በጎጥ በረት ውስጥ የተፈለፈለውና የጎሳ ጡጦ ጠብቶ ያደገው አሻባሪው የሕወሓት ቡድን በኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ስልጣኑን ከተነጠቀ በኋላም የስልጣን አባዜ የሚያመጣው እብደት ከእኛ በላይ ላሳር በሚል ትእቢት ተወጥሮ እኩይ ምግባሩን ሲያስቀጥል ቆይቷል።
የሽብር ቡድኑ ኢትዮጵያን የሚፈልጋት እርሱ እስከገዛት ብቻ በመሆኑ የኢፌዲሬ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመሰንዘር ኢትዮጵያ ላይ በገሃድ ጦርነት ከፍቷል። ኢትዮጵያም በቡድኑ እብሪትና ጥቃት ምክንያት ሳትፈልግ ጦርነት ውስጥ ለመግባት ተገዳለች።
ይህንን ተከትሎ መንግስት ባደረገው ልዩ የሰላም ማስከበር ዘመቻ እና በመከላከያ ሰራዊታችን አስደናቂ ብቃት አማካኝነት የሽብር ቡድኑ በጥቂት ቀናት ውስጥ ተቀጥቅጦ ወደ ጎሬው ለመግባት ተገዷል። የኢትዮጵያ መንግስት ባሳለፍነው ዓመት በሰኔ ወር አጋማሽ ለትግራይ ህዝብ ሲል የጥሞና ጊዜ ለመስጠት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ውሳኔ ሲያስተላልፍ፤ የሽብር ቡድኑ በአንጻሩ ለሰላም ቦታ እንደሌለው ከማሳየት አልተቆጠበም።
ይህን ተከትሎም አሸባሪው ቡድን በጦርነቱ ገፍቶበት በአዲስ መልክ ሂሳብ አወራርዳለሁ ብሎ በመምጣት በአፋርና አማራ ክልል ወረራ ፈፅሟል። ይሁንና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና ሕዝባዊ ሠራዊቱ (ልዩ ኃይላት፣ ፋኖ፣ ሚሊሻ) ኢትዮጵያን ወደ ሲዖል አወርዳታለሁ ብሎ የዛተውን የሃበሻ ናዚ ቡድን ሠራዊቶቻችን ዳግም አይቀጡ ቅጣት ቀጥተውታል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ከቀናት በፊት ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የተመራው ዘመቻ ለህብረ ብሔራዊ አንድነት የኢትዮጵያን ሕልውና የማስጠበቅ ዘመቻ የመጀመሪያውን ግብ በማሳካት ተልዕኮውን ማጠናቀቁን አሳውቀዋል።
በመግለጫቸውም በዘመቻው፣ ወራሪውና አሸባሪው የሕወሓት ኃይል እንዲበታተንና እንዲደመሰስ መደረጉን፣ በአሸባሪው ኃይል የተወረሩ ቦታዎችን ነጻ በማውጣትም የመጀመሪያው ግብ በድል መጠናቀቁን ያስገነዘቡት ሚኒስትሩ፣ ‹‹በዚህ ዘመቻ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አሸንፈዋል፤ የመከላከያ ሰራዊት፣ አየር ሃይል፣ ኮማንዶና ሜካናይዝድ ጦሩ በኢትዮጵያ በታሪክ ወርቃማ ሆኖ የሚጻፍ ታሪክ ፈጽመዋል፣ የአማራና የአፋር የጸጥታ ሃይሎችም የራሳቸውን ከፍተኛ ተጋድሎና አኩሪ ድርሻ የተወጡበትም ነበር›› ብለዋል። ወራሪውን ኃይል በገባበት የደመሰሰው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትም የያዛቸውን አካባቢዎች አጽንቶ እንዲቆይ መወሰኑን አሳውቀዋል።
ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ታኅሣሥ 15 ቀን ባስተላለፉት መልዕክት፣ መንግስት በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ሕልውና ላይ የተከፈተውን ግልጽና ረቂቅ ዘመቻ ለመመከትና ለመቀልበስ ብሎም በዘላቂነት የኢትዮጵያን አሸናፊነት ለማረጋገጥ የነደፈው ዕቅድ ሁለገብና ሁሉንም ግንባሮች ለመመከት የሚያስችል ስልት መሆኑን አብራርተዋል።
ዘመቻ ለህብረ ብሔራዊ አንድነት የኢትዮጵያን ሕልውና የማስጠበቅ ዘመቻ የመጀመሪያውን ግብ በማሳካት ተልዕኮውን ማጠናቀቁን ተከትሎ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ስትራቴጂያዊ በሆኑ ቦታዎች እንዲሠፍርና የጠላትን እንቅስቃሴ በአንክሮ እንዲከታተል መደረጉን አሳውቀዋል።
‹‹የማንኛውም ውሳኔያችን መርሕ ኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ድል እንድትጎናጸፍ ማስቻል ነው፤ ግዛታዊ አንድነታችን የሚጠበቅበትና በዘላቂነት ኢትዮጵያ አሸናፊ የምትሆንበትን መንገድ መቀየስ ነው። ይህንን ውሳኔ የወሰንነው በስሜት ሳይሆን የሚያስገኘውን ዘላቂ ጥቅም ከግምት አስገብተን ነው›› ብለዋል። ለውሳኔው ከዚህ በፊት በትግራይ ክልል ካጋጠሙ ችግሮች በመማርና፤ በሽብር ቡድኑ ሴራና ወጥመድ አለመግባትን ታሳቢ ያደረገ ስለመሆኑም አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣም የኢትዮጵያ መከላከለያ ሰራዊት የያዛቸውን አካባቢዎች አጽንቶ እንዲቆይ መወሰኑን እንዴት አያችሁት? ፋይዳውስ ምንድ ነው? የሚል ጥያቄዎች በማንሳት የውትድርናና የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያዎችን አናግረናል።
በርዕሰ ጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ካጋሩን መካከልም የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት የድጋፍና የልማት ማህበር ፕሬዝዳንት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ፣ አንዱ ናቸው። ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ የኢትዮጵያ መከላከያና ሕዝባዊ ሠራዊቱ (ልዩ ኃይላት፣ ፋኖ፣ሚሊሻ) አሸባሪ ቡድኑን አንኮታኩተው አኩሪ ገድል መፈፀማቸውን ይናገራሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት ሕወሓቶች ዛሬም የሚከተሉት ስትራቴጂ ትላንት የመጡበትን መንገድ ነው። ይህ መንገድ እንደማያስኬድና የማያዋጣ መሆኑን በማያዳግም እርምጃ ተምረውበት ተሸንፈው ወደ መጡበት ተመልሰዋል።
ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ እንደሚያስረዱትም፣ በወታደራዊ ስራቴጂ ሁሌም አዋጭ የሆነ መንገድ ይነደፋል። ቢቻል መስዋትነትን በማያስከፍል፤ ካልተቻለ ደግሞ በጣም በአነስተኛ መስዋትነት ግዙፍ የማሸነፍ አውዶችን መፍጠር ያስፈልጋል። ይህ የሚሆነው ደግሞ በስሜት ሳይሆን በስሌት ነው፤ ቆም ብሎ አካሄድን በመገምገምና በማሰብ ነው።
ሁሉም ነገር እቅድ ይፈልጋል። ውጊያ በቀናት ልዩነት አይደለም በደቂቃና በሰዓት የሚለዋወጥ ባህሪ አለው። ወታደራዊ ተልዕኮዎችም እያንዳንዱ ጉዞን በመገምገም የሚከወኑ ናቸው። አንድን ዘመቻ ውጤታማ በሆነ መልኩ በመምራት ድልን ለመጎናጸፍም ግራና ቀኝ ማስተዋል፣ አዳዲስ እቅዶችንና ስትራቴጂዎችን መንደፍ የግድ ይላል።
የጠላት ኃይል ተዳክሞ እየተበታተነ ባለበት እና የወገን ኃይል በጥሩ ሞራል ላይ በሚገኝበት ሁኔታ የኢትዮጵያን ጠላት ተከታተሎ እስከመጨረሻው መደምሰስ በጦርነት ይደገፋል። አንድ ሲያጠቃና ረጅም ርቀት ተጉዞ ሲዋጋ የቆየ ሰራዊት እያሸነፈም ቢሆን ይቁም ማለት አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜም አለ።
ከዚህ አንጻር መንግስት ወራሪውን ቡድን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ወደ መጣበት የሸኘው የኢትዮጵያ መከላከለያ ሰራዊት የያዛቸውን አካባቢዎች አጽንቶ እንዲቆይ መወሰኑም በአንዳንዶች ዘንድ ብዥታን ቢፈጥርም ከወታደራዊ ስትራቴጂና መለኪያዎች አንጻር ውሳኔው በጣም ትከክልና ተገቢ ነው ይላሉ።
ውሳኔው በእቅድና ወደ ፊት ሊገጥም የሚችል ሁኔታን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንደተወሰነ የሚያምኑት፣ ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አሕመድም ቀደም ሲል ያለፈበት እንደመሆኑ ወታደራዊ ብልሃትና ስልት የሚጠፋው መሪ አይደለም›› ይላሉ።
መንግስት ካቀረባቸው አመክንዮዎች አንጻርም ሰራዊቱ ባለበት ተጠናክሮ እንዲቆይ መደረጉ አዎንታዊ ሚና እንዳለው የሚያስረዱት፤ ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እንደ ትላንቱ ሁሉ ዛሬም ወራሪ ኃይል እንዳልሆነ በቂ ምስክር የሚሰጥ ነው፤ የትግራይ ሕዝብም ይህን ለመረዳት ከዚህ በላይ ምስክር ሊያገኝ እንደማይችል ያስገነዝባሉ። ‹‹ውሳኔው የትግራይ ህዝብ ከአሸባሪው ሕወሓት ፕሮፓጋንዳ በመውጣት እውነቱን ሲረዳ የሽብር ቡድኑን በራሱ ተዋግቶ ነጻነቱን እንዲያውጅ ያደርጋልም›› ይላሉ።
ሰራዊቱ የያዛቸውን አካባቢዎች አጽንቶ ይቆይ ማለት፣ ከዚህ በኋላ ጦርነቱ ተጠናቋል ማለትም እንዳልሆነ አፅንኦት የሚሰጡት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፤ በሽብር ቡድኑ የአገርን የግዛት አንድነትና ሰላምን ለአደጋ የሚዳርግ ሁኔታ ተፈጥሮሯል ተብሎ በሚታሰብበት ጊዜ የመከላከያ ሰራዊቱ በማንኛውም ቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ እርምጃ እንደሚወስድም ታሳቢ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ሳያስገነዝቡ አላለፉም። ‹‹በቀጣይም የውጊያና የግዳጅ ሂደቱን ማስፋፋት የሚያስችለውን አቅም ገንብቶ የቆመ መከላከያ ሰራዊት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋልም›› ነው ያሉት።
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ሰለሞን ተፈራም የአሸባሪ ቡድን አመራሮችና አባላት በፖለቲካ ቁማር በዋነኝነት የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ሕዝብ ላይ ጦርነት አውጇል፣ ተነስና እራስህን አድን በሚል የትግራይ ሕዝብና ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ሲያታልልበትና ሲያሳምንበት እንደነበር ያስታውሳሉ።
የትግራይ ህዝብም በሽብር ቡድኑ እብሪትና የተሳሳተ ትርክት በስሌት ሳይሆን በስሜት ጦርነት ውስጥ መግባቱን የሚገልጹት ምሁሩ፣ በዚህም አላማው ለማይታወቅ ጦርነት ልጆቹን ጨምሮ አላስፈላጊ ከፍተኛ መስዋትነት ለመክፈል መገደዱን ይጠቁማሉ።
“የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ነጻ ያወጣቸውን ቦታዎች አጽንቶ እንዲቆይ መወሰኑ በመንግስት ጥልቅ ግምገማ ተደርጎበት የተላለፈ ትክክለኛ ውሳኔ ነው ብዬ አስባለሁ፣ ውጤቱ ከፍተኛ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ትርፍ አለው” ሲሉም ፋይዳውን ያብራራሉ።
አሸባሪው ቡድን የራሱን ሬሳ በመሰብሰብ ጅምላ ግድያ ተፈጽሟል በሚል የኢትዮጵያ መንግስት ላይ ውጫዊ ጫና እንዲፈጠር ለማድረግ ያሰበውን ሴራ ለማክሸፍ ፋይዳው የጎላ ስለመሆኑ የሚያስገነዝቡት ምሁሩ፣ ‹‹ውሳኔው የአሸባሪ ቡድኑ አመራሮች በውጭ ከሚገኙ አጫፋሪዎቻቸው ጋር በመቀናጀት መልኩ ሙታንን ሰብስበው ወደ መቀሌ በማጓጓዝ የጅምላ ግድያ ተፈፀመብን በሚል ሊሰሩ አስበው ለነበረው የፖለቲካ ቁማር ግዙፍ ኪሳራን የሚያስታቅፍ ነው›› ይላሉ።
ውሳኔው ‹‹የሽብር ቡድኑ ‹ከእኔ ውጭ› በሚል ለእኩይ ፍላጎቱ ማስፈጸሚያ እንዲመቸው ሲደሰኩረው እንደቆው ሳይሆን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የትግራይ ወራሪና ጠላት እንዳልሆነ በተጨባጭ የሚያረጋግጥ ነው›› የሚሉት ምሁሩ፣ የትግራይ ህዝብም ይህን የሕወሓት የተሳሳተ ትርክት በግልጽ የሚረዳበት አጋጣሚ የሚፈጥር ስለመሆኑም ያመላክታሉ። ዋነኛ የትግራይ ጠላት ‹‹የኢትዮጵያ መከላከያ ሳይሆን የሽብር ቡድኑ አመራሮች መሆናቸውን የሚረዳበት የጥሞና ጊዜ እግኝቷልም›› ይላሉ።
በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚሰነዘሩ የጥፋት እጆችና የሚጠነሰሱ ሴራዎች እንዲሁም የጣልቃ ገብነት ፍላጎቶች የሚሰጠው ምላሽ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነም የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ሰለሞን ተፈራ አፅንኦት ሰጥተው ያስረዳሉ።
በዚህ ረገድ ከዚህ ቀደም አንዳንድ አገራትና ተቋማት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ክልል መውጣት አለበት የሚል ጥያቄን በማቅረብና በዚህ ሽፋን የራሳቸውን አገር የማፍረስ አላማ ለመስፈጸም ሲተጉ እንደነበር የሚያስታውሱት መምህሩ፤ አሁን ላይ አስፈላጊ ሆኖ እስኪገኝ ወታደሩ ባለበት እንዲጸና መወሰኑም እነዚህን አካላት ዳግም እኩይ አላማቸውን እንዳይፈፅሙና ድራማቸው እንዲከሸፍ ያደረገ ስለመሆኑም ነው ያስረዱት። የመንግስት ወቅታዊ እርምጃ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ጣልቃ እየገቡ የሚፈተፍቱ የውጭ ኃይላትን አንደበት የሚያዘጋ ነው ባይ ናቸው።
የትግራይ ዜጎች ጥያቄ እንዲጠይቁና ከስህተታቸው እንዲታረሙ ያደርጋልም፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም በሽብር ቡድኑ ሴራ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የነበረው የተንሸዋረረ ዕይታ እንዲያስተክክልም ያስችላል ነው ያሉት።
አስተያየት ሰጪዎቹ በቀጣይ ምን ይደረግ ለሚለውም ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ሰለሞን ተፈራ የትግራይ ህዝብ በተሰጠው የማገናዘቢያ ጊዜ በመጠቀም አሸባሪውን ቡድን ሊፋለምና የትግራይ እናትና አባቶች ልጆቻችን የት ናቸው፣ የት አደረሳችኋቸው፣ በልጆቻችን ደም ምን አተረፋችሁ ብለው ሊጠይቁ፤ የሽብር ቡድኑን አመራሮችም አሳልፎ መስጠት እንዳለባቸው፣ የትግራይ ተወላጅ ልሂቃንና ፖለቲከኞች ከዝምታ ይልቅ ሕዝቡን በማንቃት በኩል ትልቅ የቤት ስራ ሊሰሩ እንደሚገባቸው ነው ያስገነዘቡት።
የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት የድጋፍና የልማት ማህበር ፕሬዝዳንት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ በበኩላቸው፣ ‹‹የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ተክለ ቁመና በእጅጉ እየተጠናከረ ነው። የኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት እንዲሁም አንድነት ተጠብቆ እንዲቀጥልም የመከላከያ ኃይሉን በሁሉ ረገድ ይበልጡን እያጎለበቱ መጓዝ የግድ ይላል ነው›› ያሉት።
የኢትዮጵያን አልደፈር ባይነት እውነትና መልካም ገፅታ እንዲሁም ትንሳኤዋ ሩቅ እንዳልሆነ በማስተዋወቅና በማስገነዝብ ረገድ የተጀመሩ ተጋድሎዎችም ይበልጥ መጠናከር እንዳለባቸው ያመላከቱት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፣ ‹‹ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ ምዕራባውያኑ እንደሚያስቡት በቀላሉ የምትፈርስ አገር እንዳልሆነች በማስገንዘብ የዜግነት ግዴታችንን ልንወጣ ይገባልም ነው›› ያሉት። ባልተገባ ጦርነት ከፍተኛ ዋጋ የከፈለውና ልጆቹን የገበረው የትግራይ ህዝብ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ የአሸባሪውን ቡድን አመራሮች በቃችሁ ሊላቸው እንደሚገባም ሳያስገነዝቡ አላለፉም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይም፣ የትግራይ እናቶች ይህንን ሁሉ ምስቅልቅል ያመጣባቸውንና ልጆቻቸውን ነጥቆ ያስጨረሰባቸውን አሸባሪ ኃይል መጠየቅ አለባቸው። የትግራይ ሕዝብም እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ ይሄንን አሸባሪ ታግሎ የማስወገድ አቅምና ችሎታው አለው። ድጋፍና እርዳታ ባስፈለገ ጊዜም የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ከክልሉ ሕዝብ ጎን ይቆማል።
አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ሰራዊቱ ወደትግራይ ሳይገባ ባለበት ፀንቶ እንዲቆይ መደረጉ አዎንታዊ መሆኑን ገልጸው፤ ነገር ግን አሸባሪው ሕወሓት ዳግም እንዳያንሰራራ መንግስት እየተከታተለ ሁሉን አቀፍ እርምጃ መውሰድ ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት እንደሌለበትም ሳያስገዘንቡ አላለፉም።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 19/2014