግም አድዋ ፍልሚያ ላይ ነን። በሕወሓት የራስ ወዳድነት ሱሰኝነት የጠኸየው ኢትዮጵያዊነት የግፍ እጆችን አሰልሎ፣ የእኔነት ቅጥሮችን ሰባብሮ በታደሰ የትንሳኤ ማለዳ ሊመጣ ዋዜማ ላይ ነው። እንዴት ነበር የነጮችን አገዛዝ ተቃውማችሁ የነጻነት ምድር የፈጠራችሁት ካሏችሁ ከላይ የነገርኳችሁን አንድ ሳታስቀሩ ንገሯቸው።
መልስ ሶስት
እንዴት ነበር ከራሳችን አልፈን ለመላው ጥቁር ህዝብ የቆምነው?
በአፍሪካ የታሪክ ድርሳን ውስጥ አድዋና አንድነት፣ አድዋና ነጻነት፣ አድዋና አፍሪካ ይጠቀሳሉ። አድዋ ስንል ኢትዮጵያ እያልን ብቻ አይደለም። አድዋ ውስጥ አፍሪካ አለ። አድዋ ውጥ መላው የጥቁር ዘር አለ። አድዋ ውስጥ እውነት፣ ፍትህና ነጻነት ከነደምግባታቸው አሉ። አድዋ በኢትዮጵያውያን አንድነትና ህብረት የመጣ እንጂ የመላው አፍሪካ፣ የመላው ጥቁር ህዝብ የመነሳት ጅማሮ ነው።
አድዋ የፈጠረው ሀገር ነው። የፈጠረው አህጉር ነው። አድዋ በኢትዮጵያውያን ሞት አፍሪካውያን የተፈጠሩበት ነው። በኢትዮጵያውያን ጀግንነት የጥቁር ዘር ቀና ያለበት ነው። ከራሳችን አልፈን ለመላው ጥቁር ህዝብ የቆምነው የሀገርና የሉአላዊነትን ሚስጥር ስለምናውቅ ነው።
አሁንም ለተነሱብን ጠላቶቻችን እንዴት ከራሳችን አልፈን ለሌሎች እንደምንተርፍ እናሳያቸዋለን። እነ አሜሪካና መሰል የወንበዴ አሸርጋጆች በንዋይ ልክፍት ሰው የመሆን ጥጉ ጠፍቷቸው ከነፍሰ በላ ቡድን ጋር ለተቧደኑ ለእነሱ እኛ ሀገር፣ እውነት፣ ፍትህ፣ ነጻነትየፈጠሩን ህዝቦች ነን ላትችሉን አትነካኩን እላቸዋለው።
ከትላንት እስከዛሬ አሜሪካ ጣልቃ የገባችባቸውና ያሸነፈቻቸው ሀገራት የነጻነትንም ሆነ የሉአላዊነትን ጥግ የማያውቁ ናቸው። ሀገር ሰው ብቻ ሲኖርባትና ሰው ነጻነትና እውነት በአንድ ላይ ሲኖሩባት የተለያየች ናት። እኛ ኢትዮጵያውያን እንደምዕራባውያኑ ወይም ደግሞ በዳበረ ኢኮኖሚያቸው ድሀ ሀገራትን እንደሚያውኩ የሰው ጭራቆች ሰው ብቻ አይደለንም እኛ ሰውና ነጻነት ነን።
እኛ ሰውና ጥበብ ነን። እኛ እውነና ፍትህ ነን። እኛ ትዕግስትና ይቅርታ ነን። እኛ የዝምታና የመነሳት መጀመሪያና መጨረሻ ነን። እኛ ክብር ሰትተን ክብር የምንፈልግ ለሰው ልጅ ሁሉ ትሁታን ነን። በዚህ ሁሉ ውስጥ ደግሞ አለም የሌለው፣ ይሄን ሁሉ የጸጋ ጥጋችንን አልፎ ለመጣ የማይመለስ፣ ይቅርታ የሌለው ሀገር የመውደድ ልዕልና አለን። ከራሳችን አልፈን ለሌላው የቆምነው በዚህ ነው። ሌሎች በሌላቸው የሀገር ፍቅርና የሀገር መውደድ አባዜ።
መልስ አራት
እንዴት ነበር ለዓለም የስልጣኔ ፋና ወጊ የሆንነው ?
ታሪኮቻችን ከጥንት የጀመሩ ናቸው። ታሪክ፣ ስልጣኔና ዘመናዊነት የኢትዮጵያዊነት ጌጦች ናቸው። ኢትዮጵያዊነትን ተደግፈው፣ ጥቁርነትን ተረማምደን ወደ ነጮች መንደር ያቀኑ ናቸው። አሁን ላይ በምንም ነገር ወደ ኋላ ብንቀርም የምንም ነገር ጀማሪዎቹ እኛ ነበርን።
እኛ የዓለም መልኮች ነበርን..ኢትዮጵያ ስትናገር ዓለም ታደምጥ ነበር። በኦሪትና በአዲስ ኪዳን ላይ ነበርን። ግብራችን በአምላክ ተወዶ ታላቁ መጽሀፍ ላይ ስማችን ተደጋግሞ ተጽፏል።
ነብዩ መሀመድ የእውነትና የፍትህ አገር ሲል ኢትዮጵያን ጠርተዋታል። አባቶቻችን በእውቀት የተካኑ፣ በማስተዋል የበረቱ ነበሩ። ለዓለም ጥበብን ያስተማሩ፣ ለሰው ልጅ ማስተዋልን የሰጡ ነበሩ። በንፋሳትና በደመናት ላይ ስልጣን የነበራቸው፣ የከዋክብትን ውልደትና ጭንገፋ በብራና የቀመሩ ከዓለም ሌላ አብራኮች ነበሩ።
ዓለምን ያሳመሩት እኚህ ነፍሶች ናቸው። ዓለምን ያደመቁት እኚህ ማንነቶች ናቸው። እኚህ ማንነቶች ምንጭና ኩሬአቸውን ኢትዮጵያ ያደረጉ ከእኛነት ሌላ እኔነት የማያውቁ የመቻልና የአንድነት ክንዶች ናቸው።
አክሱምና ላሊበላን የሰሩ እጆች፣ እኚህ እጆች ዛሬም አሉ። እኚህ ልቦች፣ እነዚህ ጥበቦች ኢትዮጵያን ከጠላቶቿ ሊታደጉ ዛሬም አሉ። እኚህ ህብረቶች፣ እኚህ አንድነቶች በትውልዱ ልብ ላይ ዛሬም አሉ።
ዓለምን ለመፍጠር የተጠበብነውን ጥበብ ዛሬ ሀገራችንን ከጠላት ለመታደግ እንጠቀመዋለን። አድዋን ለመፍጠር የተጓዝነውን የተጋድሎ ትግል ዛሬም በሀገር ውስጥና በውጪ ባሉ ጠላቶቻችን ላይ እንደግመዋለን። የኢትዮጵያ ታሪክ በማሸነፍ ተጀምሮ በማሸነፍ የሚጠናቀቅ ነው።
በታሪካችን እጅ የሰጠንበት አንድም ሀገራዊ ጉዳይ የለም። ትላንት በዛሬ ሲገለጥ ኢትዮጵያዊነት ማሸነፍ እንደሆነ እንደርስበታለን። ትላንትም ዛሬም የኢትዮጵያ ህዝብ ደህነቱንና ችግሩን ችሎ ነው። ከጠገበ ጠላቱ ጋር እየተፋለመ ያለው። ይሄ የሀገር ፍቅራችን ምን ያክል እንደሆነ የሚያሳይ ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ በሀገሩና በክብሩ ከመጡበት ሆዴ..ችግሬ የማይል ህዝብ ነው። በዚህ የልዕልና ርምጃው አድዋን ፈጥሯል። አሁንም ዳግማዊ አድዋን ሊፈጥር ከጫፍ ደርሷል። የአባቶቻችንን አደራ ላለማስደፈር እያደረግንው ላለው የህልውና ትግል ውለታችንን ከመጪው ትውልድ እንቀበላለን እላለው።
አባቶቻችን ለእኛ ነበር የሞቱት እኛም ላለውና ለሚመጣው አዲስ ትውልድ የሚከፈለውን ሁሉ በመክፈል ሀገራችንን ከሕወሓትና ከአጃቢዎቹ በመጠበቅ በነበር ክብሯ እንደምናስቀጥላት ስነግራችሁ ከልቤ ነው። እኛ አባቶቻችን በፈጠሩልን የነጻነት ወንዝ ላይ ሳንጎድል…በመትረፍረፍ ስንፈስ ኖረናል። መጪው ትውልድም እኛ በምንፈጥርለት የነጻነትና የክብር ጥላ ውስጥ ማረፍ አለበት እላለው። ይሄ ሁሉ እንዲሆን ሀገር ታሪክና ህዝብ ያስፈልገናል። ሀገር ታሪክና ህዝብ የሚፈጠረው ደግሞ በአንድነት ነው።
የምዕራባውያኑ የተንኮል እጅ በደረሰበት ሁሉ እየደረስን ለሀገራችንም ሆነ ለትውልድ አለንልህ ልንለው ይገባል። ሊጥሉን፣ ሊያደናቅፉን ያልሞከሩት፣ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም። ከአላማቸው በላይ አላማ አንግበን፣ በርትተንና ጠንክረን ባንቆም ኖሮ እሄኔ ጥለውን ነበር። ግን በነኩን ቁጥር እየበዛን ጭራሽ እንደ ያሪኮ ቅጥር ዓለምን በይበቃል ድምጽ ልንደረምሳት ደርሰናል። ይሄ የአንድነት ክንድ ያስፈራል..የአባቶቻችን የአድዋ ሚስጢር ይሄ ነው። ይሄ የአንድነት ድምጽ ሀገር ታሪክና ትውልድ የሚፈጠሩበት ነውና ልንበረታበት ይገባል እላለው።
እንዴት ነበር ቅድመ ዓለም ድህረ ዓለምም የስልጣኔ ፋና ወጊ የወጣችሁ ካሏችሁ ኢትዮጵያዊነትን ከአንድነት ጋር እያጣቀሳችሁ እንዲያ በሏቸው።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 22/2014