አሜሪካም ሆነች ምዕራባውያን ሀፍረታቸውን ቅርጥፍ አድርገው በልተው ከአሸባሪው ሕወሓት ጎን የቆሙት ለስትራቴጂካዊ ብሔራዊ ጥቅማቸው ሲሉ፤ ሲጠሩት አቤት ሲልኩት ወዴት የሚል ተላላኪ መንግስት ለማስቀመጥ፤ የኢትዮጵያ የኤርትራና የሶማሊያ መቀራረብ ለቀጠናው ስጋት ስለሚሆን፤ ከቻይናና ከራሽያ ጋር ያላት ግንኙነት ነገ መላው አፍሪካን ሊያሳጣን ይችላል ከሚል ስጋት፤ የነጻነትና የሉዓላዊነት ተምሳሌት የሆነችውን ኢትዮጵያን ካላንበረከክን ነገ ሌሎች ሀገራት የእሷን ፈለግ ተከትለው አንበረከክም ይሉናል በሚል ስጋት፤ ወዘተረፈ ከሚል ስጋት የመነጨ ተደርጎ የሚቀርበው መከራከሪያ ምልክቱን በሽታ፤ በሽታውን ምልክት አድርጎ አዛብቶና አፋልሶ የወሰደ ትንተና ነው የሚል ዕምነት አለኝ።
ምን አልባትም እውነትንና ፍትሕን ታቅፈን በዲፕሎማሲው በሚዲያው በሰብዓዊ መብት ተቋማትና በመንግስታቱ ድርጅት የተወሰደብንን ብልጫ ውጫዊ ምክንያት ለመስጠት እና ሀጢያት ተሸካሚ ፍለጋ የሄድንበት ርቀት እንጂ ዛሬ ለተዳረግንበት ቅርቃር የበቃነው አሸባሪው ሕወሓት ከትጥቅ ትግሉ አንስቶ ላለፉት 46 ዓመታት በተለይ ከዲሞክራቶች ጋር የገነባው መርህ አልባ ግለሰባዊ ግንኙነት ነው ብዬ አምናለሁ። ከፍ ብለው የተዘረዘሩት የተንሸዋረሩ ዕይታዎች ይሄን ግለሰባዊ ግንኙነት ፖሊሲያዊ ተቋማዊና አደረጃጀታዊ ለማድረግ በሽፋንነት የቀረቡ ናቸው። ለዚህ ነው ከምልክቱ ይልቅ በሽታውን ማከም መፈወስ ላይ ማተኮር የሚያስፈልገው። ትክክለኛውን ችግር በአግባቡ መለየት የመፍትሔውን 50 በመቶ መፈጸም ነውና። ከባይደን አስተዳደር ጋርም ሆነ ከምዕራባውያን ጋር ያለን ግንኙነት የሻከረው የግለሰቦችንን ጥቅምና ፍላጎት ለማስጠበቅ ሲባል የተፈጠረ ስህተት ነው።
ሀገራችን በዘመናዊውም ሆነ በጥንታዊ ታሪኳ እንዲህ ያለ እልኸኛ አፋራም ገገማና ገልጃጃ የውጭ ኃይላት ጣልቃ ገብነት ገጥሟት አያውቅም ። ወደፊትም ይገጥማታል ተብሎ አይጠበቅም። በመንግስታቱ ድርጅት ታሪክ በገዛ ወንዟ ላይ የኃይል ማመንጫ ግድብ በመገንባቷ ሁለት ጊዜ ለጸጥታው ምክር ቤት የቀረበች የመጀመሪዋ ሀገር ናት። በትግራይ ክልል የሀገር መከላከያ ሰራዊቷ በተመሳሳይ ሰዓት 40 አነስተኛና ከፍተኛ ወታደራዊ ካምፖቹ ሀገር በከዱ ትግራዊ ከፍተኛ መካከለኛ ዝቅተኛ አዛዦች ወታደሮች እና በሕወሓት ልዩ ኃይል ፖሊስና ሚሊሻ በቴሌቪዥን መስኮት ወጥተው ያለ አንዳች ሀፍረት “መብረቃዊ” ያሉትን ጥቃት በውድቅት ሌሊት በመፈጸም ያልታጠቁና እንቅልፍ ላይ የነበሩ ከ6ሺህ በላይ የሰራዊቱን አባላት በግፍ በመጨፍጨፍ ከነፍስ ወከፍ እስከ ከባድ የጦር መሳሪያ ስንቅና ደመወዝ በመዝረፍ ወደ አዲስ አበባና ወደ አስመራ በመዝመት የመንግስት ለውጥ ለማምጣት አስበውና አልመው ተንቀሳቅሰዋል።
በሀገራችን ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ የማያውቅ ታሪክም ሆነ ትውልድ ይቅር የማይለውን ክህደት በጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ሲፈጽሙ በግዕብታዊነት አይደለም። ለ27 ዓመታት በበላይነት ይዘውት ከነበረው አገዛዝ በሕዝባዊ አመጽና በኢህአዴግ ውስጥ በተፈጠረ የለውጥ ኃይል ቅንጅት በልካችሁ ሁኑ ሲባሉ ጭራቸውን ቆልፈው ኮሽታ ሳያሰሙ መቐሌን የመማጸኛ ከተማቸው ሲያደርጉ እኔን ጨምሮ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ “ፕላን B”አቸውን የገመተ አልነበረም ። በመለኮታዊ ጣልቃ ገብነት በሰላም የተቋጨ መስሎን የኢትዮጵያን አምላክ አመስግነን ነበር ። አንዳንዶቹም የወሎው ሼህ ሁሴን ጅብሪል ትንቢት የተፈጸመ መስሏቸው ነበር ። መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ነው ያልነውም ሆነ ትንቢቱ ተፈጸመ ያሉት በስህተት ነበር። ሁላችንም የእፉኝቷን ሕወሓት ኢተገማችነት ስተን ነበር ።
አሸባሪው ሕወሓት በመማጸኛ ከተማው መሽጎ እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም። ለአራት ግምባሮች አበክሮ ተዘጋጅቷል። ለወታደራዊ ለዲፕሎማሲያዊ ለፕሮፓጋንዳዊና ለኢኮኖሚያዊ ግንባሮች ሌት ተቀን ሲዘጋጅ ባጅቶ ነው የጥቅምቱን ክህደት የፈጸመው። ለዚህ ክህደቱም አሜሪካ ምዕራባውያን ግብጽና ሱዳን ቡራኬያቸውን ሰጥተዋል። ከሀገር ውስጥ ቡችሎቹ ከእነ ኦነግ ሸኔ ከቅማንት ከአገው ሸንጎ ከጉምዝ ከጋምቤላ ታጣቂዎች ይሁንታን አገኝቷል። እኔ በዚህ እገፋለሁ እናንተ በያላችሁበት ተነሱ ብሏቸዋል። በወሎ ግንባር ከሚሴና አካባቢው የሆነውም ይኸው ነው።
ቡድኑ የቀዝቃዛው ጦርነት የፈጠረለትን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከትጥቅ ትግል አንስቶ ከአሜሪካና ከምዕራባውያን ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበረው። ወደ አገዛዝነት ከመጣ በኋላም የቀጣናው ተላላኪና ጉዳይ አስፈጻሚያቸው ነበር። በትጥቅ ትግሉ ወቅት ከጌይል ስሚዝ ከፖል ሔንዝና ከመሳሰሉት ጋር እጅግ የቀረበ ግንኙነት ነበረው። በተለይ ጌይል አንሶላ እስከ መጋፈፍ የደረሰ ግንኙነት ነበራት። ለዚህ ነው በትጥቅ ትግሉ ወቅት የማህበረ ረድኤት ትግራይ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ እስከመሆን ደርሳ የነበረው። በመንግስትም ሆነ በግለሰብ ደረጃ የነበራቸው አጋርነት ነው በእርዳታ ስም በአየርና በየብስ የጦር መሳሪያ እንዲደርሳቸውና እስካፍንጫቸው እንዲታጠቁ ያደረጋቸው ።
በተለይ የ1977 ዓ.ም ደርቅን በሽፋን በመጠቀም ያገኙት ሁለንተናዊ ድጋፍ ጨዋታውን የቀየረ ነበር። የእርዳታ እህል የእናቶችና የህጻናት አልሚ ምግብ ሳይቀር ሱዳን ላይ ሽጠው የጦር መሳሪያ የገዙበት፤ የፓርቲ ጉባኤ ያካሄዱት በእነ ጌይል ስሚዝ አይዟችሁ ባይነት ነበር ። ወደ አገዛዝ ከመጡ በኋላም መርሕ አልባው ግንኙነት ተቋማዊና ቤተሰባዊ ሆኖ ቀጥሏል ። መለስ ጌይል ስሚዝ ስትወልድ አሜሪካ ድረስ ሄዶ እንኳን ማሪያም ማረችሽ ብሏል። ይህ ግንኙነት እንደዋርካ ሰፍቶ እነ ሱዛን ራይስን አንቶኒ ብሊንከንን ሳማንታ ፓወርን ሊንዳ ቶማስ ፊልትማንን እና ደቀመዛሙርታቸውን አካቶ ዛሬ ላይ ደርሷል። ሕወሓት አገዛዝ ላይ በቆየባቸው 27 ዓመታት የጥቅሙ ተጋሪ ነበሩ ።
ለአንዳንዶቹ የገና በዓል አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር በመቶ ሺህዎች ዶላር የተገዛ ስጦታ ይላክላቸው ነበር። እነዚህ ግለሰቦች ለጥቅማቸውና ለውለታቸው ሲሉ የጠለፉት የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ነው ኢትዮጵያንም የዐቢይን አስተዳደርም ደመኛቸው ያደረጉት ። እጀ እረጅሞች ስለሆኑ ተጽዕኗቸው አውሮፓ ሕብረት ፣ እንግሊዝ ፣ መንግስታቱ ድርጅት ፣ ሚዲያው እነ አመነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ግብጽ ፣ ሳኡዲ አረቢያና ሌሎቹ ዘንድ ይደርሳል ።
አሸባሪው ሕወሓት የጥቅምት 24ቱን ክህደት ጭፍጨፋና የጦር መሳሪያ ዘረፋ ሲፈጽም እነዚህ የልብ ወዳጆቹ ቀድመው ያውቁ ነበር ። የዐቢይ መንግስት ጥቃት ሊፈጽምብኝ ሲል ደርሸበት ቀድሜ ራሴን ለመከላከል ስል እርምጃ ወስጄበታለሁ የሚል የይስሙላ ደብዳቤ ጥቃቱ በተፈጸመበት ሌሊት በትኗል ። ሆኖም ይሄን ሴራ ከጥንስሱ ጀምሮ ግጥም አድርገው ያውቁታል ። ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የመከላከያ ሰራዊት ትጥቅ ስንቅ ሎጀስቲክስ ወታደር ያለው ትግራይ ክልል ስለሆነ እሱን በቀላሉ ተቆጣጥሬ ወደ አዲስ አበባ በመገስገስ የመንግስት ለውጥ አደርጋለሁ ብሎ አበክሮ አሳምኗቸው ነበር።
ይሁንና በወቅቱ ስልጣን ላይ የነበረው የትራምፕ አስተዳደር በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማይክ ፓምፒዎ አማካኝነት በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃትም ሆነ ሕወሓት ግጭቱን ቀጣናዊ ለማድረግ ወደ አስመራ የተኮሰውን ከባድ መሳሪያ አውግዞ ነበር። ይህ ከሪፐብሊካኖች ጋር ያለው ግንኙነት እምብዛም እንደነበር ያስረዳል። በአንጻሩ ሪፐብሊካኖች የእስራኤል ጥቅም በተዘዋዋሪ ለማስጠበቅ ግብጽን ይደግፉ ነበር ። የታላቁ የህዳሴ ግድብን ድርድር ከአፍሪካ ሕብረት አውጥተው ጫና በመፍጠር ለግብጽ አይን ያወጣ ድጋፍ በማድረግ ጉዳዩ ሁለት ጊዜ ለመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እንዲቀርብ ከማድረግ ባሻገር የኢትዮጵያን እጅ በመጠምዘዝ ለማስፈረም የሄዱበትን እርቀት ያስታውሷል።
በአወዛጋቢው ትራምፕ ምትክ ዴሞክራቱ ጆ ባይደን ወደ ስልጣን ሲመጣ ለአሸባሪው ሕወሓት ሰርግና ምላሽ ሆነ። የእነ ሱዛን ራይስና ደቀመዛሙርት ወደ ስልጣን መምጣት እልል በቅምጤ ሆነለት። ሶስት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ተደምስሶ ቆላ ተምቤን ወርዶ የነበረው ሕወሓት ባገኘው አለማቀፍ የዲፕሎማሲ የፖለቲካ የሚዲያና የእነ አምንስቲ ድጋፍ አፈር መላስ ጀመረ። በሶስት ሳምንት የተቋጨው የሕግ የበላይነትና የሕልውና ዘመቻ በተናበበ በተቀነባበረና በተቀናጀ ዘመቻ ጥላሸት ተቀባ። በሰላም ማስከበር ተልዕኮው የተመሠከረለት ወታደራዊ ዲሲፕሊኑና ስሙ በሀሰተኛ ክስ ጠፋ። አሜሪካ አውሮፓ ሚዲያዎቻቸው እንደ ሒውማን ራይትስ ያሉ ተቋሞቻቸውና ፖለቲካዊ አላማ ማስፈጸሚያ የመንግስታቱ ድርጅት ስም የማጉደፍ ዘመቻ ከፈቱበት የዐቢይን መንግስት ርሀብን በጦር መሳሪያነት ተጠቀመ ፤ ሰራዊቱ የዘር ማጥፋት ፈጸመ ፤ አስገድዶ ደፈረና ሌሎች ክሶችን ደረቱበት። ሌት ተቀን እረፍት ነሱት።
11 ጊዜ በመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አቆሙቱ ፤ በሀሰት ወንጅለው ለዓለም አሳጡት። የሚያሳዝነው መንግስት ላይ ይሄን ሁሉ ጫና ሲፈጥሩበት ስለሰሜን ዕዝ ጥቃት ስለማይካድራ ጭፍጨፋ ትንፍሽ አላሉም ነበር። መንግስት ከስምንት ወራት በኋላ ለሰብዓዊነት ሲል የተናጠል ተኩስ አቁም አድርጎ ሲወጣም አበጀህ አላሉትም። ይልቁን ከበባው ይነሳ ፤ የረድኤት ድርጅቶች ያለገደብ እንዲንቀሳቀሱ ይፈቀድ ፤ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ድርድር ይጀመር በማለት ውትወታውን በአዲስ መልክ ጀመሩት።
የሚያሳዝነው አሸባሪው ሕወሓት የተናጠል የተኩስ አቁም አልቀበልም ብሎ የአማራንና የአፋርን አካባቢዎች ሲወር መርጦ አልቃሾች እምጥ ይግቡ ስምጥ ድምጻቸው አልተሰማም። በአማራና በአፋር ክልሎች በወረራ የያዛቸውን ከተሞችና ገጠሮች ሀብት ንብረት መርፌ ሳይቀር ሲዘረፍና ሲያወድም ፤ በጋሊኮማ በአጋምሳ በጭና በንፋስ መውጫ በቆቦ በውጫሌ በመርሳ በአንጾኪያ ገምዛ ወዘተረፈ በሺህዎች የሚቆጠሩ ንጹሐን ሲጨፈጨፉ፤ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ህጻናትና ወንዶች ሳይቀሩ በቡድን አስገድዶ መድፈር ሲፈጸምባቸው ፤ ሀብት ንብረታቸው ሲዘረፍ፤ የደረሱ ሰብሎች ታጭደው ሲጫኑ፤ ከ10 ሽህ በላይ የሚጠጉ የትምህርትና የጤና ተቋማት ሆን ተብለው ሲወድሙ ሲዘረፉ ፤ የወሎ የወልድያ የመቅደላ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች ኮሌጆች ሲዘርፉ ሲወድሙ ፤ እንደ ላሊበላ አውሮፕላን ማረፊያ መንገድና ድልድይ ያሉ መሠረተ ልማቶች ሲፈራርሱና ሲዘረፉ፤ ወዘተረፈ ሰምተው እንዳልሰሙ አይተው እንዳላዩ ሆነው እንዲያልፉ ያደረጋቸው ከሕወሓት ጋር የገቡት የወዳጅነት ቃል ኪዳን ነው።
እንዲህ ጠምደው የያዙን ተላላኪ መንግስት ለማስቀመጥ ነው፤ ከቻይና ጋር ስለተወዳጀን ነው፤ ብሔራዊ ጥቅማቸውን እና በቀጣናው ያላቸውን ጅኦ ፖለቲካዊ ስፍራ ለማስከበር ነው እያልን ምክንያትና ሰበብ እንደረድርላቸዋለን እንጂ አንድም የባይደን አስተዳደር ሹመኛ በግልጽ ወጥቶ በሀገራችንም ሆነ በመንግስታችን ላይ እየተከተለው ያለው ፖሊሲ እኛ በደረደርንለት ምክንያት መሆኑን ገልጾና ተናግሮ አያውቅም ። የአሜሪካን ጥቅም ተነክቷል ብለው ሲያምኑ በአደባባይ ወጥተው ለመግለጽና ጥቅማቸውን ለማስከበር አያመነቱም ። ታዲያ ኢትዮጵያ ላይ ሲደርሱ አፋቸውን ማን ለጎማቸው !? ማንም። የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው በግለሰቦች ፍላጎትና ጥቅም በመጠለፉ ነው አፋቸው የተለጎመው ። በእነ ሱዛን ራይስ አንቶኒ ብሊንከን ሊንዳ ቶማስ ጌይል ስሚዝና ሌሎች ጥቅምና ፍላጎት ስለተጠለፈ ነው በአደባባይ ወጥተው ምክንያታቸውን የማይገልጹት።
መቼም በአደባባይ ወጥተው የእነ ሱዛንን ጥቅምና ፍላጎት የሆነውን ሕወሓት ለምን ከአገዛዝ አወረዳችሁ ብለው አይከሱንም። አይጠይቁንም። ኢትዮጵያ በቀጣናው ትልቅ ሀገር ስለሆነች እንዳትፈርስ ፤ የግዛት አንድነቷ እንዳይናጋ ነው እያሉ ይሸነግሉናል እንጂ እውነቱን አይነግሩንም። እውነቱን ስላልነገሩን በእነሱ ቦታ ሆነ ምክንያት መደረቱን ትተን ፤ የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ እየተከተለ ያለው የተሳሳተ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የአሜሪካንን ጥቅም ለማስከበር ሳይሆን የግለሰቦችን ጥቅምና ፍላጎት ለማስጠበቅ መሆኑን ለራሳቸው ለዴሞክራቶች ፤ ለአሜሪካ ሕዝብና ለሪፐብሊካኖች ሳንታክትና ሳንሰለች ማጋለጥ ይጠበቅብናል።
#በቃ #እምቢ #NoMore
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com