በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን ካለንበት ወቅት ጋር ይመሳሰላሉ ያልናቸውን በ1970 የወጡ ዜናዎች ለመዳሰስ ሞክረናል፤ ዚያድ ባሬ ኢትዮጵያን ለመውረር ያደረገው ሙከራ ከንቱ ድካምና ውድቀት መሆኑን ዜናዎቹ ይጠቁማሉ። ዜናዎቹ የሀገር ሰላምና ጸጥታ በማስከበር የተደረጉ ድሎችንና የልማት ሥራዎችን ያካተቱ ናቸው።
በጦር ሜዳ ለሚገኙ ጀግኖች የማዕረግ ዕድገት ተሰጠ
(ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት)
አብዮታዊት ኢትዮጵያ ከውጭ ወራሪ ኃይሎችና ከውስጥ አድኃሪ መደቦች ጋር በምታደርገው መራራ ብሔራዊና አብዮታዊ ጦርነት በአሸናፊነት እንድትወጣ ሌት ተቀን በመሥራት በታታሪነትና አብዮታዊ ስነምግባር ለአብዮቱ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደረጉና በማድረግም ላይ ለሚገኙ መለዮ ለባሽ አባሎችና የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ትናንት የሚከተለውን ሹመት ሰጥቷል።
ሌተና ኰሎኔል ተስፋዬ ወልደሥላሴ የሙሉ ኰሎኔልነት ማዕረግ፣ሌተና ኰሎኔል ስዩም መኰንን የሙሉ ኰሎኔልነት ማዕረግ፣ሌተና ኰሎኔል አሰፋ ሞሲሳ የሙሉ ኰሎኔልነት ማዕረግ፣ሌተና ኰሎኔል ገብረክርስቶስ ቡሊ የሙሉ ኰሎኔልነት ማዕረግ፣ሌተና ኰሎኔል እምቢበል አየለ የሙሉ ኰሎኔልነት ማዕረግ፣ሌተና ኰሎኔል አለማየሁ አየለ የሙሉ ኰሎኔልነት ማዕረግ፤ ሻለቃ ጐሹ ወልዴ የሌተና ኰሎኔልነት ማዕረግ፣ሻለቃ ለገሠ ኃይሌ የሌተና ኰሎኔልነት ማዕረግ፣ሻለቃ አድማሱ ገብረሃና የሌተና ኰሎኔልነት ማዕረግ፤ ሻምበል እሸቱ ገብረሕይወት የሻለቅነት ማዕረግ፣ሻምበል እርቅይሁን ባይሳ የሻለቅነት ማዕረግ፤ የመቶ አለቃ ገብሩ ተሰማ የሻምበልነት ማዕረግ
ከባሕር ኃይል
ሌተናል ኮማንደር ሽፈራው ጥላሁን የኮማደንርነት ማዕረግ
ከፖሊስ ሠራዊት
ሌተናል ኰሎኔል ሰይድ አብደላ የሙሉ ኰሎኔልነት ማዕረግ፣ሻለቃ አረጋው እሸቱ የሌተናል ኰሎኔልነት ማዕረግ፤ ሻምበል ግርማ ይልማ የሻለቅነት ማዕረግ፣ ሻምበል ብርሃኑ ከበደ የሻለቅነት ማዕረግ የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ለአብዮታዊት ኢትዮጵያ በሁሉም አቅጣጫ በመዋጋትና በመታገል ላይ ለሚገኙት ሁሉ የሚሰጠውን ሹመት እንደሚቀጥል አንድ የደርጉ ቃል አቀባይ አስታውቋል።
(ታኅሳስ 23 ቀን 1970 ከወጣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
70 የሶማሊያ ወታደሮች ተገደሉ
ሐረር (ኢ-ዜ-አ-) በሐረርጌ ክፍለሀገር በበደኖ ከተማ አካባቢ ዲዳሳቦና ደነባ በተባሉት ቀበሌዎች የሚገኙት መለዮ ለባሾች፣ወዝአደሩና አባት ጦረኞች በመተባበር ባደረጉት አሰሳ ፸ የሶማሊያ መደበኛ ወታደሮች ሲገድሉ ከመቶ ሃምሳ በላይ ማቁሰላቸው ተገለጠ።
በዚሁ ጊዜ በተካሄደ ጀብዱ የጠላትን ምሽግ ሠፈር እንዳልነበር አድርገው መደምሰሳቸውን አንድ የክፍለሀገሩ ቃል አቀባይ ገልጧል። በሌላ በኩል ደግሞ በጋራ ሙለታ አውራጃ አስተዳደር ውስጥ ጫካ ገብተው የነበሩ አምስት አርሶ አደሮች ከነሙሉ ትጥቃቸው መንግሥት በሰጠው ምህረት በመጠቀም እጃቸውን ሰጥተዋል።
በጥፋታቸው ተጸጽተው ወደ ሰላማዊ ኑሮአቸው የተመለሱት የገበሬ ማኅበር አባላት በጋራ ሙለታ አውራጃ አስተዳደር ቀበሌዎች አርሶ አደሮች መሆናቸው ታውቋል። አርሶ አደሮቹ በአሁኑ ጊዜ ፈርሶ የነበረውን ማኅበራቸውን መልሶ ለማቋቋም በየገበሬ ማኅበራቸው እየቀረቡ መመዝገባቸውን አንድ የክፍለሀገሩ ጽ/ቤት ቃል አቀባይ አስታውቋል።
(ጥር 28 ቀን 1970 ከወጣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
ጦርነቱን በሚደግፉትና በሚቃወሙት የሶማልያ ባለሥልጣናት መካከል ውዝግብ ተፈጠረ
በኢትዮጵያ የሚካሄደውን ጦርነት በሚደግፉና በሚቃወሙት የሶማልያ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች መካከል እጅግ የከረረ ውዝግብ ሰሞኑን የተፈጠረ መሆኑን ከተጨበጠ መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ዚያድ ባሬና አጫፋሪዎቹ በኢትዮጵያ አብዮትና አንድነት ላይ የተከፈተው ጦርነት እንዲቀጥል ሲገፋፉ፤ ሌሎች ወገኖች ደግሞ ጦርነቱ ለሶማልያ ሕዝብ ደህንነትና ለአካባቢው ሰላም ጠንቅ ስለሆነ ባስቸኳይ እንዲቆም የሚሉ መሆናቸው ታውቋል።
ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ተገዶ እንዲዘምት የተደረገው የሶማሊያ ሠራዊት በኢትዮጵያ መሬት ላይ መቆየቱ የማያዋጣ መሆኑን ዚያድ ባሬና ደጋፊዎቹ ቢረዱም፤ የተመለሰ እንደሆነ ለሥልጣናቸው አደገኛ ይሆናል ብለው ስለሚገምቱ እዚያው እንዲያልቅ የሚፈልጉ መሆናቸውን መረጃው ጠቁሟል። ወደ ኢትዮጵያ እንዲዘምት የተደረገው ሠራዊት እንዲመለስ ዚያድ ባሬ ፈጽሞ የማይፈልግ መሆኑን ከዚህ ቀደም ለአንድ የአፍሪካ መሪ ገልጦ እንደነበር ታውቋል።
ጦርነቱ ይቀጥል የለም መቆም አለበት በሚል ሳቢያ በሶማሊያ መሪዎች መካከል ሰሞኑን በተፈጠረው ውዝግብ ምክንያት ሞቃዲሾ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ የፖለቲካ ስጋት ላይ እንደምትገኝ መረጃው ጠቅሶ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በሶማሊያ ፖለቲካ ለውጥ የሚመጣ መሆኑን አመላክቷል።
(የካቲት 22 ቀን 1970 ከወጣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
የአዲስ አበባ- ድሬዳዋ የባቡር አገልግሎት ሰሞኑን ይጀምራል
የሐረርጌ ክፍለ ሀገር ሕዝብ ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ ሰሞኑን በሚቀጥለው የባቡር አገልግሎት ልዩ የጉዞ ፕሮግራም በማዘጋጀት ለእናት ሀገር ጥሪ ገንዘብ የሚሰበሰብ መሆኑን የድሬዳዋ ኢሣና ጉርጉራ አውራጃ አብዮታዊ ዘመቻ አስተባባሪ ኮሚቴ ገለጠ።
ኮሚቴው ስለዚሁ ጉዳይ በሰጠው መግለጫ፤ የአድኃሪው የሶማሊያ መንግሥት በአብዮታዊት ኢትዮጵያ ላይ በፈጸመው ወረራ ምክንያት የባቡር ሐዲድ ድልድዮችና መስመሮች ፈራርሰው ከጅቡቲ እስከ ሚኤሶ ድረስ የነበረው የባቡር አገልግሎት ለአሥር ወራት መቋረጡንና አሁን ግን ለጊዜው ይኸው መስመር በመጠገኑ ከአዲስ አበባ እስከ ድሬዳዋ የባቡር አገልግሎት ሰሞኑን እንደሚጀምር አስታውቀዋል።
በዚሁ የጉዞ ፕሮግራም በመሳተፍ ሠፊው ሕዝብ እንዲተባበር ኮሚቴው በተጨማሪ አሳስቧል። የጉዞው ፕሮግራም ዝርዝር በቅርቡ እንደሚገለጥ ታውቋል።
(የካቲት 29 ቀን 1970 ከወጣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 19/2014