ነገረ ፈሊጥ፤
ቃላት ከተለምዶ ፍቻቸው በማፈንገጥ በግልም ሆነ ተጣምረው የተለየ ትርጉም ሲሰጡ ፈሊጣዊ አጠቃቀም ይባላል:: የትኛውም ቋንቋ በራሱ የባህል ዐውድ ውስጥ እየሰፋ፣ እየተስፋፋና እያደገ ከሚሄድባቸው ተፈጥሯዊ ባህርያቱ መካከል አንዱ በፈሊጣዊ አነጋገር የቃላት ቅንጅት በሚፈጠሩ አዳዲስ እሳቤዎች አማካይነት ራሱን በማጎልበት እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ጥናት ያረጋግጣል::
ለምሳሌ በዚህ ጽሑፍ ርዕስ ኢትዮጵያ የተጎላመሰችው “ዐይን” እና “ገብ” የሚሉት ሁለት ቃላት ተጣምረው በፈጠሩት ፈሊጣዊ አነጋገር አማካይነት ነው:: “ዐይነ ገብ”፡- አትኩሮትን የሚስብ፣ ተመልካች የበዛበት፣ ከሁሉ አስቀድሞ ለዐይን ደምቆ የሚታይ ማለት ሲሆን፤ ኢትዮጵያም “ዐይነ ግቧ” ተብላ የተጠቀሰችው ፈሊጣዊ ትርጉሙ በሚገባ ስለሚገልጻት ነው:: እንጂማ ሁለቱን ቃላት በወትሯዊ ትርጉማቸው እንጠቀምባቸው ብንል “ዐይን”ም ሆነ “ገብ” በየግላቸው የሚሰጡት ትርጉም በእጅጉ ከፈሊጣያዊ አነጋገሩ የተለየ እንደሚሆን መገመት አይከብድም::
አንድ ተጨማሪ ማጠናከሪያ፤
የፋሽስት ኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን በግፍ ከወረረበት ከ1928 ዓ.ም ጀምሮ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከሥልጣን እስከተወገዱበት ጊዜ ድረስ የንጉሡ የቅርብ ሰውና አማካሪ፤ በኋላም ለረጅም ዓመታት ያህል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን በአማካሪነት ያገለገሉት ጆን ሐዛወይ ስፔንሰር (ሰውዬውን ከሲ.አይ.ኤ ጋር የሚያያይዙ ብዙዎች መሆናቸው ሳይዘነጋ) “Ethiopia at Bay” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ አንድ የታሪክ መጽሐፍ አላቸው::
ደራሲው ከቀደምት የኢትዮጵያ ታሪክ በመንደርደርና የራሳቸውን የረጅም ዓመታት የኢትዮጵያ ቆይታ በማስታወስ ያዘጋጁት ይህ መጽሐፍ ብዙዎች እንዲያነቡት የሚበረታታ ብቻ ሳይሆን ለበርካታ የታሪክ ጸሐፍትም እንደ ተቀዳሚ ዋቢ እያገለገለ የሚገኝ ድንቅ ሰነድ መሆኑንም ማስታወስ ያስፈልጋል:: ይሄው መጽሐፍ ከሦስት አሥርተ ዓመታት በፊት በነፍሰ ሄር መንግሥቱ ኃ/ማርያም አርአያ (ሌ/ኮ) እና በመዝገቡ ምትኬ ቢልልኝ “ጥርስ የገባች ሀገር” በሚል የፈሊጣዊ አነጋገር ርዕስ ተተርጉሞ ለንባብ ቀርቦ በሽሚያ ማንበባችንን አስታውሳለሁ::
የመጽሐፉ ጠቃሚ፣ ይዘት፣ ፋይዳና ተነባቢነት እንደተጠበቀ ሆኖ “ጥርስ የገባች ሀገር” የሚለው ርዕስ ግን በወቅቱ (ምናልባትም ዛሬም ድረስ?) አነጋጋሪ እንደነበር ትዝ ይለኛል:: እርግጥ ነው በረጅሙ የአገራችን የታሪክ ጉዞ መካከል ኢትዮጵያ የተፈተነችባቸው የፈተና ዓይነቶች በርካቶች እንደነበሩ ይታወቃል:: ውቅያኖስ አቋርጠውና ባሕር ቀዝፈው ከመጡ አውሮፓውያን ወራሪዎች እስከ የጎረቤት ጠንቆች ድረስ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የወረራ ነጋሪት ተጎስሞባታል::
እውነታው ይህን ይምሰል እንጂ ይህቺ ዐይነ ግቡ እናት አገራችን በአንድም የታሪክ አጋጣሚ በወራሪዎች መንጋጋ ውስጥ ገብታ አልታኘከችም:: አላምጠውም አልዋጧትም:: እንኳን በጥርሳቸው ውስጥ ገብታ ልትላመጥ ቀርቶ “ጉልበታቸውን ብርታታቸው” አድርገው በትዕቢት ካበጡት ጠላቶቿ መዳፍ ውስጥ ገብታም እንኳ አልተንበረከከችም:: ለነገሩስ በጋለ አሎሎ የሚመሰለው የኢትዮጵያዊነት ፍም ብሔራዊ ስሜትን እንደምን ጠላቶቿ ወደ አፋቸው ያቀርቡታል? እንደምንስ በሰደድ እሳት የሚመሰለው የጀግኖች ልጆቿን ክንዶች ተቋቁመው ሊገዳደሯት ይሞክራሉ:: በፍጹም አልተቻለም፤ አይቻልምም::
ክፉዎቹ ባላንጣዎቿ እንደሚመኙት ኢትዮጵያ በጥርስ የምትላመጥ “ማስቲካ” ሳትሆን የጠላቶቿን ጥርሶች አራግፋ በድዳቸው እያስለቀሰች ወደመጡበት የምትሸኝ ክንደ ብርቱ መሆኗን የተጻፉ ታሪኮቿ፣ በቃል የተላለፉ ገድሎቿና በዐይን ምስክሮች የተረጋገጡ የዜና መዋዕልዋ ድርሳናት ምስክሮች ናቸው:: ታሪኳ የተሸመነው፣ ልጆቿም የተጎናጸፉት ይህንን መሰሉን በደም መስዋዕትነት የቀላ የክብር ፀጋ ነው::
የኢትዮጵያ ዐይነ ግቡነት እስከምን?
ሀ-ግዕዝ፤ ከዘፍጥረት ዜና መዋዕል፤
የኢትዮጵያ ዐይነ ግቡነት የሚጀምረው ከዘፍጥረት ታሪክ ነው:: የቅዱስ መጽሐፍ ታሪክ አሀዱ ብሎ ምዕራፉን የሚከፍተው የዚህችን ምሥጢራዊት አገር ወንዝ ግዮንን በመጥቀስ ነው:: ይህ ወንዛችን ከኤደን ገነት መንጭቶ ከወጣው ታላቅ ወንዝና በአራት ከተከፈሉት ቅርንጫፎች አንዱ ከሆነ ዘንዳ (ኢትዮጵያ የሚሏት ሀገር ሰፍታለች፣ ጠባለች፣ እዚያ ነበረች እዚህ ነች ወዘተ. የሚለውን ጉንጭ አልፋ የጂኦግራፊ አተካራን ወደ ጎን በመግፋት) አገራችን ለገነትም ሆነ ከፈጣሪ የመፍጠር አጀንዳ ጋር በእጅጉ የተቆራኘች ባለ ብዙ ዝና የታሪክ እመቤት መሆኗን ለማመን አይከብድም:: ላለማመን የሚደፈረው የኢ-አማኒነት የጥርጣሬ መንፈስ ማንነትን የሚቆጣጠር ከሆነ ብቻ ነው::
በአይሁድና በክርስትና እምነቶች ታሪኮች ውስጥም ቢሆን ኢትዮጵያ የነበራትና ያላት ቦታ የከበረ ብቻም ሳይሆን እንደ ድርና ማግ ተሰላስለው በተሸመኑ ተዓማኒ እውነታዎች የዳበረ ስለመሆኑ ሺህ ጊዜ ሺህ ማስረጃዎችን መጥቀስና ማጣቀስ ይቻላል:: ከኢስላም ታሪክም ጋር እንዲሁ እንደምን በጠበቀ ቤተሰባዊ ቁርኝት እንደተጋመድን የነብዩ መሐመድን ምሥክርነትና የአዛኑን የጸሎት ጥሪ በሰማን ቁጥር ወደ ማስተዋላችን የሚመጣውን የነብዩን ደቀ መዝሙር የቢላል ኢብን ራባኽን ታሪክ በመጥቀስ ብቻ እውነቱን ማሳየት ይቻላል::
የኢትዮጵያ ዐይነ ግቡነት የሚጀምረው ከፈጣሪ ከራሱ መለኮታዊ ምርጫ ጋር መሆኑን በአሜንታ ከተቀበልን ዘንዳ ሌሎች በዘመናት ታሪኮቻችን ውስጥ የተፈጸሙትን ክስተቶች የምናስታውሰው በፀና መሠረት ላይ ቆመን መሆኑ ሊሠመርበት ይገባል:: የዓለማችን ሦስቱ ዋነኛ እምነቶች (አይሁድ፣ ክርስትናና ኢስላም) ተከባብረው በአንድነት እንዲኖሩ የተደረገው በሰው ብልሃት በተፈጠረ ጥበብ አማካይነት ሳይሆን በፈጣሪ ውሳኔ ጭምር ስለፀና መሆኑንም መቀበል ግድ ይለናል::
ሁ-ካዕብ፤ የጥንታዊ ታሪካችን ምስክርነት፤
በፈጣሪ ዘንድ የታወቀ፤ በሰብዓዊያን ሰነዶች ውስጥ በክብር የሰፈረውና በራሷ በኢትዮጵያ የታሪክ ውሎዎች ውስጥም ተደጋግሞ የሚጠቀሰው የዘመናት ጉዞዎቿ መልክ የሚያሳየን ብትደነቃቀፍም አለመውደቋን፣ ብትዝልም አለመረታቷን ነው:: ከጥንታዊ ግሪካውያን ፈላስፎች መካከል ደራሲው፣ ጂኦግራፈሩና የታሪክ ምሁሩ ሄሮዶቱስ (ቅልክ ከ484-425) እና ደራሲና ባለቅኔው ሆሜር (ቅልክ 8ኛው መቶ ክፍለ ዘመን) በአድናቆት የኳሏት ታሪኮቿ ልቦለድ ሳይሆኑ የታነጸችው በእውነትና በፀና መሠረት ላይ መሆኑን አረጋግጠው ነው::
ዛሬ አገራችንን የገጠማትን የእኩያን ክፋት በሚገባ ተረድተው በተባበሩት መንግሥታትና በዓለም አቀፍ መሰል ሸንጎዎችና በተለያዩ መድረኮች ላይ ለኢትዮጵያ ወቅታዊ ፈተና ሳያሰልሱ “አለንልሽ” በማለታቸው ከሚጠቀሱት አገራት መካከል ሕንድና ቻይናን ማስታወሱ ብቻ በቂና ከበቂም በላይ ነው::
ከ2000 ዓመታት በላይ የሚቆጠር የተመዘገበ የታሪክ መስተጋብር የምንጋራው እነዚህ ሁለት አገራት ከኢትዮጵያ ጋር የነበራቸው የንግድ ሽርክና ምን ያህል ጠንካራ እንደነበር ደጋግሞ ይገለጻል:: ከሩሲያ ጋርም እንዲሁ በሼክሲፔር በኩል ደም ጠቀስ የሆነው ታሪካችን ጉልህና አጠንክሮ ያስተሳሰረን የአሻር ውርስ ነው:: ይህ ዘመናት ያስቆጠረው ወዳጅነት ግድ ብሏቸውና ወዳጅ ወዳጅን እንደማይከዳ ተረድተው ፍቅራቸው ሳይቀዘቅዝ ዛሬም ድረስ መዝለቁ የግንኙነታችንን ጥብቀት ያሳያል:: እስካሁን በጽናት ከጎናችን ስለቆሙ ምሥጋናችን ይድረሳቸው::
በክፋትና በሴራ አገራችንን ለማዳከም ቀን ከሌት ሸር ሲጎነጉኑ ውለው ከሚያድሩት አገራት መካከል አሜሪካንን እንደ አንድ አብነት እንጥቀስ:: ይህቺ ታላቅነቷን በተግባር ሳይሆን በአንደበቷና በአዋሻኪ የራሷና የወዳጆቿ ሚዲያዎች የምትናገረውና የምታስነግረው አሜሪካ ይሏት አገር በአንድ ክፉና ወሳኝ ወቅት ከአገራችን ጎን ቆማ ብርታት እንደሆነችን ብናስታውስ አይከፋም:: የተበከለውን የዛሬውን ቀልቧን ማጽዳት እንዲያስችላት የበጎነቷን ታሪክ በማስታወስ “ምሥጋና ቢስ” ያለመሆናችንን እነሆ እናረጋግጥላታለን::
ግንቦት 1 ቀን 1928 ዓ.ም ፋሽስቱ ሙሶሎኒ “የኢጣሊያ መንግሥት ኢትዮጵያን ድል አድርጎ ይዟል:: ከዛሬ ጀምሮ ኢትዮጵያ የኢጣሊያ ቄሳር ግዛት መሆኗን ለዓለም እናሳውቃለን” ብሎ በእብሪት ፉከራው ሲያቅራራ “በወራሪነቱ እንጂ የኢጣሊያን ገዢነት አናውቅም!” በማለት መከራው ጠንክሮባት ለነበረችው አገራችን ድምጻቸውን ካሰሙት መንግሥታት መካከል አሜሪካ፣ ሶቪዬት ኅብረት፣ ሜክሲኮና ኒውዝላንድ ቀዳሚ ተጠቃሾች ነበሩ:: የአሜሪካ መንግሥትና መሰል ተገለባባጭ መንግሥታት እንዲህ ዓይነቱን የወዳጅነት ታሪካቸውን ዘንግተው ዛሬ በጠላትነት ቢሰለፉብንም የአንድ ወቅት መልካምነታቸውን እንዳልዘነጋን በማስታወስ ታላቅነታችንን ማሳየቱ ማስተዋል ስለሆነ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ልብ ግዙ፤ ተጸጸቱ እንላቸዋለን::
ሂ-ሣልስ፤ ማሳረጊያ፤
በዐይነ ግቧ ኢትዮጵያ ላይ ዓይናቸውን ተክለው ለበጎነትም ሆነ ለክፋት የሚቃኟት አካላት ብዙዎች ናቸው:: የአንዳንዶቹ ዐይን በ“ጥላ ወጊ” ይመሰላል – ውድቀታችንን ስለሚመኙ:: የአንዳንዶቹ ደግሞ ፍቅርና ርህራሄ የሚስተዋልበት ነው-በክፉ ቀን ፈጥነው አለን ስለሚሉ:: አንዳንዶቹ ዐይናፋር ተሽኮርማሚዎች ደግሞ ሁኔታዎችን እያዩና የጉዳዩን አነፋፈስ እየመረመሩ ግፊቱ ወደ በረታበት ለመገለባበጥ ራሳቸውን ያዘጋጁ ናቸው:: አንዳንዶችም “ዐይን አውጣ” ይሏቸው ብጤ ናቸው – በማያገባቸው እየገቡ በሉዓላዊነታችን ክብር ላይ ካላደራደርን የሚሉ::
በዓይነ ግቧ ኢትዮጵያ ላይ ብዙ ዐይኖች ያፈጠጡ ቢሆንም የእውነቱ መደምደሚያ ግልጥ ነው:: ረዳታችን ፈጣሪ፣ አለኝታዋ ሕዝቧ፣ ኩራቷ ሠራዊቷ፣ ትኩረታችን ሰላማችን፣ ትግላችን ድህነታችንን ከማሸነፍ ጋር እንጂ ጦርነት ምርጫችን አይደለም:: ግድ ካልሆነ በስተቀር የአረር ሽታን መታጠንን አንፈቅድም:: ከዚህ በተረፈ በድላችን የምንኩራራ፣ ስንፈተንም ኡኡታ በማሰማት ዓለምን የምናውክ ጯሂዎች ያለመሆናችንን እንደ ትናንቱ ዛሬም እያረጋገጥን ጉዞችንን ከተመኘነው ብልጽግና አንገታም:: ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 16/2014 ዓ.ም