የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን አቅሙ የፈቀደውን ሰብአዊ፣ ቁሳዊና ኢኮኖሚያዊ በደሎችን ይፈጽምባቸው ከነበሩ ቦታዎች ተጠራርጎ ወጥቷል። ይህም ሆኖ ግን ቡድኑ የሌባ አይነደረቅ መልሶ ልብ ያድርቅ እንደሚባለው አይነት፣ በየጊዜው እራሱን እንደእስስት እየለዋወጠ ሲመቸው ጥቃት እያደረሰ ሳይመቸው ደግሞ ተበዳይ ሆኖ ክሱን እያሰማ ይገኛል። ለነገሩ ‹‹ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ከውጭ ታሳድራላች›› ይል የለ ያገሬ ሰው።
ቡድኑ አሁንም የማህበራዊ ድረ ገጽ (ፌስቡክ) አርበኞችን በገንዘብ በመግዛት የሆነውንም ያልሆነውንም በስማ በለው እንዲነዙ በማድረግ ከወደቀበት ለመነሳት በመውተርተር ላይ ነው። በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ላይ ደግሞ የመሳሪያ ሽያጭ፣ የእርዳታ፣ የንግድ ስምምነት፣ የሰብአዊ ድጋፍ ብቻ የቻሉትን ሁሉ ማዕቀብ በማድረግ በል በለው የሚሉ መኖራቸው ለአሸባሪውን መንፈራገጥ ምክንያት ናቸው።
ልቡ በውጪ ሀይል ድጋፍ ተስፋና በአሸባሪነት ተግባር የተደፈነው ሕወሓት ዛሬም መቃብር አፋፍ ላይ ሆኖ የጦርነት ነጋሪቱን ከመጎሰም አልተቆጠበም። ከሳምንታት በፊት የአማራና የአፋር አንዳንድ ከተሞችን አውድሞ፣ ዜጎችን ለስነልቦናዊና እና አካላዊ ጉዳት በመዳረግና የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በመፍጠር እኩይ አላማውን ለማሳካት ሲውተረተር ነበር። አሸባሪው አንዴ ሽብርተኛ ስለሆነ ሲመቸው ገድሎ፣ ሳይመቸው ዘርፎ ለመሄድ የቆመ ነው።መልሰው ጥቃት ለማያደርሱ የቤት እንስሳ ያልራራ ለሰው ልጅ የማይመለስ ጠላት ነው። የእኩይ አላማው መጨረሻ ደግሞ በህዝቦች መካከል ቅራኔ በመፍጠር በኦነግ ሸኔ ተንጠላጥሎ በአሜሪካ ድጋፍ አዲስ አበባ መግባት ነበር።
አሸባሪው ሕወሓት የሁል ግዜ መዝሙሩ በሀገሪቱ የብሄር ብሄረሰቦች መብት አልተከበረም ነው። የእሱ አካሄድ ግን ለሌሎች ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሊያስብ ቀርቶ የትግራይን ህዝብ ራሱ ነፃ አወጣሀለሁ እያለ የጥይት እራት ከማድረግ መዝለል አልቻለም። ከዚህም አልፎ ህዝቡን ከሌላው ወገኑ ከሆነው የኢትዮጵያ ጋር ተስማምቶ እንዳይኖር እያደረገውም ይገኛል። የሽብር ቡድኑ አካባቢውን የጦርነት ቀጣና ከማድረጉም በላይ የትግራይ እናቶች በድህነት አቅማቸው ወልደው ያሳደጓቸውንና ነገ ለቁም ነገር ይበቁልናል ብለው ተስፋ የጣሉባቸውን ልጆቻቸውን በለኮሰው እሳት የጥይት ራት እየዳረጋቸውም ይገኛል።
የቡድኑ የከፋፍለህ ግዛ አካሄድ አንዱን ብሄር ከሌላው በማጋጨት ብቻ የተወሰነ አልነበረም። ይልቁንም እንታገልለታለን የሚሉትን የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድምና እህቶቹ ጋር በሰላም እንዳይኖር እያደረጉት ይገኛል። በቀንደኛ የሕወሓት ፖለቲከኞችና አድር ባይ ምሁራኖቻቸው የጥላቻ ትርክቶችን በመፍጠር የህዝቡን የቀደመ አብሮ የመኖር እሴት በማበላሸት ብቻውን እንዲቀር ለማድረግ መጠነ ሰፊ ስራዎችን በአደባባይ ጭምር እየሰሩ ነው። በዚህም በህዝቡ ላይ በተለይም በወጣቱ ክፍል የፈጠሩት ስነልባናዊ ጫና እለት እለት እያደገ ጫና እየፈጠረ ይገኛል።
አሸባሪው ሕወሓት በአስራ አንደኛዋ ሰአትም ክፋቱን እየመነዘረ የስልጣን ኮርቻውን ለመቆናጠጥ እንቅልፍ ሳይተኛ እያደረ ነው። በየቦታው ያሰማራቸው ቅጥረኞችና ባንዳዎችም ስራ ከእርሱ ያልተሻሉ መሆናቸውን እያየን ነው። እነዚህ ባንዳዎች ካለፈ ታሪካቸው በመማር ቢያንስ እንኳን ለራሳቸው አላሰቡም። ዛሬ ታግለው ስልጣን እንዲይዙ የሚያግዟቸው ቡድኖች ነገ እንደሚያስጠጓቸው ምን ያህል እርግጠኞች ናቸው። ለነገሩ ለዛሬ ሆድ መሙያቸው ካገኙ ስለነገ የሚያስቡ ባለመሆናቸው ስለነገ ህይወታቸው ይጨነቃሉ ማለት የዋህነት ነው።በለመዱት ባንዳነታቸውንና ቅጥረኝነታቸውን እየቀጠሉ መኖር ለእነሱ ክብር ነውና።
በዚህ ረገድ በየቀኑ በየጓዳውና ጎድጓዳው በፍተሻ እየተገኘ ያለው የጦር መሳሪያም የባንዳውን አርቆ አላሚነት ማሳያዎች ናቸው። ይህም ሆኖ የአዲስ አበባ ህዝብ አንድ ሆኖ ነቅቶ ከጠበቀ፣አጋልጦም ከሰጠ ህልማቸው ህልም ሆኖ እንደሚቀር ጥርጥር የለውም። ለዚህም ነው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ቀን ተሌት በፈረቃ በየመንደሩና ጎጡ አካባቢውን በመጠበቅ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር በመንግሥት የጠየቀው። ህዝቡም ሴት ወንድ ሳይል ጥያቄውን ተቀብሎ የጥበቃ ሥራውን እያቀላጠፈው የሚገኘው።
የህዝብ ትብበሩ ተላላኪዎችንና ባንዳዎችን የሚያስደነግጥ በመሆኑ መዘናጋት አያስፈልግም። ግርግር ለሌባ ይመቻል እንዲሉ አጋጣሚውን በመጠቀም ያለፉበትን ለመዝረፍ ያሰፈሰፉ መኖራቸውም መታወቅ አለበት።በመሆኑም ነዋሪው ቤቱ ሲገባ መንደሩንና አካባቢውን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን በሚሰራበትና በሚተላለፍበት ሁሉ መጠራጠሩን መተው የለበትም። ሀገርን ማዳን እራስን ማዳን እንደሆነ ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል።
ከ1888 ዓ.ም የአድዋ ጦርነት ጀምሮ ኢትዮጵያን እየፈተናት ያለው ባንዳና ቅጥረኛ ነው። ይህ ለሆዱ ያደረ ቡድን ጥቂት ቢጓዝ አንጂ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ያቀደው ምኞቱ አይሳካለትም። ሩቅ አልሞ ቅርብ አዳሪው የሽብርተኛ ቡድን በየቦታው የደበቀው የጦር መሳሪያ በቅጥረኞቹ በማዘዋወር ለጥቃት ያዘጋጀው ሁሉ እየከሸፈበት ይገኛል። ነቅቶ ጥበቃውን በማጠናከር ላይ ያለው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪም እንቅልፍ እንዳያሸንፈው። ለሀገር ዘመቻ ህልውና እንዲህ የተነቃቃውን ማህበረሰብ መደገፍ ደግሞ ግድ ይላል። ዛሬም አሸባሪው ሕወሓት በየአገልግሎት ተቋማትም ውስጥ እጃቸውን የሚጠመዝዛቸው አካላት ስለማይጠፉ መንግሥት ጥርጣሬውን በማስፋት መንጥሮ ሊያወጣቸው ይገባል።
ለአሸባሪው ቡድን የተገዙት የማህበራዊ ድረገጽ አርበኞችም በኢትዮጵያ ስም ከሀገር ወጥተው መልሰው ጡት የመንከስ ተግባራቸውን አጠናክረው በመቀጠላቸው ህዝብን የማሳሳቱ በተለይም ወጣቱ እንዲሳብ ማልያቸውን እየቀያየሩ የሽብር ተግባራቸውን እየገፉበት ስለሆነ በዚህ ረገድም አካባቢን ከመጠበቅ ባልተናነሰ ማህበረሰቡ ጆሮ ባለመስጠት ተገቢውን ምላሽ ሊሰጣቸው ይገባል። ከዳር ሆነው እሳቱን የሚያቀጣጥሉት የውጭ ኃይሎች መልካም የሚያስተምሩትንና እውነታውን የሚናገሩትን ድረገጾች እየዘጉ አጉራ ዘለሎችን በገንዘብ እየደገፉና እያበረታቱ መሆኑም ከህዝብ የተደበቀ አይደለም።
ዋናው ነገር ነገሮችን በሰከነ መንገድ አይቶ መልካሙን በማጠንከር ኢትዮጵያን ከከፉዎች መንጋጋ ውስጥ ማውጣት ላይ ነው። ነግቶ ሲመሽ የምናየው፣ በልተንና ጠጥተን ጠግበን ነገን የምናልመው፤ ደስታና ፍሰሐ ብቻ ሳይሆን ሀዘንም የሚያምረው በሀገር ነው። ሀገርን ማስቀደም ከሁላችንም ይጠበቃል። አሸባሪው ቡድን በሰው ልጅ ላይ ያደረሰውን ግፍና ሰቆቃ በማየት ዜጎች በግንባር ተዋግቶ መሞትን እንደ ክብር እያዩት መጥተዋል። እውነትም ለሀገር ክብር በግንባር መሰዋት ከምንም በላይ የክብር ክብር ነው።
ዛሬም ኢትጵያውያን አንድ ከሆኑ ግን አሸባሪው ቡድን እድሜ አይኖረውም። የውጭ ጠላቶችም ቢሆኑ ከአሸባሪው ቡድን ጋር ትናንት የነበራቸው የጥቅም ቁርኝት እንዳይቀርባቸው ስለሆነ፣ ቁርጣቸውን ሲያውቁ መመለሳቸው አይቀሬ ነው። ነገሩ የጊዜና የቀን ጉዳይ ብቻ ነው።
ሰላም ከአራት ኪሎ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 20/2021