አገር እንባ አላት።አገር ስሜት አላት።አገር ታለቅሳለች።በልጆቿ የመዳኗን ያክል ትታመማለች። የኢትዮጵያ አብዛኛው ህመሟ ደግሞ እንደ ሕወሓት ካሉ አረመኔ ቡድኖች የሚመነጭ ነው።በአመነው ህዝብ አሸሪው ሕወሓት የኢትዮጵያን ህዝብ አደራ የበላ ጅብ ነው።
በአለም የፖለቲካ ታሪክ የሚጠላትን አገር የመምራት እድል ያገኘ ብቸኛው ፓርቲ አሸባሪው ሕወሓት ነው። ቡድኑ ስር በሰደደ ፍጹም ሴይጣናዊ በሆነ የእኔነት ስሜት ተሞልቶ ለሃያ ሰባት አመታት በስልጣን በቆየባቸው አመታትም፣ ለማየት ለመስማትም ሆነ ለመንገር የሚዘገንኑ ኢ ሰብአዊ ድርጊቶችን ፈጽሟል።
ቡድኑ አገር ለመጥቀም ከተጓዘባቸው ይልቅ አገር ለማፍረስ የሄደባቸው ጎዳናዎች ረጅምና ፈጣን ናቸው። ለዚህ ደግሞ በስልጣን ቆይቶ ሲሰራቸው የቆያቸው ተግባራት ምስክር ናቸው።በታሪክ ተሰምቶ የማይታወቅ የውሸት ድራማ እየጻፈ በተላላኪዎቹ እያስተወነ በህዝቦች መካከል መለያየትን ፈጥሯል።በዚህ የማስመሰል ድራማ ውስጥ አገር አፍርሶ የራሱን ቤት ገንብቷል።በውሸት ትርክት በህዝቦች መካከል ጠብን በመፍጠር ህዝብ አለያይቶ ስልጣኑን አራዝሟል።
በህዝቦች መካከል የብሄር ግጭቶችን በማስነሳት የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ በመቀልበስ አገሪቱን ወደ ለየለት የርስ በርስ ብጥብጥ ለማስገባት ያልሰራው የፖለቲካ ሸር አልነበረም።በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ግጭቶችን በማስነሳት ሞትና የንጹሀንን እልቂት እንደ ትልቅ አላማ በመጠቀም የግል ጥቅሙን ለማስከበር ብዙ ደክሟል።
በጣም ነው የሚገርመው በአስተዳደሩ ውስጥ ኢትዮጵያ የምትባል አገር አልነበረችም። ታሪክ፣ ባህል ማንነት ስፍራ አልነበራቸውም።የኢትዮጵያንና የህዝቦቿን ጥቅምና ሉአላዊነት ለሌሎች አሳልፎ በመስጠት የግል ጥቅሙን ሲያስቀድም ነበር።
ከአገሩ ይልቅ እንደ አሜሪካ ያሉ ባዕድ አገራትን ሲጦርና ሲያገለግል የኖረ መንግሥት ነው።ዛሬ ላይ ከየአቅጣጫው የሚጮሁትም አጉራሿ፣ተላላኪዎቹ ናቸው።አንዴ ማዕቀብ አንዴ ደግሞ እርዳታ አቆማለው የሚሉትም ወዳጃቸውን ለማትረፍ ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርታ ቢያደርግለትም፣ አውሬ ነበርና ይቅርታ ሊያንፀው አልቻለም።የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ከሆኑት ግብጽና ሱዳን ጋር በማበር እንደ አይናችን ብሌን የምናየውን የህዳሴ ግድብና ሌሎች መሰረተ ልማቶቻችን ዋስትና እንዳያገኙ በማድረግ የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ሲያራምዱ እንደነበር ሁላችንም የምናስታውሰው ሀቅ ነው።በአገሪቱ ጉዳይ ላይ የአሜሪካንንና የሌሎች አገራትን ጣልቃ ገብነት በመቀበል እንዲሁም በክልሎች መካከል ጠብን በመፍጠር በዚህ ሁሉ ውስጥ ትግራይን ራስ ገዝ ለማድረግ ሴራ ሲያሴሩም እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
ባለፉት አንድ አመታት ኢትዮጵያ በሕወሓት ቡድን እንደደረሰባት ያለ አስከፊ መከራና ውርደት ደርሶባት አያውቅም። ኢትዮጵያ አገራችን በብሄር ቁርሾ ተከፋፍላ ወደለየለት የእርስ በርስ ጦርነት እንድትገባ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም። ከጎረቤት አገራት ጋር በማቃቃር የተጀመረው ለውጥ እንዲቀለበስና ወደ ጦርነት እንድንገባ ያልሰሩት የተንኮል ሥራ የለም።
ከለውጡ በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉን በትእግስት አልፈው ፊታቸውን ወደ ሰላም ሲያዞሩ፣ እጃቸቸውን ለሥራ፣ አእምሯቸውን ለልማት ባዘጋጁበት ሰአት ይባስ ብሎ ለአገር ዳር ድንበር ዘብ የቆመውን የመከላከያ ሠራዊት ከኋላ በመውጋት በአገር ላይ በይፋ ጦርነት ከፍቷል።
ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ እንደሚበለው ለዳግም ጥፋት ከግብረአበሮቹ ጋር ሆኖ ኢትዮጵያን ለመበታተንና ታሪኳን ሊያበላሽ ነፍጥ ከማንሳት አልተቆጠበም።በመሸገበት ሆኖ እንደለመደው አገር ለማፍረስና ህዝብ ለማስጨነቅ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት በመፍጨርጨር ላይ ይገኛል።
አሁን ላይ አገር ለማፍረስ ያለ የሌለ ኃይሉን እየተጠቀመ ይገኛል።ባለቀና በተሟጠጠ ተስፋ ውስጥ ሆኖ የለመደውን ትናንትና ዛሬም ሊደግመው መውተርተሩን አላቋረጠም።መንግሥት ለትግራይ ህዝብ የጽሞና ጊዜ በመስጠት ሠራዊቱን ከክልሉ ያስወጣበትንና የተኩስ አቁሙን እንደ መልካም አጋጣሚ በመቁጠር በንጹሀን ላይ ያደረሰው ጉዳት እጅግ ዘግናኝ መሆኑ በግልፅ እየተመለከትን እንገኛለን።
በአፋር፣ በአማራ ክልል የተለያዩ ቦታዎች በርካቶችን ያለርህራሄ በጅምላ ጨፍጭፏል።ንጹሀንን ገድሏል። ሴቶችን ደፍሯል።ነፍሰጡሮችን በአሰቃቂ ሁኔታ ሆዳቸውን በስለት በመቅደድ የሰው ልጅ የማይፈጽመውን አረመኔአዊ ድርጊት ፈፅማል።ሕጻናትን በአደንዛዥ እጽ እያሳበደ ወደ ጦርነት ማግዷል።
የኢትዮጵያን ህዝብ መጨፍጨር ብቻ ሳይሆን ምንም የማያውቁ እንስሳትን ሳይቀር ርህራሄ ያልፈጠረበት ነው። በስልጣን ዘመኑ የተወዳጃቸውና ከእጁ የበሉ የሰይጣን ቁራጭ የክፋት ወዳጆቹም ተግባሩን ከመኮነን ይልቅ አብረውት አይዞህ እያሉት ናቸው።
አሸባሪ ሕወሓት ዘመኑን ሙሉ አገርና ህዝብ ገሎ ለራሱና ለጥቂት ወዳጆቹ ብቻ የኖረ ከሆድ ሌላ አእምሮ የሌለው ቡድን ነው።ከትናንት እስከዛሬ የተጓዘባቸው ጎዳናዎች ከጥፋት ባለፈ ልማት ያልነበረባቸው ነበሩ።ቡድኑ ትናንት ለኢትዮጵያ አልጠቀመም ዛሬም ወደ ፊትም አይጠቅምም።
ትናንትም ዛሬም በአሸባሪው ሕወሓት ልብ ውስጥ ኢትዮጵያ የለችም። ብቸኛ ደስታው እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አይነት ነበር።.አሁንም ይሄው ነው። ሕወሓት ከትናንት እስከ ዛሬ ኢትዮጵያን የሚያስለቅስ አረመኔ ቡድን ነው። ይህን ጠንቅቆ የተረዳው የኢትዮጵያ ህዝብም የቡድኑን ግብአተ መሬት ለማፋጠን ሆ ብሎ ተነስቷል። ቡድኑን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድም የገባበት እየገባ እያንኮታኮተው ይገኛል።
በኢትዮጵያውያን የጋራ ተጋድሎ አስከፊ ሽንፈት የደረሰበት አሸበሪው ሕወሓት በአንጻሩ እንደትናንቱ ሁሉ ይሄው ዛሬም ድረስ በንጹሀን እንባና ደም እየነገደ ይገኛል።ዛሬም ድረስ በለመደው ውሸትና ማስመሰል ህዝብ ያጭበረብራል።ውሸቱ አያልቅም…አንድ ጊዜ አዲስ አበባ ልገባ ነው፣ ሌላ ጊዜ ስልታዊ ማፈግፈግ አድርጌአለሁ እያለ ይገኛል።
ሌላ ጊዜ ደግሞ ጉዳያችን ከማዕከላዊው መንግሥት ከዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ጋር እንጂ ከአማራ ህዝብ ጋር አይደለም ሲል ያብላል። ይሄ አልሰራ ሲለው ደግሞ በሌላ ውሸት ይመጣል። በቃ ውሸት ብቻ። እኔ አገር በእውነት እንደምትመራ ያላወቀ ብቸኛው ቡድን ቢኖር አሸባሪው ሕወሓት ይመስለኛል።ብዙ የዓለም መሪዎች አገራቸውን በእውነት መርተው አርነት አውጥተዋል።
በታሪክ እንደምናውቀው ኢትዮጵያን ነክቶ በሰላም የኖረ የውጭም ሆነ የውስጥ ጠላት የለም። አብዛኞቹ በለኮሱት እሳት ተቃጥለዋል። በቆፈሩት ጉድጓድ ተቀብረዋል። ዛሬም የምናየው ከዚህ የተለየ አይደለም። ኢትዮጵያን የሚጠብቃት አይተኛም።በኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን ያነሱ ሁሉ ዳግም ላይነሱ የሚደርቁበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን በጽኑ አምናለሁ።
ኢትዮጵያ የእውነትና የፍትህ አገር ናት። ማንንም ጎድታ ራሷን መጥቀም አትሻም። ሌሎችን ጥላ መቆም አያምራትም። ይሄ የአባቶቻችን ሀቅ ነው። እኔና እናንተም በዚህ እውነት ላይ በቅለን የጸደቅን ነን። ኢትዮጵያ የሚለው ስም የፍትህ ስም ነው።
እኛ የእውነት ወዳድ የአባቶቻችን ልጆች ነን።ጥንት አባቶቻችን ጠላትን እየረቱ፣ ወረተኛን እያንበረከኩ አገራችንን ጠብቀው አቆይተውልናል። እኛም የዚህ ትውልድ ጀግኖች አገራችንን ጠብቀን ለሚመጣው ትውልድ የማስተላለፍ አደራ አለብን። በብርሃናችን ዋዜማ ላይ ከእርምጃችን ሊገታን የመጣን ማንኛውም ምድራዊ ኃይል ለመታገስ አቅሙ የለንም። ይህ የሁላችንም የጋራ እውነት እንደሆነም ጥርጥር የለውም።
መንግሥት ለአገርና ለህዝብ ቅድሚያ ሰጥቶ ለጋራ ለውጥ እየተጋ ባለበት በዚህ የመንጋት ዘመን ላይ ወደ ኋላ ሊጎትተን የሚችልን ማንኛውንም ኃይል ለመጋፈጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዝግጁ መሆኑን በተግባር ጭምር እያስመሰከረ ይገኛል።አሸባሪውን ሕወሓት ያሉ በሉአላዊነታችን ላይ የሚመጣን ኃይል እንደማይታገስም ከፍ ባለ ተጋድሎ ለዓለም በተጨባጭ እያስመሰከረ ነው።
ለዓለም ፋና ወጊ የሆነ ህዝብ ዛሬ ላይ በስልጣን ጥመኞች መከራውን ሲያይ እንደማየት የሚያበሳጭ ነገር የለም።በአሁኑ ወቅትም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከዓለም ፊት ተፈጥረን በዚህ ልክ መጎሳቆላችን ለእኛ የሚገባ አይደለም ብሏል። ይህን ታሪክ ለመለወጥ ተነስቷል።
ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ወቅት፣በተባበረ ክንድ ወደፊት የምንሄድበት መንገድ ላይ ነን።እንደ ጥንት አባቶቻችን እኛም በአንድ ላይ ቆመን ጠላቶቻችንን ድል አድርገን መከራችንን የምንሻገርበት ጊዜ ላይ ነን። ኢትዮጵያ ከፊት ለፊት የሚጠብቃት የመነሳት ዘመን አለ።የከፍታ ዘመን አለ።
እኛ በኢትዮጵያ ትንሳኤ ማግስት ላይ ቆመናል። የጠላቶቻችንን እኩይ ሃሳቦች ተረማምደን ወደዛው ለማምራት ጠላቶቻችንን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መቀወር የሚያስችል ታሪካዊ ምእራፍ ላይ ነን ። ኢትዮጵያን ወደ ፊት ለመራመድና ከነክብሯ ለማስቀጠል አሸባሪውን ሕወሓት እስከ አስተሳሰቡ ለማስወገድም የመጨረሻው ምእራፍ ላይ እንገኛለን። ያስለቀሰንን ይህንን ቡድን ግብአተ መሬት ፈጽመን ሳቃችንን የምንስቅበት ጊዜ ከመቼውም ይልቅ ቀርቧል!
አበቃሁ ቸር ሰንብቱ
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 18 ቀን 2014 ዓ.ም