ከታኅሳስ ወር ጀምሮ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል የበጋ ወቅት ስለሆነ በተለይም በገጠሪቱ የአገራችን ክፍል ለሚገኘው አርሶ አደር የእረፍት ጊዜው ነው። በእንዲህ አይነቱ የእረፍት ወቅት ደግሞ ገና፣ ጥምቀት፣ ሰርግና ሌሎች ጉዳዮች ይበዛሉ። እነዚህ ጊዜያት የጨዋታና የደስታ ናቸው። ወጣቶችና ልጅአገረዶች የደስታ ጊዜያቸው ነው። አዋቂዎችም ቢሆን ከሌሎች ወቅቶች በተለየ የሚጫወቱት በዚህ በበጋ ወቅት ነው። በበልግ እና በክረምት ወራት ሰርግ ወይም ሌላ ጉዳይ ቢኖር እንኳን ሰፊ ጊዜ ተሰጥቶት ዘና የሚባልበት አይደለም። ቢያንጎራጉሩም በሥራ ቦታ ላይ ሆነው ነው።
በዚህ በገና ሰሞን ደግሞ ጎረቤት ከጎረቤት በቤታቸው በመጠራራት ስለሀገራቸው ፣ ስለቀያቸው፣ ስለሚቀጥለው ዓመት አዝመራቸው እንዲሁም የአንቶኔ ልጅ የእንቶኔን ልጅ ሊያገባ ነው የሚሉ እና መሰል ጨዋታወችን እያነሱ ወጋቸውን ያቀልጡታል።
‹‹በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ›› የተባለው ደግሞ ለልጆች ነው። የገና ወቅት የበጋ ወቅት ነው። በዚህ ወቅት ልጆች የሥራ ጫና የለባቸውም። የግብርና ሥራ አይታዘዙም፤ ከብትም አይጠብቁም። በዚህ ወቅት ሰብል ስለሚሰበሰብ ከብቶች አይጠበቁም። በመሆኑም ልጆቹ ገና ሲጫወቱ ቤተሰብ ተቆጣኝ አልተቆጣኝ ብለው ሳይሆን በሙሉ ነፃነት ነው። ለአሸንዳ ለልጅ አገረዶች ነፃነት እንደሚሰጠው ሁሉ የገና ጨዋታም ለልጆች ነፃነትን ይሰጣል።
በነገራችን ላይ የገና ጨዋታ ልዩ የሚያደርገው በበጋ ወቅት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ልጆች ወሩን ሙሉ ነፃነትን እንዲያገኙ ምቹ አጋጣሚ ስለሚፈጥር ነው። ለአንድ ቀን ለአንድ ቀንማ በክረምት የሚከበሩ በዓላትም ነጻነት ይሰጣሉ።ለምሳሌ በፍልሰታ (ነሐሴ 16) እና በእንቁጣጣሽ ልጆች እንዲጫወቱ ተብሎ ለበዓሉ ቀን አባቶች ናቸው ከብት የሚጠብቁት። አባቶች እንኳን ባይመቻቸው ሌላ በጎልማሳነት ዕድሜ ላይ ያለ (ጨዋታውን የማይሄድ) ሰው ከብት ይጠብቃል።
ወደ ገናችን እንመለስ። የገና ጨዋታ ብዙ የተባለለት ነው። አሁን ላይ የገና በዓል አከባበር ድምቀቱ ከገጠር ይልቅ ወደ ከተማ ያዘነበለም ይመስላል። በእርግጥ ብዙ ባህሎች ከገጠር ይልቅ ወደ ከተማ እየገቡ ነው። የገና ጨዋታ ከባህል ስፖርቶች አንዱ ሆኖም እውቅና ተሰጥቶታል። የገና ጨዋታ ራሱን ችሎ የመገናኛ ብዙኃን የዜና ሽፋን ለመሆን በቅቷል። ጨዋታውም የራሱ የሆነ ህግና ደንብ ያለው ነው። የራሱ የሆነ ጥበብም አለው።
የገና ጨዋታ ጥበብ፤ ታዳጊዎች (ልጆች) ሲጫወቱ እርስበርስ በቃል ግጥም እንዲሸነቋቆጡ አጋጣሚውን የሚፈጥረም ነው ። ይወዳደሳሉ፤ ይተራረባሉ። በተለይም በጨዋታው የተሸነፈው ቡድን በአሸናፊዎች ይተረባል፤ አሸናፊዎች ደግሞ የድል መልዕክት ባላቸው ስንኞች ራሳቸውን እያሞካሹ ይጫወታሉ።
መጭውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ ስለገና ጨዋታ አንዳንድ እንበል። የገና ጨዋታ ሁለት ቡድኖች ጎራ ለይተው የሚጋጠሙበት ልዩ ባህላዊ ትዕይንት ነው። ለሁለቱ ቡድኖች እኩል እኩል ቁጥር ያላቸው ተጋጣሚዎች ላይኖራቸው ይችላል። የአንደኛው ቡድን በርከት ብሎ፣ የሌላኛው ቡድን አነስ ያሉ ተጋጣሚዎች ሊይዝ ይችላል። በነገራችን ላይ እያወራሁ ያለሁት በባህልና ስፖርት እውቅና አግኝቶ በተቋማዊ አሰራር ስላለው ጨዋታ ሳይሆን ስለእረኞች ልማዳዊ ጨዋታ ነው።
አንደኛው ቡድን ከቀኝ ወደ ግራ ከያዘ፣ ሌላኛው ቡድን ደግሞ ከግራ ወደ ቀኝ ያለውን ስፍራ ይይዛል። አቅጣጫውን ያልለየ ተጫዋች ካለ፣ ‹‹ሚናህን ለይ›› ተብሎ፣ ካስፈለገም በዱላ ቸብ ተደርጎ፣ ቦታውን ይይዛል። በጨዋታ መሃል ሚናውን ስቶ በሌሎች ሚና በኩል ከተገኘ ‹‹ከሚናህ!›› የሚል ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል። በሰሜኑ በተለይም በአማራ አካባቢዎች ‹‹ጥንጓን›› ወይም ‹‹ሩሯን›› የሚመቱበት የዱላው ራስ ‹‹ገና›› ይባላል። ዱላው ከወደ ራሱ እንደ ከዘራ ቆልመም ያለ ነው።
የገና ጨዋታ አሁን አሁን በዘመናዊ መልኩ በከተሞች ከምናየው ትዕይንት ይለያል። በስፖርታዊ ውድድር ውስጥ በገባው ዘመናዊ የገና ጨዋታ ህግ መሰረት፤ ዱላውን (ገናውን) ወደ ላይ ማንሳት አይቻልም። በጥንታዊው ወይም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በሚደረገው የገና ጨዋታ ላይ ግን እንደተፈለገው በማንሳት፣ ሩሯን (ጥንጓን) አክርሮ መለጋት ይቻላል።
በዘመናዊው የገና ስፖርት ጨዋታ ፤በእግር ኳስ ጨዋታ ኳሷ ስትገባ ነጥብ እንደሚቆጠርበት አይነት የግብ ሥፍራ አለው። በልማዳዊው ጨዋታ ግን የገና ጨዋታው የሚካሄድበት ሜዳ ወይም የእርሻ ማሣ፣ ሁለት ጫፎች ወይም ሌላ ምልክት ነገር የግብ ቦታዎች ናቸው። ጨዋታው በውጤት አሊያም በሽንፈት እየታጀበ ይቀጥላል።
አንዱ ቡድን ሩሯን (ጥንጓን) እንዳለማ (እንዳገባ) በተቃራኒው ቡድን ላይ የተረብ መዓት ይዥጎደጎዳል። በገና ጨዋታ ላይ የሚሰነዘሩ ተረቦች ታዲያ እንደ መዝናኛና እንደ ማድመቂያ ነው የሚቆጠሩት። የሚተርበው ቡድን እንኳን በተረቡ ይዝናናል ይስቃል እንጂ ቂም መያዝ ብሎ ነገር በገና ጨዋታ አይታሰብም። ተሸናፊውም በእልህ ለማሸነፍ ይነሳሳል እንጂ በጨዋታ አድማቂው ተረብ አይቆጣም።
በጨዋታው ላይ የሚሰነዘሩ ወይም የሚወረወሩ ተረቦች በአብዛኛው በአካላዊ ገፅታ ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ለምሳሌ ቁመት፣ እርዝመትና እጥረት፣ ውፍረትና ቅጥነት ወዘተ…
‹‹አሲና በል አሲና ጋማዬ
እያሃ … አሲና ጋማዬ››… እያሉ ተጋጣሚዎች ጨዋታውን ያደሩታል።
ለምሳሌ አጫጭሮቹን የቡድን አባላት ለመተረብ አሸናፊዎቹ እንዲህ ይላሉ።
ይህን ወዳጅ ብላ ታስከትለዋለች፤
አንድ ቀን ጩልሌ ታስወስደዋለች ።
አጭሮቹ በተራቸው ደግሞ፡-
እረጅም ነህና ሞኝነት አታጣም ፤
እቆርጥልሃለሁ አሳጥሬ በጣም።
ይኸን ረጅሙን ጎምዶ ጎማምዶ፤
ግማሹን በርጩማ ግማሹን ማገዶ።
እያሉ የአፀፋ ምላሹን ያዥጎደጉዱታል። አሁንም ወፍራሞች ደግሞ ቀጭኖችን እንዲህ ይሏቸዋል፤
ሲሄድ ቅትር ቅትር ሲበላ እንዳንበጣ ፤
ወዘና የሌለው የጨጓራ ቋንጣ።
የተረብ በትር ያረፈባቸው ቀጭኖችም ከአፀፋ ምላሽ አይቦዝኑም፤
እየው አካሄዱን አረማመዱን፤
እንደ ቃሪያ ሎሚ ወጥሮ ሆዱን።
በጥንቱ የገና ጨዋታና አሁንም በአንዳንድ የገጠር አካባቢዎች ሴቶች ባይጫወቱም በሜዳው፣ ዙሪያ ሆነው የሚደግፉትን ቡድን ያበረታታሉ፤ የሚነቅፉትን ደግሞ በተረብ ይሸነቁጡታል።
ወንድ ነው ብዬ ብሰጠው ጋሻ፤
ለእናቱ ሰጣት ለአመድ ማፈሻ።
ወንድ ነው ብዬ ብሰጠው ጦር፤
ለአባቱ ሰጠው ለቤት ማገር ።
እያሉ የገናን ጨዋታ ያደምቁታል።
ገና ጨዋታ በትክክል በአገራችን መቼ እንደተጀመረ በጽሁፍ የተደገፈ መረጃ ባይገኝለትም ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ ይዘወተር እንደነበር ይነገርለታል። አሁን ላይ ደግሞ በተለይም ከክርስቶስ ልደት ጋር ተያይዞ በየዓመቱ በደመቀ ሁኔታ እየተከበረ ይገኛል። እረኞች የገና ጨዋታን ከታህሳስ ጀምሮ እስከ ጥር እና ከዚያም እስከ ክረምቱ መግቢያ ድረስ ይጫወቱት እንደነበር አባቶች ይናገራሉ። በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የገና ባህላዊ ስፖርት በስፋት ይዘወተር እንደነበርም ይነገራል። በገና ጨዋታ ልጆች ልክ እንደ ሆያ ሆየ በየቤቱ እየዞሩም ይጫወታሉ።ልጆች በየቤቱ እየዞሩ በስፋት ከሚጠቀሟቸው ግጥሞች መካከል ፡-
በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ፤
በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ።
የኔማ ጌታ የሰጠኝ ሙክት፤
ባለቦቃ ነው ባለምልክት ። የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።
ልጆች ደግሞ ‹‹ፍየሌን ነብር በላት፤ ለገና ብየ ሳደላድላት…›› እያሉ ይጫወታሉ። ‹‹ማታ ነው ድሌ ይሄ ነው አመሌ›› በማለት ሌሎች የፍቅር ዘፈኖችም ይዘፈናሉ።
ታህሳስ ገሠገሠ ከተፍ አለ ገና፤
እጠብቅሀለሁ አንተ ልጅ ቶሎ ና፤
ይወዘውዘኛል አልጠላኝም ገና ፤
ፍቅር ሞገደኛው እየነሳኝ ጤና።
ምግብ አያስበላ አያስለብስ ልብስ ፤
ሞገደኛው ፍቅሩ ይዞኝ በታህሳስ።
በማለዳ ጀንበር በገና ጨረቃ፤
እኔን እኔን ብላ መጣች ተደብቃ።
የገና ጨዋታ ወጥ የሆነ ህግ የለውም፤ ከአካባቢ አካባቢ እንዲሁም በከተማና በገጠር የተለያየ ህግ ሊኖረው ይችላል። የሚያስፈልገው የተጫዋች ቁጥር ሲሞላ ወገን ወገናቸውን ይዘው በዱላ ቀልጣፋ የሆኑ ተጫዋቾች ጥንጓን (መጫወቻ ኳሷን) ወደፊት እንድትቀጥል ይመቷታል ወይም ይመልሷታል። ተጫዋቾች ብዙ ጊዜ በጨዋታው ስለሚመሰጡ ጥንጓን በተጨዋቾች ከእግር መካከል በገባች ጊዜ ከሰው እግር ጋር ደርበው ስለሚመታቱ የእግር መሰበር ሊያጋጥም ይችላል። ይህ ሁነት ተጨዋቾቹ ወገን ለይተው እስከመፈናከት ሊያደርስ ይችላል።
አንዳንድ ጊዜ ጨዋታው በመጨረሻ ፀብ ስለሚያነሳ ጉዳት ያጋጥማል። ጥንጓም ኃይለኛ ለጊ በመታት ጊዜ ዐይን እስከ ማጥፋት ትደርሳለች። ተጫዋቾች ‹‹ሚና›› ብለው በሚጫወቱበት በቆልማማ ዱላ ቢደባደቡም የሚገላግል ዳኛ አልነበረም፤ ጨዋታውን በሚመለከቱ አባቶችም በድብድብ ከመሳቅ በስተቀር ሽምግልናቸው ለገና ጨዋታ አልተለመደም። ‹‹እግር ይበሳል፣ ያንከላውሳል›› እያሉ ማስፈራራት፣ ራስን መቀወር ወይም እንቆራቆስ ብሎ እጅና እግርን በዱላው መምታት በገና ጨዋታ የተለመደ ነበር።
በንጉሣውያን ዘመን የንጉሡና የንግሥቲቷ እንዲሁም የመኳንንቱም አሽከሮች የጌቶቻቸውን ስም በጉብዝና እየጠሩ እና እያወደሱ ከሚጫወቱባቸው ባህላዊ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የገና ጨዋታ ነው።
በገና ጨዋታ አሸናፊ ለሆኑት ቡድኖች ፊሪዳና ጠጅ ተሰጥቷቸው እየበሉና እየጠጡ፣ እየዘፈኑ ሲሸልሉና ሲያቅራሩ ሜዳውን የጦርነት ድል ያገኙበት ያስመስሉት ነበር። ከጨዋታው በኋላም
ማታ ነው ድሌ
ይሄ ነው አመሌ
አሲና በል አሲና ገናዬ
ኦ! ጉ! አሲና በል አሲና ገናዬ
ግፋው ግፋው አለኝ እኔ እንደምን ልግፋው
የአንድ በሬ ጨጓራ እንደ ቅል የነፋው።
የብብቱ ሽታ
የመንፈቅ በሽታ።
የጀርባው መረሬ፣ ያውላል ጥንድ በሬ።
ከአሥር ጋን አተላ
አይተርፈው በአንኮላ።
እግርህ የሸረሪት
ሆድህ የእንቁራሪት
ቀን እንደጠላሁህ እንዳትመጣ ሌሊት። እየተባለ ይዘፈናል።
ስድብ ለተራው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በመኳንንቱና በነገሥታቱም ላይ ሊሰነዘር ይችላል። በሚደርስባቸው ስድብ ግን ምንም ዓይነት ቁጣና ቅጣት አያደርጉም። ‹‹በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ፤ በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ›› የተባለላቸውም ለዚህ ነው።
የገና በዓል መነሻውና የስነ ቃል ምንጩ ከገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል ቢሆንም አሁን ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኗል። በባህላዊም ሆነ በዘመናዊ መንገድ ጨዋታው ሆነ በዓሉ በድምቀት የሚከበረው በከተሞች በተለይም ደግሞ አዲስ አበባ ነው። ለዚህም ዋናው ምክንያት በገጠር አካባቢ ለሚኖሩ ሰዎች ስለበዓሉ ተገቢ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት አለመሰጠቱ ነው። እንዲያውም በተቃራኒው በገጠሩ ክፍል ገናን መጫወት እንደ ኋላቀርነት እየተቆጠረ መጥቷል። በመሆኑም ገና እና መሰል የባህል ጨዋታዎች በገጠሩ የሃገሪቱ ክፍሎች በድሮው ልክ እየተከበሩ አይደለም።
በከተማ አካባቢ የሚኖረው ህዝብ በማንበብም ሆነ መገናኛ ብዙኃንን በመከታተሉ ሳቢያ አንድ ማህበረሰብ ባህሉን መክብሩ አኩሪ መሆኑን ግንዛቤ ስለተፈጠረለት አሁን አሁን በገጠር ይዘወተሩ የነበሩ የባህል ጨዋታዎች ከገጠር ይልቅ በከተማ አካባቢዎች በስፋት ሲዘወተሩ እያየን ነው።
በውጭው ዓለም የሚኖሩ ሰዎች ለራሳቸው ባህል እየሰጡት ያለው ክብር እጅጉን ከፍ ያለ ነው ። አሁን ላይ በአገራችን በተለይም በገጠሩ የአገሪቱ ከፍል የሚኖረው ማህበረሰብ የአኩሪ ባህል ባለቤት ሆኖ ሳለ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በማህበረሰቡ ላይ ግንዘቤ ለማስጨበጥ የሚሰሩት ስራ ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የባህላዊ ጨዋታዎች የሚከበሩበት ድባብ በከፍተኛ ደረጃ እየደበዘዙ መጥተዋል። ስለሆነም ይህንን አኩሪ ባህል ወደነበረበት ለመመለስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የራሱን አስተዋጾ ማበርከት ይኖርበታል ። መልዕክቴ ነው!!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 21/2014