ልጆች የጀግንነት መነሻው ልጅነት መሆኑን ታውቃላችሁ አይደል? አዎ፣ የጀግንነት መነሻው ልጅነት ነው። የሁሉም ነገር መነሻው ልጅነት እንደሆነው ሁሉ ጀግንነትም መሰረቱ እዚሁ እድሜ ላይ ነው። በመሆኑም በዚህ በወርቃማው የእድሜ ዘመናችሁ ላይ ሆናችሁ የወደፊት ሕይወታችሁን መሠረት ከወዲሁ ትጥላላችሁ ማለት ነው።
ልጆች ጀግንነት በጦር ሜዳ ብቻ ነው እንዴ የሚስተዋለው? “አይደለም” ካላችሁ ትክክል ናችሁ። ምክንያቱም ሰው በየተሠማራበት የሙያ መስክ ሁሉ ውጤታማ ከሆነ፣ ውጤት ካስመዘገበ እሱ ጀግና ነው። ባጭሩ የወደፊት ማንነታችን መሠረቱ ልጅነታችን ነው እያልን ነው። ትምህርት በልጅነት ነው፤ አካል ብቃት እንቅስቃሴ በልጅነት ነው። ሥነ ምግባር የሚታነፀው ከልጅነት ጀምሮ ነው። ከዚህ አኳያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጀግኖች ልጆችን እንፈልግና የጀገኑበትን ምክንያት እንመርምር።
ልጆች ግሬታ ተንበርግንን ታውቋታላችሁ? ብዙዎቻችሁ እንደምታውቋት አልጠራጠርም። ምክንያቱም በጣም ብዙ ጊዜ በአካባቢ ጥበቃ ሥራዋ በዓለም አቀፍ ጀግኒቷ ስለምትታወቅና ብዙ ጊዜም በመገናኛ ብዙኃን ስለምትቀርብ ነው። ግሬታ የተወለደችው እኤአ ጥር 3 ቀን 2003 ነው። የተወለደችውም ስቶኮልም፣ ስዊድን ውስጥ ሲሆን፤ አባትና እናቷ ማሌና ኤማን እና ስቫንቴ ተንበርግ ይባላሉ።
ግሬታ ገና በልጅነቷ ጀምራ የአካባቢ መጎሳቆልና የሰው ልጅ የወደፊት ዕጣ ፋንታ አሳስቧት ወደ ማኅበራዊ አንቂነት ተግባር ገባች። ይህ ተግባሯም በአካባቢ ጥበቃ ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ ዛሬ በዓለም ላይ ታዋቂ ጀግና አሰኝቷታል፤ ለበርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶቿም ምክንያቱ ይኸው ነው፡፡ ዓለምን እየለወጠችና በሥራዋም ዓለም አቀፍ ተፅእኖን እየፈጠረች ትገኛለች። ለዚህም “ታይም” መጽሔት የ2019 “የዓመቱ ምርጥ ሰው” ሲል ማውጣቱ አንዱ የግሬታ ጀግንነት ማረጋገጫ ነው።
ልጆች ስለ ግሬታ በሚገባ በማንበብ የበለጠ ታውቃላችሁ፣ እንደ እሷ ጀግና ለመሆንም አስፈላጊውን ጥረት ሁሉ ታደርጋላችሁ ብዬ በማሰብ ወደ ሌላ ጀግና ልወስዳችሁ ነው። ከ14 ዓመቱ ማርቆስ እንጀምር። ማርቆስ በዓለም የጀግኖች ማህደር ላይ የተመዘገበው በሌላ ሳይሆን በሰብዓዊ ተግባር ነው። ማርቆስ በድንገት ኮዲ ማ የምትባል የስምንት ዓመት ልጅ ፎቅ ላይ በእሳት እየተቃጠለች ያያል። ምንም ለነፍሱ ሳይሳሳ በመሰላል ወጥቶ፣ ነበልባሉን እንደ ውሃ ዋና ሰነጣጥቆ በመሄድ ኮዲን ከሞት አተረፈ። እነሆ ዛሬ ኮዲ ዓለም አቀፍ ጀግና በመሆን ስመ ጥር ለመሆን በቅቷል።
የዘጠኝ ዓመቷ አናያህ ራከርም እንደዚሁ በሰብዓዊ ተግባሯ በዓለም የጀግኖች ማህደር ላይ የሰፈረች እንስት ነች። አናያህን ከሌሎች ለየት የሚያደርጋት እህቷን ትልቅ መኪና (ትራክ) ሊገጫት ሲል ዘላ ገብታ በማውጣቷና እህቷን አትርፋ እራሷን ለአደጋ በማጋለጥ ለወራት ሆስፒታል መተኟቷ ነው።
ልጆች አንድን ልጅ “ጀግና” የሚያሰኙት ምን ምን ጉዳዮች እንደ ሆኑ ታውቃላችሁ? እሺ፣ አንድን ልጅ ጀግና ከሚያሰኙትና በባለሙያዎች ከተረጋገጡት ጉዳዮች መካከል ነገሮችን በልበ ሙሉነት መቋቋም፣ መጋፈጥ መቻል (Bravery)፣ በአንድ ጉዳይ ላይ ጠንካራ እምነት መያዝ/መኖር (Conviction)፣ ብርታት/ጥንካሬ/ ጽናት መኖር (Courage)፣ የውሳኔ ሰው መሆን (Determination)፣ ደጋፊ፣ እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎችን መደገፍ (Helpful)፣ ታማኝነት (Honesty)፣ በአንድ ነገር በመቀስቀስ (በመነሳሳት) ለመሥራት መጣር (Inspirational) እንዲሁም በስነ ምግብር (ሞራል) የተገነባ ሰብዕና ያለው ሆኖ መገኘት (Moral integrity) ይገኙበታል። ከላይ የጠቀስናቸው ዓለም አቀፍ ጀግኖችም እነዚህ እሴቶች እንዳሏቸው በባለሙያዎች ተመስክሮላቸዋል፡፡ እናንተም የእነሱን አርአያ ለመከተል ጥረት አድርጉ። ከዛ በቃ ብሔራዊ ወይም ዓለም አቀፍ ጀግና ሆናችሁ ማለት ነው።
ልጆች፣ ከመሰናበታችን በፊት አንድ ነገር እናንሳና እንለያይ። ለዛሬ ማለቴ ነው። ኢትዮጵያ የጀግኖች አገር መሆኗን ታውቃላችሁ አይደል? አዎ፣ ኢትዮጵያ የጀግኖች አገር መሆኗን በሚገባ ማወቅ አለባችሁ። ይህ ደግሞ ከድሮ ጀምሮ መሆኑንም ማወቅ ያስፈልጋል። በዚህ ሰሞን እንኳን ስንትና ስንት ጀግኖች ታሪክ እንደሰሩ አልሰማችሁም? ሰምተናል እንደምትሉን እንገምታለን፡፡ አሁን አገር ካለችበት ሁኔታ አንጻር “እኛ ልጆቿ እያለን ኢትዮጵያ አትፈርስም” በማለት ታሪክ የሠሩ ጀግኖች መኖራቸውን አይታችኋል አይደል? በጣም ጥሩ፣ እናንተ ደግሞ የወደፊት የዚህች አገር ተረካቢና ጀግኖች ናችሁና ከአሁኑ መሠረታችሁን ማጽናትና ቤተሰቦቻችሁ የሚሏችሁን መስማት አለባችሁ፡፡ ጀግኖችን እያያችሁ ጀግና ለመሆንም መሥራት ይኖርባችኋል፡፡ በርቱ!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 17/2014 ዓ.ም