አሸባሪው ሕወሓት ጦርነት ከፍቶ እናት አገሩን ቁም ስቅል ከማሳየቱም በላይ በተለይም መሰረተ ልማቶችን የትምህርት ተቋማትን የህክምና ተቋማትን ሆን ብሎ ለማውደም ሰፊ ስራ ሰርቷል። በብዙ ድካም በአገር ሀብት የተገነቡ ተቋማት እንዳልነበር አንዲሆኑ አድርጓቸዋል። በተለይም የትውልድ መቅረጫ የነገ አገር ተረካቢ ማፍሪያ በሆኑ ትምህርት ቤቶች ላይ የደረሰው ውድመት በጣም አሳዛኝ ከመሆኑም በላይ የቡድኑን አረመኔያዊ ባህርይ ቁልጭ አደርጎም ያሳየ ሆኗል። እኛም በትምህርት ሚኒስቴር ከከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ከዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ጋር በደረሱት ውድመቶች ዙሪያ ቃለ ምልልስ አድርገናል።
አዲስ ዘመን ፦ በአሸባሪው ሕወሓት ተግባር በአፋርና አማራ ክልሎች በትምህርት ተቋማት ላይ የደረሰው ውድመት እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር ሳሙኤል፦ አገር በዚህ አሸባሪ ቡድን ቆስቋሽነት በገባችበት ጦርነት በርካታ ጉዳቶች ደርሰዋል፤ በዚህም በጦርነቱ ቀጥታ የተሳተፉ የጸጥታ መዋቅሮቻችን እንዲሁም በኢኮኖሚያችን ላይ ከፍ ያለ ጉዳት ተመዝግቧል። ይህ ደግሞ በማህበራዊ ዘርፉ ላይም ያደረሰው ጉዳት ቀላል የማይባል ነው።
በማህበራዊ ዘርፍ ጉዳት በመድረሱ ምክንያት የትምህርት ተቋማት የመጀመሪያው ተጠቂ ሆነዋል። አሁን ብቻም ሳይሆን በመጀመሪያው የህግ ማስከበር ዘመቻ ጊዜም ቢሆን በትግራይ ክልል ባሉ የትምህርት ተቋማት ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል። ይህንንም መንግሥት በተለይም የህግ ማስከበር ዘመቻውን ካጠናቀቀ በኋላ እንደ አገር በርካታ መዋዕለንዋይ በመመደብና ክልሉ የአገራችን አንዱ ክፍል ነው በማለት ብዙ ስራዎች ተሰርተው ህዝቡም ወደተረጋጋ ኑሮው እንዲመለስና ተማሪውም እንዲማር በጤናው ዘርፍ ያለው መሰረተ ልማትም ተስተካክሎ ስራ እንዲጀምር ማህበራዊ ግልጋሎቶች እንዲሰጡ ብዙ ጥረት አድርጓል። በመንግሥት በኩልም ተደጋግሞ እንደተገለጸው ከጥቅምት 23 ቀን 2013 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓም ድረስም መቶ ቢሊየን ብር ከመንግሥት ወጪ ሆኗል። ይህ የጥፋት ቡድን ባይኖርና ገንዘቡም ልማት ቢሰራበት ኖሮ አገር ምን ያህል አትራፊ ትሆን እንደነበር ማሰብ ይቻላል ።
ይህ የጥፋት ቡድን ጦርነቱን በለኮሰበት አካባቢ ተከልሎ አልቀረም፡፡ በተለይም መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ማድረጉን ተከተሎ እንደ ድክመትና ፍርሃት በመውሰድ የሽብር ጥቃቱን ወደ አማራና አፋር ክልሎች አስፋፍቶ በሂደት ደግሞ መላ ኢትዮጵያን እናፈርሳታለን ብሎ ስትራቴጂካዊና ታሪካዊ ጠላቶቻችን አላማ የነበረውን ኢትዮጵያን ማሳነስ ማኮሰስ ላይ ለተጠመዱት ኃይሎች ጓንት ሆኖ ማገልገል ጀምሯል። ችግሩም እየከፋ ሲመጣ ሁሉም በየአካባቢው ራሱን እንዲጠብቅ መከላከያን እንዲያጠናክርና የቻለም ወደ ግንባር በመዝመት አገርን እንዲታደግ የህልውና ዘመቻ ታውጇል። በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ ብዙ ጉዳዮችን እንደ አገር ተገንዝበናል።
አሸባሪው ቡድን ኢትዮጵያን ማዳከም የሚል አጀንዳ ስላለው እስከ አሁን የተለፋባቸውን መሰረተ ልማቶችና ተቋማት በሙሉ ያለምንም ርህራሄና ሀዘኔታ ጉዳት አድርሶባቸዋል። የትምህርት ተቋማቶቻችን በዚህ ጦርነት የጉዳት ሰለባ ሆነዋል።
እንግዲህ እንደ አገር የደረሰውን ውድመት የሚያጣራ ግብረ ሀይል ተቋቁሟል፡፡ ነገር ግን ትምህርት ተቋማትን በተመለከተ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በአጠቃላይ በትምህርት ሴክተሩ ላይ የደረሰብን ጉዳት ለማየት በአካል ቦታው ላይ ተገኝተናል። በአማራና ክልል ደቡብ ጎንደር፣ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ሰሜን ወሎ እንዲሁም በአፋር ካዛጊስታና ጭፍራ ግንባር ሄደን ባየነው ወደ 846 ተቋማት ከሞላ ጎደል መልሰው ተቋም መሆን በማይችሉበት ደረጃ ወድመዋል ። 4ሺ 500 ተቋማት ደግሞ መሰረታዊ የሚባል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በአጠቃላይ ትምህርት ቤት ብቻ እንኳን 6 ሺ በላይ የሚሆኑ ተቋማት ችግር ውስጥ ገብተዋል። ይህ ለአገር ትልቅ ጉዳት ነው። እነዚህ የትምህርት ተቋማት በማጣታችን ልጆቻችንን ማስተማር አንችልም፤ ተቋማቱ በመጎዳታቸው ለመልሶ ግንባታ የሚውል በርካታ ገንዘብ ያስፈልጋል፤ የትምህርት ስራ በመቋረጡ ህይወታቸው የሚጎዳ የህብረተሰብ ክፍሎች አሉ፤ ከመቶ 50 ሺ የማያንሱ መምህራን በዚህ ምክንያት በቀጥታም በተዘዋዋሪም ተጎጂ ሆነዋል፤ ስራቸው ተስተጓጉሏል፤ ህይወታቸው ተናግቷል።
በቀጥታ በጦርነት መጎዳት ብቻ ሳይሆን ጦርነቱ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች ላይ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በጦርነቱ የተፈናቀሉ ወገኖች ማረፊያ ለመሆን ተገደዋል። ከዚህ ከዚህ አንጻር የትምህርት ሴክተሩ ሰፊ ጉዳት ደርሶበታል። 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ተማሪ በቀጥታ ከጦርነቱ ጋር በተገናኘ ከትምህርታቸው ተስተጓጉለዋል። ይህ አጠቃላይ ውድመቱ በሁለቱም ክልሎች ላይ እየተሰራ ሲሆን በዚህም ምን ያህል ቢሊየን ያስፈልገናል የሚለው እየተጠና ነው።
እነዚህ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚደርሱ ተማሪዎች እንዴት አድርገን ነው በአነስተኛ ሁኔታም ቢሆን ትምህርት የምናስጀምራቸው የሚለው ነገርም አብሮ እየተሰራ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይስ የደረሰው ውድመት ምን ይመስላል?
ዶክተር ሳሙኤል ፦ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይም ያለው ነገር ተመሳሳይ ነው። በአማራ ክልል ባሉ የወልዲያ የወሎና መቅደላ አምባ አንደኛው ካምፓስ ላይ ሰፊ ጉዳት ደርሷል። ጉዳቱ የሚዘገንን ነው ። ማንኛውም ጥሩ ስነ ጽሁፍ ጸሃፊ በቦታው ያለውን ነገር በብዕሮቹ መግለጽ የሚችል አይመስለኝም። ለመግለጽም የሚበቃ ስሜት የለም። እኛም በቦታው ተገኝተን ባየነው እጅግ አዝነናል። በተለይም እኛ በትምህርት ዘርፉ ላይ የቆየን ከተቋማቱ ጋር ቅርብ ግንኙነት ያለን ሰዎች እነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች የዛሬ ስድስትና ሰባት ወር ምን ይመስሉ እንደነበር የምናውቅ እዚህ ለማድረስ ምን ያህል ሀብት እንደፈሰሰባቸው ለምንረዳ ሁኔታው በጣም ልብ የሚሰብር ነው።
መዝረፍ ለሕወሓት አዲስ ጉዳይ አይደለም፤ ማበላሸትም ባህርይው ነው፤ነገር ግን ጥግ የደረሰውን ክፋቱን እንድናይ ነው ያደረገን። መጫን የሚችሉትን ነገሮች በሙሉ ጭነዋል፤ መጫን የማይችሉ ሲሆን እንዴት አድርገው እንዳበላሹት ስናይ በጣም ይገርማል ያማል፤ ለመውሰድ የተመቻቸውን ኮምፒውተር ከጫኑ በኋላ መጫን ያልፈለጉትን ደግሞ በመደዳ ስክሪናቸውን ሀርድ ዲስካቸውን ሶኬቶችን ተጨማሪ ሀይል እየለቀቁ እንዴት እንዳቃጠሉት ብታዩ ይዘገንናል። ተቋማቱ መልሰው አገልግሎት እንዳይሰጡ የማድረግ ስራ ተሰርቶባቸዋል።
በእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ተማሪዎቻችንን ወደሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ለመመደብ ተገደናል። ይህ እንዳለ ሆኖ እነዚህ ተቋማት በአጭር ጊዜ አንሰራርተው ወደቀደመ ስራቸው ይመለሳሉ የሚለውን ደግሞ እየሰራን እንገኛለን። በጠቅላላው የደረሰብን ጉዳት ልብ የሚሰብር ነው፤ ነገር ግን ለጠላቶቻችን የምናደርገውን ነገር እናሳያቸዋለን።
የውጪዎቹን ኃይሎች ኢትዮጵያን ማፍረስ አትችሉም ብለን አሳይተናቸዋል፤ ጓንታቸው ሕወሓትም በቂ ቅጥቀጣ ደርሶበታል፡፡ የውጭ ጠላቶቻችን ደግሞ በያዙት ጓንት አገራችንን እሳት ውስጥ ለመክተት ያደረጉት ጥረት አልተሳካላቸውም። ይህንንም አሳይተናቸዋል። ቀጥለን ደግሞ እነሱ ያፈረሷት ኢትዮጵያ እንዴት የተሻለች እንደምትሆን እናሳያቸዋለን። አሸባሪው ሕወሓት መሰረተ ልማቶችን ማፍረሱ የእሱን የክፋት ጥግ ሲያሳይ ለእኛ ግን የጥንካሬ ምንጭ ሆኖናል።
አዲስ ዘመን ፦አሸባሪው ሕወሓት ባለፉት 27 ዓመታት አገር በሚያፈርስ የትምህርት ፖሊሲ አገርን ሲጎዳ መቆየቱ ሳያንስ አሁንም ትምህርት ቤቶች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ውድመት መፈጸሙ ምን ያሳያል?
ዶክተር ሳሙኤል፦ እንደ ሕወሓት ያለ ድርጅት በቅርበት የእርሱን ታሪክ ለተከታተሉ ለጻፉ ላነበቡ ሰዎች እያንዳንዱ እርምጃው መሰረታዊ ተፈጥሮውን ያሳየበት ነው። ሕወሓት ትግራይን ነጻ አወጣለሁ ብሎ በታገለበት ወቅትም ሆነ የዓለም ሁኔታዎች ተመቻችተውለት አገር ሲመራ በቆየበት ጊዜ ቀጥሎም ለውጥን ፍቅርን ይቅርታን ሰላምን ተጠይፎ ሲወጣ ከዛ ደግሞ አስገድዶን ወደጦርነት ሲያስገባን በተለይም የቀደመ ባህርይውን ለሚያውቅ ሰው እያደረገ ያለው ነገር በትክክል ባህርይውን የሚገልጽ ነው። ዋናው ግቡ አንድ ነው፤ ይህም ጠንካራ ኢትዮጵያ እንዳትኖር ከሚፈልጉ ኃይሎች አጋር አብሮ መስራት ።
ኢትዮጵያን እንዴት ማሳነስ ማኮሰስ መከፋፈል ይቻላል የሚለው ቅመም ያለው እርሱ ጋር ነው። የመጀመሪያው ጉዳይ ከቻለ ከሁላችንም ልብ ኢትዮጵያዊነትን ማጥፋት ፣ ኢትዮጵያዊነት የቆመበትን እሴት ማጥፋት ወግ ባህል ታሪካችንን ማደብዘዝና በታሪካችን እንኳን እንዳንስማማ ማድረግ ነው።
ታሪክን አጣሞ በማቅረብም እርስ በእርስ የማይስማማና የሚጠራጠር ማህበረሰብ መፍጠር ነበር ዓላማው በዚህም ባንዲራችንን ስናይ ልባችንን ትርክክ የሚያደርገንን ስሜት ማጥፋት። መስረቅ፣ መዋሸት ገድሎ አብሮ መፈለግ ለሕወሓት መደበኛ ስራው ነበር። ይህ ከኢትዮጵያዊነት እሴት እንድንወጣ የሚያደረገው ጥረት አካል ነው። የአገርን መሰረተ ልማት አያይዘውም አገርን አንድ የሚያደርገው አገር ላይ መቆም ነው ይህንን መሸርሸር ደግሞ ከ 47 ዓመት በፊት ጀምሮ የሰራው ስራ ነው።
ለዚህ እንዲረዳው ደግሞ ጊዜ የሰጠውን የፖለቲካና የሀብት ስልጣን ተጠቅሞ የህዝቡን ማንነት ማጥፋት ነው፡፡ ከዛ ቀጥሎ አገር ደሃ እንድትሆን መሰረተ ልማት ማውደም ነው። ነገር ግን እሴታችን ኢትዮጵያዊነታችንና ቁርጠኝነታችን ካለ ተባብረን አንድ እንሆናለን፤ የጠፋብንን ሁሉ እናገኘዋለን።
በሌላ በኩልም በስልጣን ዘመኑ የሰጠን የትምህርት ስርዓት ትውልዱን እንዳያስብ እንዳያሰላስል እንዳይጠይቅ ታሪኩን እንዳያውቅ ኢትዮጵያ ከልቡ እንድትጠፋ ስሜት የሌለው ለታላቅ ለሃይማኖት ለባህል ክብር የሌለው ንቅል ማህበረሰብ መፍጠር ነበር፤ በሙሉ አድርጎታል። በነገራችን ላይ ይህንን ያደረጉት በትምህርት ቤቶቻችን ብቻ ሳይሆን በሃይማኖት ተቋማቶቻችን በባህል የምንዳኝባቸው አካባቢዎች ላይ ሁሉ ነው፤ ባህላዊ እሴቶቻችንን ተክተው ፍትህ የሚሰጡንን የፍትህ ተቋማት እንዲዳከሙ አድርገዋል።
ትምህርት ምን ያደርጋል የሚል ስሜት እንዲፈጠር 17 ዓመት ተምሮ ስራ አጥ ወይንም የሚያገኘው ደመወዝ ለኑሮ የማይበቃው እንዲሆን፤ ነገር ግን ምንም ሳይማር እነሱን የተጠጋ በስድስት ወር ሚሊየነር ሲሆን የሚታይባት አገር ፈጥረው ዜጎች ትምህርትን እንዲጠራጠሩ መማር ደግሞ ምን ያደርጋል እንዲሉ መስረቅ ትክክል እንደሆነ መማር ስህተት ብሎም ድህነት እንደሆነ እንዲያስቡ አድርገዋል።
እርስ በእርሳችን እንዳንከባበር ታናሽ ታላቁን እንዳያከብር መምህራን በተማሪዎቻቸው እንዳይከበሩ ከዛ ይልቅ ግምገማ የሚባል ስርዓት ዘርግቶ በተማሪዎቻቸው እንዲዋረዱ እርስ በእርሳቸው እንዲቃረኑ አድርጎን ቆይቷል።
እነሱ ብቻ ያሉት እንዲሰማ የሚጠይቃቸው አሰላስሎ ይህ ለምን ሆነ ይህ እንዲህ መሆን ነው ያለበት የሚል ትውልድ እንዳይፈጠር ትምህርት ስርዓቱን የማበላሸት ስራ ከመስራታቸውም በላይ ትምህርት አዳርሰናል ለሚል ታርጋ ብቻ መጸዳጃ ቤት እንኳን በአግባቡ የሌላቸውን ትምህርት ቤቶች በየሰፈሩ ተክለው ትውልድ የማምከን ስራ መስራት ላይ ተጠምደው ነበር። መምህርን ዋጋ ማሳጣት በዚህ ምክንያት ደግሞ መምህራን ትውልድ ማፍራት ላይ ውጤታማ እንዳይሆኑ ማድረግ ሲሰሩበት የቆዩት አገርን ማኮላሻ መንገዳቸው ነበር።
የቀየሱት ስርዓተ ትምህርት ራሱ በአስራ አምስትና አስራ ስደስት ዓመት ሰው ከትምህርት የሚለያይ ለጥቂቶች ጥራት ያለው ለብዙሀኑ ግን ውድመት የሚያስከትል ትምህርት መስጠት ነው የያዙት፤ አሁን ላይ ይህንን ቆም ብሎ ለሚያሰላስልና ለመፍትሔው ለሚሰራ ሰው ትልቅ መንገድ ከመሆኑም በላይ አሁን ለሚሰራው የማስተካከያ ስራ ጥሩ ግብዓት ይሆነናል።
የፈረሱ የትምህርት ተቋሞቻችንን መገንባት አንድ ጉዳይ ነው፤ በተጓዳኝ ግን ትምህርት ዘርፉ ሰው የሚወጣበት የተማረውም እንደ ሰው ተከብሮ የሚኖርበት ኢትዮጵያን እንደ አገር ብቻ ሳይሆን ተሰውቶ የሚያኖሯት የሚያቆያት ተማሪ የሚፈራበት ስርዓት ማበጀት ያስፈልጋል። እስከ አሁን የተሰሩትን ሴራዎች ደባዎች እስከ አሁን የመጣንበት መንገድም እነሱ በቀየሱልን የጥፋት መንገድ ነበር፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ጠባቂ አምላክ ስላላት ምኞቱ ሁሉ አልተሳካም። ኢትዮጵያን የተሻለች አገር አድርጎ ለመገንባት አሁን ላይ ጥሩ እድል አለን።
አዲስ ዘመን ፦ይህ ጥቃት በገንዘብ ሲተመን ምን ያህል ይሆናል? እንደ አገርስ የሚፈጥረው ተጽዕኖ እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር ሳሙኤል ፦ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም በራሱ ውድ ስለሆነ እያንዳንዱ መሰረተ ልማት በጣም በውድ ወጪ ስለተሰራ ውድመቱም በዛው ልክ ብዙ ነው። ከላይ ያነሳኋቸውን የወልዲያ የወሎና መቅደላ አምባ አንዱ ካምፓስ ብናይ ወሎ 14 ዓመት ሀብት ፈሶበታል፤ ወልዲያ ከ10 ዓመት በላይ መቅደላ አምባ ከ6 ዓመት በላይ የፌዴራል መንግሥቱ 35 ቢሊየን ብር ወጥቶባቸዋል። አሁን የሚያስፈልገን ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ብቻ ወደ 19 ቢሊየን ብር ነው። ሌሎቹ በቅርቡ ነጻ የወጡትን እነዋግና ሰቆጣን ትተን 10 ቢሊየን ብር በላይ ለመልሶ ግንባታ ያስፈልጋል ። በአፋር ክልል ወደ 1ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ያስፈልጋል ። ይህ የምነግርሽ ገንዘብ ትናንት በተገዛበት እንጂ ዛሬ ላይ ባለው የገበያ ሁኔታ አይደለም። በመሆኑም ከዚህ ብዙ እጥፍ የሚሆን ሀብት እንደሚያስፈልገን ግልጽ ነው።
ይህ በገንዘብ ሲተመን ነው፤ ተቋማቱ ስራ ላይ አለመሆናቸው ደግሞ ተጨማሪ ጫናን ይፈጥራል። ይህም ሲባል በእነዚህ ዩኒቨርሲዎች ውስጥ ይማሩ የነበሩ ተማሪዎችን ወደሌላ ስንበትን መጨናነቅ ይፈጠራል። ቀጣዩ ትውልድ ሊማርባቸው የሚችሉ ተቋማት እድል እየጠበበ እንዲሄድ ያደርጋል።
በአማራ ክልል ያሉ ሁለት ተኩል ዩኒቨርሲዎችና በትግራይ ክልል ያሉ አራት ዩኒቨርሲቲዎች ወደስራ እስከሚመለሱ ድረሰ በነዚህ 6 እና 7 ተቋማት ሊማሩ የሚችሉ ተማሪዎች እድል የጠበበ ይሆናል።
በእነዚህ ተቋማት ሰርተው ሀብት ማፍራት የሚችሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ስራ እናሳጣቸዋለን፤ በተቋሙ ዙሪያ ለትምህርት ማህበረሰቡ የተለያዩ ግልጋሎቶችን በመስጠት የእለት ኑሯቸውን ይገፉ የነበሩ ዜጎችንም በሙሉ እንጎዳለን። ይህ ብቻ አይደለም ችግሩ አገር ለሌላ የመሰረተ ልማትና ስራዋ ልታውለው የምትችለውን ሀብት ወደነዚህ የመልሶ ግንባታ ስራዎች በማዋሏ እንደ አገር ድህነት ውስጥ የምንቆይበትን ጊዜ ያረዝምብናል።
ሕወሓት የደከመች አገር ሲጠሩት አቤት ሲልኩት ወዴት የሚል ታዛዥ የሆነ መንግሥት እንዲኖር ነው የሚፈልገው፤ ይህንን ግን ኢትዮጵያውያን ተባብረው እምቢ ማለት መቻል አለብን። የተጎዱትን መልሰን እናቋቁማለን፡፡ በሌሎች መስኮች ደግሞ ጠንክረን ሰርተን ጠላቶቻችንን ዓላማችሁ መቼም ግብ አይመታም ብለን ማሳየት ይኖርብናል።
አዲስ ዘመን ፦እነዚህን የወደሙ ተቋማት መልሶ መገንባት የቀጣይ የቤት ስራችን ነው፤ ነገር ግን ከማን ምን ይጠበቃል ? ጦርነት ያልነበረባቸው ክልሎችስ በዚህ ላይ ሚናቸው ምን ሊሆን ይገባል ይላሉ?
ዶክተር ሳሙኤል፦ ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት በተመለከተ ሁለት ነገሮችን ይዘን ነው የምንሰራው፡፡ አንዱ ዘላቂ መልሶ መገንባት ሲሆን ሌላው ደግሞ ጊዜያዊ በሆነ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ነው። በጊዜያዊነት ያሉ የትምህርት ተቋማት በሴክተሩ ያሉ ሁሉ ተደጋግፈው እነዚህ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህ ላይ ደግም ባለፉት ጊዜያት ያሳየነው አጋርነት ይህንን ነገር ማድረግ እንደምንችል ምልክት የሰጠም ነው። በዘላቂነት ግን የምንገነባቸው ተቋማት የተሻሉ ሆነው እንዲገነቡ ይደረጋል። ለምሳሌ አሁን ከፈረሱት ውስጥ አንዳንዶቹ ለትምህርት ተቋምነት አይሆኑም ነበር፤ መልሰን ስንገነባ ሀብት ጊዜ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ነገርግን የነገዋን ኢትዮጵያ የሚመጥኑና የሚመስሉ ተቋማት መስራት አለብን ።
በሌላ በኩል ደግሞ ጠላቶቻችን ያሰቡልን የማነስ የመኮሰስ የመድቀቅ ሁኔታ መቼም እንደማይሳካ ማሳየት ይኖርብናል። በአጭር ጊዜ በሴክተሩ ውስጥ ያሉ የአንደኛ ደረጃም ሆነ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተቋማት ዩኒቨርሲቲዎችም ለመሰሎቻቸው ካላቸው ላይ አካፍለው እነዚህ ጉዳት የደረሰባቸው ተቋማት ወደስራ እንዲገቡ ማድረግ ያስፈልጋል። በዘላቂነት ግን የተሻሉ ተቋማትን ገንብተን እንድናሳይ የንግዱ ማህበረሰብ ህዝቡ እንዲሁም የልማት አጋሮችና ሌላውም ተባብሮ የተሻሉ ተቋማተን ገንብተን ሕወሓትና ሌሎችን ያሰቡት አገራችንን የማሳነስና የማኮሰስ ጉዳይ እንዳልተሳካ ማሳየት ይገባል። ይህንን በእርግጠኝነት እናደርገዋለን።
አዲስ ዘመን ፦ ይህ ውድመት በትምህርት ማህበረሰቡ በወላጆች በተማሪዎች ላይ የፈጠረው ስነ ልቦናዊ ጫና እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር ሳሙኤል፦ ህብረተሰቡ የስነ ልቦና ጫና ላይ የሚወድቀው የትምህርት ተቋማቱ ስለወደሙ ብቻ አይደለም። ጦርነት በራሱ የአስተሳሰረንን እሴት ሁሉ ያወድማል፤ ክፉ ቀን ሲመጣ ጉልበተኛ ለመኖር ደካማውን የሚበደልበት ሁኔታ ይፈጠራል። እንዲህ እንደ አሁኑ ደግሞ ያልተገራ ባህርይ ያለው ጠላት ህጻናት ሴቶች እንዲሁም አቅመ ደካሞች ላይ የሚያደርሰው ጥፋት ሲደማመር የስነ ልቦና ጫናው ከፍተኛ ነው።
በትምህርት ተቋማት ላይ ብቻ ሳይሆን በሃይማኖት ተቋማት ላይ ሁሉ የሚያደርገው ቆሻሻ ተግባር ስነ ልቦናዊ ጫናን ያሳድራል። ይህንን ችግር እንደ አገር የተሻለ ማከሚያ ቦታዎች አሉ በኢትዮጵያ ባህል ወግና ልማድ መሰረት በመነጋገር አንዱ አንዱን በመደገፍ ከዚህ ችግር እንወጣለን። ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ጠንክረው መስራት ከቻሉ ተከታዮቻቸው ሁሉ አሁን ከደረሱበት ስነ ልቦናዊ ጫና በቀላሉ ነው የሚያገግሙት።
እናትና አባቱ ፊቱ የተገደሉት፣ የተደፈሩበት ብሎም እንደ ልጁ የሚወደው በሬው ፊቱ ላይ ታርዶ ጥቂት ተበልቶለት ለአውሬ እራት የሆነበት አርሶ አደር ቤታቸው የፈረሰባቸው ግለሰቦች መልሶ በኢኮኖሚ ማቋቋም ብቻ ሳይሆን ከገቡበት የስነ ልቦና ጫና ማውጣት ያስፈልጋል።
ለዚህ የሚሆን ደግሞ ቱባ ባህል አለን፡፡ ከቤተሰብ ከጎረቤት ጋር ከምንጠጣው ቡና ጀምረን እንደ እድር በአምልኮ ቦታ የምንሰበሰበው ሁሉ ተደማምሮ እንደ ዜጋ ደግሞ ለፈጣሪም ያለን ቦታ ሁሉ ማከሚያዎቻችን ናቸው። ተማሪዎችም በዚህ ማእቀፍ ውስጥ የሚካተቱ ቢሆንም ወደ ትምህርት ሲመለሱ ግን ቀጥታ ፊደልና ቁጥር ማስቆጠር አልያም የትምህርቱን ይዘት ማስተማር ሳይሆን ከዚህ መከራ የተሻሉ ዜጎችንም ማውጣት ላይ በትኩረት ይሰራል።
አዲስ ዘመን ፦ በጦርነቱ በትምህርት ተቋማት ከላይ በደረሰው ውድመት በአማራና በአፋር ክልሎች ላይ የመማር ማስተማር ሂደቱ ተቋርጧል፤ ይህ የተቋረጠው የትምህርት ሂደት በተያዘው ዓመት ይጀመራል? ካልሆነስ ለተማሪዎች የታሰበው ነገር ምንድን ነው?
ዶክተር ሳሙኤል፦ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የችግሩን መጠን ጠቅለል ባለ መልኩ እንዲሁም እያንዳንዷን ጉዳት በአጭር ጊዜ ትምህርት መጀመር የሚችሉ የማይችሉ የሚለውን በቅርቡ እናውቃለን። በዚህም መጠነኛ ድጋፎች ተደግፈው ወደ ስራ መግባት የሚችሉና የማይችሉትንም እንለያለን። ትምህርትን ለማስጀመርም ሌሎች አማራጮችን እንጠቀማለን።
ትምህርት ቆሞ አይጠብቅም ከትምህርት የወጣ ሰው ሌላ ህይወት ያማትራል፤ እድሜው ለስራ የደረሰው ወደ ስራ አልያም ወደስደት ሊሄድ ይችላል። በመሆኑም የተቋረጠውን የመማር ማስተማር ሂደት በአጭር ጊዜ መጀመር አለብን ብለና ። በመካከል የተቋረጡትንም ጊዜዎች ቅዳሜን እንደ ስራ ቀን ቆጥረን እንደ አካባቢው ሁኔታ ትምህርቱን እስከ አመቱ ማጠቃለያ ገፍተን ለመጨረስ እንሞክራለን። በእርግጥ ይህ ከክልል ትምህርት ቢሮዎችና ከሌሎቹም ጋር ውይይትን ይፈልጋል።
ምንም ነገር ያልተረፉ ትምህርት ቤቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ላይ ደግሞ በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ግንባታዎችን በመገንባት ድንኳኖችን በመጠቀም መስራት ሊኖርብን እንደሚችል ሁሉ እያሰብን ነው። በቅርቡም ውይይቱን አጠናቀን ወደ ስራ እንገባለን።
አዲስ ዘመን ፦ በመጨረሻም እርስዎ ማለት የሚፈልጉት ነገር ካለ፤
ዶክተር ሳሙኤል ፦ ኢትዮጵያ ያላትን አቅምና ጸጋ ያልተገነዘቡ ወደ ችግር ይልኳታል፤ ነገር ግን ስንፈተን የምናወጣው አቅም ምን እንደሚመስል አላወቁም። ከዚህ በኋላም በትምህርት ብቻ ሳይሆን በሁሉም መስክ ጠንካራ አገርን መገንባት ይኖርብናል። የእስከ አሁኑ ስብራቶቻችንን ለማከም እንዲሁም ቆም ብለን አስበን የምንወስንበትን እድልም ሰጥቶናል። አገራችን ስትነካ እንዴት አድርገን ምላሽ እንደምንሰጥ ለዓለም አሳይተናል።
የማንም እርዳታ ቢቆም የጸጥታው ምክር ቤት ደጋግሞ ቢሰበሰብ የእኛ መሪ እግራቸው ስር እንደማይወድቅ አሳይተናል። ይህንን እድል ተጠቅመን በኢኮኖሚውም በሌላውም መስክ ራሳችንን መቻል ይኖርብናል፤ ጠንካራ ኢኮኖሚ ሲኖረን የታፈረች አገር ማፍራት ስንችል ደግሞ በአግዋ በእርዳታ በብድር ማስፈራራት ይቆማል።
ጠንካራ ኢኮኖሚ ላይ የቆመ መንግሥት የጸጥታው ምክር ቤት ቢሰበሰብ ባይሰበሰብ ወዳጅ ቢበዛ ቢያንስ ብዙም ጭንቁ አይደለም፤ ምክንያቱም እጣ ፈንታችንን በራሳችን የምንወስን ህዝቦች ስለምንሆን።
ጠንካራ አገር ስንገነባ እኛን ሊገዳደሩን የሚፈልጉ ወገኖች ከአንድ ጊዜ በላይ እንዲያስቡ መልዕክት ይሆንላቸዋል።
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
ዶክተር ሳሙኤል ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
ዕፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 18 ቀን 2014 ዓ.ም