- /ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪያቸውን ተቀብለው ወደ አገር ቤት ለመጡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል /
አገር በአንድ ግዙፍ ቤተሰብ ሊመሰል ይችላል። አንድ ቤተሰብ የቆመበት መሠረት ጥንካሬ የሚታወቀው ከደስታ ጊዜያት ይልቅ ቤተሰቡ ችግር በገጠመው ወቅት ነው። የፈተና መብዛት አንዳንዱን ቤተሰብ ሲያቀራርበው አንዳንዱን ያራርቀዋል። ደካማ መሠረት ያለው ቤተሰብ ውስጥ አደጋ ሲከሰት በቤተሰቡ አባላት መካከል ልዩነቶች አፍጥጠው ይታያሉ፤ ቅሬታዎች ከተደበቁበት ይወጣሉ፤ ጣት መቀሳሰር ይበዛል፤ ልጆች ፈተናውን ተጋግዘው በጋራ ከማለፍ ይልቅ “ምን አገባኝ” ሲሉ ይደመጣሉ። የዚያ ቤተሰብ እጣ ፈንታም በመጨረሻ መፍረስ ይሆናል።
በተቃራኒው ጠንካራ መሠረት ላይ ለቆመ ቤተሰብ የፈተና መምጣት አንድነቱን ያጠናክራል እንጂ አያላላውም። ልዩነቶች ቢኖሩ እንኳን ለጊዜው ወደ ጎን ተብለው የቤተሰቡ አባላት ሙሉ ትኩረት ፈተናው ወደሚታለፍበት መንገድ ያነጣጥራል። ሁሉም እንደ አቅሙ የቻለውን ይታገላል። መውደቅ መነሳቱን እኩል ተካፍለው በመጨረሻ ችግሩ ሲታለፍ ሁሉም እኩል ደስተኛ ይሆናሉ። ይህ ወቅት ለኢትዮጵያ እንደ ሀገር በእጀጉ የተፈተነችበት ጊዜ ነው። ፈታኞቿ ተባብረው ረፍት ሊነሷት ያልፈነቀሉት ቋጥኝ፣ ያልወረወሩት ድንጋይ የለም። ኢትዮጵያ ግን በልጆቿ ትብብር አሁንም ጸንታ ቆማለች። የፈተና መብዛት የልጆቿን አንድነት አጎለበተው እንጂ አልሸረሸረውም። አቅሞቿን አስተባብራ እንድትጠቀም ምክንያት ሆናት እንጂ አላሸነፋትም።
በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ሀገራችን ሰው በፈለገችበት ጊዜ ለሀገራቸው የቁርጥ ቀን ልጆች መሆናቸውን አስመስክረዋል ብለን በድፍረት መናገር እንችላለን። አንዳንዶች ኢትዮጵያን ለመድፈር በተነሡ ጊዜ፣ ሌሎች የኢትዮጵያን እውነት በውሸት ለመሸፈን በተነሡ ጊዜ፣ የቀሩትም በኢትዮጵያ ላይ ተገቢ ያልሆነ ጫና ለማሳደር በተነሡ ጊዜ፣ ዳያስፖራ ወገኖቻችን ለኢትዮጵያ ሲሉ በአንድነት ቆመዋል። የፖለቲከኞችን በሮች አንኳኩተዋል። አደባባዮችን በሰልፍ አጥለቅልቀዋል፤ ታላላቅ ተቋማትን ሞግተዋል፤ የመሪዎችን የተሳሳተ ፖሊሲ ተጋፍጠዋል፤ ሚዲያዎች የኢትዮጵያን እውነት እንዲያንጸባርቁ ጫና ፈጥረዋል።
ዳያስፖራ ወገኖቻችን ለኢትዮጵያ ብቁ ዲፕሎማት ሆነው ሀገራቸውን አስከብረዋል። ለታላቁ የሕዳሴ ግድባችን ጥብቅና ከመቆም ባሻገር ገንዘባቸው በመላክ የግድቡ ሥራ እንዲፋጠን አስችለዋል። ለተጎዱ ወገኖቻችን በየጊዜው የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል። የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ባልተገባ ጫና በተፈተነ ጊዜ ከሚበሉት ቀንሰው ለሀገራቸው ለግሰዋል። ሀገራቸው የህልውና ፈተና ሲገጥማት በቻሉት ሁሉ ግንባር ቀደም ሆነው ተሰልፈዋል። በማኅበራዊ ሚዲያ የሚገጥመንን ፈተና ለመመከት ጊዜያቸውንና ዕውቀታቸውን ሠውተዋል።
ብዙ የዓለም አገሮች ከዳያስፖራ ወገኖቻቸው ጋር የፈጠሩት ጠንካራ ትሥሥር አገራቸውን በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲና በማኅበራዊ መስክ ለማሳደግ ጠቅሟቸዋል። ደቡብ ኮሪያ፣ ሕንድ፣ ቻይናና ሜክሲኮ ለዚህ መልካም አርአያዎች ናቸው። እነዚህ አገሮች የተማረ የሰው ኃይል ለማግኘት፣ የአገራቸውን የውጭ ምንዛሬ ዐቅም ለማሳደግ፣ በየሚኖሩበት አገር በአገራቸው ጉዳይ የፖሊሲ ጫና ለማሳደር፤ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ፤ የአገራቸው ጉዳይ የሚኖሩበት አገር የውጭ ፖሊሲ አካል እንዲሆን ለማስቻል፤ ቁሳዊና ሰብአዊ ድጋፎችን ለማሰባሰብ፤ የትምህርት፣ የጤናና የግብርና ሥርዓታቸውን ለማዘመን ተጠቅመውበታል።
ከላይ የጠቀስናቸው አገሮች የዳያስፖራቸውን ዐቅም በተሻለ ሁኔታ ለመጠቀም ያስቻለው ዘላቂነት ያለው፣ የተደራጀና የተናበበ አሠራር ስለሚከተሉ ነው። ዳያስፖራዎቻቸው ከአገራቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ዘላቂ ነው። የሆኑ ወቅቶችን መሠረት ያደረገ አይደለም። በደስታም ይሁን በፈተና ጊዜ አገራቸውን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ይደግፋሉ። በፖሊሲዎች፣ በሕጎች፣ በአሠራሮች ሂደት ውስጥ ይሳተፋሉ። ገንዘባቸውን በአገራቸው ባንኮች እንዲቀመጥ ያደርጋሉ፤ በኢንቨስመንት ይሳተፋሉ፤ በችግር ጊዜ ለወገናቸው ድጋፍ የሚያደርጉ ታላላቅ የርዳታ ድርጅቶችን በመመሥረት በርዳታ ስም ከሚመጣ ጣልቃ ገብነት አገራቸውን ነጻ ያደርጋሉ፤ ለገበሬዎችና ለአነስተኛ ነጋዴዎች የዕውቀት፣ የቴክኖሎጂና የገንዘብ ድጋፍ የሚሰጡ የልማት ማሣለጫ ተቋማትን ያደራጃሉ፤ በተለይም ትምህርትን፣ ጤናንና ግብርናን ለማዘመን የሚችሉ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግሮችን በማከናወን የሕዝባቸውን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ይተጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንግዲህ ለዘመድና ለወዳጆቻቸው ከሚያደርጉት ድጋፍ ባሻገር ነው።
እነዚህን ተግባራት ለማከናወን ዐቅምን ሰብሰብ ማድረግ፣ ወጥ በሆነ መልኩ ሥራዎችን መሥራትና በዕቅድ መመራት ያስፈልጋል። ዐቅሞቻችን በየአካባቢውና በየሁኔታው ከተበታተኑ፣ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት አይቻልም። በምንኖርበት አገር ተጽዕኖ ለመፍጠር ያለን ዐቅም የተዳከመ ይሆናል። እርስ በእርሳችን ተጋግዘን በፍጥነት ከመሄድ ይልቅ እርስ በእርሳችን በመወቃቀስ ጊዜያችን በከንቱ ይጠፋል።
ዳያስፖራ ወገኖቻችን እነዚህን ሁሉ እንደሚያስቡባቸው ተስፋ አደርጋለሁ። በየሀገራቸው ከሚኖሩ ሌሎች ጠንካራ የዳያስፖራ ማኅበረሰቦች ልምድ መውሰድ እንደሚችሉ ይታመናል። ለሀገራቸው መጠን የሌለው ፍቅር፤ ሀገራቸውና ወገኖቻቸውን በሚችሉት ሁሉ የመደገፍ የማይነጥፍ ፍላጎት አላቸው። ይሄንንም በየአደባባዩ አስመስክረዋል። ሕይወታቸውን መሥዋዕት ለማድረግ እስከመሰለፍ ደርሰዋል። ሀገራቸው ‹ወደ እናት ሀገራችሁ አንድ ሚሊዮን ሆናችሁ ኑ!› ስትላቸውም፣ ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ይሄው መጥተዋል።
አሁንም በድጋሚ ጥሪያችንን አክብራችሁ ስለመጣችሁ በራሴና በኢትዮጵያ ስም አመሰግናችኋለሁ። የመጣችሁት ወደ ቤታችሁ ነው። እናታችሁ በጓዳዋ ያላትን ሁሉ ታቀርብላችኋለች። የምታቀርብላችሁ ነገር የተሟላ ላይሆን ይችላል። ግን የእናት ቤት ከምንም ይበልጣል። በየመሥሪያ ቤቱ፣ በየንግድ ተቋማቱ በየአገልግሎት መስጫዎቹ የለመዳችሁትን ዓይነት ቀልጣፋና ዘመናዊ አሠራር ባታገኙ አይግረማችሁ። የእናታችሁ ቤት ነውና እንዴት እናዘምነው ብላችሁ አስቡበት እንጂ እንደ ባዳ አይታችሁ አትለፉት። ሰው ለእናቱ ቤት ይቆረቆራል እንጂ አይማረርም።
የተጎዱ አካባቢዎችን እንድትጎበኙ፤ ወገናችሁን እንድታንጹና እንድትደግፉ አደራ እላለሁ። አሸባሪው ሕወሓት በወገናችን ላይ ያደረሰውን ልክ የሌለው ግፍና መከራ በዓይናችሁ አይታችሁ ዓይኔን ግንባር ያርገው ላለው ዓለም እንድትገልጡ ላሳስባችሁ እወዳለሁ። አንዳንድ ተቋማት ባዘጋጇቸው መርሐ ግብሮችም ላይ ተሳተፉ። የቱሪስት መዳረሻዎችንም ጎብኙ። የልማት ሥራዎቻችንንም ተመልከቱ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ከወላጆቻችሁ፣ ከዘመዶቻችሁና ከወዳጆቻችሁ ጋር መልካም ጊዜ አሳልፉ። ሀዘኑንም ደስታውንም እኩል መጋራታችን ቤተሰባዊ መሠረታችንን ያጠናክረዋል።
መልካም የቆይታ ጊዜ ይሁንላችሁ።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ታህሳስ 18፣ 2014 ዓ.ም
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 19/2014