ባለፈው ሐሙስ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታርያት በአዲስ ወግ፤ “ሕልውናን መጠበቅ፣ልማትን ማዝለቅ፤”በሚል ርዕስ ባዘጋጀው ውይይት ላይ የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ለመልሶ ግንባታ የሚውል በጀት በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለማጸደቅ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ይፋ አድርገዋል። ብዙም የመሠረተ ልማት ውድመት ላልተከሰተበት የትግራይ ክልል መልሶ ግንባታ 100 ቢሊዮን ብር ከተመደበ፤ የትግራይ ወራሪ ኃይል ባለፉት አምስት ወራት በመሠረተ ልማት ማለትም በጤና፣ በትምህርትና በዩኒቨርሲቲዎች በመንገድና በሌሎች ተቋማት ያደረሰው ከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ መልሶ ለማቋቋም በብዙ መቶ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ተጨማሪ በጀት መፈለጉ አይቀርም። ይህ በጀት ወደ ኢኮኖሚው ሲገባ አሁን ያለውን ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት እንዳያባብሰው ከፍ ያለ ጥንቃቄና ጥብቅ ዲስፕሊን ይጠይቃል።
በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እንዲሉ ጦርነቱን ተከትሎ በደጀኑ ሕዝብ የተንቀሳቀሰውን ሀብት ጨምሮ በኢ-መደበኛ አደረጃጀት ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ የሚፈጥረው የዋጋ ግሽበትና ለኑሮ ውድነቱ አሉታዊ ተጽዕኖ ማስከተሉ ሳያንስ ለመልሶ ግንባታ የሚታወጀው በጀት ሸማቹን ለተባባሰ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት እንዳይዳርገው በኢኮኖሚው ላይ በተለይ ከሸማቾች ጥቅም አኳያ የሚስተዋለውን መዋቅራዊና ተቋማዊ ችግር አበክሮ መቅረፍ ያሻል። ተገደን ከገባንበት ቀጥሎ የዜጎች ፈተና የሆነው የኑሮ ውድነቱና የዋጋ ግሽበቱ ስለሆነ ለሌላ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ እንዳይዳርግ በዘመቻ እሳት ከማጥፋት ወጥተን ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ይኖርብናል። አሁን ለምንገኝበት ኢኮኖሚያዊ ችግር የተዳረግነው በቀደሙት 27 ዓመታት የተከተልነው የተሳሳተ ፖሊሲ መሆኑ መውጫችንን አርቆታል።
ሁለት አስር አመታትን ያስቆጠረው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት የዜጋውን ኑሮ በብርቱ እየፈተነው፤ ከኢኮኖሚያዊ ችግርነት ወደለየለት ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስነት እንዳይባባስ እያሰጋ ይገኛል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ኢኮኖሚው ለቀደሙት 27 ዓመታት የአንድ ቡድንና የጭፍራው መጠቀሚያ በመሆኑ በተከሰተው ኢ-ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ አሻጥር ጦርነትና አለመረጋጋት ተጨምሮበት ኑሮው አልቀመስ ብሏል። የውጭ ምንዛሪ እጥረት፤ የተራዘመ የግብይት ሰንሰለት፤ የትርፍ ሕዳግና የቤት ኪራይ በሕግ አለመወሰኑ፤ ከገበሬ ማሳና ከጉልት እስከ ጅምላ አከፋፋይ የተሰገሰገ ደላላ፤ በግብይት ሰንሰለቱ የተንሰራፋው ሥርዓት አልበኝነት፤ ዋጋን በአድማ መወሰን፤ ምርትን በመደበቅ ሰው ሰራሽ እጥረት መፍጠር፤ የፍላጎትና የአቅርቦት አለመጣጣም፤ የኑሮ ውድነቱን ለመከላከል በመንግሥት ዘንድ ወጥ የሆነ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት አለመኖር፤ የሎጅስቲክስ አገልግሎቱ ቀልጣፋ አለመሆን፤ ወደብ አልባ በመሆናችን በየዓመቱ ቢሊዮኖችን የምናወጣ እና ስለመብቱ የሚቆረቆርና የሚጠይቅ ሸማች አለመፈጠሩ እንደ ዚምባብዌና ቬኒዞላ ባይሆንም በሰዓታት ልዩነት ለሚተኮስ የዋጋ ግሽበት እንዲዳረግ መንስዔ ሆኗል።
በየፍጆታ ሸቀጦች ላይ የሚታየው የዋጋ ግሽበት በሌሎች ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ ግሽበትንና የኑሮ ውድነቱን እያባባሰው ይገኛል። በዚህ ሳቢያ በመዋቅራዊና በተቋማዊ ችግር የተነሳ ጽኑ ታማሚ ሆኖ ለኖረው ኢኮኖሚ ሌላ ራስ ምታት ሆኖበታል። የለውጡ መንግሥት ባለፉት ሶስት ዓመታት የኑሮ ውድነቱንና የዋጋ ግሽበቱን ወደ ነጠላ አኃዝ ለማውረድ ያደረገው ጥረት ውጤት አለማስገኘቱን አምኖ የአዲሱ መንግሥት ቀዳሚ ተግባርም ይሄን ማስተካከል እንደሆነ ቃል ቢገባም በሚፈለገው ፍጥነትና ቅንጅት እየሄደ አይመስልም።
የኑሮ ውድነቱም ሆነ የዋጋ ግሽበቱ ገፈት ቀማሽ የሆነው ደግሞ ሸማቹ ነው። የአሜሪካው 35ኛ ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ በአንድ አጋጣሚ “ሁሉም ሸማች ነው። በግሉም ሆነ በመንግሥት ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎች በአዎንታም ሆነ በአሉታዊ ጥቅሙ የሚነካ በሌላ በኩል የሸማቹ ውሳኔ በግሉም ሆነ በመንግሥት ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎች ላይ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችል ነው። “ሲሉ ሸማች በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካውና በማኅበራዊ እርካቦች የተቆናጠጠውን ከፍታ አመላክተዋል። ከዚህ የፕሬዚዳንቱ ትርጓሜ ሁለት አበይት ሰበዞችንን መምዘዝ ይቻላል። የመጀመሪያው አንተም፣ አንችም፣ እኔም ሁላችንም ሸማች መሆናችንን። ሻጩ ሸማች፣ ሸማቹ መልሶ ሻጭ ይሆናል። ሁለተኛውና ትልቁ መልዕክት በሸማቹ፣ በሻጩ እና በመንግሥት መካከል ያለውን ሚዛናዊ እና ፍትሐዊ ግንኙነት ማስጠበቅ እንደሚገባ ያመለክታል።
ለመሆኑ ሸማች ማለት ምን ማለት ነው !? እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1986 ዓም ይፋ የሆነው የሸማቾች ጥበቃ ሕግ፤” ማንኛውንም ሸቀጥ ወይም አገልግሎት ለፍጆታ የሚገዛ ሸማች ነው። “በማለት ይተረጉማል። ይህ ፕሬዚዳንት ኬኔዲ “ሁላችንም ሸማች ነን። “ካሉት ጋር ይቀራረባል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ.ም ያሳተመው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ ሸማችን ጠበብ አድርጎ፣ አኮሳምኖ “እህልን ለንግድ ሳይሆን ለምግብነት የሚገዛ በላተኛ። “ሲል ይበይነዋል። የአገልግሎት ሸመታውን በዘነጋ መልኩ። የእንግሊዘኛው ሜሪያም ዌብስተር መዝገበ ቃላት ደግሞ ቅንብብ አድርጎ፤ “ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን የሚገዛ ሰው ሸማች ነው። “በማለት ይተረጉመዋል። ሸማችነት ሸቀጥንም አገልግሎትንም እንደሚያካትት ባረጋገጠ ሙሉዑ ብያኔ ይሰጠዋል።
ወደ አገራችን ስንመጣ በሸማቹ፣ በሸቀጥና አገልግሎት ሻጭ እና በመንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት የተዛባ፣ ኢ-ፍትሐዊ፣ መርሕ አልባ እና ኢ-ዴሞክራሲያዊ ነው። መንግሥትም ሆነ ሻጭ የየራሳቸውን ፍላጎትና ጥቅም ለማስከበር ይተጋሉ እንጅ ለሸማቹ ያን ያህል ደንታ የላቸውም ማለት ይቻላል። ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ለሁለቱ ምክር ቤቶች፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በአዲሱ መንግሥት ምስረታ ንግግራቸው መንግሥታቸው የዋጋ ግሽበቱንና የኑሮ ውድነቱን ለማስተካከል ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሰራ ቃል ቢገቡም የኑሮ ውድነቱን ከሚያባብሱ ምክንያቶች አንዱ የሆነውን ሕገ ወጥ የግብይት ሥርዓት ለማስተካከል አስተዋጽዖ ይኖረዋል ተብሎ የሚጠበቀውን”የንግድ ውድድርና የሸማች ጥበቃ ባለስልጣን” እንዲታጠፍ መደረጉ እርስበርሱ ይጣረሳል። በተለይ መንግሥት በ “የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው “አባዜ ሻጭ ላይ የሚፈጥራቸው ማንኛውም ጫናቸው መዳረሻቸው ሸማቹ እንደሆነ እያወቀ እንኳ ጫናውን ቀለል ለማድረግ አያስብም።
ከለውጡ በፊት በነበሩ አስርና ከዚያ በላይ ተከታታይ ዓመታት የተመዘገበው “ዕድገት “መንግሥት በብድር በእርዳታና ብር በማተም ከፍተኛ ካፒታል በማፍሰስ ዕውን ያደረገው ስለነበር እና የአገሪቱ ኢኮኖሚ ሊጎርሰው ከሚችለው በላይ ስለነበር ለተከታታይ 20 እና ከዚያ በላይ ዓመታት የዋጋ ግሽበቱ በሁለት አኃዝ ሲቀጥል አይቶ እንዳለየ በቸልታ አልፎታል። የዋጋ ግሽበቱን ወደ ነጠላ አኃዝ ለማውረድ የማክሮ ኢኮኖሚ በተለይ የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያ ቢያደርግ ያስመዘግብ የነበረውን ባለሁለት አኃዝ ኢኮኖሚያዊ “ዕድገት “ስለሚገታውና ፖለቲካዊ ነጥብ ስለሚያስጥለው ሕዝቡን በዋጋ ግሽበትና በኑሮ ውድነት አለንጋ ማስገረፍን መርጧል። የታክስ ፖሊሲውም ሸማቹን ለተደጋጋሚ ታክስ የሚዳርግ ከመሆኑ ባሻገር ሻጩ ላይ የሚጣል ታክስና ግብር የማታ ማታ እንደ ትኩስ አሎሎ ወደ ሸማቹ የሚወረወር መሆኑን እያወቀ በዚሁ የተዛባ ፖሊሲው ገፍቶበታል። የግብር መሠረቱን ከማስፋት ይልቅ በተወሰኑ የግብር ዘርፎች ላይ የሙጥኝ ማለትን መርጧል። ባለዝቅተኛ ኑሮውን በተለይ የወር ደመወዝተኛውን በተደራራቢ ታክስና ግብር ጀርባውን እያጎበጠ በዚሁ ዜጋ ስም በተገኘ ብድር በተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሚገቡ ባለፀጋዎች የግብር፣ የታክስ እፎይታ ጊዜ ይቸራል። ሕዝብ የቆጠበው ገንዘብ ሳይቀር ማኑፋክቸሪንግን እና ግብርናን ለማበረታታት በሚል ያለ መያዣ የሀገርን ሀብት እንደ ጠላት ገንዘብ በታትኖታል።
የሸቀጥ፣ የአገልግሎት ሻጩ መንግሥት የጣለበትን ሁሉንም የግብር፣ የታክስ ዕዳና የቤት ኪራይ እንዳለ ወደ ሸማቹ ያስተላልፋል። ብዙኃኑ የቆጠበውን ገንዘብ ከባንክ ሲበደር የሚከፍለው ወለድ ሳይቀር በተዘዋዋሪ ከብዙኃኑ ከሸማቹ በእጅ አዙር በንግድ ስም ይቀበለዋል። ስለሚከራየው ሱቅ፣ የገበያ አዳራሽ፣ ቢሮ ዋጋም አይጨነቅም። በእጅ አዙር ከሸማቹ እንደሚሰበስበው እርግጠኛ ነዋ። በገበያ ሰንሰለቱ ለተሰገሰጉ ደላላዎች ስለሚከፍለው ኮሚሽን አያሳስበውም አስልቶ ሸማቹ ላይ ይጥለዋል። ወደ ውጭ ልኮ ስለሚሸጠው ቡና፣ የቅባት እህል፣ የፋብሪካ ውጤት፣ ወዘተረፈ ዋጋ መውረድ አይጨነቅም። በተለይ አንዳንዱ ሥነ ምግባር የጎደለው ኤክስፖርተር ከስሮ ሽጦ በሚያገኘው የውጭ ምንዛሪ በአስመጭነት ስም በሚያስገባው ሸቀጥ ለዚያውም ጥራቱ እዚህ ግባ በማይባል በሳምፕል በተመረተ መናኛ ሸቀጥ ከ100 እስከ 1000 በመቶና ከዚያ በላይ በማትረፍ ወደ ውጭ ሲልክ የከሰረውን በእጅ አዙር በብዙ እጥፍ የሸማቹን ጉሮሮ አንቆ ይቀበላል።
በአገሪቱ የትርፍ ሕዳግ የሚባል ነገር አይታወቅማ። በዓለማችን የትርፍ ሕዳግ የሌላትም ሆነ በነፃ ገበያ ስም ስግብግብ ነጋዴ እንደ ፈለገ የሚፈንጭባት፣ የሚፋንንባት አገር ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ትቀራለች !? የነፃ ገበያ አባት በሚባሉት ምዕራባውያን እንኳ በማንኛውም ሸቀጥና አገልግሎት ላይ የትርፍ ሕዳግ ተጥሎበት እያለ እኛ በመንግሥት ቸልተኝነት አሳራችንን እናያለን። በተለይ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የተከሰተው የኑሮ ውድነት፣ የዋጋ ግሽበት፣ ቀማኛ የንግድ ሥርዓት የሕዝቡን ታጋሽነት፣ ቻይነት በእጅጉ እየተፈታተነው ይገኛል። የህንድን የሽንኩርት፣ የሱዳንን የዳቦ እና የቱኒዚያንን አጠቃላይ የኑሮ ውድነት አብዮት ከአብዮቶች ሁሉ እናት ከፈረሳይ አብዮት ጋር ቀምሮ ነግ በኔ ማለትን መዘንጋት አያስፈልግም። በግብር ከፋዩ ዜጋ ገንዘብ ድጎማ በሌለ የውጭ ምንዛሪ የሚገባ ስንዴ፣ ዘይት፣ ስኳር፣ መድኃኒት፣ ወዘተ. ሳይቀር ለስግብግቦች በአንድ ጀምበር መክበሪያ ሲሆን ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ እግሩን የሚጎትትበት ምክንያት ለብዙዎቻችን እንቆቅልሽ ሆኖ ቀጥሏል።
ባለፉት 27 ዓመታት በነፃ ገበያ ስም እንደ ኢትዮጵያውያን ሸማቾች ፍዳውን ያየ አሳሩን የበላ ሸማች የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ሥነ ምግባር የጎደላቸው ስግብግብ ነጋዴዎች፣ አገልግሎት አቅራቢዎች እና ከሻጩና ከሸማቹ ድምር ቁጥር የሚበልጡ ደላላዎች ጋር በማበር ሸማቹን በኑሮ ውድነት በችጋር እየጠበሱት ነው። መንግሥት በነፃ ገበያ ስም ስግብግብ ነጋዴውን እና ደላላውን ስድ መልቀቁ፣ አይቶ እንዳላየ፣ ሰምቶ እንዳልሰማ ማለፉ ግንባር ፈጥረው ሊባል በሚችል ሁኔታ ሸማቹን ቁም ስቅሉን እንዲያሳዩት የፈቀደ አስመስሎታል።
በመላው ዓለም እንደሚደረገው የሸማቹን መብት እና ጥቅም የማስከበር ጉዳይ ለመንግሥት ብቻ በመተው ዘላቂ እና ስርነቀል ለውጥ ስለማያመጣ ሸማቹ መብቱን፣ ጥቅሙን፣ ጤንነቱን የሚያስጠብቅለት ጠንካራ፣ ሐቀኛ አገር አቀፍ የሸማቾች ማኅበር ማቋቋም ግድ ስለሆነ የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ባለፈው ግንቦት ተቋቁሞ ሥራ ጀምሯል። ማኅበሩ የሸቀጥና የአገልግሎት ሸማቹን መብትና ጥቅም የሚያስከብር ብቻ ሳይሆን ግዴታውንም ሆነ ኃላፊነቱን የሚያስገነዝብ ይሆናል። ማኅበሩ የነፃ ገበያ ውድድርን ከማበረታታት ባሻገር፣ እውነተኛ የገበያ መረጃዎችን ለሸማቹ ለማድረስ ያግዛል። ከዚህ በተጨማሪም ያልተገባ የንግድ ውድድርን ለመከላከል አስተዋፅዖ ይኖረዋል።
ዓለም አቀፉ የሸማቾች ጥበቃ ሕግ ሸማቾች የመምረጥ፣ መረጃ የማግኘት፣ የመደመጥ፣ የመካስ፣ የጤነኝነት፣ የተሟሉ መሠረታዊ ፍላጎቶችን፣ አማራጭ አገልግሎትና ሸቀጣሸቀጦችን፣ ስለሸቀጦችና አገልግሎቶች አጠቃቀም መረጃ የማግኘት፣ ወዘተ . መብት እንዳላቸው ያትታል። የሸማቾች ጉዳይ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1985 ስለ ሸማቾች መብት ጥበቃ ባወጣው እና አባል አገራት እንዲተገብሩት ጭምር በሚያሳስበው ሕግ አገራት፣ መንግሥታት የሸማቾችን መብት፣ ጥቅም የሚያስከብሩ አሠራሮችንና አደረጃጀቶችን የመዘርጋት ኃላፊነት እንዳለባቸው ያሳስባል። ከእነዚህ ውስጥ የሸቀጦችን እና አገልግሎቶችን ደረጃ ከጥራት፣ ከጤና አንጻር ማውጣት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
ትኩረት ለሸማቹ !
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 17/2014 ዓ.ም