አሸባሪው ሕወሓት የፈጸመውን ወረራ ተከትሎ በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች በጠላት ቁጥጥር ስር ሆነው ነበር። ታዲያ እንደ ሀገር የቀረበውን የህልውና ትግል በመቀላቀል የክልሉና የፌደራል ብሎም የክልል የፀጥታ ኃይሎች ጠላትን በማሽመድመድ ወደነበረበት መልሰውታል። ምንም እንኳን አሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ ክፉኛ የተመቱ ቢሆንም በሰሜን ሸዋ ዞን ወረራ በፈፀሙበት ወቅት አደጋዎችን ማድረሳቸው የሚታወስ ነው። በሰሜን ሸዋ ዞን የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የግል ንግድ ተቋማት፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከጥቅም ውጪ ሆነዋል። በተጨማሪ በምርታማነት ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል።
አሸባሪዎቹ በሰሜን ሸዋ ዞን ከሚገኙት 32 የወረዳ እና ከተማ አስተዳደሮች ውስጥ 14 በሚሆኑት ላይ ከፍተኛ ቁሳዊና ሠብዓዊ ጉዳት ማድረሳቸውም የሚታወቅ ነው። በአሁኑ ወቅት ዞኑ ወደመደበኛ እንቅስቃሴ የተመለሰ ቢሆንም በርካታ ስራዎች መከናወን እንዳለባቸውም ይታመናል። በአጠቃላይ ሁኔታዎችን አስመልክቶ የዝግጅት ክፍላችን ከሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ ወልደአማኑኤል ጋር ያደረገውን ቆይታ እነሆ።
አዲስ ዘመን፡- የአሸባሪው ሕወሓት በሰሜን ሸዋ ዞን ያደረሰው ጉዳት ምን ይመስላል?
አቶ ሲሳይ፡- በአጠቃላይ ይህ አሸባሪ ቡድን ከዚህ በፊት በተለያዩ ሚዲያዎችና መረጃ ማስተላለፊያ አውታሮቹ አትዮጵያን ለማፍረስ እስከ ሲዖል እንደሚወርድ ይፋ አድርጎ በአማራ እና አፋር ክልሎች መጠነ ሰፊ ወረራ ፈጽሟል። ዞናችንም የዚህ ጥቃት ሰለባ ነው። ይህ ቡድን በዞናችን ከነበሩት 32 የወረዳ እና ከተማ አስተዳደሮች 14 በሚሆኑ ላይ አንዳንዶቹ ላይ በስፋት፣ በሙሉ እና በተወሰኑት ላይ ደግሞ በከፊል ወረራ ፈጽሟል። ይህ አሸባሪ ቡድን የተለመዱ የጥፋት ድርጊቶችን ሲፈፀም ነበር። በርካታ አካባቢዎች የመንግስት ተቋማትን አውድሟል፤ የግለሰብ ተቋማትን አውድሟል ዘርፏል፤ የአርሶ አደሩን ሃብት ዘርፏል፣ የኢኮኖሚ ምንጩ የሆኑትን እንስሳት አርዶ በልቷል። በምድር ላይ ፀያፍ የሚባሉ ወንጀሎችን ፈጽሟል። በዞናችን አሸባሪው ሕወሓት ከሸኔ ጋር በጥምረት ጉዳት አድርሰዋል። እነዚህ ቡድኖች ቤተ እምነቶችን ጭምር ሳይቀሩ ጥቃት ፈጽመዋል። መነኮሳትን ጭምሮ በርካታ ህጻናትና ሴቶችን ደፍሯል።
በዚህ ወቅት ህብረተሰባችን ችግሩን ለመመከት መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ አድርጓል። በሀሳብ በመደገፍ፣ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ለአማራ ፋኖ፤ ልዩ ኃይል፤ ሚሊሻ፣ ለአካባቢ ፖሊስ፣ ለፌደራል ፖሊስ በአጠቃላይ በግንባሩ ለተሳተፉ ኃይል ሁሉ የደጀንነት ሥራ ሰርቷል። በሃብት በስንቅ ደግፏል። ወጣቱ በጦርነቱ ላይ በስፋት በመሳተፍና ቁሳቁስ በማቅረብ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ አድርጓል። በዚህም በዞናችን የተለያዩ አካባቢዎች ትልቅ ተጋድሎ ተፈጽሟል። በዞናችንም የተሰማሩ ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች ዳግም ታሪክ እና ገድል የተፈፀመበት አካባቢ ነው። ጁንታው ላይመለስ መጠነ ሰፊ ጥቃት የተፈፀመበት ቦታ ነው። በአሁኑ ወቅት ወደመጣበት ተመልሷል። በርካታ የጁንታው ኃይል ሙትና ቁስለኛ ብሎም ምርኮኛ የሆነበት ነው። በዚህ ላይ መላው ኢትዮጵያውያን ያደረጉት አስተዋፅኦ እጅግ የላቀና መተኪያ የሌለው ነው። ጦርነቱ የመላው ኢትዮጵያውያን በመሆኑም ሁሉም የሀገራችን ዜጎች ትልቅ ድርሻ አላቸው።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ሕወሓት ቀድሞ ከወረራቸውና የአማራ ክልል የሚገኙ ዞኖች መነሻ በማድረግ ሰሜን ሸዋ ዞን የጠላትን ቅስም ለመስበር የተለየ ዝግጅት አድርጓል?
አቶ ሲሳይ፡- ከዚህ አኳያ ይህ አሸባሪ የሚጠቀምበት የትግል ስልት የመጀመሪያው የውሸት ፕሮፓጋንዳ ነው። ሁለተኛው አካላዊ ጦርነት ነው። ቀድሞ ከወረራቸው አካባቢዎች የሚከተላቸውን ሐሰተኛ አካሄዶች የመረዳትና የማወቅ ዕድል አግኝተናል። ይህም በመሆኑ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በሁለት መንገድ ይከተሉ ነበር። አንደኛው በውስጥ ባንዳ ሲሆን ይህ ኢትዮጵያን በየዘመናቱ እየገጠማት የመጣ ነው። ይህ አሁንም አጋጥሞናል። ህብረተሰቡን ለመበተን፣ ቀየውን ጥሎ እንዲሸሽ ለማድረግ ብዙ የተሰራ ቢሆንም ህብረተሰቡን ቀድሞ በመረጃ ማስታጠቅ በመቻሉ ህብረተሰቡን በከፍተኛ ሁኔታ ጠላትን መረዳት እንዲችል ተደርጓል።
ሕብረተሰቡም በየትኛው አካባቢ ጠላት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ እና ያጠመዱትን መሳሪያ ዓይነትና ቦታ ቀድሞ ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ የጠላትን ህልም አክሽፈዋል። በዚህ ደረጃ አርሶ አደሩ የሰራው ሥራ እጅግ የሚደነቅ ነው። በአጠቃላይ ሲታይ ህብረተሰባችን ጁንታው የሚከተለውን ስልት ቀድሞ ከወረራቸው ቦታዎች መነሻ በማድረግ ብዙ ነገር ተገንዝቧል። ይህን መነሻ በማድረግም ጠላት ክፉኛ እንዲመታ ሆኗል። ከዚህም በመነሳት ህብረተሰቡ ቀዬውን ጥሎ አልፈረጠጠም፤ ይልቁንም ጠላትን ሲያብረከርክ ነበር፤ ውጤቱንም መላው ኢትዮጵውያን የተመለከቱት ነው። ነገር ግን በዚህ መረጃ የተወናበደ ግለሰብና ሠፈር የለም ማለት አይደለም፤ ግን በዓማካይ ሲታይ የጁንታው ሃሳብ አልተሳካም።
በአካላዊ ጦርነት ጁንታው የሚከተለው ስልትም የታወቀ ነው። በመጀመሪያ በወረራቸው አካባቢዎች ሲከተል የነበረውን ለመድገም ነው የሞከረው። ይህም ከባድ መሳሪያዎችን ወደ ማህበረሰቡ በመተኮስ ነዋሪዎች ተረብሸው ቀያቸውን ጥለው እንዲሄዱ ማድረግና የሥነ-ልቦና ጫና መፍጠር ነበር። ይህ በተወሰነ ደረጃ ሰርቷል፤ ግን ቀድሞ መረጃ በመሰጠቱ ህብረተሰቡ በቀየው ሆኖ ሳይበተን ለመከላከያ ሰራዊትና የፀጥታ ኃይሎች ደጀን መሆኑን አስመስክሯል። ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ቀድሜ ልሰዋ፤ ቀድሜ ልገኝ የሚል ማህበረሰብም ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ሸኔ በሰሜን ሸዋ በተደጋጋሚ ጥቃት ሲያደርስ እንደነበር የሚታወቅ ነው። አሁን ዞኑ ሙሉ ለሙሉ ነፃ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ሲሳይ፡- ነፃ ነው ብለን የምንዘናጋበት ሂደት የለም። ሌላው ቢቀር አሸባሪው ሕወሓት ጦርነት አለቀ ብሎ መዘናጋት አይገባም። የአሸባሪ ሕወሓት ጦርነት አሁንም አለ። ከእኛ አካባቢ ስለለቀቀ ሳይሆን እስከ መጨረሻው የኢትዮጵያ ስጋት እስከማይሆንበት ድረስ ትግል ይኖራል ማለት ነው። እንደ ሰሜን ሸዋ ዞን ከዚህ በፊትም የደረሱ ጥፋቶች አሉ። ከዚህ በፊት የደረሱ ጥፋቶችን ሲያወግዙትና ሲያወሩት ብቻ ሳይሆን ያደረሱትን ጥፋቶች መልሶ ለማቋቋም በርካታ ሥራዎች ሲሰሩ ነበር።
አሸባሪቹ ሸኔ እና ሕወሓት በይፋ ጥምረት ፈጥረው በጋራ ኢትዮጵያን እናጠቃለን ብለው ወደ ጥቃት ገብተዋል። በመሆኑም እነዚህን አካላት ሙሉ ለሙሉ ከኢትዮጵያ ምድር አፅድተናል ማለት አንችልም። ስለዚህ አሉ ማለት ነው። በአካባቢያችን ከሸኔ በተጨማሪ የአሸባሪ ሕወሓት ትርፍራፊዎች ሊኖሩ ይችላሉ። የማጽዳትና የመከታተል ሥራ ይጠይቃል። ሁሌ ዝግጁ መሆንንም ይጠይቃል። ለቀጣይም ቢሆን በተለይም አካባቢያችን ለሸኔ ቅርብና ተጋላጭ ነው። ይህንንም ከሌሎች አካላት ጋር በመናበብ ከኦሮሚያ ክልል ጋር፤ ከአፋር ክልል እና ሌሎች አጎራባች አካባቢዎች ጋር በመናበብ ብዙ ሥራዎች እየሰራን ነው። በቀጣይም ብዙ ሥራም ይጠይቀናል። አሁን ግን የአሸባሪዎቹ ሸኔ እና ሕወሓት በጋራ ጥምረት የፈጠሩት ጦርነት ተጠናቋል ተብሎ መዘናጋት አያስፈልግም።
አዲስ ዘመን፡- ዞኑ በተደጋጋሚ አደጋ የጎበኘው ከመሆኑ አኳያ ጉዳት በመድረሱ መልሶ የማቋቋም ሥራው ምን ይመስላል?
አቶ ሲሳይ፡- እንደ ዞናችን መልሶ የማቋቋም ሂደቱን በተለያየ መልክ ነው የምንወስደው። ከዚህ በፊት የተፈናቀሉት ወገኖች ኢትዮጵያ ህዝብ ከውጭና ከውስጥ ሆነው በትብብር በመሥራት ላይ ሆነን ነው አሁን ይህ ጦርነት የተከሰተው። ቤታቸውን በመስራትና ንብረቶችን በማሟላት ላይ በነበርንበት ወቅት ነው ይህ አደጋ እንደገና በመጥፎ ሁኔታ ጉዳት ያደረሰው። አሁን ባለው አረዳድ እና ሁኔታ የዚህኛው እና የዚያኛው ጦርነት የሚል የለም። ሕብረተሰባችንን መልሰን ማቋቋም አለብን። ይህ በራሱ እቅድ የሚመለስ እና ብዙ ሥራ የሚጠይቀን ነው። በወቅቱ በዞናችን በርካታ ተፈናቃዮች ነበሩ። እንደምናስታውሰው በተለይም የመጨረሻው የተፈናቃይ ከፍተኛ ቁጥር የነበረው በሰሜን ሸዋ ዞን ነው። ወደ 450ሺ ዜጎች ነበሩ። የመጨረሻው የተፈናቃዮች መዳረሻ የነበረው ደብረ ብርሃን እና በከተማዋ ዙሪያ ያሉ አካባቢዎች ነበሩ። ከእነዚህ ውስጥ 205ሺ የሚሆኑት በደብረብርሀን ከተማ ነበሩ። ብዙዎቹ በዘመድ ቤት በመጠለል ይህን መጥፎ ወቅት ሲያሳልፉ ነበሩ።
በአሁኑ ወቅት ትራንስፖርት በማመቻቸት 90 ከመቶ የሚሆኑትን ወደ ቀያቸው መልሰናል። በዚህ ወቅት ዞናችንም ሆነ የሌሎች አካባቢዎች አጋዥ ድርጅቶች እና ግለሰቦች የዕለት እርዳታ ተፈናቃዮች ቀዬ በማስጠጋት ሰፊ ሥራ እየተሰራ ነው። ሙሉ ለሙሉ ወደቀያቸው እንዲመለሱ እያደረግን ነው። በተለይም መጠለያ ቤቱ ሊገባበት በሚችልበት አካባቢ ለመኖር እንዲችል ወይንም በአካባቢ ለመኖር የሚያስችል አማራጭ ያለው ሁሉ እየተመለሰ እንዲኖር እየተደረገ ነው። ይህ ከመሆኑ በፊት እንደ ዞናችን ከአጭር ጊዜ አኳያ ብዙ ተግባራትን አከናውነናል። ለምሳሌ ምንም መሠረተ ልማት በሌለበት ተፈናቃይ ሊገባ አይችልም። ስለዚህ የውሃ፣ የመብራትና የስልክ አገልግሎት እንዲሟሉ በማድረግ በኩል ሰፊ ስራዎች ናቸው የተከናወኑት። በዞናችን ወራሪው
ቡድን ባወደመባቸው አካባቢዎች ተጠግነው መሰረተ ልማቶች ተስተካክለው ማህበረሰቡ እየተገለገለ ነው መጠነኛ ችግሮች ቢኖሩም። ከሚመለከታው ድርጅቶች ጋር በመነጋገር ፈጣን ምላሽ ሰጥተዋል። ተቋማትም ተጠግነው ሠራተኞች ወደ ሥራቸው እየተመለሱ ነው። ከረጅም ጊዜ አኳያ ደግሞ በእቅድ የሚመለሱ እና የድጋፍ ሰጪ አካላትንም የሚፈልጉ ስራዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ነዋሪዎችም ግድ ካልሆነባቸው ቀያቸውን መልቀቅ የማይፈልጉ መሆኑን ስለምንረዳ የሚጠበቅብንን ሁሉ እየሰራን ነው። በመሆኑም ወደ ቀያቸው የመመለሱ ሥራ አሁንም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ለሰሜን ሸዋ አጎራባች አካባቢዎች አንዱ አፋር ክልል ነው። በዚህ አካባቢ ተደጋጋሚ ግጭት ቢኖርም በአሁኑ ወቅት አሸባሪውን ሕወሓት በጋራ መክተዋል። በዚህ አካባቢ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ሲሳይ፡- ከግጭት ምንም እንደማያተርፍ የእኛም ሆነ የአፋር ህብረተሰብ ያውቀዋል። በጋራ ሆነን ነው ይህን ጦርነት የመከትነው። ከአፋር ወንድሞች ጋር መረጃ በመለዋወጥና ጠላትን በመመከት ትልቅ ጀብድ የተፈፀመበት አካባቢና ክስተት ነው ያለው። በሁለቱም በኩል ያለው ህብረተሰብም ሆነ አመራር ሠላም ወዳድ ነው። ለሚስተዋለው መፈረካከስና ግጭት ሲሰራበት የኖረ ሴራ ነው። በዚህ አካባቢ ያለው ክፉ ነገር እና ሴራ ጠንሳሽ ሕወሓት መሆኑ ይታወቃል። አሁን በጋራ እየተዋጋን ነው። አሁን የተጀመረው ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማሳደግ አመራርና ህዝቡ በጋራ ይሠራል። አይደለም ከአፋር ክልል ቀርቶ ከሩቅ ያሉትም በጣም አስፈላጊ መሆናቸውን አይተናል። አሸባሪው ሕወሓት ያላላውን እና አንዳችን ሌላችንን በጥርጣሬ እንድንተያይ ያደረገን ሥራ እያከሸፍነው ኢትዮጵያዊነታችንን እያጠነከርን ነው። አሸባሪው ሕወሓት ሕዝብን በመከፋፋል እርስ በእርስ ሲያጋጭ ከመቆየቱም በላይ ሌሎች አሸባሪዎችን በመፍጠርም ትልቅ ሚና ነበረው። ነገር ግን ይህ ጦርነት መላው ኢትዮጵውያን እንድንተባበር ያደረገን ነው። እስካሁን ከአፋር ክልል ጋር ብዙ ሥራዎችን ሰርተናል፤ በቀጣይም ከአፋር ወንድሞቻችን ጋር ተናበን ብዙ ሥራ እንሰራለን።
አዲስ ዘመን፡- ግጭቱ ባስከተለው ዳፋ ሳቢያ በዞኑ ያለው የመስኖ ሥራ እንዳይስተጓጎል ምን እየተሠራ ነው?
አቶ ሲሳይ፡- በጦርነትም ውስጥ ሆነን እቅዳችን ከድህረ ጦርነት በኋላ ሊከሰቱ የሚችሉ ነገሮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት መሥራት እንደሚገባ ታምኖበት ብዙ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው። አሸባሪው ሕወሓት በከፈተው ወረራ እና ጦርነት ሽንፈትን ተከናንቦ ወደ ኋላ እየፈረጠጠ ቢሆንም ጦርነቱ ፍፃሜውን አግኝቷል የሚል ድምዳሜ የለንም። ይሁንና ግን ድህረ ጦርነት ምን መሠራት አለበት የሚለው ጉዳይ ትኩረት የሚሻ ነው ብለን እናምናለን።
ጦርነት ሀብት አውዳሚና ጨራሽ ነው፡ የወደመን ነገር መተካት ደግሞ ሀብት ይፈልጋል። ይህ ሁሌ በምክረ ሃሳቦችን የሚቀርብና ስንነጋገር የቆየንበት ነው። በመሆኑም እስካሁን በጦርነት ሂደት የወደሙ ሀብቶችን የምንተካው በመለመን ብቻ አይደለም። ያለንን አቅም አሟጠን መጠቀም አለብን። በመጀመሪያ ያለንን አቅም፤ ሀብትና ፀጋ አሟጠን መጠቀም በሚለው ላይ ትኩረት እናደርጋለን። ከዚህ በፊት ከነበሩን ልምዶችም እንወጣለን ብለን እናምናለን። ለምሳሌ በመስኖ ሥራ በዓመት ሁለቱ የሚመረት ከሆነ ፈጥኖ የሚደርስ ልማት በመስራት ሦስት ጊዜ በማልማት ምርታማነትን ማካካስ ነው።
መለመን ብናስብ እንኳን ወቅቱ ለመለመን የሚሆን አይደለም፤ በራሳችን ክንፍ መብረር የመጀመሪያው አማራጭ ነው። ከዚህ ቀደም እናግዛችኋለን ብለው የሚያስቡ ኃይሎች ከህልውና ዘመቻ ጋር ተያይዞ ያላቸው አቋም እያየነው ነው። ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር የመስኖ ስራ በከፍተኛ ሁኔታ እና በልዩ ትኩረት እየገባንበት ነው። ክልሉም ሆነ ሌሎች አጋዥ አካላት በዚህ ላይ ትልቅ ድጋፍ እያደረጉ ነው። ምርታማነት ላይ የደረሰውን ኪሣራ ለማካካስ የመስኖ ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ ነው። ለአርሶ አደሮች በፍጥነት የሚደርሱ ምርጥ ዘር በነፃ እየቀረበላቸው ነው። በቆማላ የዞኑ አካባቢዎች የቆላ ስንዴ እየቀረበ ነው። ይህንን በላቀ ደረጃ በመደገፍ ችግሩን ማቃለል አለብን። ችግሮችን ደጋግመን በመተረክ ከችግር ልንወጣ አንችልም። አርሶ አደሩም ሆነ የመንግስት ሰራተኛው ከተለመደው አሠራር በመውጣት ወደ ልማት መግባት አለብን የሚል አቋም ተይዞ በሥፋት እየተሰራ ነው።
አንዳንድ ያደጉ ሀገራት ሚስጥር ጥቃት ሲደርስባቸው በቁጭት ወደ ልማት እና ህዝባቸውን ማነቃነቅ ይገቡና በዚያው ተተኩሰው ይገኛሉ፡ እኛም ይህንን መተግበር አለብን። እኛም የጠፋው አመዱ ላይ ማለቃቀስና ማዘን ሳይሆን ሠርተን እንለወጣለን፤ ዋናው ነገር ይህን ሀገር አፍራሽ ሥርዓት ከድርጊቱ ማስቆም ነው ብሎ መነሳት ይገባል፤ እኛም በዚህ ደረጃ አስበን እየሰራን ነው። ሀብት አባካኝ የሆኑ ልማዶች መቅረት አለባቸው። ለምሳሌ እኛ ሀገር ብዙ ነገሮቻችን ጥሩ ማህበራዊ ግንኙነቶች አሉ። ግን ያለአግባብ ሠርግና ድግሶች መቀነስ አለባቸው።
በዚህ ዓመት ህብረተሰባችን መረዳት ያለበት ሃብት የተረፈበት አካባቢ የለም። ትንሽ የተረፈ ሀብት አለኝ የሚል ግለሰብ በሌላ አካባቢ በዚያው ልክ እጥረት መኖሩንና የሚራብ ወገን መኖሩን ማሰብ አለበት። በመሆኑም ሃብት የምናባክንበት ወቅትና ሁኔታ መኖር የለበትም ብለን እየሰራን ነው። በተረፈ ለጊዜያዊ ፍጆታ የሚሆኑትን እርስ በእርስ በመረዳዳትና ከረጂ ኃይሎች ጋር በመሆን መወጣት ይቻላል። ሌላው አቅደን እየሰራን ያለውን ትርፍ አምራች የሆኑ አካባቢዎች የተጎዱ አካባቢዎችን የሚያግዙበት አሰራር ዘርግተናል። ሃብት በማሰባሰብ እገዛ ማድረግ ይቻላል። በዚህም እቅድ ሳይደርሳቸው ምንጃርን የመሳሰሉ ትርፍ አምራች አካባቢዎች ምርት እያሰባሰቡ ነው። ህብረተሰባችን ደግሞ መተጋገዝ ያውቅበታል፤ ይህን ችግርም ይወጣዋል። በመሆኑም ሁሉም የሚችለውን ጠጠር በመወርወርና ሃብትን በአግባቡ በመጠቀም ከችግሩ የምንወጣበትን ስልት መከተል አለብን።
አዲስ ዘመን፡- ይህን ወቅት እንደ አመቺ ሁኔታ በማሰብ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እና ሌሎች ወንጀሎች እንዳይስፋፉ ምን የተቀየሰ ስልት አለ?
አቶ ሲሳይ፡- ትልቁ ሃብታችን ህብረተሰባችን ነው። በዚህ ወቅት ህብረተሰባችን ጦርነት አልቋል ብሎ መዘናጋት የለበትም። አካባቢን ተደራጅቶና ተራ አውጥቶ በመጠበቅ ሮንድ በማድረግ ሌት ተቀን ፍተሻ እና ክትትሉ እጅግ ማራኪና ለዚህም ውጤት ካበቁን እንቅስቃሴዎች አንዱ ነው። በዚህ ወቅት ደግሞ አሁን ላይ ጦርነት አብቅቷል ብሎ እነዚህን ልምዶች ከተወ አደገኛ ነው ማለት ነው። አሁን በዚህ ሰዓት አሸባሪ ሠላም የማይፈልግ ኃይል እንቅስቀሴ ይኖራል። ምንም ጥርጥር የለውም። ህገ ወጥ የሰዎች እንቅስቃሴ ይኖራል፣ ህገወጥ የጦር መሳሪያ እንቅስቃሴ ሊኖር ይችላል። ይሄ ምንም አያጠራጥርም። እሱን ህብረተሰቡ ቆቅ ሆኖ መከታተል አለበት። ይህ የሽብር ቡድን ስልትም ሊቀይስ ይችላል። አሁን የፊት ለፊት ጦርነቱ ባይሳካ ብሎ ከተነተነ ሌላ ስልት ሊቀይስ ይችላል።
የጥፋት ስልት ጦርነት ብቻ አይደለም። ብዙ ዓይነት የጥፋት ስልቶች አሉ። ስለዚህ ህብረተሰቡ መጀመሪያው ነገር ጦርነት አብቅቷል ከሚል አመለካከት መውጣት አለበት። ምክንያቱም ጦርነቱ ገና ነው። ጦርነቱ ቢያልቅ እንኳን አካባቢህን ነቅቶ መጠበቅ፣ ጸጉረ ልውጥ መከታታል፣ ህገ ወጥ የሆኑ ነገሮችን መከታተል የጋራ እና የእኔ ሥራ ነው ብሎ ይህን ባህል ማድረግ አለበት።
የተደራጀ፣ የተጠናከረ፣ የሚናበብ ህዝብ ባለበት አካባቢ ማንኛውም የውጭም ይሁን የውስጥ የጥፋት ኃይል ተግባሩን ለማሳካት የሚያስብበት እድል ትንሽ ነው። አይስብም ብሎ መውሰድ አይቻልም። ግን የማሳካት እና የማሰብ እንዲሁም የማቀድ እድሉ እጅግ በጣም ትንሽ ነው። መዘናጋት በበዛበት እና መናበብ በሌለበት አካባቢ የጥፋት አጀንዳዎችን ለማሳካት ምቹ ሁኔታዎችን ስለሚፈጥር ህብረተሰባችን የነበረውን የእርስ በዕርስ መናበብ እና ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር የነበረውን መናበብ ልምድ እንደ ባህል ወስዶ ማስቀጠል ያስፈልጋል።
ሌላኛው ነገር ያለአግባብ የሚባክኑ የጥይት ተኩስ አሁን ላይ አያስፈልግም። የማያስፈልግበት ምክንያትም ጥይት በመተኮስ የምናተርፈው ነገር ስለሌለ ነው። የመጀመሪያው ጥይት መተኮስ ሀብት ጨራሽ ነው። የቅርብ ጊዜ ሥራችን ስናስታውስ በግንባር ላይ ሆኖ ጥይት አልቆበት አንድ ጥይት አጥቶ እጁን የሚሰጥ ወይንም ራሱን የሚሰዋ ሰው እንደነበር ይታወቃል። ይህ ባለበት አካባቢ እና ሃገር ውስጥ ሆነን በደስታ መግለጫ መልክ እና በሌሎች ሁነቶች ይህን ያህል የጥይት ብክነት መፈጸም ኢኮኖሚያችንን እየጎዳን መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። በውጭ ምንዛሪ ጭምር የተገዛ ሃብት ነው፤ ስለዚህ በመተኮስ ትርፍ የለም።
ሕብረተሰባችን የልማት፣ የተስፋ እቅድ እንዲያቅድ እንጂ የጥይት ድምፅ እየሰማ የደህንነት ስጋት ውስጥ መግባት የለበትም። እኛ ለደስታ ብለን ጥይት በተኮስን ቁጥር ህፃናትም ሆኑ አዋቂዎች በተለይ ችግሩ የደረሳባቸው አካላት ስለሚኖሩ ፍርሃትና ስጋት ውስጥ ይወድቃሉ፤ እነዚህን ማሳብ ይገባል። ሌላው ላይ የሚፈጥረው የአዕምሮ ጫና መታሰብ አለበት።
ደስታ ለመግለፅ የራሳችንን ወገን መጉዳት የለብንም። ጥይት አለአግባብ መተኮስ ፈርጀ ብዙ የአዕምሮ እና የኢኮኖሚ ጫና እንዳለው መታወቅ አለበት። ይህ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ መወገድ አለበት። ይህን ለማስቆም በፀጥታ ክትትል የሚለው አንድ ነገር ሆኖ ይህን የሚያደርገው አካል ነገሮችን አገናዝቦ መታቀብ አለበት። ብክንት ነው፤ ለሌላው ወገን አዕምሮ የሥነ ልቦና ጫና እንደሚፈጥር መገንዘብ አለበት። ከዚህ በዘለለ የፀጥታ መዋቅራችን የተለየ ክትትል ያደርጋል። ከምንም በላይ ግን እንደማይጠቅም ማወቅ አለብን።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ሕወሓት አማራ ክልል ላይ ወረራ ሲፈፅም የውስጥ ባንዳዎችን በዋናነት እንደተጠቀመ መረጃ እና ማስረጃ እየወጣ ነው። በዚህ ረገድ እነዚህን አካላት በማፅዳት በኩል ዞኑ ምን እየሠራ ነው?
አቶ ሲሳይ፡- የባንዳን ነገር ከዚህ ቀደምም ብለናል። በኢትዮ-ጣሊያን ጦርነት ወቅትም ባንዳ ነበር። መንገድ የሚያሳይ፣ ምግብ የሚያበላ የሚያጠጣ አለ። በአሁኑ ወቅትም አሸባሪው ሕወሓት አማራ እና አፋር ክልልሎች ላይ ወረራ ሲፈፀም ባንዳ ነበር፤ ብዙም አይገርምም። ዋናው ነገር በህግ ቁጥጥር ስር ውለው የፈፀሙት ድርጊት በአግባቡ እየተጣራ ነው። ይህ ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው። በቀጣይም ህብረተሰቡም እነዚህን በጥንቃቄ እየለየ እና እያጋለጠ የዕርምት እርምጃ እንዲወሰድባቸውና በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ህብረተሰቡ መነጽር መሆን አለበት። ነገር ግን የበቀል ዕርምጃ እንዳይኖር መጠንቀቅና መረጃዎችን ማጥራት ይገባል። በመረጃ ላይ መስራትና ማጥራትም ይገባል። እነዚህ ኃይሎች ምንም ይሁን ምንም ለጉዳታችን አስተዋፅኦ አድርገዋል። በመሆኑም በህግ ተጠያቂ ይሆናሉ።
አዲስ ዘመን፡- የዝግጅት ክፍላችን እንግዳ ስለሆኑ እናመስግናለን።
አቶ ሲሳይ፡- እኔም ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ። ሃሳቤን ሳጠቃልል በዚህ ጦርነት መሠረተ ልማቶች ተጎድተዋል፤ ተዘርፈዋል። ይህንን የሀብት ውድመት ለማካካስና ለመመለስ የሁሉንም አካላት ርብርብ የሚጠይቅ ነው። በአንድነታችንና በትብብራችን ተፈናቃዮችን ወደቀያቸውና ወደተለመደው ህይወታቸው መመለስ እንችላለን። ስለዚህ ከውስጥም ይሁን ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ የኢትዮጵያ ሠላምና ልማት ወዳዶች በዚህ ላይ ድጋፍ እንዲያደርጉ የአደራ መልዕክት ማስተላለፍ እወዳለሁ። በዚህ ህልውና ዘመቻ በሕይወት ካጣናቸው ሰዎች ውጪ ሁሉንም ያጣነውን ነገር መመለስ እንችላለን፤ ለዚህም መተባበር አለብን።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ታህሳስ 21 ቀን 2014 ዓ.ም