የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ታላላቅ ከሚባሉት ዓለምአቀፍ ድርጅቶች አንዱ ነው፡፡ ይሕ ዓለም አቀፍ ተቋም በየአገሩ በጤና ተቋማት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እንዲመዘገቡ ብሎ በሥራ ላይ ያዋለው ‹‹Surveillance system for attacks on health care›› (SSA) የተሰኘ መተግበሪያ አለው። ይህ መተግበሪያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጭምር ዕውቅና የተሰጠው ነው፡፡
እኤአ በ2017 ይፋ የሆነው መተግበሪያው በህክምና ተቋማት ላይ ጥቃት ያደረሱ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ የሚረዳ ነው፣ በየአገሩ በጤና ተቋማትና ባለሙያዎች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን ያሳያል፡፡ መረጃው ዓለም እንዲውቀው ለሁሉም ይፋ ይደረጋል፡፡
ማንኛው ግለሰብ፣ ድርጅት፣ አገርና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ሆነ ተመራማሪዎችም መረጃ በቀላሉ ማግኘትና እርዳታም ሆነ ጥናት ማድረግን ጨምሮ በሚፈልገው መልኩ በግብአትነት ሊጠቀሙበት ይችላሉ ፡፡
በየትኛው ጦርነት ሆን ብሎ የህዝብ አገልግሎት መስጫዎችን በተለይም የጤና ተቋማትን ማውደም የተከለከለ ነው፡፡ የጤና ተቋማትን ማውደም የጦር ስትራቴጂ ሳይሆን የጦር ወንጀል ነው፡፡ በኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ነውረኛው አሸባሪው ሕወሓት በአንፃሩ ከዚህ እሳቤ ጋር ፈፅሞ የሚተዋወቅ አይመስልም፡፡
አሸባሪ ቡድን ለ20 ዓመታት ነፍሳቸውን ሰጥተው ሲጠብቁት የነበሩ የሰሜን እዝ አባላትን አስከፊ በሆነ መልኩ በመጨፍጨፍና በማዋረድ በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ላይ ጥቃት በመሰንዘር ግልፅ ጦርነት በመክፈት የአገርን ሉአላዊነት ከመድፈር ባሻገር በወረራ ይዟቸው በቆያቸው ከተሞች የተለያዩ የመሰረተ ልማት አውታሮችና የህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን አውድማል፡፡
ቡድኑ በኢትዮጵያ ጥምር ጦር አስደናቂ ብቃት በጥቂት ቀናት ተንኮታክቶ መፍረክረክ ሲጀምር የህዝብ ሃብትና ንብረት የሆኑ መሰረተ ልማቶችን የማውደም ልክፍት ይበልጥ ተጠናውቶትም ታይቷል። የሽብር ቡድኑ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ያደረሰውን ውድመትና ዘረፋ በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ጣቢያዎች፣ በጤና ኬላዎችና ሆስፒታሎች ላይ ያለ ርህራሄ አርፏል፡፡
በተለይም በጦርነቱ ብሸነፍ እንኳን ሕዝቡ በሕክምና ዕጦት እንዲማረርና መንግሥት ተረጋግቶ እንዳይቀጥል የዓመታት የቤት ሥራ ልስጠው የሚመስል ዕቅድ በማውጣት በርካታ ጤና ተቋማትን አውድማል፡፡ የሽብር ቡድን በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ያደረሰውን ውድመትና ዘረፋ በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ጣቢያዎች፣ በጤና ኬላዎችና ሆስፒታሎች ላይ ያለ ርህራሄ አርፏል፡፡
አሸባሪውና ዘራፊው ቡድን በገባበት ከተማ ሁሉ የጤና ተቋማትን በማፈራረስና በመዝረፍ “ነበሩ” ወደሚያሰኝ ታሪክነት ቀይሮቸዋል፡፡ ብዙዎች በመድሃኒት እጦት በሰቀቀን እንዲያልቁ ምክንያት ሆነዋል፡፡ በቀጣይነት የሚያመጣው መከራና እልቂትም በቀላሉ የሚገመት አይደለም።
ወትሮውንም የተዳከመ የጤና አገልግሎት ባለባት ኢትዮጵያ ለኅብረተሰቡ የጤና አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት ላይ የተፈጸመው ዘረፋ፣ ውድመትና ጉዳት እጅግ አሳዛኝ ከመሆኑ ባሻገር በአሁኑ ወቅት በወራሪው ቡድን ተግባር የአካልና የስነ ልቦና ጉዳት የደረሰባቸው ነፍሰጡር እናቶች፣ አረጋውያንና ህፃናት በተለይም ተከታታይ ህክምና የሚያሻቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ለከፋ የጤና ችግር ተጋላጭ ሆነዋል፡፡
የኢፌዴሪ የጤና ሚኒስቴርም ከቀናት በፊት ይፋ ባደረገው መረጃም በወረራ ቡድኑ ስር ቆይተው የመንግሥት ኃይሎች ዳግም በተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ከ2 ሺ 700 በላይ የሚሆኑ የጤና ተቋማት ተዘርፈውና ጉዳት ደርሶባቸው አገልግሎት መስጠት እንደማይችሉ ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡
ኢትዮጵያና ዜጎቿ በወሮበላው ቡድን ጤና እና ጤና ተቋማቶቿን ተንጥቃ ወራትን ስትቆስል ብትቆይም ዓለም አቀፉ ተቋም ግን ይህን አላየሁም አልሰማሁም ብላል፡፡ ኢትዮጵያ ከመቀነቷ ፈትታ ባላት አቅም ሁሉ መንገድ አስይዛ የገነባችው የጤና ተቋማት በዱርዬ ሲወድም ዝም የማለት ሞራል አግኝቷል፡፡
ዓለም አቀፍ ተቋም በየአገሩ በጤና ተቋማት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እንዲመዘገቡ ብሎ በሥራ ላይ ያዋለው ››Surveillance system for attacks on health care››(SSA) በተሰኘው መተግበሪያ ላይ በኢትዮጵያ የደረሰው ጉዳትም አልተመዘገበም፡፡ ማንኛውም ሰው ወደ መተግበሪያው የኢትዮጵያን ስም ሲያስገቡ የሚመለከተው ቁጥር ዜሮ ነው፡፡ መረጃው ምንም አይነት ጉዳትም ሆነ ጥቃት የለም ይላል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የጤና ተቋማት እንዲስፋፉ እና ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ እሰራለው የሚል ድርጅት፣ እንዴት በሺዎች የሚቆጠሩ የጤና ተቋማት ሲወድሙ፣ የመድሃነት መጋዘኖች ተዘርፈው ከጥቅም ውጭ ሲሆኑ ዝም አለ? እንዴትስ ማውገዝ ተሳነው? ጉዳቱስ እንዴት ሳይመዘገብ ቀረ ? ሊሆን ይችላል ? ብሎ መጠየቅ ደግሞ የጤናማ ሰው ተግባር ነው፡፡
መልሱ በጋራ ከሚሰሯቸው የዛሬዎቹ መሰል ድራማዎች ውስጥ በጉልህ ይታያል። ለእኔ ካለጥርጥር ሆን ተብሎ የእብሪተኛና አሸባሪን ቡድን ኢ ሰብአዊ ተግባራትን ለማድበስበስ የተሴረ ሴራ ነው፡፡ ምክንያቱም ደግሞ ዓለም አቀፉን ድርጅት የሚመራው ሰው፣ የጤና ተቋማቱን ባወደሙት አሸባሪዎች ወገን መሆኑ ነው፡፡
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ የቀድሞ የውጭ ጉዳይና የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ለመሆን ተወዳድረው እ.ኤ.አ. ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ከተማ በተካሄደው ጉባዔ የእንግሊዙን ተፎካካሪያቸውን ዶክተር ዴቪድ ነባሮንና የፓኪስታኗን የልብ ሐኪም ዶክተር ሳኒያ ኒሽታርን በመብለጥ የድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል፡፡
ሰውየው ዓለም አቀፉን ተቋም እንዲመሩም ከዓመት ያላነሰ ጊዜ የወሰደ፥ በመንግሥት የታገዘ ሰፊ የምረጡኝ ቅስቀሳ የተደረገላቸው ሲሆን መላ ኢትዮጵያውያን በሚባል መልኩም ድጋፋቸውን ሳይሰስቱ ሰጥተዋቸው እንደነበርም አይዘነጋም፡፡
የዓለም ጤና ድርጅትም የባለሙያነት ስነምግባርና መርህ አንጻር ማንኛውም ሰራተኛ በምንም መንገድ በአንድ ሃገር የፖለቲካ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት አይችልም፡፡ መሪውም ከዓለም ጤና ድርጅት ጥቅም ውጪ የሌላ አካል ጥቅም ለማስጠበቅ በምንም መልኩ መንቀሳቀስ አይፈቀድለትም፡፡
ይሑንና የትግራይ ክልል ተወላጁ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ለመላው የዓለም ህዝብ ወኪል በመሆን የዓለም ጤና ድርጅትን በዋና ዳይሬክተርነት እያገለገሉ ቢሆንም ህግና ስነምግባርን ባልጠበቀ መልኩ ለአንድ በአሸባሪነት ለተፈረጀ ቡድን ሽፋን ለመስጠት ሲንቀሳቀስ ስንታዘብ ቆይቷል፡፡
ከሀኪም ይልቅ ፖለቲከኛ የሆኑት ሰው፣ የዓለም አቀፍ ተልዕኮ ዕድልን ተጠቅሞ የሕወሓትን ጁንታን ለመርዳት ሲያደርጉ የሚታየው ጥረት እንደ አንድ የዓለም ዓቀፍ ድርጅት መሪ ሳይሆን ወገንተኛነት የተጫነው የአንድ ቡድን አክቲቪስት መምሰል ከጀመረም ውሎ አድሯል።
በዚህ ተግባራቸውም በመንግስት ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለማሳደር የቡድኑን ጥፋት ለመሸፋፈንና ነፍስ ዘርቶ እንዲመጣ ለመደገፍ ሲፍጨረጨሩ ታዝበናቸዋል፡፡ ለዚህም ሰውየው ባለፉት አንድ አመት በግል የማህበራዊ ገጻቸው ላይ የሽብር ቡድኑን የሚደግፍና በትክክልም የቡድኑ አባልና ደጋፊ ስለመሆናቸው የሚያረጋግጡና የኢትዮጵያን መንግስት ለመወንጀል የተቀመሩ መልዕክቶችን በተደጋጋሚ ማጋራታቸውን በቂ ምስክር ይሆናል፡፡
በጣም የሚያስገርመው ደግሞ ሰውየው ትግራይ ክልል ሲሆን ሁሌም ያሳስባቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም‹‹ሰዎች በረሃብ ምክንያት እየሞቱ ነው፤ የጤና አገልግሎት ተቋማት ወድመዋል፥ አስገድዶ የመድፈር አድራጎት በብዛት እየተፈጸመ ነው ሲሉ አድምጠናል።
በትግራይ ክልል በርካቶችም እየሞቱና አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የሚነግሩን ሰው፣ የሽብር ቡድኑ ባለፉት ወራት በወረራ ይዟቸው በቆያቸው የአፋርና የአማራ ክልል ስለፈጸመው ኢ ሰብአዊ ድርጊትና ድርጊቱ ስለተፈፀመባቸው ንፁኃን ትንፍሽ አይሉም፡፡
በሚያሳዝን በሚያሳፍርና በሚያስቆጣ መልኩ በሽብር ቡድኑ አባላት ንፁሃን ዜጎች ሲገደል፣ ሲደፈርና የጤና ተቋማት እንዳልነበር ሲወድሙ አይተው እንዳላየ ሰምተው እንዳልሰማ ከመሆን ሌላ ድርጊቱን እንኳን ለመኮነን አልደፈሩም፡፡ አደባባይ ወጥተው መኮነን ቀርቶ በማህበራዊ ገፃቸው ላይ አንድ መስመር አላሰፈሩም፡፡
ከዓለም አቀፍ መስፈርት አንጻር ደረጃቸውን ያልጠበቁና ደካማ የጤና አገልግሎት ባሉባት ኢትዮጵያ በእብሪተኛው ቡድን ለኅብረተሰቡ የጤና አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት ላይ የተፈጸመው ዘረፋ፣ ውድመትና ጉዳት በ‹‹የኤስ ኤስ ኤ››ው መረጃ ላይ አለመታየቱም ቡድኑን አሳልፎ ላለመስጠት የሚደረግ ድጋፍ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡
የሽብር ቡድኑና አፍቃሪ ደጋፊዎቹ መሰል ሴራ በብዙ መስዋዕትነትና የታሪክ ውጣ ውረድ የተገነባችውን ኢትዮጵያ ለማዳከምና ለማፍረስ ታሳቢ የተደረጉ ቢሆንም ውጤታቸው ግን እንደሚታሰበው አልሆነም፡፡ መሰል ሴራም ኢትዮጵያን አንገዳገዳት እንጂ ፈፅሞ ሊጥላት አይችልም፡፡
በአሁን ወቅት የኢትዮጵያ ልጆች ግን የሽብር ቡድኑን በጋራ ክንድ በወረራ ከያዛቸው ቦታዎች አባረው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ግብአተ መሬቱን ሊያስፈፅሙ ከጫፍ ደርሰዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የወደሙ ጤና ተቋማትን ዳግም ለማደራጀት ቆርጠው ተነስተዋል፡፡ ‹‹ጋን በጠጠር›› እንዲሉ ተቋማቱ ወደ ቀድሞ ስራቸው ሙሉ በሙሉ እስኪመለሱ ሁሉም በየፊናው ከገንዘብ ጀምሮም የተለያዩ መድኃኒቶች፤ የጤና መሳሪያዎችን ካለው ላይ ማካፈሉን ቀጥሎበታል፡፡
የወቅቱ የድርጅቱ መሪም የቡድኑን ግብአተ መሬት አፈፃፀም በቅርቡ እንደሚመለከቱት ጥርጥር የለኝም፡፡ በድርጅት ውስጥ የሥነ ምግባር ጉድለት፣ ማጭበርበር፣ ጾታዊ ጥቃትና የሙያ ደረጃዎችን ያልጠበቁ አሰራሮች በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩ መምጣታቸውን ተከትሎ ሰውየው ዳግም የመመረጡ ሁኔታ ብዙም ውሀ የሚያነሳ አይሆንም።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 19 ቀን 2014 ዓ.ም