አሸባሪው ሕወሓት ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ተጠቅሞበት የነበረውን የመነጣጠል ስልት መውረሱ የወራሪው ፋሽስት ከፋፍለህ ግዛ የክፋት ሴራ ወራሽ እና አስጠባቂ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
ጣሊያን ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመውረር በመጣበት ጊዜ “ጸባችን ከሸዋው መኳንንት ከአጼ ምኒልክ ጋር ነው፣ እናንተን የአጼ ዮሐንስ ዘሮችንማ ለንግሥና ነው የምናበቃችሁ፣ ዘመናዊ ጦር እናስታጥቃችኋለን፣ እናንተ ብቻ ምኒልክን በመውጋት አግዙን” በማለት አሸባሪው ሕወሓት እንዳደረገው አማራውን ብቻ ነጥሎ ለማጥቃትና ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ይጥር ነበር፡፡
የፋሽስቱ እኩይ ዓላማ ወራሽና የምዕራባውያን ኢምፔሪያሊስቶች የግብር ልጅ የሆነው ባንዳው ሕወሓትም ፈጣሪዎቹ ፋሽስቶች እንዳደረጉት “እኛ ጸባችን ከአማራ ልሂቃን እና ከብልጽግና መሪዎች ጋር ነው” በማለት ኢትዮጵያን ከፋፍሎ ለማጥፋት እየጣረ ይገኛል፡፡ ወራሪው የአገር ውስጥ ፋሽስት ይህን ይበል እንጂ በተግባር ግን ጸቡ ከመላው የአማራና የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር እንደሆነ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች የተፈጸሙ ግፎች ይመሰክራሉ፡፡
አሸባሪው ሕወሓት ከፍጥረቱ ጀምሮ ኢትዮጵያ ጠል፣ ከሃዲ ባንዳ ነው፡፡ ፈጣሪዎቹ የውጭ ኃይሎች ጸረ ኢትዮጵያን ርዕዮተ ዓለምን ገና ከውልደቱ ጀምረው በጡጦ እያጠቡ አሳድገው ለወግ ለማዕረግ አብቅተውታል፡፡ ፀረ ኢትዮጵያ ኃይላት ከኢትዮጵያ ጋር ፊት ለፊት ገጥመው ያልተሳካላቸውን ህልም ለማሳካት ኢትዮጵያን እርስ በእርስ በማጋጨት ለማፍረስ ኢትዮጵያ ጠል ርዕዮተ ዓለም የሚሸከም የአገር ውስጥ ባንዳን እንደ አንድ ፖለቲካ ድርጅት መፍጠር ስለነበረባቸው አድርገውታል፡፡ ለተልኳቸው መሳካት አሸባሪው ሕወሓትን መስርተው ኢትዮጵያን ለማፈራረስና ኢትዮጵያውያኑን በእጅ አዙር ለመግዛት ተጠቅመውበታል፡፡
በመሆኑም ባንዳው አሸባሪው ሕወሓት በሕዝብ ትግል ከኢትዮጵያ ጫንቃ ተወግዶ ከአራት ኪሎ ተባርሮ መቀሌ ከመሸገ ጀምሮ የራሱን ርዕዮተ ዓለም ይሸከሙልኛል ያላቸውን ፌደራሊስት ኃይሎች በማሰባሰብና እንዲሁም ትግራይ ውስጥ ራሱ ጠፍጥፎ በሠራቸው ድርጅቶች ወጣቶችን በማሰባሰብ እና በመደገፍ እስከ ግብዓተ መሬት ዋዜማው ድረስ ርዕዮቱን የፋሽስት ወራሪ ተልዕኮን አስቀጥሏል፡፡
ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቅድሚያ ማጥፋት አለብኝ ብሎ በሚያስበው በአማራው ውስጥም እንደ ቅማንት ያሉ ተጻራሪ የፖለቲካ ኃይሎችን በመደገፍ እንደ ፈጣሪዎቹ አማራን ከፋፍሎ ለማጥፋት የቻለውን ሁሉ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዕርዮቱ ተሸካሚ እና ተልዕኮ አስፈጻሚዎች ሕዝቡን በመነጣጠል እና ግጭት በመፍጠር የፈለገውን አካባቢ በቀላሉ ለመዋጥ ልዩነቶች እንዲሰፉ በሁሉም የኢትዮጵያ ግዛት ሰፊ ሥራዎችን(ሴራዎችን) ሲሠራ ኖሯል፡፡
አሸባሪው ሕወሓት ጣሊያኖች ያደርጉት እንደነበረው ትንንሽ ልዩነቶች በመፈለግና እነዚህን ልዩነቶች በማጎን ሕዝቡን በእምነት እና በቋንቋ በመከፋፈል ለእነርሱ እንዲመች ለማድረግ በገንዘብ ጭምር ተዕልኮ አስፈጻሚዎቻቸውን ሲደግፍ ከርሟል፡፡
ቡድኑ የከፋፋይነት እና የነጣጣይነት ተግባሩን ከውጭ ፀረ ኢትዮጵያ ኃይላትና ከፋሽስት ኢጣሊያ የወረሰ ነው ስንል ድርጅቱ በአገር ግንባታው ረገድም በጋራ የተገነባውን ታሪክ ጠልቶ የተመሰረተ ቡድን መሆኑንም ለማጠየቅ ነው፡፡ ከጅምሩም ቢሆን ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ አላት ብሎ የማያምነው ክብር ጠሉ ወራዳው አሸባሪው ሕወሓት ትግራይን ከኢትዮጵያ ነጥሎ እንደ አገር ለመመሥረት ካለው ፍላጎት በመነጨ ዓላማ የኢትዮጵያን የሦስት ሺህ ዓመት አኩሪ ታሪክ ድልድይን ክዶ ነበር የተነሳው፡፡
በመሆኑም ፋሽስት ሕወሓታውያን የትግራይ ሪፐብሊክን ለመገንባት ተቀዳሚ ዓላማቸው ያደረጉ በመሆናቸው በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑም አልነበሩም፡፡ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ለማፈራረስ እና ለመበተን የተመሠረተ ሆኖ እያለ በታሪክ የሚጠላትን በግዛት አንድነቷ የማያምንባትን አገር እንዲያስተዳድር ጊዜ ሰጥቶት ሃያ ሰባት ዓመታት በስልጣን ላይ የቆየ አገር አፍራሽ ሴረኛ ቡድን ነው፡፡በሀሰት ትርክት የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ለማፍረስ ተልዕኮ በመውሰድ ዕድሜ ልኩን ለፍቷል፣ እስከ ዕለተ ሞቱ እየለፋም ይገኛል።
ይህ የሀሰት ትርክት በአሸባሪው ሕወሓት የተፈበረከ ሳይሆን ጣሊያኖችም ሆነ ግብጻውያን ይከተሉት የነበረ ኢትዮጵያን የመከፋፈልና የማዳከም የቆየ የጠላት ስትራቴጂ ነው፡፡ የጠላት ውርስ አስቀጣዩ ሕወሓትም ህልውናውን ለማስቀጠል የጥላቻ ፖለቲካን ኢትዮጵያ ውስጥ መትከል አማራጭ አድርጓል፡፡ በተለይም የኢትዮጵያ አንድነት መሠረት ነው ብሎ የሚያስበውን አማራውን ከሌላው ኢትዮጵያ ጋር ተጋብቶ እና ተዋልዶ፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ባህል እና ወግ ተጋርቶ የኖረ ሳይሆን ሲጨቁን እና ሲበዘብዝ የኖረ በማስመሰል በሌላው ኢትዮጵያዊ በጥርጣሬ እንዲታይ በማድረግ የኢትዮጵያን አንድነት ሲሸረሽር ኖሯል፡፡
በአጠቃላይ የአሸባሪው ሕወሓት ጦርነት ለዓመታት ይከተለው የነበረው የነጣጥለህ እና ከፋፋለህ ግዛ መርህ አገር የማፍረስ ሴራውን እውን እንዲያደርግለት ታሳቢ ያደረገ የተልዕኮ ጦርነት ነው፡፡ ሕወሓት የተሳሳተ የአሸናፊነት ሥነ-ልቦና በሕዝብ ዘንድ በማስረጽ እና ከእውነታው ፍጹም የተቃረነ ዕይታ በተለይም በትግራይ ሕዝብ ላይ ባለፉት 27 ዓመታት ያለቅጥ ሲጭንበት ቆይቷል፡፡ ቡድኑ ከሚሰርቃቸውና ከሰረቃቸው ተራራ፣መሬት እና በአማራው ሕዝብ ዘንድ በነሐሴ ወር ከሚደረጉ ባህላዊ ክዋኔዎች ባለፈ ድልም እየሰረቀ የትግራይን ሕዝብ በሀሰት የድል ታሪክ ለእብሪት ዳርጓል፡፡ አፈ ጮሌዎቹ የሕወሓት መስራቾች ሁሉንም የትግል ውጤት ወይም ድል የራሳቸው በማስመሰል ለትግራይ ሕዝብ ለዘመናት በመተረክ በተዛባ የአሸናፊነት ስነ-ልቦና ሕዝቡን ዓላማ በሌለው ጦርነት እየማገዱት ይገኛሉ፡፡
ከዚህ በተጻራሪው አሸባሪው ሕወሓት መንበረ ስልጣኑን ከያዘ ጀምሮ ለሚፈልገው ኢትዮጵያን የማፍረስና ትግራይን እንደ አገር የመመሥረት የክህደት ዓላማ እንቅፋት ይሆነኛል ብሎ ለሚሰጋውና ጠላቴ ብሎ የሚያስበውን አማራው ተሸናፊነትን፣ አንገት ደፊነትን እና ተንበርካኪነትን ባህል እና ታሪኩ እንዲያደርግ ጨቋኝ፣ ነፍጠኛ እና ትምህክተኛ በማለት ተዋርዶ እና ተሸማቆ በአገሩ በነጻነት ተንቀሳቅሶ እንዳይኖር ጥሯል፡፡
ኢትዮጵያውያን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ታጥቆ የመጣውን ጣሊያን በጦርና በጎራዴ በማሸነፍ ጀግንነታቸውን ያስመሰከሩበትን የአዕምሮ የተዋጊነት ሥነ-ልቦናን ጭምር ለመስለብ ያላደረገው ጥረት የለም፡፡ ሕወሓት አማራው መሳሪያ ቀርቶ የጅንፎ ሽመል እንኳን እንዳይዝ በመከልከል፣ አምዕሮውም ትጥቅ እንዲፈታ በማድረግ የአማራውን አይበገሬነት፣ የተዋጊነት እና የአርበኝነት ስሜት ለመግደል ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡
ስለሆነም ከውጭ ኃያላኑ ጋር የሚደረገው የውክልና ጦርነት በአጭር ጊዜ በድል ለማጠናቀቅ ከታሪካችን ልምድ መውሰድ ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የአፍሪካ ቀንድ የጂኦ ፖለቲካ ሁኔታም በጣም ውስብስብ ከመሆኑም በላይ ኃያላኑ አገራት አካባቢውን ለመቀራመት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ውስጥ የገቡበት መሆኑ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ለአብነት ያህል ጅቡቲ ላይ ወደ ሰባት የአውሮፓ አገራት ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ መስርተዋል፡፡ ኃያላኑ የአውሮፓ አገራት ወደ አፍሪካ ቀንድ ያስፋፋበት ምክንያት ምንድንነው ተብሎ ሲታይ አሸባሪን በተለይ የባህር ላይ ውንብድናን ለመከላከል ነው ቢሉም ትክክለኛ ዓላማው ይህ እንዳልሆነ አሸባሪውን ሕወሓትን ደግፈው በኢትዮጵያ ላይ ከሚያደርጉት ሴራ መታዘብ ይቻላል፡፡
እውነተኛው ዓላማቸው የአፍሪካ ቀንድ አገራትን በቀኝ ግዛት መያዝ ስለመሆኑ መገመገት ይቻላል፡፡ የአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ወታደራዊ የጦር ማዘዣ ጣቢያ ያላቸው የውጭ ኃይሎች ከኢትዮጵያ በስተቀር ሌሎች የአፍሪካ ቀንድ አገራት አገራቸውን ተቀራምተዋል ብዬ አምናለሁ፡፡
ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት የቅኝ ግዛት ዘመንን የሚያስታውስ ነው፡፡ በቅኝ ግዛት ዘመን ኢትዮጵያ ዙሪያዋን በአውሮፓ ተከብባ ነበር፡፡ ኢትዮጵያን በቀጥታ በቅኝ ግዛትነት መያዝ ያልቻሉት ኃያላኑ አገራት እየተከተሉት ያለው ስልት ርዕዮታቸውን ሊያስፈጽም የሚችል ተላላኪ ስርዓት ማኖር ነው፡፡ ለዚህም የትሮይ ፈረስ ሆኖ የሚያገለግላቸውን እየሞተ ያለውን የአሸባሪው ሕወሓት የሽብር ኃይል ጉልበት በመስጠት ወደ ስልጣን እንዲመለስ ማድረግ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር ግልጽ ጦርነት ውስጥ ትግባ እንጂ ከጀርባ ከብዙ ኃያላት ጋር እየተደረገ ያለውን ጦርነት መመከት የሁሉም ታሪካዊ ኃላፊነት ነው፡፡
በምንባለ ሞላ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17 ቀን 2014 ዓ.ም