በብዙ ዘርፎች ውስጥ ማጭበርበርና መዋሸት አሁን ላይ እየተለመደ ነው። በጉዳዩ ብዙ የተባለበት ነው። ዳሩ ግን አንዳንድ ማጭበርበሮች ደግሞ ተጭበርባሪውን ብቻ ሳይሆን ሰሚውንም ያሳዝናሉ።
ከአራት ዓመት በፊት (2010 ዓ.ም መሆኑን አስታውሳለሁ) ካስተዋልኩት አንድ ገጠመኝ ልጀምር። አንድ እህቱ የተጭበረበረችበት ጓደኛዬ ‹‹ጋዜጠኛ ነህና እስኪ ይሄን ነገር እይልኝ›› ብሎ አራት ኪሎ የሚገኝ አንድ ሕንጻ ላይ ይዞኝ ወጣ። የሆነች አነስተኛ ክፍል ውስጥ አንዲት ሴትና አንድ ወንድ ተቀምጠው ይመዘግባሉ፤ ከውጭ ብዙ ተሰላፊዎች አሉ። ሥራ ፈላጊዎች ናቸው።
መመዝገብ እንደምንፈልግና ህጋዊነታቸውን ጠየቅናቸው። ጥያቄያችን አላማራቸውም። በተለይም ወንዱ ልጅ አይን አይናችንን እያየ መደናገጥ ይታይበታል። እኔ ቀጫጫ ስለሆንኩ ባላስነቃም አብሮኝ ያለው ጓደኛዬ ግን ሥራ ፈላጊ እንዳንመስል አድርጎናል። ብቻ ግን ጥርጣሪያቸው ጨመረ፤ ሰዓቱ ገና አራት ሰዓት አካባቢ ቢሆንም ሊወጡ እንደሆነ ነገረን። አጭበርባሪዎች መሆናቸውንም አረጋገጥን።
በወቅቱ በአገሪቱ የነበረው ጉዳይ የለውጥ ዋዜማ ውጥረት ስለነበር በዚህ ወቅት ስለአንድ ተራ ነገር ማውራት ሰሚ አያስገኝም ብለን ትዝብታችንን ብቻ ነግረናቸው ወጣን።
ከዓመታት በኋላ ያስታወስኩት ሰሞኑን ተመሳሳይ ማስታወቂያ አይቼ ነው። አራት ኪሎ የሥራ ማስታወቂያ ሰሌዳው ላይ አራት ይሁን አምስት ቦታ ተለጥፏል። አንድ አይነት ነው። የሚጠቅሰው ቦታም ሆነ የሚፈልገው የሰው ሃይል ብዛት ተመሳሳይ ነው። ይሄንኑ ማስታወቂያ በየመብራት ምሰሶዎች ላይ አየዋለሁ። የመመዝገቢያ ቦታው እዚያው አራት ኪሎ (ለጊዜው ልዩ ቦታውን ልተውለትና) ነው።
ከዓመታት በፊት ያጋጠመኝን ስላስታወስኩ የሆነች ሥራ የምትፈልግ የማውቃት ልጅ እንድትሄድ አደረኳት። ስትሄድ መመዝገቢያ 400 ብር መክፈል እንዳለባት ጠየቋት። ብር ከጠየቁሽ እንዳትከፍይ ስላልኳት አልከፈለችም። ያኔ ያስተዋልኩትም እንደዚሁ 400 ብር እያስከፈሉ ነበር። የዘንድሮውንም ልጅቷ ስትነግረኝ፤ በጣም ብዙ ሥራ ፈላጊዎች ተሰልፈው የቻሉ እየከፈሉ ተመዘገቡ፤ ያልቻሉም እየተውት ወጡ።
ምንም እንኳን ትልልቅ አገራዊ ጉዳዮች ቢኖሩብንም፣ ምንም እንኳን በቢሊዮን የሚቆጠር ትልልቅ ዘረፋዎች የሚፈጸሙ ቢሆንም፣ እንዲህ አይነት ጥቃቅን ዘረፋዎችና ማጭበርበሮችም ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል። ምክንያቱም የሚያደርሱት ጥፋት ከትልልቅ ዘረፋዎች አያንስም። እንዲያውም የእነዚህ ይከፋል። ምንም ሥራ ከሌለው ተመራቂ ላይ ነው እየዘረፉ ያሉት።
ህጋዊ አሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች አሰራራቸው ይታወቃል። ተቀጣሪው ከተቀጠረ በኋላ ነው የሚከፍለው። የሚቀጥረውን ድርጅት ስለሚያውቁት ሰራተኛው ያጭበረብራል የሚል ሥጋት የለባቸውም፤ ሲጀመር የሚቀበሉት ከሰራተኛው ሳይሆን ከቀጣሪው ድርጅት ነው። ሰራተኛው አምኖ የተዋዋለበት ስለሆነ ይታወቃል። እንደተቀጠርክ ከመጀመሪያው ደሞዝ ላይ ይህን ያህል ተብሎ በውል የታወቀ ነው።
አንዳንድ ቅድሚያ የሚቀበሉ ካሉ ደግሞ ግልጽ የሆነ ስም እና ሕጋዊ ማህተም ያላቸው ናቸው። እነዚህኞቹ ግን (የሚያጭበረብሩት) ማህተም የላቸውም። ተቋማዊ አሰራር (የኤጀንሲው ስም እንኳን) የላቸውም። የትኛውም ህጋዊ አሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ስም አላቸው። የሚያጭበረብሩት ግን ስም እንኳን የላቸውም። የቀጣሪውን ድርጅት ስምም አይጠቅሱም። ለሽያጭ ሰራተኛ ወይም ሌላ የሥራ አይነት ይጠቅሱና የመመዝገቢያ ቦታውን ይጠቁማሉ፤ ስልክ ያስቀምጣሉ።
ከእነዚህ ሥራ አጥ ወጣቶች ላይ ማጭበርበር ግን ምን አይነት ህሊና ነው? አራት ኪሎ ላይ ቢሮ መከራየት የሚያስችል አቅም እያለ እንዴት አንድ ምግብ ለሁለትና ሦስት ከሚበሉ ሥራ ፈላጊዎች ላይ ይዘረፋል? በነገራችን ላይ ቦታው አራት ኪሎ እንዲሆን የተፈለገበት ምክንያት ሥራ ፈላጊዎች እዚያው አቅራቢያ እንዲያገኙት ነው፤ ራቅ ካለ ሀሳባቸውንም ሊቀይሩ ይችላሉ።
እንዲህ አይነት ትንንሽ ማጭበርበሮች በአገር ደረጃ ትኩረት ስለማይደረግባቸው ማንም ልብ አይላቸውም። በተለይም አሁን ባለንበት ወቅት ደግሞ ማንም የእነርሱን ጉዳይ አጀንዳ የሚያደርግ አለመኖሩ ጠቅሟቸዋል።
እነዚህ ሰዎች ተይዘው ውርደት ላይ ከመውደቃቸው በፊት ከድርጊታቸው ቢቆጠቡ የተሻለ ነው። አስታውሳለሁ 2011 ዓ.ም ይሁን 2012 ዓ.ም እንዲህ አይነት ህገ ወጥ ኤጀንሲዎች ተጥረግርገው ተዘግተው ነበር። ዛሬም ቢሆን አመልካች ካለ ይዘጋሉ።
ችግሩ ግን እንዲህ አይነት ስም የለሽ ኤጀንሲዎችን መንግሥት ትኩረት አድርጎ ካልተከታተላቸው በግለሰብ ብቻ ምንም አይሆኑም። ፖሊስም ትዕዛዝ ካልተሰጠው ማንም ግለሰብ ይዤህ ልሄድ ቢለው የሚሄድ አይመስለኝም።
በብዙ አገልግሎቶች ውስጥ ሥራን ለማቀላጠፍ ደላላ መኖሩ ጥሩ ነው። አሰራሩን ለማያውቁ ሥራም ሆነ ቤት ፈላጊዎች ምቹ መንገድ ነው። ዳሩ ግን የበለጠ ለማወናበድና ለማጭበርበር ከሆነ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ለምሳሌ የቤት ደላሎችም ብዙ ሰው ሲያማርራቸው ይሰማል። የተያዘን ቤት ‹‹ይሄ እኮ ይሄን ያህል ይከራይ ነበር›› እያለ በማሽቃበጥ ተከራይ ላይ ዋጋ ያ ስጨምራሉ።
በነገራችን ላይ በቤት መከራየት ላይ አንድ የታዘብኩት ትልቅ ነገር ደግሞ ዕቃ አውራጅ ነን የሚሉ ወጣቶች ናቸው። በአካባቢው በቡድን የተደራጁ ናቸው የተባሉት ወጣቶች አዲስ ከሚገባ ሰው ላይ ዝርፊያ ነው የሚፈጽሙት ማለት ይቀላል! በፌስታል የሚያዝ ዕቃ እንኳን ቢሆን የግድ እኛ ካላስገባነው ነው የሚሉት። ይሄ ነገር አውቶብስ ተራም ያየሁት ነው።
ሰውየው አጋዥ ካስፈለገው አውራጅና ተሸካሚ መጥራት ካስፈለገው ይጠራል፤ ካላስፈለገው ግን በአካባቢው የተደራጀን ነንና የግድ ትከፍላለህ ማለት ዝርፊያ ነው።
ከሁሉም በላይ የከፋው ግን ከሥራ ፈላጊ ወጣቶች ላይ የሚደረገው ዘረፋ ነው። እነዚህ ወጣቶች ያንን 400 ብር እንዴት እንደሚያገኙት አውቀውት ይሆን ግን? እነዚህ ወጣቶች ከክፍለ ሀገር የመጡና ቤት ተከራይተው የሚኖሩ ናቸው። ቤተሰቦቻቸው የተትረፈረፈ አቅም ያላቸው ላይሆኑ ይችላሉ። አዲስ አበባ ውስጥ ከዘመድ ጋር ቢሆን ራሱ ብር አይኖራቸውም፤ ምክንያቱም ቤት እንዳልተከራዩ ከታወቀ ምናልባትም የታክሲ ብቻ ቢሰጣቸው ነው።
ብሩን እንግዲህ ከየትም ያግኙት! ግን ለምን ያለአግባብ ይዘረፋሉ? እንኳን እነዚህ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ማንም ሀብታም ቢሆን 400 ብር ሜዳ ላይ መጣል አይፈልግም። ችግሩ እኮ 400 ብር መክፈላቸው ብቻ ሳይሆን ሥራ የማያገኙበት መሆኑ ነው። የጨነቀው ብዙ ነገር ያደርጋልና ከየትም አምጥተው ብሩን ሊከፍሉ ይችላሉ፤ ችግሩ ግን የተባለውን ሥራ አያስገኙላቸውም።
ምንም እንኳን እንደ ሥራ ፈላጊ ሆነው ሲያስቡት ከባድ ቢሆንም፤ በተቻለ መጠን ግን ከእንዲህ አይነት አጭበርባሪዎች መቆጠብ ያስፈልጋል። ቅድመ ክፍያ ቢከፈል እንኳን ማህተም ያለው ወይም ስም ያለው መሆን አለበት። ምኑም የማይታወቅ አካል በቅድሚያ ክፈሉ ካለ እያጭበረበረ መሆኑን መጠርጠር አለበት። ለእንዲህ አይነት ግፍ የማይፈሩ አጭበርባሪዎች ግን ሁላችንም ልንከታተላቸውና ልንጠይቅ ይገባል!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 20/2021