አዲስ አበባ፡- ለግንባታው ዘርፉ የግብዓት ግዥ በዓመት የሚወጣውን 160 ቢሊዮን ብር ለመቀነስ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር አርጋው አሻ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በየጊዜው እየዘመነ መምጣቱን ተከትሎ የግብዓት ግዥው በተመሳሳይ ልክ እያሻቀበ ነው፡፡
ወጪውንም ለመቀነስ ከዩኒቨርሲቲ የምርምር ማዕከላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ለአንድ ህንፃ ግንባታ ከአንድ ሺህ በላይ ግብዓቶችን መጠቀም ግድ በሆነበት በአሁኑ ወቅት እነዚህ ግብዓቶች አብዛኞቹ ከውጭ የሚገቡ በመሆናቸው አገሪቱ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚገመት ከፍተኛ የውጭ ምንዘሪ እያወጣች እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡ ዶክተር አርጋው እንደሚሉት የዩኒቨርሲቲኢንዱስትሪዎች ትስስር በጥናትና ምርምር ታግዞ እንዲጎለብት ማድረግ ዘርፉን ከማዘመኑ ባለፈ አገሪቱን ከአላስፈላጊ የግብዓት ግዥ ወጪየሚታደጋት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዕድገት ሲታሰብ ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶች በምርምር እየታገዙ በአገር ውስጥ ምርቶች የሚተኩበት ሥልት መቀየስ እንዳለበት አመልክተው ለዚህም ዩኒቨርሲቲዎች በቅርበት በአካባቢው ያለውን ግብዓት ፣ የሰው ኃይል እና ቁሳቁስ መጠቀም የሚያስችል ጥናትና ምርምር ሊያካሂዱ ይገባል ብለዋል፡፡
ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶችን በአገር በቀል ቴክኖሎጂዎች እንዲተኩ ማድረግ የዩኒቨርሲቲዎች ቀዳሚ ሚና መሆን አለበት፡፡ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ከሚጠቀምበት የግብዓት ጥራት ችግር፣የባለሙያው የክህሎት ክፍተት እና መሰል ጉዳዮች ጋር ተያይዞ በመገንባት ላይ የሚገኙ ሕንጻዎች ሲደረመሱ ማየት በአገሪቱ እየተለመደ መምጣቱም ዶክተር አርጋው ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 28/2011
በሙሀመድ ሁሴን