ባቡሬ… ባበሬ..ባቡሬ
ባቡሬ ይዞኝ ገባ ድሬ
ከ120 ዓመታት በፊት ወደ ኋላ፤ ከምዕተ ዓመት በላይ በትውስታ የተሞላ ጎዞ ከሼ መንደፈር ትዝታ። ሺ መንደፈር የድሬዳዋ ባቡር ጣቢያ ነው። ብዙዎች ስያስቡት አሻግሮ ወደ ኋላ የሚመልስ ዘመን አይሽሬ ትዝታ፣ ፈርጀ ብዙ ገጠመኝ፣ የጠበቀ ትስስር፣ ከባቡር እና ተጓዦቹ ጋር ይነሳል።
ይሄው ከመቶ ዓመታት በላይ ከመሐል አገር አዲስ አበባ እስከ ምስራቅዋ ፀሀይ መውጫ ድሬዳዋ ብሎም ጅቡቲ ድረስ በረጅሙ ተዘርግቶ ተሳፋሪን ያመላልሳል፣ ዕቃዎች ያጓጉዛል፣ ለብዙዎች የሕይወት ቁርኝት ሰበብ የኢኮኖሚ ለውጥ መሠረት ሆኗል።
የአገሪቱ ታሪክ ከኢኮኖሚ ጋር ተጋብቶ ክፍለ ዘመን የተሻገረ፤ከጎረቤት አገር ጋር በማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁናቴ ያስተሳሰረ ታሪካዊ ተቋም የዛሬ የሳምንቱ በታሪክ የታሪክ ማውሻችን ትኩረት ነው ።
ስያሜ
ቀድሞ ስያሜው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የምድር ባቡር ኩባንያ ይባል ነበር። በኋላ ላይ የኢትዮጵያ-ፈረንሳይ የምድር ባቡር ኩባንያ የተሰኘው ቀጥሎም ደግሞ የኢትዮ-ጅቡቲ የምድር ባቡር በመሰኘት ስሙን ለዋውጧል። ከመቶ ዓመታት በፊት በየብስ ትራንስፖርት ኢትዮጵያን የተዋወቀው ባቡር። አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ይሰኛል።
የጅማሮው መነሻ
አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለሕዝባቸው በማስተዋወቅ የሚታወቁት አፄ ምኒሊክ አንድ ነገር ይሰማሉ። አፄ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ ያሰርዋቸውን ነጮች ለማስለቀቅ እንግሊዛውያን በቀይ ባህር ወደብ በኩል የተለያየ መሳሪያ ምድር ላይ ተነጥፎለት የሚጓዝ ተሽከርካሪ አስገብተው ነበር፤ የሚል ወሬ ሰምተው ስለሱ መጠየቅ ቀጠሉ።
ከዚያም ስለ ባቡር ቴክኖሎጂ ከቅርብ ሰዎቻቸው መረጃ አጣርተው ይህ አይነት ተሽከርካሪ አገራቸው ላይ ይኖር ዘንድ ማሰብ ጀመሩ። በወቅቱ የእሳቸው ግዛት ሸዋ ነበረና የባቡር ሀዲዱን ከሸዋ ውጪ ማዘርጋት እንደማይችሉ ገባቸው። ለዚህም ጊዜ ጠበቁ። ንጉሱ በ1882 የንጉሠ ነገሥትነት ዙፋን ላይ ከወጡ በሁዋላ ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገር ጅቡቲ ጋር በየብስ ትራንስፖርት ለማገናኘት አቀዱ። በሁለቱ አገራት መካከል እንደ አማካይ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል ቦታ በአውሮፓውያኖቹ ይጠቆማሉ።
የባቡር ሐዲዱ በድሬዳዋ በኩል ከመዘርጋቱ በፊት በሐረር በኩል እንዲሔድ ታስቦ ነበር። የመጀመያው ባቡር በእንፋሎት (በስቲም) የሚጓዝ በመሆኑ ውሃ አስፈላጊ ሆነ። ድሬዳዋ የውሃ ክምችቷ ከሐረር የበለጠ መሆኑ፣ የመሬት አቀማመጧ ሜዳማ መሆኑ ለባቡር ዝርጋታው ተመራጭ እንድትሆን አደረጋት።
ጥቆማውን ተቀብለው ግንባታው በ1882 ዓም ተጀመረ። ከጅቡቲ ተነስቶ አዲስ አበባ የሚደርሰው የባቡር ሀዲድ ዝርጋታም ተከናውኖ በ1895 ዓ.ም. ታህሳስ 14 ምሽት ሁለት ሰዓት የመጀመሪያው ባቡር ከጅቡቲ በመነሳት በርካታ በረሀማና ሞቃታማ አካባቢዎችን አቋርጦ ድሬዳዋ እንደገባ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ። የባቡሩ እዚያ ደረጃ መድረስ አዲስ ነገርም አብሮ ፈጠረ። ለኢትዮጵያ አዲስ የየብስ ትራንስፖርት ከማስተዋወቁም ባሻገር የበረሀዋ ንግስት ድሬዳዋ ከተማ መወለድ ምክንያት ሆነ።
የባቡር ሐዲድ ግንባታው ሙግቶች
ዛሬ አባይ ግድብ ላይ የሚታየው የውጪ ኃይሎች ተፅዕኖና ተገቢ ያልሆነ የመልማት መብታችንን የሚጻረር ተግባር ያኔም የባቡር ሐዲዱን ለመገንባት ሲታሰብ አጋጥሟል። ኢትዮጵያ የልማት ግስጋሴዋን የሚፃረሩ የውጪ አገራት ያኔም አጋጥመዋል። አፄ ምኒሊክ የባቡር ሐዲዱን ለማስጀመር ወጥነው ሲነሱ ወቅቱ ከጣሊያን ጋር እሰጣ አገባ የገቡበትና የአድዋ ጦርነት የተቃረበበት ነበርና ጣሊያን ግንባታውን ለማካሄድ ከተባበረችው ፈረንሳይ ጋር ፕሮጀክቱን ለማስቆም ሞክራም ነበር።
እንግሊዝም በወቅቱ የዜይላ ወደብን ትጠቀምበት ስለነበር የባቡር ፕሮጀክቱን ግንባታ የያዘችው ወደብ ጥቅም ይቀንሳል ብላ ስላመነች ኢትዮጵያ ከፈረንሳይ ጋር የገባችው ውል እንዲፈርስ ብዙ ጥረት አድርጋለች። የወቅቱን ክስተት በተመለከተ ከተፃፉ የታሪክ ድርሳናት መካከል የአልፍሬድ ኤልግን ታሪክ የፃፈው ኬለር የተባለ ደራሲ መጽሐፍ ውስጥ አፄ ምኒሊክ የባቡር ሐዲዱን ለማዘርጋት የነበራቸውን ጉጉትና በተለየ መልክ ይተርከዋል።
ሲዊዛዊው አልፍሬድ ኢልግ የአፄ ምኒሊክ የልብ ወዳጅና ልዩ አማካሪ የቴክኒክ ሰው መሆኑ ልብ ይሏል። አፄ ምኒሊክ ባቡሩን ለማሰራት እጅግ ጓጉተው ስለነበር ከውጪ የሚመጣውን ተፅዕኖ ተቋቁመው የባቡር ሐዲዱን ለማዘርጋት የተለያዩ ሙከራዎችን ያደርጉ እንደነበረና በዚህም የጅቡቲ ቅኝ ገዢ ከሆነችው ፈረንሳይ ጋር መነጋገራቸውን ፣ ነገር ግን በወቅቱ ከጣሊያን ጋር ወደ መካረር ተገብቶ የአድዋ ጦርነት በመቀስቀሱ የግንባታው ጉዳይ ቆሞ እንደነበር መጽሐፉ ይተርካል።
ከአድዋ ጦርነት በኋላ አፄ ምኒሊክ የባቡር ሐዲድ ዝርጋታ እቅዳቸውን በአማካሪያቸው ኤልፍሬድ ኢልግ ታግዘው ማድረጋቸው ቀጠሉ። እንግሊዞችና ፈረንሳዮች በፅኑ የተቃወሙት የሐዲድ ግንባታ ኢትዮጵያ በአድዋ ላይ በተቀዳጀችው ድል ማግስት እንግሊዝ ስትለሳለስ ፈረንሳይ ግንባታውን ለመተባበር ፍቃደኛ ሆና በድጋሚ ለመጀመር ተወሰነ።
በነገራችን ላይ የባቡር ሐዲድ ግንባታ በውጪ አገሮች ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥም በአጼ ምኒሊክ የቅርብ ሰዎች ጭምር ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። ከእነዚህ የቅርብ ሰዎች መካከልም እቴጌ ጣይቱ አንዷ ነበሩ። ምክንያታቸው ደግሞ ፈረንጆች ሐዲዱን ተጠቅመው ድጋሚ ይወሩናል የሚል ነበር። ብቻ እንደምንም አጼ ምኒሊክ ጫናውን ተቋቁመው ባቡር ለአገራቸው ለማስተዋወቅ በዚያም ለመጠቀም ጥረታቸውን ቀጠሉ። በዚህም የወጠኑትን ከግብ ማድረስ ችለው ባቡር በኢትዮጵያ ምድር መተዋወቅ ቻለ።
ከአዲስ አበባ ተነስቶ እስከ ድሬዳዋ ብሎም ጅቡቲ የደረሰው የባቡር አገልግሎት ባቡሩን ያንቀሳቅስ የነበረው የእንፋሎት ከዚያም ከሰል ነበር። አሁን ደግሞ ዘመን በወለደው ቴክኖሎጂ ተሻሸሎ በኤሌክትሪክ ፍጥነቱን ጨምሮ እየተመዘገዘገ ይገኛል። አዲሱ የባቡር መስመር ነባሩን መስመር እየተወ የተገነባ ሲሆን፣ የነባሩ መስመር ቅሬተ አካል የሆኑት የብረት ሀዲዶች እዚያም እዚህም ሲታዩ የቀደመውን ትዝታ ይቀሰቅሳሉ። ጥንት ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያን ለመለወጥ አገሪቱን ለማሳደግ ያደረጉት ጥረት ያሳያል።
የባቡር ትራንስፖርት መጀመር በሁለቱ አገራት ሕዝቦች መካከል የፈጠራቸው በጎ ግንኙነቶች ዛሬም ድረስ ቀጥለዋል። ከ100 ዓመት በላይ የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር በኢትዮጵያውያንና በጅቡቲያውያን መካከል ከማኅበራዊ መስተጋብሩ ባሻገር የአገራቱ ኢኮኖሚና የንግድ ልውውጥ የጀርባ አጥንት ሆኖ ዘልቋል። ባቡር ጣቢያዎች አካባቢዎች እንደ ውሀ፣ ቆሎ፣ አትክልት ያሉ የምግብ ግብአቶችን ከሚሸጡት ጀምሮ አብዛኛው የአገሪቱ የገቢ ወጪ ንግድ በዚሁ ባቡር ላይ የተመሰረተ ነው ።
በአዲስ አበባ የሚገኘው የቀድሞው የባቡር ጣቢያ ለገሀር ላይ የነበረ ሲሆን፣ የአሁኑ ደግሞ አዲስ ከአበባ ከተማ ብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ሰበታ ላይ የተቋቋመ ነው። የቀድሞው ባቡር ወደ አዲስ አበባ ከተማ ሲገባ በሚያሰማው ከፍ ያለ ድምጽ ስለሚታወቅ ነዋሪው ጓጉቶ ይጠብቅ ነበር፤ ምክንያቱም ሁሉም ሰው ይሠራል፤ ሁሉም ገቢ ያገኛል። ኢትዮጵያ የባቡር መስመሩን ከአዋሽ ወደ ኮምቦልቻ ወልዲያ ሀራና መቀሌ ለማስፋፋት እየሰራች ትገኛለች።
ይህንን ጽሑፍ ስናዘጋጅ ልዩ ልዩ ድህረገፆች፣ኬለር የአልፍሬድ ኢልግ ታሪክ የፃፈው መጽሐፍና አፄ ምኒሊክ የተሰኘው የጳውሎስ ኞኞ መጽሐፍትን በምንጭነት ተጠቅመናል። ስለ ኢትዮጵያ ቸር ያሰማን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 17/2014 ዓ.ም