ነገረ ጉርሻ፤
ጉርሻው ላያጠግበኝ አፌን አስነክተው፣
እንደጠገበ ሰው አሙኝ ተመልሰው።
እከሌ ተብሎ ስሙ የማይጠቀስለት የሀገሬ “አፈ ሊቅ” በተቀኘው ዘመን ዘለቅ ቅኔ የተንደረደርኩት ሃሳቤን በአግባቡ ይገልጽ ስለመሰለኝ ነው። እንጂማ ስለ የማዕድ ላይ ጉርሻ ጉዳይ ምን አዲስ ነገር ላስተዋወቅ እችላለሁ? የዕለት ተዕለት የቤተሰብና የወዳጅነት መገለጫ ድርጊት ለሆነውና ከልጅ እስከ አዋቂ ወጉ ላደረገው ይህን መሰሉን ነባር ባህል በተዋቡ ቃላት እያራቀቅሁ ላመሳጥር ብልስ ማን “አባ ከና” ብሎ ያነብልኛል?
ለማንኛውም ከነካካሁት አይቀር ጥቂት ልበል። ጉርሻ፡- በሌላ መታወቂያው ዳረጎት ይባላል። ጉርሻ፡- ራት ወይንም ምሳ ሳይሆን ማቆያ ነው። ማቆያነቱ፤ የራስ ምሳ ወይንም እራት እስኪቀርብ ድረስ እንደ ማስታገሻ የሚሰጥ ዳረጎት ሲሆን በጋራ ማዕድ ላይ የሚከወን ከሆነም ፍቅርና ወዳጅነትን እንዲገልጽ ታስቦ የሚሰነዘር “የበሞቴ በረከት” ነው። ይህ “አፈር ልሁን” እየተባለ በመሃላ ታጅቦ ለአፍ የሚደርሰው የጉርሻ ስንዝር “ኩራት ራት ነው” ከሚለው ፍልስፍና ጋር አይጣጣምም። “ጠግቤያለሁ!” እየተባለ በመግደርደርና በተቃውሞ አታካራ የሚገጠምበት የግብግብ “ወግነቱ” አልቀር ብሎ እንጂ እጅ መጥኖ የሰነዘረውን ጉርሻ ለአፍ ሳያቀብል አፍሮ መመለስ ወግ አይደለም።
ጉርሻ በገንዘብ መልክ የሚሆን ከሆነም ለመልካም አገልግሎት በፈቃደኝነት የሚሰጥ ስጦታ ተብሎም ሊጠቀስ ይችላል። ይኼኛው ጉርሻ ብዙውን ጊዜ እንደ ማዕዱ አቻው “እዩልኝ! ስሙልኝ” እየተባለ “ነጋሪት አይጎሰምለትም፤ አታሞም አይደለቅለትም።” “እንዲያው በሞቴ” ተማጽኖም አይመለከተውም። አጉራሹ በተቻለ መጠን “ቀኝ እጁ የሚሰጠውን ግራ እጁ እንዳያውቅ” ብዙ ጥንቃቄ ያደርጋል።” አባባሉን የተዋስኩት ከቅዱስ መጽሐፍ ወርቃማ ጥቅሶች መካከል መሆኑን ልብ ይባልልኝ።
አንዳንዶች ጉርሻን የጉቦ ሌላኛው ግልባጭ አድርገው ሲጠቀሙበት ይስተዋላል። “ቃል እንደተርጓሚው፤ ቀስትም እንደ ወርዋሪው” ስለሆነ አተረጓጎሙ “ልክ ነው! ልክ አይደለም!” እየተባባልን ለእንካ ሰላንትያ እጅጌያችንን መሰብሰቡና ለሙግት መወራረዱ የሚበጅ አይሆንም። ጉርሻን እንዳሻን ብንተረጉመው እስከ ተግባባንበት ድረስ መብታችን ነው።
ልንነጋገርበት የሚገባው ዋናው ጉዳይ፤ “በጉርሻ መካከል ስንጥር ጠቅጥቆ የሚያጎርስን ‹ወዳጅ መሰል› ጠላት ምን ስም እንስጠው?” የሚለው ሊሆን ይገባል። እንዲህ ዓይነቱ ክስተት የሚያስታውሰን ኢየሱስ ክርስቶስና ይሁዳ በመጨረሻው እራት ላይ በአንድ ወጭት ውስጥ እጃቸውን ነክረው ከበሉ በኋላ ከሃዲው ይሁዳ ጌታውንና መምህሩን እንዴት አሳልፎ እንደሰጠው ነው። ነገረ ጉርሻ ይህንን ያህል ርቀት በንባብ ካጓጓዘን ዘንዳ፤ ወደ ዋናው ሀገራዊ ጉዳይ አቅንተን ጥቂት እንቆዝም።
በእርዳታ ጉርሻ ውስጥ የተጠቀለሉ ስንጥሮች፤
እንደ አለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን ሀገሬ በቀደምት ታሪኳ ውስጥ የባዕዳንን የእርዳታ ጉርሻ ተቀብላ ስለመሆኗ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። የተደራጀ ጥናት የሚኖር ከሆነም “መረጃው ከእኛ ዘንድ አለ” ባዮች ቢያሳውቁን አይከፋም። የድርቅ፣ የመፈናቀልና የርሃብ ችግሮች ባጋጠሙን ወቅቶች ሁሉ በፍቅርና በርህራሄ እጃቸውን ዘርግተው ያጎረሱንን በርካታ ድንበር ዘለል እጆች ባናመሰግን ከውለታ በልነት ልናመልጥ አንችልም። ስለ በጎነታቸው ክብር ይግባቸው። በአንጻሩም፤ “የስጦታ ፈረስ ጥርሱ አይታይም” እንዲሉ፤ ይሉኝታ ጠፍሮን በጉርሻቸው መካከል ስንጥሮች መሸጎጣቸውን በግልጽነት እያስተዋልን እንኳን “ሆድ ከሀገር ይሰፋል” የሚል ትዕግሥት ሸብቦን የተጎዳንባቸውን ሀገራዊ ጉዳዮች ማስተናገዳችንንም አንክድም።
“በየዐሥርት ዓመቱ ለሚከሰተው የኢትዮጵያ ድርቅ” በሚል የሟርት ቀጠሮ አንዳንድ እርዳታ ሰጭ ተቋማትና መንግሥታት ጉርሻዎቻቸውን እየጠቀለሉ ማዘጋጀት የሚጀምሩት በሀገራችን ጉሮሮ ላይ የሚሰኩትን ስንጥሮች ገና ለገና በረቀቀ ዘዴ እየሰገሰጉ መሆኑ አይጠፋንም። አንዳንድ የማኅበራዊ ጉዳዮች ኃያሲያን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የተራድኦ ድርጅቶችን ብዛት ያህል በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ስለመገኘታቸው ጥርጣሬ አላቸው። ግምታቸው በጥናት ተረጋግጦ እውነት ከሆነ ቀልባችንንና ጆሯችንን ሰጥተን ብናደምጣቸውና እንደ ሀገር ተረጋግተን ጉዳዩን ብንመረምር ሳይበጀን አይቀርም።
ይህ ጸሐፊ ለዓመታት አገልግሎት የተሰናበተው አንድ ግዙፍ ተቋም ከዘፍጥረቱ ጀምሮ እስከ ዛሬይቱ ዕለት ድረስ በልማትና እርዳታ ፕሮግራሞች ስም “ከውጭ የተራድኦ ድርጅቶች ሰብስቦ” ያፈሰሰው ገንዘብና ቁሳቁስ በምን ያህል ቢሊዮን ብሮች እንደሚገመት ለማስላት በእጅጉ ያዳግታል። እርዳታን እንደ ልዩ ሲሳይ (fairy godmother) መቁጠር የብዙ ተቋማት ተሞክሮ ስለሆነ እከሌና እከሌ ብሎ ብቻ መወሰን ሊያዳግት እንደሚችል መገመት አይከብድም።
ጨከን ብለን ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ውስጥ “እንደ ጉድ ጎርፏል! ፈሷል!” የሚባለውን የእርዳታ መጠን ግምቱና ውጤቱ ታውቆ ብንወያይበት መልካም እንደሆነ እናስባለን። “ማንም ሀገር ያለ እርዳታ ራሱን ችሎ ሊቆም አይችልም!” የሚለውን የወበከንቱ የድህነት ጌቶችን “Lords of Poverty” ሃሳብም ደጋግመን ብንፈትሽ ሳይበጀን አይቀርም። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ይህንን የልማትና እርዳታ ጉዳይ በተመለከተ ጊዜው ሰንበት ቢልም በአንደኛው ዳጎስ ያለ መጽሐፉ ውስጥ ዳሰሳ ለማድረግ ሞክሯል።
በሀገሬ ምድር “ተንዠቅዥቆ ፈሷል” እስከመባል የደረሰው የባዕዳን የእርዳታ ጉርሻ ያስገኘው ዘላቂ ትሩፋት እስከ ምን ደረጃ እንደሆነ ደፍረንና ጫን ብለን “የትዝብት እባጫችንን” እያፈረጥን መወያየቱ ጊዜው ራሱ ግዴታ የሚያስገባን ይመስለናል። በጉርሻቸው መሃል ተሰንቅረው “የጎረስናቸውን” ሁለንተናዊ (Holistic) የእርዳታ ፋይዳዎችም ረጋ ብለን እያንጓለልን ብንፈትሻቸው አንዳች ውጤት ላይ ሳንደርስ አንቀርም።
ጸሐፊው ቀደም ሲል በጠቀሰው መጽሐፉ ውስጥ “ጠርጥር ገንፎ ውስጥ ይገኛል ስንጥር” ከሚል ሀሜት በፀዳ መልኩ ማስረጃዎችን በማጣቀስ በርካታ ጉዳዮችን ለመዳሰስ ሞክሯል። ዝርዝሩ እንኳን ቢቀር የተጠቀመበት ምሳሌ ዛሬም ቢሆን ትምህርት ሰጭነቱ የጎላ ስለሆነ ቢታወስ አይከፋም።
ምሳሌው በሀገራችን የሚገኙ ሁለት የአዞ መኖሪያዎችን የሚመለከት ነው። የመጀመሪያው “አዞ ገበያ” በመባል የሚታወቀው የጫሞ ሐይቅ ክፍል ነው። ሁለተኛው በአርባ ምንጭ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው ሰው ሰራሹ የአዞ ርባታ ጣቢያ ነው። በጫሞ ሐይቅ ውስጥ የሚኖሩት አዞዎች ውለው የሚያድሩት በነፃነት ነው። ምግባቸውም ሆነ ዕድሜያቸው በሰው ልጆች ፈቃድ አልተገደበም። ቢርባቸው ወደፈለጉበት ቦታ ተንቀሳቅሰው አድነው መብላት ይችላሉ። ሲዋኙም ያለ ገደብ እንዳሻቸው እየተንፈላሰሱ ነው።
በሰው ሰራሹ የአዞ ርባታ ጣቢያ ውስጥ የሚኖሩት ግን እንደዚያ አይደሉም። አድነው አይበሉም። እንቅስቃሴያቸውም ሙሉ ለሙሉ በአርቢዎቻቸው በጎ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ምግባቸውም ሆነ ነፃነታቸው የተገደበ ነው። ጠቅላላ ኑሯቸውንም ሆነ ሕይወታቸውን የሚወስኑት ጌቶቻቸው ናቸው። የተዘጋጀላቸው ትንሽ ኩሬም ከመጠናቸው ጋር አይስተካከልም። ውሃው በየጊዜው ቢቀየርላቸውም ቶሎ ቶሎ ስለሚቆሽሽ ንጽህናው እንደነገሩ ነው።
በሰው ሰራሽ ኩሬ ውስጥ የተከማቹት እነዚያ ምስኪን አዞዎች ገራምና የተመቻቸው ቢመስሉም እውነታው ግን እንደዚያ አይደለም። የሚቃመሱት ምግብ በሰው እጅ ሲወረወርላቸው የሚሻሙት እየተበጣበጡና ሁከት እየፈጠሩ ነው። ጠንካራውና ብርቱው ባለጉልበታም ደካማዎቹን አዞዎች እያተረማመሰ በብልጠቱና በአቅሙ ተማምኖ ከሚወረወረው ምግብ ቀዳሚ ተጠቃሚ ለመሆን የተቻለውን ትግል ሁሉ ያደርጋል። ሌላው ደግሞ የተወረወረውን ምግብ አገኘሁ ብሎ አንዱ አዞ የሌላኛውን ጓደኛውን አዞ ጭራ ወይንም እግር፣ አለያም እጅ በጥርሱ ነክሶ ይቆረጥማል። በዚህም ምክንያት ብዙዎቹ የሰው ሰራሹ አዞ እርባታ ጣቢያ ምስኪኖች አካለ ጎደሎ እንደሆኑ ማስተዋል ይቻላል።
የሚያሳዝነው ሌለው ትርዒት ምግብ አቅራቢዎቹ ራሳቸው የአዞዎቹን መናከስና ጠብ በማየት መደሰታቸው ነው። አንዳንዴም በግላጭ ሆን ብለው እየተጣሉ እንዲታገሉ ለማድረግ ምግባቸውን የሚወረውሩላቸው አመቻችተው ነው። በመጨረሻም የሁሉንም አዞዎች ለስላሳ ቆዳ ገፎ ለመውሰድ ሲባል አርቢዎቻቸው አርደዋቸው ታሪካቸው ይደመደማል። ተረፈ አካላቸውም መልሶ ለጓደኞቻቸው መብል በመሆን ያገለግላል።
ይህ ምሳሌ ከሀገራችን የባዕዳን እርዳታ ጋር በሚገባ የሚገጥም ይመስለናል። ምድራችን ተዝቆና ታፍሶ የማያልቅ ሀብት በማኅጸኗ ታቅፋ እያለ እኛ ግን ለዘመናት ስንማጠን የኖርነው የባለጸጎችን እጅ ነው። እንዳሻን ልንቀዳው የምንችለው የተትረፈረፈ ሀብት እያለንም ለምን በጠብታ በሚመሰል የውጭ እርዳታ ላይ አፋችንን ለጉርሻ እንደምንከፍት ያለማወቃችንም እንቆቅልሻችን ነው። ለባዕዳን ችሮታ “ላም እሳት ወለደች እንዳትልሰው ፈጃት፤ እንዳትተወው ልጅ ሆነባት” የሚለው ብሂል እውነታውን በሚገባ የሚገልጽ ይመስላል።
እርዳታ ሰጭዎቻችን ከስንዴያቸውና ከዱቄታቸው፣ ከዘይትና ከሩዛቸው ጋር ሸጉጠው ካጎረሱን ጉርሻ ጋር ጠቅልለው የለገሱን “ስንጥር” ለአሸባሪው የትህነግ ቡድን ጥፋት እንደምን ጉልበት እንደሆነ ተደጋግሞ ተጠቅሷል። በኬላዎች ላይ የጉርሻውን ምንነት አብጠርጥረን እንፈትሽ ሲባልም የደረሰብን ዓለም አቀፍ ኡኡታ እንደምን ከአጥናፍ አጥናፍ አስተጋብቶ እንደነበር አንዘነጋም። በድህነታችን የበለጸጉት ባዕዳንና የእኛዎቹ የቤት ውላጆች እርዳታውን ለራሳቸው ቤትና ከርስ እንደተጠቀሙበትም ጥቁምታ ሲሰጠን ባጅቷ።
ማንም ሀገር በባዕዳን ጉርሻ ከድህነት እስራት ተላቆ ስለመበልጸጉ ማስረጃ ማቅረብ አይችልም። እርዳታ ሰጭዎቻችንም ቢሆኑ ለዚህ እውነት ባዕዳን ናቸው ማለት አንችልም። እርግጥ ነው በአንድ ቁና ጥሬ አንድ እንቅብ ወሮታ ከእኛ እንደሚጠብቁ አይጠፋንም። ሰብዓዊነትና የሰው ልጆች ፍቅር ግድ ካላቸው ዜጎቻቸው በሚሰበስቡት ሀብት መካከል የፖለቲካቸውንና የሸር ስንጥሮቻቸውን እየሰገሰጉ የሚልኩልን አንዳንድ መንግሥታት ሴራቸው አይታወቅ ከመሰላቸው ተሳስተዋል። ክብራችን በድህነታችን የሚለወጥ ከመሰላቸውም አመለካከታቸውን ቢቃኙ አይከፋም።
ሀገሬ ከስንዴ ልመና ለመላቀቅ በመወሰን የተበጣጠሰውን ማሳዋን አገጣጥማ በጋ ከክረምት ምርት ለማፈስ መጨከኗን መስማታችን አንድ ጉልህ እርምጃ ነው። በመላው ዓለም የተበተኑ ልጆቿ ሆ ብለው የሚያሰሙት የሰሞኑ “አለንልሽ” ርብርብም ግዙፍ የሚሰኝ መልእክት ለዓለም ማኅበረሰብ እንደሚያስተላልፍ ተስፋ እናደርጋለን።
”ከሰው ቤት እንጀራ፤ ካልጫ መረቁ፣
[የልጅ] እጅ ይጥማል፤ ዘንጋዳ ደረቁ።‘
በማለት ሰሞኑን እየጎረፉ በመምጣት ላይ ላሉት ልጆቿ ኢትዮጵያችን በአራራይ ድምጽ ስታንጎራጉር ዓለም እያደመጠ ነው።
የልመና እጃችን ታጥፎ እርፍና ማሽን እንድንጨብጥ፣ አስተሳሰባችንም ተቃኝቶ ፀጋችንን እንድንቃኝ መልዕክቱ በስፋትና ጎልቶ በመተላለፍ ላይ ነው። በአሸባሪው ትህነግ ምክንያት ለተፈናቀሉትና ኑሯቸው ለወደመባቸው ዜጎቻችን የእርዳታው ጉርሻ በባዕዳን እጆችም ቢሆን እየቀረበልን እንዳለ እየሰማንም እያየንም ነው። በዚህ ባልሰከነ የመታደጊያ እርዳታ መካከል በጉርሻው ቅንጥብጣቢ ለመበልጸግ የሚልከሰከሱ የቤትና የውጭ ኅሊና ሙቶች መታየታቸው በሹክሹክታ እየተነገረ ስለሆነ መንግሥት ጠንከር ብሎ ጥብቅ ክትትል በማድረግ መረር ያለ እርምጃ ለመውሰድ ሃሞቱን ሊያኮሰትር ይገባል። ተረጂዎቹ ወገኖቻችንም ጉርሻው አማልሏቸው ከወትሮው የአምራችነታቸው ትጋት እንዳይቦዝኑ ሊበረታቱ ይገባል።
እርግጥ ነው በሀገር ደረጃ የአግዋን ጉርሻ ተነጥቀናል። አንዳንድ መንግሥታትም መሰንዘር የሚገባቸውን የበጎነት እጃቸውን ሰብስበው ቂም እንደቋጠሩብን ይታወቃል። አንዳንዶችም ጉርሻቸውን ወደ አፋችን ከማስጠጋታቸው በፊት ቅድመ ሁኔታዎችን እንድናከብር ሸምቀቆውን በማጥበቅ ላይ መሆናቸውን በግልጽ ቋንቋ እየነገሩን ነው። እኛም ስለ ካሁን ቀደሙ በጎነታቸው አመስግነን መልሰን በድፍረት በሚገባቸው ግልጽ ቋንቋ የምንነግራቸው እውነት አለን።
የኢትዮጵያ ተስፋ የእነርሱ ምጥን ጉርሻ ሳይሆን የራሷ የተፈጥሮ ሀብትና የልጆቿ ትጋት ነው። የተራቆተውን ማዕዷን ምሉዕ ለማድረግም እየተጋን መሆኑን ይወቁልን። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ሲገለጥ ምን መልክ እንዳለው ከመከራዋ ለመታደግ ከመላው ዓለም ተሰባስበው ወደ ቄያቸው በመትመም እየተረባረቡ ካሉት ከራሷ ልጆች ትምህርት እያገኙ እንደሆነ ተስፋ እናደርጋለን።
ኢትዮጵያ ጦርነቱን ብቻም ሳይሆን ድህነቷንም በቅርቡ እንደምታሸንፍ እርግጥ መሆኑን ይመኑልን። “መቀበል ብቻም ሳይሆን መስጠትም” ባህላችን እንደነበረና እንደሆነ የተሰነደውን የታሪካችንን ምዕራፍ ገልጠው ያንብቡ። ካላመኑ እውነቱን ከደጃፋችን ደርሰው ይመልከቱ። ቢቻላቸውም በጉርሻቸው መካከል የሚሰነቅሩትን ስንጥር እርግፍ አድርገው ይተውት። ካልመሰላቸውም የመሰላቸውን ያድርጉ። ኢትዮጵያ በጉሮሮዋ ላይ የሚሰነቀርን ስንጥር እንደትናንቱ ዛሬም እያየች ለመታነቅ ዝግጁ አይደለችም። ይኸው ነው። ሰላም ይሁን።
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 20/2021