የኢፌዴሪ ህገ-መንግሥት ሩብ ምዕተ ዓመት ሊሞላው እየተንደረደረ ነው፡፡ አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብን መፍጠር ዓላማው ያደረገው ይህ የቃል ኪዳን ሰነድ ዛሬ ላይ በሁሉም ዜጎች ዘንድ ሙሉ በሙሉ ቅቡልነት ኖሮት ሲተገበር እንዳልነበር በገሃድ ታይቷል፡፡ አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብን የመፍጠር ጉዳይ ደግሞ አገር እንደ አገር የምትመራበት ህገ መንግሥት የአብዛኛውን ዜጋ ይሁንታ ሊያገኝ ይገባል፡፡ አሁን አሁን በአገራችን የሚታየው ሀቅ ግን የእሳትና የውሃ ያህል ሆኖ ይታያል፡፡
በአንድ በኩል ‹‹ህገ መንግሥት ይቀየር›› ሲባል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ህገ መንግሥቱ ይሻሻል›› የሚሉ በሁለት ጎራ የተከፈሉ ሃሳቦች በተለያየ መልክ ሲሰነዝሩ ይስተዋላል፡፡ በመሰረቱ ህገ መንግሥታችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁሉም አገራት የሚጋሯቸውን የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ሙሉ በሙሉ ብቻ ሳይሆን ቃል በቃል ገልብጦ የያዘ ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ አገራችን ኢትዮጵያ በተለየ ሁኔታ ከድህረ 1983 ዓ.ም በኋላ ከመበታተን የታደጋት ይኸው ህገ መንግሥት መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡
ስለሆነም ‹‹ህገ መንግሥቱ ይቀየር›› የሚሉት አስተሳሰብ አገር ህግ አልባ እንድትሆን ከማለም ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ የሆኖ ሆኖ ግን ህገ መንግሥት በተፈጥሮው በህብረተሰብ ንቃተ ህሊና እና ከአገር ዕድገት እኩል እየተሻሻለ እና እየዳበረ የማይሄድ ከሆነ ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን መሆኑ የዓለም ተሞክሮ ይነግረናል፡፡ ለዚህም ነው አሜሪካ ላለፉት 200 ዓመታት ለ27 ጊዜ ህገ መንግሥቷን ያሻሻለችው፡፡ ምርጥ የሚባለው የህንድ ተሞክሮ እንደሚነግረን ደግሞ አገሪቱ ባለፉት 60 ዓመታት ለ94 ጊዜ ህገ መንግሥቷን ማሻሻሏን ነው፡፡ ይህ የሚያሳየን አገራቱ ከህብረተሰባቸውና ከአገራቸው ዕድገት እኩሉ የሚያድግ/የሚዳብር ሕገ መንግሥት ይዘው መጓዛቸውን ነው፡፡ ኢትዮጵያ በ1987 ዓ.ም ያፀደቀችው ህገ መንግሥት ከወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የተሟላና ተገቢ ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ይህም ሆኖ በማፅደቁ ሂደትም ሆነ በትግበራ ሂደት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ደግሞ ከምሁራን እና ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በኩል የሚነሳው ‹‹የህገ መንግሥት ይሻሻል›› ጥያቄ ቦታ እያገኘ ነው፡፡
ይህ ጉዳይ ግን በተናጠል አቋም ከመያዝ ባለፈ ሁሉን በሚያግባባ መልኩ ተቀምሮ ለመንግሥት ቀርቦ አገራዊ ፋይዳ ባለው መልኩ አልተግባባንበትም፡፡ በመሆኑም ይህን ጉዳይ በባለሙያ ተደግፎ ሁሉን አካታች የሆነ ጥናት በማድረግ ህገ መንግሥቱ አገሪቱ አሁን ከደረሰችበት የዕድገትና የማህበረሰብ ንቃተ ህሊና ደረጃ አኳያ ሊሻሻሉ የሚገባቸውን አንቀፆች መለየት ሊቀድም ይገባል፡፡ አንቀፆቹ በጥናት ከተለዩ በኋላ በቂ እና ጥልቅ ውይይት ተደርጎ ዜጎች የሚያምኑባቸውን ጉዳዮች ነቅሶ በመያዝ አገራዊ አቋም አስይዞ መገኘት ይገባል፡፡
የመለየቱ ሥራ በበቂ ሁኔታ ከተጠናቀቀ በኋላ ቀሪው ሥራ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ያሉ ፍሬ ነገሮችን የማሻሻል ሂደት ይሆናል፡፡ ይህም ቢሆን ህገ መንግሥታዊ ሥርዓት ስላለው እሱኑ መከተል ተገቢ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው፡፡ እዚህ ላይ የማሻሻሉ ሥራ በተለይ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ እንዲከናወን ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፤ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነውና፡፡
በአጠቃላይ ህገ መንግሥቱን በሚመለከት ከተለያዩ ወገኖች የሚሰነዘሩት ሀሳቦች እንደ መብት መናገር ቢቻልም በሚገባ ሊጤኑ እንደሚገባ ግን መግባባት አለብን፡፡ መጠቆም ብቻ ሳይሆን ሃሳብን መሰንዘር ህገ መንግሥታዊ መብት ቢሆንም የምንሰነዝራቸው ሃሳቦች ግን ምን ያህል ህገ መንግሥቱን ሊንዱ እንደሚችሉ የተመዘኑ አይመስልም፡፡ ስለሆነም የሕገ መንግሥት ይቀየር ጉዳይ እና የህገ መንግሥት ይሻሻል ሃሳቦች መልዕክታቸውም ሆነ አተገባበራቸው ፍፁም ለየቅል እንደሆኑ ሊታመን ይገባል፡፡ ይሁንና ህገ መንግሥቱን ከኅብረተሰብና ከአገር ዕድገት እኩል እንዲራመድ አድርጎ ማሻሻሉ ግን ተገቢ ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 28/2011