ከለውጡ በፊት ዲያስፖራው በአገሩ ልማት እንዲሳተፍ፣ ኢንቨስት እንዲያደርግ ፣ለቤተሰቡ የሚልከውን ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ እንዲልክና የአገሩ ዲፕሎማት እንዲሆን ለማድረግ ያላሰለሱ ጥረቶች ሲደረግ ቢቆይም የተመዘገበው ውጤት አመርቂ አልነበረም።
ይህ ሊሆን የቻለባቸው የተለያዩ ተጨባጭ ምክንያቶች ቢኖሩም ከሁሉም በላይ ጎልቶ የሚጠቀሰው ግን በአገሪቱ ግላዊና ፖለቲካዊ ነፃነት አለመኖር፣ የመንግሥት ፖሊሲዎችና አመለካከቶችም ለዲያስፖራውና ለግሉ ዘርፍ አመቺ አለመሆኑ፣ ዘረኝነትና ሌብነት መስፋፋት፣ እና በሌሎችም ምክንያቶች ነው፡፡ ይህ እንዳለም ሆኖ፣ በተጨማሪነት ደግሞ ዲያስፖራው እና መንግሥት አንዱ አንደኛውን እንደጠላት ሲተያይ ኖሯል፡፡
ነገር ግን በአገሪቱ የመጣውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ በውጭ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች በመንግሥት ላይ የነበረውን የጠላትነት አመለካከት በመቀየር ፊታቸውን ወደ አገራቸው እንዲመልሱና በአገራቸው ጉዳይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ የሚቻልበት ልዩ ዕድል የተፈጠረበት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ተከፍቷል፡፡
በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎም መንግሥት በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ባመቻቸው ዕድል መሰረት በርካታ ዲያስፖራዎች በፖለቲካው፣ በኢንቨስትመንት፣ በንግድና በቱሪዝም ዘርፎች በመሰማራት ራሳቸውንና አገራቸውን በመጥቀም ላይ ይገኛሉ፡፡
በተለይ የትግራይ ወራሪ ቡድን ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ተቀናጅቶ አገሪቱን ለመበተን በግንባር ከከፈተው ጦርነት ጎን ለጎን የከፈተውን ሐሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ዲያስፖራው ማኅበረሰብ በመቀልበስ የኢትዮጵያን እውነትና ሐቅ በአንድነት በዓለም አደባባይ በመግለጽና በማስረዳት ትልቁን የጦርነት ዘመቻ በመምራት ድል አድርገዋል። እንዲሁም ዲያስፖራው ምዕራባውያንና አሜሪካ የኢትዮጵያን እውነቱን በመሸፈን የሐሰት ፕሮፖጋንዳ በማራመድ በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ገብቶ በመፈትፈት አገሪቱን ለማፈራረስ የሸረቡትን ሴራ በመቃወም “በቃ” ወይም “#Nomore” ዘመቻን በመላው ዓለም ከማቀጣጠል ባለፈ የመላ አፍሪካ አገራት ትግል እንዲሆን አስችሏል።
ከዚህ ባሻገር የአሸባሪው ወራሪ ቡድን በከፈተው ጦርነት አገሪቱ ከገባችበት የኢኮኖሚ ቀውስ እንድታገግምና በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ እንዳልሆነ ለዓለም ማኅበረሰብ በማሳየት ረገድ ዲያስፖራው ማኅበረሰብ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ለማስቻል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አንድ ሚሊዮን ዲያስፖራዎች ለገና በዓል ወደ አገራቸው ገብተው በጦር ግንባር የተገኘውን ድል በአገራቸው ከወገኖቻቸው ጋር በደስታ እንዲያከብሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የእንጀራ ጉዳይ ሆኖባቸው አካላቸው ከአገራቸው ቢርቅም ሁሌም በመንፈስ ከእናት አገራቸው የማይለዩት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የሆኑት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የጠቅላይ ሚኒስትሩንና የእናት አገራቸውን የቁርጥ ቀን ጥሪ ተቀብለው ከወዲሁ ወደ አገራቸው እየተመሙ ይገኛሉ።
ከዚህ አኳያ የእናት አገሩን የቁርጥ ቀን ጥሪ ተቀብሎ የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ ወደ አገር ቤት ለሚገቡ ዲያስፖራዎች በመንግሥት በኩል እየተደረገ ስላለው ዝግጅትና ኅብረተሰቡ በበኩሉ ሊወጣው ስለሚገባ ኃላፊነት በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህል፣ ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው ከሰሞኑ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።
ዶክተር ሂሩት እንደገለጹት፤ ሁሉም እንደሚያውቀው ዓለም የኢትዮጵያን እውነት በመሸፈን የጠላትን የሐሰት ፕሮፖጋንዳ እያናፈሰ እና እያራመደ ይገኛል። ይህንን ተከትሎ ዲያስፖራ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን የሕልውና ዘመቻ በመቃወም ሐሰተኛ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻውን በመታገል በድል የተወጡ ጀግኖቻችን ናቸው። በተለይ የሐሰት ፕሮፖጋንዳውን ለመቀልበስ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን በመዝመትና የተለያዩ የተቃውሞ ሰልፎች በተሳካ ሁኔታ በዓለም አደባባይ በማድረግ በድል የተወጡ ጀግኖች ናቸው። ዓለም የኢትዮጵያን እውነት ሲክድ የኢትዮጵያን እውነት ለዓለም በማሳወቅና በማስረዳት ረገድ ከፍተኛ ዘመቻ በማድረግ በድል አድራጊነት የተወጡ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ናቸው።
በተለይ ዲያስፖራው ማህበረሰብ ምዕራባውያንና አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት በመቃወም ዓለምን ያጥለቀለቀውን የ”በቃ” ወይም “#Nomore” ዘመቻን በመጀመርና ዘመቻውን በማቀጣጠል መላ የዓለም አገራትን ከማዳረስ ባሻገር የመላ አፍሪካ አገራት ትግል እንዲሆን ማስቻላቸውን ዶክተር ሂሩት ጠቅሰዋል ። ስለዚህ አገሪቱ በሐሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ዘመቻው የተከፈተባትን ትልቁን የጦርነት ግንባር በመፋለም ግንባር ሲመሩ የቆዩና ድል ያደረጉ ዲያስፖራ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እናት አገራቸው ያቀረበችላቸውን ጥሪ ሳያቅማሙ ተቀብለው ወደ አገራቸው ሲገቡ ክብር ያለው አቀባበል ማድረግና ጥራቱ የተጠበቀ አገልግሎት መስጠት ከመንግሥትና ከሁሉም ዜጋ ይጠበቃል።
በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዲያስፖራው ባደረጉት ጥሪ መሠረት በአገር አቀፍ ደረጃ እንግዶችን ለመቀበል ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ ነው። በዚህም መሠረት አዲስ አበባ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ዋና ከተማ ከመሆኗ አንጻር የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የመጀመሪያ መዳረሻ ከተማ ናት። በከተማ ደረጃ ኮሚቴ ተቋቁሞ ዲያስፖራዎችን ለመቀበል ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።
ዶክተር ሂሩት እንዳሉት፤ ከሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ አኳያ እየተደረጉ ያሉ የዝግጅት ሥራዎችም ከምንጊዜውም በላይ ጀግኖቻችንን ለመቀበል ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል። በተለይ ከአየር መንገድ ጀምሮ እስከሚያርፉበት ሆቴል ድረስ ያሉ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ለእንግዶች መልካም አቀባበል ከማድረግ ባለፈ ደረጃውን የጠበቀና የሚያረካ አገልግሎት ለመስጠት ሰፊ ዝግጅት አድርገዋል። ደረጃውን የጠበቀና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት ብቻ ሳይሆን አገልግሎቱን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ለእንግዶች ያላቸውን አክብሮት ለመግለጽ ሁሉም የዘርፉ ተዋናይ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት የአገልግሎት ዋጋ ሲቀንሱ የቀነሱበት ዋና ምክንያት ጀግኖች ዲያስፖራ እህትና ወንድሞቻችን ለአገራቸው ለከፈሉት መስዋዕትነት በክብር ለመቀበልና ለማስደሰት ነው ። በዚህም ሆቴሎች፣ ለቱሪስት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች፣ አስጎብኝ ድርጅቶች በሙሉ ለሚሰጡት አገልግሎት ከ30 በመቶ ጀምሮ ቅናሽ አድርገዋል። ዝግጅታቸውን በስፋት በጥራት እና በብቃት አጠናቀው እንግዶቻቸውን በጉጉት እየተጠባበቁ ነው። ከዚህ አኳያ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በዚህ መልክ መዘጋጀታቸውን ቢሮው ሰፊ ክትትል፣ ድጋፍና ምክክር በማድረግ እየተከታተለ ይገኛል።
ኢትዮጵያ የታወቁ ኃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት ያሏት አገር ናት ። ከነዚህ በዓላት በተጨማሪ በከተማይቱ አገራቸውን ይበልጥ የሚያውቁበትና የኢትዮጵያን ምርት የሚገዙበት ትልልቅ ባዛሮች፣ የሙዚቃ ድግሶች በዓይነቱ እጅግ ለየት ያለ እስካሁን ያለውን ትግላችን፣ ንቅናቄያችንንና ዘመቻችንን የበለጠ ከፍ የሚያደርግ የሙዚቃ ኮንሰርትና ድግስ ተዘጋጅቷል። በጣም አጓጊና በአገሪቱ የሲኒማ ታሪክ ትልቅ ቦታ ያለው እንዲሁም ለዲያስፖራው ትልቅ ትርጉም የሚሰጥ ሲኒማ ቤት ይመረቃል። ትልልቅ የሆኑ የግጥም ምሽቶች ተዘጋጅተዋል። በጥቅሉ ከባህልና ቱሪዝም አንጻር እጅግ የሚያዝናና እና የሚያስደስት ጊዜ የሚያሳልፉበት፣ ልምዳቸውንና እውቀታቸውን የሚያካፍሉበት በተለይም በሰፊው የኢትዮጵያን ባህል፣ ወግና የሚታደሙበትና ባህላዊ አገራቸውንንና ታሪካቸውን የሚያስታውሱበትንና የሚያስተዋውቁበትን ጌጣጌጥና ቁሳቁስ የሚሸምቱበት ይሆናል። ራሳቸውን ዘና አድርገው የሚደሰቱበት የተለያዩ የኪነጥበብ ዝግጅቶች ተዘጋጅተዋል። ይህም የበለጠ አገራቸውን የሚወዱበት፣ የሚናፍቁበት እና የአገራቸውን ክብር በኩራት የሚያዩበት ልዩ ጊዜ እንደሚያሳልፉ በሙሉ እምነት መግለጽ ይቻላል።
በሌላ በኩል የቱሪስት መስህብ ቦታዎቻችን ከምንጊዜውም በላይ ምቹና አስፈላጊ አገልግሎቶችን በማሟላት ዝግጁ ሆነዋል። አስጎብኚዎችና አስጎብኝ ድርጅቶች ደግሞ የጉብኝት መርሐ ግብሮችን ወይም ፓኬጆችን በማዘጋጀት የተለያዩ ጉብኝቶችን አዘጋጅተዋል። ለቱሪስት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶችም ወይም ማህበሮች ታክሲዎቻቸውን በማዘጋጀት ምቹ በማድረግ እና የዋጋ ቅናሽ በማድረግ ዝግጁ ሆነዋል። ስለዚህ ከቱሪዝም አንጻር ሙሉ ዝግጅቱ ተጠናቋል።
ጀግኖቻችን ወደ አገራቸው ሲገቡ የከተማዋ ነዋሪዎች ከምንጊዜውም በላይ የደመቀ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ማድረግና ክብር መስጠት ይገባል ያሉት ዶክተር ሂሩት፤ በተቋማት፣ በገበያና በመዝናኛ ቦታዎች ለጀግኖቻችን ሰላምታ ማቅረብ የሁሉም ነዋሪ መርሕ ሊሆን ይገባል። በዚህም ሂደት የኢትዮጵያን አብሮነትና ወንድማማችነት የበለጠ የምናበለጽግበት ትልቅ አጋጣሚ ነው። የከተማዋ ነዋሪ የቱሪዝም መዳረሻ ከተማ ውስጥ መኖሩን አውቆ ጀግኖቻችንን ወደ መዲናዋ ሲመጡ በክብር ከመቀበል በተጨማሪ መረጃ በመስጠትና አስፈላጊውን ድጋፍ ከምንግዜውም በላይ ማድረግ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው ።
መዲናችን ያላት የአልጋ አቅም 20 ሺ ነው ያሉት ዶክተር ሂሩት፤ የአልጋ ችግር ሊገጥም ስለሚችል ከሆቴል ውጪ ያሉ አፓርትመንት፣ ቪላ ቤት፣ የእንግዳ ማረፊያ ያላቸው ግለሰቦች አስፈላጊውን መሠረተ ልማት በማሟላት ለእንግዳ ማረፊያ ማዘጋጀት አለባቸው። ዝግጅቶቻቸውን ሲጨርሱ በሚኖሩባቸው ክፍለ ከተሞች ባሉ የባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤቶች ቀርበው እንዲያስመዘግቡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ይህም በመዲናዋ ሊገጥም የሚችል የአልጋ እጥረት ካለ ከወዲሁ ዝግጁ በመሆን ሊገጥም የሚችለውን ችግር ቀድሞ በመረዳት ለመፍታት ታስቦ ነው። ስለዚህ ቪላ ቤት፣ አፓርትመንት ያለው እና የእንግዳ ማረፊያ ብሎ ሰርቶ ክፍት የሆኑ ቤቶች ያላቸው ባለሃብቶች በሙሉ በተመጣጣኝ እና ተገቢ በሆነ ዋጋ ለማከራየት የሚያስችል ዋጋ በመተመን በሚኖሩበት ክፍለ ከተማ ባሉ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤቶች በመቅረብ እንዲያስመዘግቡ ጥሪ ቀርቧል። እንዲሁም ጀግኖች ለአገራቸው ለከፈሉት መስዋዕትነት በነጻም የማረፊያ ቤት እሰጣለሁ፣ አስተናግዳለሁ የሚል አካል ካለ በተጠቀሰው ቦታ በመቅረብ በማስመዝገብ ለወገኑ አገልግሎቱን መስጠት ይችላል ብለዋል።
በአጠቃላይ አሁን ላይ የገጠመንን ችግር አብረን በአንድነት ቆመን እንደተወጣነው ሁሉ ከዚህ በኋላ ደግሞ ብሔር ብሔረሰቦችን መሰረት ያደረገው የኢትዮጵያ ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት እጅግ ተጠናክሮ በኅብረት እና በፍቅር መኖር እንድንችል ዲያስፖራ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን ሲመጡ፤ ከምንጊዜውም በላይ አብሮነትን በማሳየት፣ በማስተናገድ፣ የደመቀ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል በማድረግ እህት ወንድሞቻችን አይረሴ ትውስታ እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራ ከአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ይጠበቃል። የሚመጡት እንግዶች የበለጠ አገራቸውን የሚወዱበት፣ የሚያከብሩበት በወገናቸው የሚኮሩበት አይረሴ ጊዜ የሚያሳልፉበት ጊዜ እንዲሆንላቸው ሁሉም የመዲናዋ ነዋሪዎች ተገቢውን ወይም የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል። ስለዚህ ከሁሉም ጋር ተዋዶና ተፋቅሮ የሚኖረው የመዲናዋ ነዋሪም ጥሪውን ተቀብሎ በተግባር እንዲያሳይ ዶክተር ሂሩት ጥሪ አቅርበዋል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 17/2014 ዓ.ም