የአገሬ ሰው “ያሉት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” ይላል የቃልን ኃያልነትና የከበረ ዋጋ ሲገልጽ። ቃል ዕምነት ነው፣ እዳም ነው፤ ቃል እውነትና ሕይወትም ነው። ቃል እውነትና ሕይወት እንዲሆን ግን ፍጻሜና ተግባር እንዲሁም ቁርጠኛ እንቅስቃሴና ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣትን ይፈልጋል። ቃል ሰዎችን ወደ መልካም ጎዳና የሚመራ መንገድና ምግባርን ማሳያ መስታወትም ነው። በተለይም በኃላፊነት ደረጃ ላሉ ሰዎች ደግሞ ቃል አርአያነትን መግለጫና ተከታዮችን ማፍሪያ መንገድም ነው። ቃል ከፍ ሲልም ታሪክ መጻፊያና አገርን ማበልጸጊያም እንደሆነ ማንም አይጠራጠርም።
ይህንን የምለው ያለምክንያት አይደለም። የአገራችንን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ቃልና ተግባር ስምምነት ለማሳየት ፈልጌ ነው። በቅርቡ በተደረገው አገራዊ ምርጫ በበዓለ ሲመታቸው ወቅት ያነሱትን ብቻ አስታውሰን በሕልውና ዘመቻው ላይ የፈጸሙትን ገድል እንመልከት። እነዚህ ሁለቱ ሁኑነቶች ምን ያህል የተዋሃዱና ቃልና ተግባር እንዴት እንደተሳሰሩ በግልጽ ያሳዩናልና። በበዓለ ሲመታቸው ወቅት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከታሪክ ጭምር እያጠቀሱ በንግግራቸው ተንትነውልናል፤ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ያልተገባ የውጭ ጣልቃ ገብነት የሚፈጽሙትንና ጫና ለመፍጠር የሚሞክሩትንም በምን መልኩ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አሳስበዋል። ከዚያም አልፈው ይህንን በሚያደርጉት ላይ ምን ዓይነት እርምጃ እንደሚወሰድም አንስተዋል። የሁልጊዜ ዝማሬያቸው፣ መነባንባቸውና ንግግራቸውና ህልማቸውም የኢትዮጵያን ብልጽግናን ማየት እንደሆነም አበክረው አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ብልጽግና እንዳይመጣ በሚፈልጉት ዘንድ የበዛ ጫና እንደሚኖርም ለሕዝብ አብራርተዋል። ይህም ቢሆን ግን እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ ተከፍሎም ቢሆን አገር አሸናፊ እንድትሆን ማድረግ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራ አመላክተዋል። መቼም ይህ የሁሉም ምኞት ነው ልትሉ ትችሉ ይሆናል። እውነትም አላችሁ። ተናጋሪም ሞልቶን ነበር። ተግባር አጣን እንጂ። እርሳቸም የሚለዩትም በዚህ መለኪያ ይመስለኛል። ለዚህ ደግሞ ንግግራቸው ጣፋጭ ተግባራቸውም እንዲሁ ጣፋጭ፤ ቃላቸውም በተግባር የሚገለጽ እንደሆነ በሕልውና ዘመቻው ላይ ያሳዩት ተጋድሎ በቂ ማሳያ ነው።
ከውስጥም ከውጭም በጠነከረ መልኩ የመጣውን ፈተና ወንበራቸው ላይ ተቀምጠው ድልን በመጠበቅ አይደለም የተዋጉት። ግንባር ድረስ ወርደው ከጥምር ጦሩ ጋር በመሆን በጦር ሜዳ ጭምር አመራር በመስጠት ነው የጠላትን እኩይ ዓላማ የተዋጉት። ይህን ሲያደርጉም ቃላቸውንና ኢትዮጵያዊነታቸውን ብለው እንጂ ማንም አስገድዷቸው አይደለም። እንደቀደመው የኢህአዴግ ዘመን የአሻንጉሊት መንግሥት የኢትዮጵያ ጠላት የሚጠላውን ጠልተው፣ የኢትዮጵያ ጠላት የሚደግፈውን ደግፈው ስልጣናቸውን ማቆየት ይችሉ ነበር። ነገር ግን ወርቅ የሆነውን ሕዝብ አንጥረውና አንድነቱን አምጥተው ጠላት እንዲሸማቀቅ ለማድረግ ፈለጉ። ዘምተውም ሕዝቡን አዘመቱ፤ አጠነከሩትም። ከዚያም ልቀው እኛ ኢትዮጵያውያን ነን ብለው አስባሉ፤ ጠላትንም አስጠነቀቁ፤ ደግሞም አዋረዱ።
በበዓለ ሲመታቸው ወቅት ሥልጣን ከዘርና ከጠመንጃ አፈ ሙዝ አለያም ከሴራና ከተንኮል የሚመዘዝ ሳይሆን በእውነተኛ ዲሞክራሲ በሕዝብ ድምጽ ከምርጫ ኮሮጆ ብቻ የሚመነጭ መሆኑን ተናግረው ነበር። በዚህም የሕዝብን የስልጣን ባለቤትነት እናረጋግጣለን ባሉት ልክ የትግራይን የበላይነት አረጋግጣለሁ ብሎ በአገር ላይ የመጣን ከሃዲ ባንዳ ልኩን ጦር ሜዳ ድረስ ወርደው ልኩን አሳዩት። ስልጣን ሳያሳሳቸው ነፍሳቸውን አስይዘው ጦርነት ውስጥ ገቡ፤ የተደላደለ ወንበራቸውንም ለቀው የጥምር ጦሩን ረሃብና ጥም እርዛትና ዳገት ቁልቁለት መውጣት መውረድ በተግባር አብረውት ተሰልፈው ፈተናን ተፈትነው ድሉን በጋራ አጣጣሙ።
ይህንን አድርገው የመጀመሪያ ምዕራፉን አጠናቀው ሲመለሱም “አሸባሪው ኢትዮጵያን መገዳደር ይሞከር ይሆናል፤ ተገዳድሮ ማሸነፍ ግን ትናንትም አልተቻለም፤ ዛሬም አይሆንም፤ ነገም አይቻለውም” አሉ። ምክንያቱም ሠርተው የመጡትን ስለሚያውቁ። ቀጥለውም፤ ኢትዮጵያ የሚለው ስም ሁሌም ከአሸናፊነት ጋር የሚያያዝ መሆኑን አመላክተው፤ “ከጥቂት ጊዜያት በፊት ኢትዮጵያን ሊወጋ የተነሳው ጠላትን በጋራ በመሆን ጦር ግንባር ድረስ ተዘምቶበት አንገት እንዲደፋ ሆኗል፤ ኢትዮጵያውያን ደግሞ አንገታቸውን ቀና አድርገዋል” በማለት የሕዝቡን ብሩህ ተስፋ ገለጹ።
አገራችን ታፍራና ተከብራ እንድትኖር ለማድረግ በጦር ግንባር እየተከፈለ ያለው መስዋዕትነት የኢትዮጵያን የአሸናፊነት ስም የሚመልስ መሆኑንም አበሰሩ። “ዛሬም ሆነ ወደፊት ጠላቶቻችን ጉልበታቸው ዝሎ፣ የጥላቻና የጠበኝነትን መንገድ ጥለው፣ የፍቅርና የሰላምን መንገድ እስኪመርጡ ትግላችን ይቀጥላል” በማለትም በትግሉ ውስጥ ሁሌም እንደሚኖሩ ቃላቸውን በድጋሚ ሰጡ። “ትናንት ሰይፍ ይዘንም ሆነ ሰልፍ ሰርተን ስንነሳ ዋና ጸባችን አገር ሊያፈርሱ፣ ወገንን ሊያተራምሱ፣ ወንበራቸውን ሊያደላድሉ፣ ኪሳቸውን ሊሞሉ ከተነሱ የሴራ ቁንጮዎችና ኢትዮጵያ ጠሎች ጋር ብቻ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ቃላቸውን በተግባር ለማሳየት አገርን የከዱ አመራሮቻቸውን ከሕወሓት ጋር ያበሩ አገር ሻጮችን ከጥምር ጦሩ ጋር በመሆን በእርሳቸው አመራር ሰጪነት አራግፈውታል።
ኢትዮጵያን አንገት ለማስደፋት ሲንቀሳቀሱ የነበሩትን እንደአሜሪካ ዓይነቶችንም ቢሆን ትናንት ከውጭ አጋርነት ጋር በተያያዘ የተናገሩትን ዛሬ ተግብረውታል። ይኸውም “የወዳጆቿን አጋርነት አገራችን አጥብቃ ትፈልጋለች። ይሁን እንጂ ክብርና ሉአላዊነት በሚሰዋ መልኩ መሆን የለበትም፤ ሊሆንም አይችልም” ብለው ነበርና ዛሬ ያንኑ ቃላቸውን “እረፉ!” ከሚል ማስጠንቀቂያ ጋር በተለያየ ዘመቻ በተግባር አሳይተዋል።
በበዓለ ሲመታቸው ጊዜ “የተጣለብንን አደራ ለመወጣት ያለንን ሁሉ ሳንሳሳ እንሰጣለን፤ እንቅልፍም አንተኛም፤ አንዘናጋምም” እንዳሉት እንደ አገር የተነሳው ሕዝብ ከአሁን በኋላ ወደ ኋላ የሚል እንደማይሆን ራሳቸው በተግባር ግንባር ድረስ ዘምተው አሳይተዋል።
የኢትዮጵያውያን ፍላጎት ሁሌም ሰላምና ፍቅር እንደሆነም ሆነው ያሉትን አድርገውና ሆነው አሳይተውናል። ነገሮች ያለቁና የተጠናቀቁ እስኪመስሉ ድረስ ኢትዮጵያን የማያውቁ ሁሉ በሥጋትና በፍርሐት ተውጠው ቢቆዩም፤ ሠግተው ሊያሠጉ፤ ፈርተው ሊያስፈራሩ የሞከሩ የውስጥና የውጭ አካላት ቢኖሩም ሁሌም በኢትዮጵያውያን የአሸናፊነት ምሥጢር፣ ጽናትና ተጋድሎ ድል እንደመጣ በአንደበታቸው አለመሳሳታቸውንና ሌሎችንም እንደማያሳስቱ አሳይተውበታል።
“ወደ ትግል የገባነው ሐቅን ይዘን ነውና የኢትዮጵያ አምላክ እንደወትሮው ከእኛ ጋር ነበር፤ ለዚህም ማሳያው ልባችንን አጀግኖ የኢትዮጵያን አሸናፊነት በዓይናችን አሳይቶናል። ውድቀታችንን ሲመኙ የነበሩትን ሁሉ አሳፍሮ ዳግም የኢትዮጵያን ስም በወርቅ ቀለም እንድንጽፍ አስችሎናል። ከዚህ በኋላም ማንም ተነስቶ ኢትዮጵያን ማውረድ ከማይችልበት ማማ ላይ እየሰቀልናት ነው” ያሉትም ያለምክንያት አልነበረም። በእርግጥ እርሳቸው እንደጠቆሙት ኢትዮጵያውያን በአንድ ነገር ይታወቃሉ፤ በአማኝነታቸው። እምነት ከምግባርና ከተግባር ጋር ሲሆን ደግሞ አሸናፊነት መምጣቱ ግድ ነው። ስለዚህም ጦረኛው በጦር ግንባር ላይ ሲፋለም በቤቱ ያለው በጸሎቱ ስለአገሩ ይለምናል። በቤተክርስቲያንና በመስጅድም አገሩ እንድታሸንፍ ለአምላኩ ያመለክታል።
ሕዝቡ ሁልጊዜ የአንደበቱ መክፈቻ፤ የሥራው መጀመሪያ አገሩ ናት። እርሷን እያነሳ በመሥራቱና በመጸለዩ የዛሬውን የድል ተስፋ ማየት ችሏል። “ከገጠመን ፈተና ይልቅ በዕድሎቻችን ላይ አተኩረን ከሠራን ኢትዮጵያን ኃያልና ራሷን በሁሉም መስክ የቻለች አገር እናደርጋታለን” ያሉት የግንባሩ መሪ ጠቅላይ ኢታማዦር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ ዜጋው ለአገሩ መዋደቁ ግዴታው ቢሆንም አመስግነውታል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ወዳጆች የሆኑትንም የዓለም አገራትን ከማመስገን አልተቆጠቡም። እንዲያውም፤ “ከፈጣሪ ቀጥሎ በፈተናችን ጊዜ አብረውን ለቆሙ እና በዓለም አደባባይ ለተሟገቱልን ሁሉ ኢትዮጵያ ከፍ ያለ ምስጋና ታቀርባለች” በማለት ነበር ምስጋናቸውን የቸሯቸው። የመጀመሪያውን ምዕራፍ በድል አጠናቀው ከተመለሱ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠንከር ያለ መመሪያም አስተላልፈዋል። ይኸውም “በህልውና ዘመቻው ወቅት ያየነውን የኢትዮጵያውያንን አንድነት እስከ ዓለም ፍጻሜ ሀብታችን አድርገነው መቀጠል አለብን” የሚል ነው። ሃብት ሕብረት ነው፤ ሃብት ፍቅር ነው፤ ሃብት መተሳሰብና አብሮ ማደግ ነው። ሃብት ችግርን አብሮ ማለፍ ነው።
በተለይም ዛሬ ላይ ያለንበት ሁኔታ ይህንኑ ሕብረታችንን ካልተጠቀምንበት የምናልፈው አይሆንም። እናም እርሳቸው እንዳሉት ትግሉ ገና አልተጠናቀቀም። ነጻ ያልወጡ አካባቢዎች አሉን፤ የተበተነው ጠላት እንዲማረክ ማድረግ አለብን። ከበፊቱ የበለጠ አካባቢያችንን ነቅተን የመጠበቂያ ጊዜው አሁን ነው። ፍተሻና አሰሳዎችን አጠንክረን መቀጠል ይገባናል። ከሁሉም በላይ ተፈናቃዮችን ካሉበት ችግር ማላቀቅ ከሁላችንም የሚጠበቅ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ይሆናል።
“አሁን የፈተነን ኃይል ዳግመኛ የኢትዮጵያ ፈተና ሆኖ እንዳይመጣ የሚያስችል ዘላቂ መፍትሔ ያሻናል፤ በተጋድሏችን ያገኘነውን ድል ለማቅለል የሚፈልጉትን ፊት እንንሣቸው፤ በጋራ ታግለን በጋራ ያስገኘነውን ድል፣ እንደ ቅርጫ ሥጋ ሊመድቡ የሚነሡትን አቃራጮች እናነውራቸው። ምክንያቱም ያሸነፈችው ኢትዮጵያ ናት፤ ከዚህ የወረደ ነገር አንቀበልም” ብለዋልም። ስለሆነም አሸናፊነት የዛሬ ብቻ ሳይሆን የነገም የተነግ ወዲያም እያለ እንዲቀጥልና ኢትዮጵያዊነት እንዲህ ነው እንድንልበት ሁሉን ችለንና ተጋፍጠን እንዳለፍን አሁንም ያንን ማድረግ ይኖርብናል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚነግሩን አሁን በብዙ መልኩ ጉሮ ወሸባዬ የምንልበት ጊዜ ነው። ድላችን ከእጃችን ላይም ደርሷል። የተለቀቁት ቦታዎችና ሕዝባችንም ደስታቸውን እያከበሩ ይገኛሉ። ነገር ግን ስጋትም መኖሩን መዘንጋት አይገባንም። ተስፋውን አይተን የቀረውን በአሸናፊነት ለመደምደም ምን ያህል ቁርጠኞች ነን የሚለውን ጥያቄ በቆራጥነት የመለሱ ናቸው። ኢትዮጵያ የምትበለጽገው እኛ አገራችን እንድትለወጥ በፈለግንበት መጠንና ልክ ነውም የሚል አቋም አላቸው። በዚህም ሰው ብቻ ሳይሆን ራሳቸውም ታግለው አገር እንድታሸንፍ ማድረግ ችለዋል።
መንበረ ልዑል
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 18 ቀን 2014 ዓ.ም