“ማንነት” የሚለውን ጽንሰ ሀሳብ ይዞ ለመጻፍ መነሳት እጅጉን ከባድ ቢሆንም፣ የማንነት መገለጫው ብዙ መሆኑ ላይ ተስማምቶ የተወሰኑ ሃሳቦች ላይ ሀሳብ መለዋወጥ ይቻላል። ሁሉ፤ የግል የሆኑ የማንነት መገለጫዎች አሉ። ፆታ የማንነት መገለጫ ነው። ቋንቋ (ምንም እንኳን የእኛ አገር ፖለቲካ ቋንቋ ላይ ብቻ ተጣብቆ ቢያፋጀንም) ሙያ የማንነት መገለጫ ነው። ቤት አሰራራችን፣ ኃይማኖት፣ የፖለቲካ አቋም፣ የትምህርት ደረጃ፣ ተሰጥኦ፣ ታማኝነት፣ የምንከተለው ርእዮተ አለም፣ ባንዳነት ወዘተ ሁሉ የማንነት መገለጫዎች ናቸው። ጀግንነት፣ ፈሪነት . . . ም እንደዛው።
ጉዳዩን እንደ አገር ካየነው የራሳችንን አገር፣ ኢትዮጵያን ወስደን ስለ ማንነት የበለጠ መረዳት እንችላለን። ኢትዮጵያ (ልክ ምኒልክ “እምዬ” እንደሚባሉት ሁሉ) “አንቺ” መባሏ እራሱ አንድ ማንነት ነው (ይህ ማንነቷ ካልሆነ አገራቸውን “አባት አገር” በማለት በተባእት ፆታ ከሚጠሩት ሩሲያ፣ ጀርመን … ጋር ምንም ልዩነት የለውም ማለት ይሆናልና እኛ አገራችንን “እናት ኢትዮጵያ”፤ “እናት አገራችን” በማለት ስንጠራት “ማንነታችሁ አይደለም” የሚለን ካለ ተሳስቷልና አንቀበለውም)።
ኢትዮጵያ የኃይማኖተኞች አገር መሆኗ አንድ ማንነት (National Identity) ነው። የጀግኖች አገር መሆኗ አንድ ማንነት ነው። ከ80 በላይ ቋንቋ የሚነገርባት አገር መሆኗ አንድ ማንነት ነው። የ13 ወር ፀጋነቷም እንዲሁ ሌላ ማንነቷ (ማንነታችን) ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያዊ ማንነት ሲባል እነዚህና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች አብረው መምጣታቸው እርግጥ ነውና በዚሁ አልፈነው፤ የአፋርን ማንነትም (ለምሳሌ “ዳጉ” ለአፋሮች ባህላዊ እሴታቸው ሲሆን የማንነታቸውም መገለጫ ነው።) በዚሁ በኢትዮጵያዊ ማንነት ማእቀፍ ውስጥ አድርገነው፤ ነገር ግን ከሌሎች አኳያ ብዙም ያልተነገረለትን ማንነት ይዘንለት አንዳንድ ቁም ነገሮችን እናንሳ።
አፋር እንደ ማንኛውኛውም የአገሪቱ ስፍራ አንድ የአገሪቱ አካል ነው። አፋሮችም እንደ ማንኛውም አካባቢ እንደሚኖር ማህበረሰብ ኢትዮጵያዊ ናቸው። ነገር ግን ሁሉም እንደየ አካባቢው ሁኔታ፣ ታሪካዊና ባህላዊ አውዱ፣ ተፈጥሯዊና ትውፊታዊ እሴቱ ወዘተ ይበየናልና፣ በእነዚህና ሌሎች በርካታ ምክንያቶች እንደየ አካባቢው ስለሚለያይ እነዛን እያነሱ መጨዋወት የግድ ይሆናል። በዚህ ሂደትም የማይታወቁት እንዲታወቁ፣ ያልታዩት ተገላልጠው ለአደባባይ እንዲወጡ ማድረግ የሂደቱ አካል ነውና ያንንም ማድረግ ይጠበቃል። (በነገራችን ላይ “አፋር” ስንል አካባቢውንም ነዋሪውንም ታሳቢ እያደረግን መሆኑን ልብ ይሏል።) ስለ አፋር ከተሰጡ ምስክርነቶች እንጀምር።
የዘር ግንድ ተመራማሪ አርኪዮሎጂስቶች አካባቢውን በአለማችን ከሚገኙ ቁልፍና ወሳኝ ስፍራዎች ሁሉ ቀዳሚው መሆኑን ያለ መታከት ሲመሰክሩለት ነው የቆዩት። የቱሪዝም ባለሙያዎችም ከዚሁ ባላነሰ ቋንቋ ነው የሚያሞካሹት። ይህ ደግሞ እነሱ ስለፈለጉ ሳይሆን አፋር እንደዛ ሆኖ ስለተገኘ ነውና አፋር ስመ-ጥር ቢሆን አይደንቅም። የድንቅ ነሽ ወይም ሉሲ እና አርዲ አፅሞች በዚሁ በአፋር መገኘታቸውን አንስተን እንጨዋወት ካልን በዚህች ገጽ የሚታሰብ አይደለምና ጉዳዩን ለአንባቢ ትተን ማለፉ ይበጃል።
ያልተዘመረላቸውን፣ እነ ሻለቃ መሀመድ ያሲን (1937 – 1971)ን የመሳሰሉ ጀግኖችን ያፈራው፣ 96,707 ስኩዌር ኪ.ሜ የሚሸፍን የቆዳ ስፋት፤ ከ18 እስከ 45 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሙቀት ያለው አፋር በ1999 (እአአ) በተካሄደ የህዝብ ቆጠራ የሕዝብ ብዛቱ 1,188,000 ሲሆን፤ በከፍተኛ ደረጃ ጥቅም ላይ የሚውል የስነቃላዊ ትውፊት ባለቤትም ነው። ለስነቃሏ ማስረጃ እናቅርብ።
ከአፋርኛ ወደ አማርኛ (በተወላጁ ሙሃመድ አልጋኒ)፣ ከአማርኛ ወደ እንግሊዝኛ ብሪቲሽ ካውንስል ይሰሩ በነበሩት በማይክል ዳንኤል) ከተተረጎሙት የአፋር ተረቶች (አንዱ “አልጋ ወራሹ ልዑል” ነው) መረዳት እንደሚቻለው ተረቶቻቸው ጥልቅ ብቻ ሳይሆኑ ረቂቅና ሁለንተናዊነት የሚስተዋልባቸው ናቸው።
ከላይ በጠቀስነው የትርጉም ስራ ውስጥ እንደምንመለከተው “በአፋረር ተረቶች ውስጥ ጎልቶ የሚታየው የእንቆቅልሽ ብሂል ነው (ለምሳሌ፣ አልጋ ወራሹ ልዑል)። ይህ በቅርብ ምስራቅ ሀገሮች የሚታ[ይ] ጥንታዊ የታሪክ አነጋገር [“አተራረክ” ለማለት ይመስላል] ስልት ነው። (በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሚገኘውን ሳምሶንን ታሪክ እና የኤዲፐስን አፈ-ታሪክ ማመሳከር ይቻላል።”
ይህ፣ እዚህ እንደ ቀልድ ጠቀስ ያደረግነው ጥልቅ ጥናትና ምርምር ቢደረግበት የገዘፈ የአፋር ሕዝብን ማንነት እንደሚያሳይ ምንም ጥርጥር አይኖርምና የሚመለከታቸው (በተለይም የዘርፉ ተመራቂዎች) ልብ ቢሉት ጥሩ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ይሆናል።
ስለ አፋር አካባቢና ህብረተሰቡ ለመግቢያ ያህል ይህንን ካልን ወደ ዋናና ተነሳንበት፤ ከወቅቱ ጋርም በእጅጉ ወደ ተቆራኘው ርእሰ ጉዳያችን እንዝለቅ።
ከአፋር ሕዝብ ማንነቶች አንዱ ጀግንነት (patriotism)፤ የጀግንነት መንፈስ (patriotic spirit) ነው። አልተዘመረላቸውም እንጂ ለአፋሮች ጀግንነታቸው መገለጫቸው ነው። ጀግንነታቸው ብቻ አይደለም፣ በጀግንነታቸው መስዋእትነት የሚከፍሉለት፣ እየከፈሉለትም ያሉት ኢትዮጵያዊነታቸው (National Identity) ደግሞ ሌላውና ቀዳሚ ማንነታቸው ነው። ለዚህ ማረጋገጫችን ደግሞ ሩቅ ሳንሄድ የሽብር ቡድኖ ኢትዮጵያን ካላፈረስኩ ሞቼ እገኛለሁ በማለት ወደ አፋር ሲያቀና የተከናነበው ውርደትና ቅሌት ብቻ ሳይሆን የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ “የአፋር ህዝብ እያለ ኢትዮጵያ አትፈርስም።” ያሉትና ስለጀግንነትና ጀግና በሚፃፉ የጀግንነት ጥቅሶች (patriotic quotes) መጽሐፍ ውስጥ ሊካተት የሚገባው ንግግራቸው ነው።
ከዚሁ ከNational Identity አኳያ (ሰንደቅ ዓላማ አንዱ የNational Identity መገለጫ (ኤለመንት) የጀግንነት መንፈስ (patriotic spirit) የሚያሰርፅ መሆኑን ልብ ይሏል)፤ የቀድሞው የአፋር ሕዝብ ባህላዊ መሪ፣ በሽግግር መንግስቱ ወቅት የአፋር ክልል ፕሬዚዳንት የሆኑት ሱልጣን ሐንፍሬይ አሊ ሚራህ “እንኳን እኛና ግመሎቻችን የኢትዮጵያን ባንዲራ ያውቋታል” ያሉትም እንዲሁ።
በወቅቱም “እንኳን እኛና ግመሎቻችን የኢትዮጵያን ባንዲራ ያውቋታል” ከማለታቸው ጋር በተያያዘ፤ “በዚያ ቀውጢ የወያኔ ዘመን፣ የአገር ክብርና ፍቅር መገለጫ የሆነችውንና በስሟ ስንትና ስንት መስዋዕትነት የተከፈለባትን ክቡሯን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ፣ የወያኔው መሪ መለስ ዜናዊ ’ጨርቅ’ ብሎ በማንኳሰስ፣ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን አእምሯችን ፈጽሞ ያልተዘጋጀበትን ጸያፍ ነገር ውስጣችን ከቶ ለህመም የዳረገን ወቅት ስለነበረ፤ በዚያ የንዴትና የቁጭት ስሜት ውስጥ እያለን፣ የአፋሩ ሱልጣን አሊሚራህ በአንድ መጽሔት ላይ ባደረጉት ቃለ-ምልልስ፤ “የኢትዮጵያን ባንዲራ እንኳን እኛ ግመሎቻችን ያውቁታል” በማለት ታሪካዊውን ጥቅስ እንደ መድሐኒት አቅምሰውን ከህመማችን ፈወሱን።” ተብሎ ተፅፎላቸው ነበር።
የዚህ የአፋር ህዝብ (በአግባቡ ሲጠና Loyalty patriotism ከሚለው ስር ሊመደብ የሚችል) ጀግንነት፤ ከአገር ፍቅርና ታማኝ ዜጋነት የሚመነጭ ጀግንት ዛሬ ላይ ጮክ ብሎ እየተነገረ፤ በተለያዩ መንገዶችም እየታየና በተለያዩ የህትመት ስራዎች ላይም እየተፃፈ ይገኛል። ይህ ያሁኑ ነው።
ነገር ግን፣ “አፋር አሁን ብቻ ነው የጀግናነቱ ማንነት (patriotic identity) ለአደባባይ የበቃው፣ ከዚህ በፊትስ የለም፣ አልነበረምን?” እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ለሚያነሳ፤ ወይም የሚያነሳ ካለ መልሱ “አይ ከድሮም፣ ክጥንት ከጠዋቱ ጀምሮ የነበረ፣ አሁንም ያለ፣ ወደ ፊትም የሚኖር ነው።” የሚል ጥም ቆራጭ መልስ ከመስጠት ያለፈ ሌላ ማለት አይቻልም። ይህንን የምንልበት ምክንያትም ደግሞ የቆምንበት መሰረት በአስተማማኝነቱ ስለሚፈቅድልን እንጂ ሌላ አይደለም። ወይም፣ ባጭሩ “አፋር ባንዳ ሆኖ አያውቅም!!!” ብሎ መመለስ ይቻላል።
አስቀድሞ፣ አፋር አፋር ሆኖ የዚህች አለም (ኢትዮጵያ) አባል መሆን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ጀግንነት (patriotism) የሞራል ግዴታ (moral duty) መሆኑን አሳምሮ ያወቀ፤ በርካታ ብሔራዊ ጀግኖች (national heroes)ንም ያፈራ፤ አገር ማለት ምን ማለት እንደሆነ በጥልቀት የተረዳ፤ በዚህም ምክንያት ለአገሩ ሲል የማይከፍለው መስዋእትነት እንደሌለ ብዙዎች ብዙ የጻፉ ቢሆንም በቅርቡ ለንባብ የበቃውና ዝቅ ብለን የምንጠቅሰው ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ስለ አፋር፣ አገር ወዳድነቱና ብሔራዊ ጀግንነቱ ከማስረዳቱም በዘለለ የአፋር ህዝብ የሞራል ልዕልና ያለው ህዝብ መሆኑን ከበቂ ማብራሪያና ትንታኔ ጋር ለንባብ አብቅቷልና ደራሲውን ልናመሰግነው ይገባል።
ደራሲ በያሲን መ. ያሲን (ዶ/ር) (የአባታቸውን የሻለቃ መሐመድ ያሲንን የግል ማስታወሻ ተጠቅመው፣ በአስፈላጊ መረጃዎች አጎልብተውና በሚገርም የአጻጻፍ ብቃታቸው ከትበው እንካችሁ ያሉን (አሁንም ከልብ እናመሰግናቸዋለን!!!) ይህ መጽሐፍ በውስጡ ስለ አፋርም ሆነ ቀይ ባህር በርካታ የማናውቃቸውን ምስጢሮች አምቆ የያዘ ሲሆን፤ በተዝረከረከ መልኩ የምናውቃቸውንም በተሰደረ ሁኔታ ሰንዶ የያዘ በመሆኑ የምን ግዜም ተፈላጊ መጽሐፍ ያደርገዋልና ሁሉም ሰው ቢያነበው ስለ አትራፊነቱ ሊጠራጠር አይገባም።
በዚህ በያሲን መጽሐፍ (የቀይ ባህር እዳ፤ ከሻለቃ መሐመድ ያሲን ማስታወሻዎች፣ 2014 ዓ.ም) ውስጥ ተገቢውን ስፍራ ከያዙት መካከል አንዱና ልዩ ትኩረትን ያገኘው አፋር አካባቢና አፋሮች ሲሆኑ፤ በመጽሐፉ ማንነታቸው፣ የፖለቲካ አቋምና ተሳትፏቸው፣ ጥርት ያለ ኢትዮጵያዊነታቸው፣ የአገር ፍቅራቸው፣ ታማኝነታቸው፣ እዚህ እየተነጋገርንበት ያለው ጀግንነታቸው … ሁሉ በሚገባ (በመረጃ ተደግፎ – ቀን፣ ወር፣ ዓ.ም) የተገለፀ ሲሆን፤ አንዱም ደራሲው “የአፋር ወጣቶች በሰሜኑ የመደብ ፍልሚያ” በሚል ርእስ፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጥቅምት 26 1971 ዓ.ም እትምን ጠቅሰው ያሰፈሩት እና “በሰሜኑ ወጣቶች በተለይም የጢኦ ወጣቶች ከአብዮቱ ጎን ተሰልፈው ፀረ አብዮተኞችንና ወንበዴዎችን በማርበድበድ ላይ” እንደ ነበሩ መግለፃቸው ነው። ይህ ነው እንግዲ የአፋርና አፋሮች የጀግንነት ታሪክ፤ እየደገሙት ያለውም የነበራቸውን ጀግንነት ነውና አዲስ አይደለም።
ታሪክ እራሱን ይደግማል እንዲሉ ሆነና ዛሬም የእናት ጡት ነካሾች ይህንኑ ባንዳዊ ተግባር በመፈፀማቸው ምክንያት የጀግናውን የአፋር ክንድና ክርን እየቀመሱ፤ ቀምሰውም እየተደመሰሱ ሲሆን ለዚህም ከብዙዎቹ አንዱና የአንድ ግንባር ድል ዜና የሆነውን “ወደ አፋር የገባው እና ወደ ወልዲያ ሊሰብር ያለመው የጁንታው ሀይል አይቀጡ ቅጣት እየቀመሰ ነው። የአፋር ጸጥታ ሀይልና አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ጁንታው ጦርነቱን በከፈተባቸው የዞን አራት ግንባሮች በሙሉ ድልን በመጎናጸፍ ላይ ይገኛል።” የሚለውን የmereja.com ዘገባ መመልከቱ ብቻ ይበቃል። (ይህ ዘገባ የበለጠ ትርጉምና ስሜት የሚሰጠው የሽብር ቡድኑ ለአፋር ሕዝብና ሰራዊት የነበረው ተራ ግምትንና “በቀላሉ በአፋር በኩል በር አስከፍቼ ወደ ጅቡቲ እወጣለሁ” የሚለው እቅዱንና በክልሉ በሚገኛ ንፁሀን ላይ የፈፀመውን ኢሰብአዊና አረመኔያዊ ተግባር ለተረዳ ነው።
ከዚህ ሁሉ፣ ከላይ ከዘረዘርናቸው አፋሮችን ገላጭ አስተያየቶች የምንረዳው ዐቢይ ጉዳይ ቢኖር አቻምየለህ ታምሩ የተባሉ ጸሐፊ “ኢትዮጵያዊነትማ እንደ አፋር ነው!” በሚል ርእስ ስር፤ የአገርን አንድነት፣ ብሔራዊ ክብርና ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ያሚቻለው ከጠላት ጋር የቆሙ የውስጥ ባንዶችን ያለ ምህረት መቅጣት ሲቻልም ነው። አባቶቻችን የጥቁር ሕዝብ የነጻነት ጮራና የተስፋ አርአያ የሆነች አገር ትተውልን ያለፉት የውስጥ ባንዶችን ያለ ምህረት በመቅጣታቸው ነው። የውስጥ ባንዳን የሚታገስ ሕዝብ በጠላቶቹ የሚፈራ፣ በወዳጆቹ የሚከበርና ሉዓላዊ የሆነ አገር ሊኖረው አይችልም።
በዚህ ረገድ የአፋር ሕዝብ ከሰሞኑ ከውስጡ በበቀሉ ባንዶች ላይ ያሳለፈው ሕዝበ ውሳኔ እጅጉን የሚያስደምም ብሔራዊ ተግባር በመሆኑ አገራችንን የምንወድ ሁሉ ልንኮራበት ይገባል። የክልሉ ሕዝብ ባደረገው ጉባዔ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲዖልም ቢሆን እንገባለን ካሉት ከፋሽስት ወያኔ ጋር አሰላለፋቸውን ያስተካከሉ የአፋር ክልል የቀድሞ ባለስልጣናትን የአፋር ደመኛና የኢትዮጵያ ጠላት ናቸው በማለት በአሸባሪነት እንዲፈረጁ ካደረገ በኋላ በተገኙበት እርምጃ ይወሰድባቸው ዘንድ ውሳኔ አስተላልፏል። ይህ የአፋር ሕዝብ ቆራጥነት የአገርና ሕዝብ ጉዳይ ግድ የሚለው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ ስሜት ያለው ሰው ሁሉ ሊቀናበት የሚገባው የአገር መውደድ ተምሳሌት ነው።
በማለት ያሰፈሩትን ነውና እኛም በዚሁ እንሰናበታለን። በመሰናበቻችንም የሱልጣን ሐንፍሬይ አሊ ሚራህ “እንኳን እኛና ግመሎቻችን የኢትዮጵያን ባንዲራ ያውቋታል” ተጠቃሽ ጥቅስ፤ ርእሰ መስተዳድሩ “አፋር እያለ ኢትዮጵያ አትፈርስም!!” ያሉትን ለታሪክ የሚበቃ ንግግር በመጥቀስ ብቻ ሳይሆን፤ ጠቅላይ ሚነኒስትር ዐቢይ አህመድ “የማያውቁ ተነሱባት፤ የሚያውቁ ተነሱላት። የማያውቁ ዘመቱባት፤ የሚያውቁ ዘመቱላት።” ያሉትንና አፈሮችን ከሚያውቁት በመመደብ ነው።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 22/2014