‹‹ፀቤን ከሚያውቅ አድርግልኝ›› ከአባቶች ፀሎት አንዱ ነው። ለወዳጅነት ብቻ ሳይሆን ለጠላትም ፀሎት ይደረጋል ማለት ነው። ‹‹ለጠላቴ ልቦና ስጥልኝ›› የሚባልም አለ። ይሄኛው በዕድሜ የገፉ አዛውንቶችና መነኩሳት የሚሉት ነው። መጣላት ለማይችሉት ማለት ነው። መጣላት የሚችሉት ግን ‹‹ፀቤን ከሚያውቅ አድርግልኝ›› ነው የሚሉት።
ይህን የሚሉት እንግዲህ ጀግንነታቸውን ለማሳየት ነው። ተጋጣሚያቸው ጅል ከሆነ ግን የጀግንነታቸውን ትርጉም ያደበዝዘዋል። ለዚህም ይመስላል ‹‹ጅል በምን ያሸንፋል ቢሉ ‹እምቢ› ብሎ የሚል ሌላ አባባልም አለ። ጅል የሚያሸንፈው እምቢ ብሎ ነው ማለት፤ እንደ ጀግኖቹ ተዋግቶ ሳይሆን ሽንፈቱን ባለማመን ሌሎች እንዲጎዱ በማድረግና ከግጥሚያ ደንብ ውጭ የሆኑ ነገሮችን በማድረግ ነው።
የአባባሉ ባለቤት የገጠሩ ማህበረሰብ ስለሆነ በዚያው ዓውድ ላብራራው። አንድ ገበሬ ከሌላ ገበሬ ሲጣላ የሚደባደቡት በተለመደው በዱላ ወይም በትግል ነው። በጣም ሲከፋም የተጣላውን ሰውየ ለይቶ በጥይት በመምታት ነው። ይሄን ማድረግ የማይችል ፈሪ ግን የተጣላውን ሰው ሳይሆን ሚስቱን ወይም ትንንሽ ልጆች ይደበድባል። ወይም ምንም የማያውቁትን እንስሳት ይገላል፤ ወይም የተሰበሰበ ሰብል ተደብቆ ያቃጥላል። እንዲህ አይነት ሰው በማህበረሰቡ ዘንድ እንደ ፈሪ ነው የሚታየው።
ለሽምግልና የተቀመጡ ሽማግሌዎችንም ያስቸግራል። አሸናፊና ተሸናፊን ለማስታረቅ ሽማግሌዎች ይቸገራሉ። መሸነፉን አይቀበልም። ለዚህም ነው ‹‹ጅል በምን ያሸንፋል ቢሉ ‹እምቢ ብሎ›› የተባለው።
‹‹ፀቤን ከሚያውቅ አድርግልኝ›› የሚሉት ለዚህ ነው። ጀግና ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን መሸነፍም ያውቅበታል። አሸናፊውም ተሸናፊውም ጀግና ሲሆኑ አሸናፊው ኩራት ይሰማዋል፤ ምክንያቱም ጀግና ነው ያሸነፈ። ተሸናፊውም የአካባቢውን የፀብ ደንብ በማክበሩ እንደ ጀግና ይቆጠራል። ‹‹እሱ እኮ ቢሸነፍም እንደማንም ፈሪ ሴት አልደበደበም፣ ልጆችን አልመታም፣ እህል አላቃጠለም›› እየተባለ ይነገርለታል። በማህበረሰባችን ውስጥ አሸናፊ ብቻ ሳይሆን ተሸናፊም እንዲህ ነው።
እንግዲህ ከላይ ያየናቸውን ነገሮች ይዘን አሸባሪውን ሕወሓት ልብ እንበል። ከታሪካችንም፣ ከማህበረሰባችን ወግና ባህል አንፃርም ቡድኑ እየተከተለ ያለው የፈሪ ባህሪ ነው። በታሪካችን ኢትዮጵያ ሳይደርሱባት ደርሳ አታውቅም፤ የደረሱባትን ግን እንደ አመጣጣቸው መልሳለች። የጀግና ምልክት ይሄው ነው። ሳይደርሱበት አይደርስም፤ የደረሱበትን ግን አይለቅም። አሸባሪው ሕወሓት ይህን ታሪካዊ እና ባህላዊ የአገሪቱን መለያ ጥሶና አፈራርሶ ፀብ ጀመረ። ለዚያውም የአገር ዳር ድንበር አስከባሪውን የመከላከያ ሠራዊት በመተናኮል። ፀብ መጀመር የፈሪ ምልክት ነው።
ቆራጥ ጎበዝ እና ነብር አንድ ናቸው
ሰው ደርሰው አይነኩም ካልደረሱባቸው
የሚል የሕዝብ ቃል ግጥም አለ። የጀግናን ባህሪ ለመግለጽ የሚያንጎራጉሩት ነው። ነብር የሚባለው እንስሳ ከሚመገባቸው የዱር እንስሳት በስተቀር ሰውን አይተናኮልም። እረኞች ዋሽንት እየተጫወቱ አብረውት ይውላሉ። የነብር ትልቁ ችግር ከነኩት አይለቅም። አንዳንዶች በፍርሃት፣ አንዳንዶች ደግሞ ለአደን ይተናኮሉታል። ያኔ ማንም አያስጥለውም። ‹‹የነብርን ጅራት አይዙም፤ ከያዙ አይለቁም›› የተባለው ለዚህ ነው። ካልነካኩት አይነካም።
ይህ የማህበረሰብ የጀግንነት ባህል የሕወሓትና የፌዴራሉ መንግሥት ጦርነት ምንነት ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። አሸባሪው ሕወሓት የማይነካ ነገር ነካ፤ ከዚያ ዋጋውን አገኘ።
ጀግና ስላልሆነ የፈፀማቸው ድርጊቶች ሁሉ የፈሪ ድርጊቶች ናቸው። ቡድኑ ና ሸኔ ከታጠቀ ኃይል ይልቅ በምርኩዝ የሚሄዱ አዛውንት እና በዳዴ የሚሄዱ ሕጻናት ነው የሚገድሉት። ይሄ በጦርነት ሕግ በፍፁም የተከለከለ ከመሆኑም ባሻገር ስለዓለም አቀፉ የጦርነት ሕግ ምንም በማያውቀው ማህበረሰባችን እንኳን የፈሪ ምልክት ነው። ፊት ለፊት መግጠም የማይችል ፈሪ የሚያደርገው ነው።
አሸባሪው ሕወሓት የሰራው ሥራ ከዚያ አካባቢ ወደፊት እንኳን ጀግና እንዳይወጣ የሚያደርግ ነው። ጀግንነት አካላዊ ውጊያ ሳይሆን ስነ ልቦና ጭምር ነው። የ90 ዓመት አዛውንት፣ የ4 ዓመት ሕጻን ደፍሯል፤ ጀግና ይሄን አያደርግም። ይሄ ክስተት ደግሞ በታሪክ ተሰንዶ ይቀመጣል። ታዲያ በምን ሞራል ነው ቀጣዩን ትውልድ ጀግና ሊያፈራበት የሚችል? ለቀጣዩ ትውልድ ‹‹አባቶችህ ይህን አድርገዋል›› የሚል አሳፋሪ ታሪክ ነው የሚቀመጥለት። በዚህም ወደፊት እንኳን ጀግና እንዳይወጣ ነው ያደረገ።
ጠላት የሚጠቀምበትን ምሽግ መስበር የጀግና መለያ ነው። እሱ እንኳን ቢቀር ‹‹ጠላት›› የሚሉትን ወገን ቢሮ ወይም ሌላ መገልገያ ማውደም በጦርነት ያጋጥማል እንበል። ግን የሲቪል ተቋማትን ማውደም ምንኛ ነው? ችግሩ ከመንግሥት ነበር ወይስ ከሕዝቡ?
አሸባሪው ሕወሓት ያደረገው ሁሉ የፈሪ እና የዘር ጥላቻ ድርጊት ነበር። ጤና ጣቢያ የአማራ እናቶች የሚወልዱበት እንጂ ብልጽግና ፓርቲ ስብሰባ የሚያደርግበት ወይም የጦር መሳሪያ የሚያከማችበት አይደለም። ጤና ጣቢያ እና ሆስፒታልን ማውደም የዛሬውን ብቻ ሳይሆን የነገውንም ትውልድ መግደል ማለት ነው። ትውልድ እንዳይተካ ማድረግ ነው። ይህ አሸባሪ ቡድን ችግሩ ከመንግሥት ጋር ሳይሆን ከሕዝቡ ጋር ነበር ማለት ነው።
ትምህርት ቤት የነገ ሀገር ተረካቢ ሕጻናት የሚማሩበት እንጂ የዛሬ ባለሥልጣናት የሚኖሩበት አይደለም። ትምህርት ቤት የፓርቲ ጽሕፈት ቤት አይደለም። ይሄ አሸባሪ ቡድን ግን ዓላማው የዛሬው ሳይሆን ነገ ትውልድ እንዳይኖር ነው። ይሄ ግልጽ የዘር ጥላቻ እና የፈሪ ድርጊት ነው።
ከምንም በላይ ደግሞ ዘግናኝ እና አሰቃቂ ድርጊቶችን አድርሷል። ጦርነት ገጠምኩ ያለው ከመንግሥት ጋር ነበር። ጭፍጨፋ የፈፀመው ግን ስለጦርነት ምንም የማያውቁ ሴቶችና ሕጻናት ላይ ነው። ክላሽ የያዙትን ተደብቆ መጫወቻ የያዙ ሕጻናት ላይ ነው። ይሄ የፈሪ ምልክት ነው። በመነኩሳት ላይ ያደረሰው ሰይጣናዊ ድርጊት ደግሞ የከፋ ሰይጣናዊነት ነው።
ተንኮለኛ ገደል
በሬ ያሳልፋል
ዝንጀሮ ይጠልፋል
ጅል ያመጣው ነገር
ለሁሉ ይተርፋል
ይህ የማህበረሰባችን እንጉርጉሮ መልዕክቱ ለፈሪ ነው። መግቢያ ላይ እንዳልኩት ፈሪ ጦሱ ነው ለሌላ የሚተርፍ። ምክንየቱም መሸነፉን እንኳን አያውቅም። አሸባሪው ሕወሓት በዚህ ባህሪው እልፍ የትግራይ ልጆችን የእሳት እራት አድርጓል። በባህላችንም፣ በመገናኛ ብዙኃን መተዳደሪያ ደንብም አስከሬን ማሳየት ነውር ስለሆነ እንጂ ለማየት የሚዘገንን ጭፍጨፋ አስደርሶባቸዋል።
ይሄ እንግዲህ ቡድኑ ባመጣው መዘዝ ነው። መዘዙ ለሁሉም የትግራይ እናቶችና ሕጻናት ደርሷል። በገባባቸው የአማራና አፋር ክልሎች ውስጥም ያየነውን የሰማነውን አይነት ግፍ አድርሷል። መዘዙ ለሁሉም ተርፏል።
‹‹ፀቤን ከሚያውቅ አድርግልኝ›› ማለት ይሄ ነው እንግዲህ! ተሸንፎ አሸንፌያለሁ ማለት። ስለዚህ ተሸናፊው እንኳን ሽንፈቱን ባያምን ደጋፊዎቹ እመኑ!።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 21 ቀን 2014 ዓ.ም