“…ፋኖ ተሰማራ ፋና ተሰማራ
እንደነ ሆቺሚኒ እንደ ቼጉ ቬራ
……
ለዕድገት በኅብረት እንዝመት(2)
ወንድና ሴት ሳንል በአንድነት
አገሬ አገሬ ማለት ብቻ አይበቃም
ስንደክምላት እንጂ በተቻለን አቅም… ”
እንደ ኢትዮጵያውያን የዘመን ቀመር 1960ዎቹ አጋማሽ ላይ የነበረ ሁሉ ያስታውሰዋል። በዚያ ወቅት በአገር ደረጃ የነበረውን የሚያስታውስ ዜማ ነው። ወቅቱ በኢትዮጵያ ታላቅ የለውጥ ማዕበል የተነሳበት ነበር። ብዙዎች ይህን ሲሰሙ የዕድገት በኅብረት ዘመቻን ያስታውሳሉ። በተለይም በዘመቻው ዋንኛ ተሳታፊ በነበሩ ዘማቾች የሚዘወተር ጥዑም ዜማ ነው። በዚህ ዘመቻ ኢትዮጵያውያን ወጣት ተማሪዎችና መምህሮቻቸው ናቸው የተሳተፉት። የዛሬው የሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን አንዱ ርዕሰ ጉዳይም ይሄ ነው።
በኢትዮጵያ ታሪክ በተለይም በ1966 ዓ.ም ሕዝባዊ አብዮት የንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን መንግሥት ለማስወገድ ወደ ሥልጣን በመጣው የደርግ መንግሥት ወቅት ከተናከወኑ እጅጉን ከሚጠቀሱ ታሪካዊ ሁነቶች መካከል የዕድገት በኅብረት ዘመቻ አንዱ ነው።
ዘመቻው ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችና መምህራን ወደ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ በመዝመት ሕዝቡን በማንቃት በኢትዮጵያ በመጣው አብዮት ውስጥ ሚናውን እንዲጫወት አገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የተደረገበት ነበር። ዘማቾቹ በአገር ደረጃ በታወጀው ዘመቻ ለአገሪቱ ለውጥ ለሕዝቡ መሻሻል እጅጉን ጠቃሚ የሆነ ተግባራት ከውነዋል።
በዘመቻ መልክ በአገር ደረጃ ማኅበረሰቡን ተሳታፊ ባደረገ መልኩ ከተሰሩና አመርቂ ውጤት ከተገኘባቸው ዘመቻዎች መካከል ደግሞ ተጠቃሹ “የዕድገት በኅብረት” ዘመቻ ነው:: ዘመቻው በገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በተለይም በአርሶ አደሩ ዘንድ ስለተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ግንዛቤ በመፍጠር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳስገኘ ይገልጻል።
ዘመቻው የተፀነሰው በ1966 ክረምት ወራት ላይ ሲሆን፣ ተግባራዊ የተደረገው ግን የዛሬ 47 ዓመት ታህሳስ 12 ቀን 1967 ዓ.ም ዘመቻው ታውጆ ነው፤ በዘመቻው ከ10ኛ ክፍል ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ያሉ ተማሪዎችና መምህራን ተሳትፈዋል፤ በዚህም ተማሪዎቹ የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ አድርገዋል። መነሻው በኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይማሩ የነበሩ ተማሪዎችና መምህራኖቻቸው ወደ ገጠር ሄደን ሕዝቡን ለሥራ እንቀስቅስ፣እናስተምር፣ እናደራጅ በሚል ያቀረቡት ጥያቄ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህን መሠረት አድርጎ ወደ ተግባር የተለወጠው ዘመቻ የናይጄሪያና የታንዛኒያ መሰል ገበሬዎችን የማደራጀት ዘመቻ ተሞክሮ ተወስዶ የተተገበረ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ወደ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ የተጓዙት ዘማች ተማሪዎችና መምህራን ከአርሶ አደሩ ጋር ቅርርባቸው እየጨመረ መጣ። ይህ ቅርርብ ግን በወቅቱ ገጠሩን ያስተዳድሩ በነበሩት የመሬት ከበርቴዎች ዘንድ ሳይወደድ ቀረ። ከበርቴዎቹ ዘማቾቹን በክፉ አይን ማየትና መጠርጠርም ጀምሩ። በወቅቱ በመንግሥት በኩል የዘመቻው ዓላማ በተደጋጋሚ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ይገለፅም ነበር።
ዘመቻውን አስመልክቶ ከተፃፉት መጽሐፍት መካከል በወቅቱ የደርጉ ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩት ፍቅረ ስላሴ ወግ ደረስ “እኛና አብዮቱ” በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ እንዳሰፈሩት፤ በዘመቻው 60ሺ ተማሪዎችና መምህራኖቻቸው ተሳትፈዋል። እነዚህን ዘማቾች በ57 የክፍለ አገር ማስተባበሪያና በ517 ምድብ ጣቢያዎች ለመላክ ታቅዶ እንደነበር መጽሐፉ ያትታል። በኋላ ላይ መንግስት ባወጣው ሪፖርት ዘማቾች በ51 ማዕከላት፣ በ397 ማስተባበሪያዎች ተልከው ነበር።
ሻምበል ኪሮስ አለማየሁ የዘመቻው መሪ ተደርገው እንደተሾሙና በዋናነት ሥራውን እንደመሩት ዘመቻውን በተመለከተ የተፃፉ ድርሳናት ያወሳሉ። በወቅቱ በመንግሥት የታወጀው የዕድገት በኅብረት ዘመቻ ጥሪ ይህን ይመስል ነበር።
“እናት አገር ለሰፊው ህዝብ የቆሙ ልጆችዋን ደጋግማ ትጠራለች።
ተማሪዎች ከፊል ፊዩዳልና ከፊል ከበርቴ የሆነው ሥርዓት ለብዙ ዓመታት በሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ያስከተለው መቆርቆዝና ያደረሰውን በደልና ጭቆና ባደባባይ አጋልጠዋል። ሕዝቡ ከተኛበት እንዲነቃ የቅስቀሳ ትግላቸውን በየጊዜው አፋፍመዋል። የየካቲቱ ሕዝባዊ ንቅናቄ ሲጋጋልም እንደጦር ይፈሩ የነበሩት የጥቁር ሕዝቦች መፈክሮችን ከሰፊው ሕዝብ ጋር አስተዋውቀዋል። ሕዝባዊ ንቅናቄው በበዝባዦችና በተበዝባዦች መካከል የሚደረግ ትግልና አሮጌው ሥርዓት የወለደው እንጂ ተራ የሆነ የሰዎች ግጭት እንዳልሆነ በልዩ ልዩ መልኩ ገልፀዋል። ….. ባለፈው ሥርዓት የተጎዳው አርሶ አደር እና ላብ አደር ከጎኑ ከቆመው መለዮ ለባሽ ጋር የሚያነቁት የሚያስተምሩትና አለሁልህ የሚሉትና የመደብ ጠላቶቹን የሚያንበረከኩለት ተማሪዎች መሆናቸው ስለታመነበት የእድገት በኅብረት የዕድገትና የሥራ ዘመቻ ሀሳብ ተፀነሰ…… ”
ከላይ የሰፈረውና ለማስረጃነት የቀረበው የዕድገት በኅብረት አዋጅ ሀሳብ ሙሉ እንዳልሆነ ልብ ይሏል። ይህ በመላው አገሪቱ የሚገኙ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችና መምህራን ያካተተው ዘመቻ ጅማሮው ላይ በወቅቱ በነበረው ፖለቲካዊ ሁኔታም ፈተና ገጥሞትም ነበር።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ /ኢህአፓ/ና ሌሎች በወቅቱ በፖለቲካ ትግል ላይ የነበሩ አካላት ዘመቻውን በፅኑ ተቃውመውት እንደነበርም መረጃዎች ይጠቁማሉ። አገሪቱን ይመራ የነበረው የደርግ መንግሥት ተማሪዎችንና መምህራንን ወደ ገጠር ልኮ ራሱን ከተማ ላይ ሊያጠናክር ፈልጎ ነው የሚል ሀሳብ አንስተው ነበር። ነገር ግን በአብዛኛው የዘመቻው ተሳታፊዎችና ማኅበረሰቡ ዘንድ ይህ ተቀባይነት አልነበረውም። ዘመቻው ለአገርና ለሕዝብ የሚሰጠው ጥቅም ከፖለቲካዊ አመለካከትና ፓርቲ ከፍ ያለ መሆኑን በመረዳት ዘመቻው እውን ሊሆን ችሏል።
በወቅቱ ሕዝባቸውን ለማንቃትና ለማደራጀት ብርቱ ፍላጎት የነበራቸው መምህራንና ተማሪዎች ለአገራቸው በጎ ተግባር ለማበርከት የነበራቸው ሞራልና ልበ ሙሉነት የዘመቻው ቀን በምን መልክ እንደታየ ገስጥ ተጫኔ በመጽሐፋቸው አስፍረውታል። በተለይም ዘመቻው ሲታወጅ እና በጃን ሜዳ ዘማቾች ሲሸኙ የነበረው ድምቀት ገስጥ ተጫኔ “ነበር”በዘነበ ፈለቀ ብለው ባወጡት መጽሐፋቸው ተርከውታል።
ዘማቾች አርሶአደሩን ማንበብና መጽሐፍ በማስተማር፣ ስለ ፍትሕና ነፃነት መብትና ግዴታው የመሳሰሉ መሠረታዊ ጉዳዮች በማስተማር እየተግባቡ የሚያውቁትን እያሳወቁት ቆዩ። በመሐል ግን አርሶአደሩ የተለያዩ ጥያቄዎችን በከበርቴዎቹ ላይ ማንሳትና ስለ መብቱ መሟገት ጀመረ። ይህ ሁኔታም አንዳንድ ዘማች ተማሪዎች ዘመቻ ጣቢያውን በመልቀቅ ወደአካባቢያቸው መመለስና አንዳንድ የዘማች ጣቢያዎች መዘጋት ጀመሩ።
ይህን ተከትሎም አገሪቱን ይመራ የነበረው የደርግ መንግሥት ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎችን ለዘማቾቹ ይሰጥ ነበር። ዘማቾች በየጣቢያዎቻቸው ቆይተው የዘመቱበትን ጉዳይ በጽናት እንዲያሳኩም ተነገራቸው። በዚህም ዘማቾች ወደ ጣቢያ ተመልሰው ሕዝቡን በማንቃትና በማስተማር የቆዩበት ሁኔታም ታይቷል። ይህ ዘመቻ ለሁለት ዓመታት የቀጠለ ነበር።
ዘመቻውን አስመልክቶ የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ በዘመቻው 5 ሚሊዮን 537 ሺ ገበሬዎች በ19 ሺ 341 ማኅበራት እንዲደራጁ ተደርጓል፤ 63 ሺ 500 የፍርድ ሸንጎዎች፣ 55 ሺ የመከላከያ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል። በመሠረተ ልማት ረገድም 264 ክሊኒኮች፣ 158 ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል። 750 የጤና ረዳቶች ሰልጥነዋል። 500ሺ የቀንድ ከብቶች ተከትበዋል። ይህ አኅዝ ዘማቾች በዘመቻ የቆዩባቸው ሁለት ዓመታት የሰሩትን አጠቃላይ ስራ የሚያመላክት እንዳልሆነና ቁጥሩ ከዚህ ከፍ እንደሚልም ሌሎች መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይህን ጽሑፍ ስናዘጋጅ ከተለያዩ ድህረ ገፆች በተጨማሪ የባህሩ ዘውዴ “የኢትዮጵያ ታሪክ”፣የፍቅረ ስላሴ ወግ ደረስ “እኛና አብዮቱ” ፣የገስጥ ተጫኔ “ነበር”በዘነበ ፈለቀ የተሰኙ መጽሐፎች ተጠቅመናል።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 17/2014 ዓ.ም