አዲስ አበባ:- በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ መሪነት ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና ፕሬዚዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ መሐመድ ትናንት በናይሮቢ ባካሄዱት ውይይት ኬንያና ሶማሊያ ተባብረው በሰላም ለመስራት ተስማሙ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ድረ ገጽ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በሁለቱ ሀገራት ለተፈጠረው ውጥረት መንስኤ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
በውይይቱም ሁለቱም ወገኖች ተባብረው ለሰላም ለመሥራት እና ውጥረቱን ለመቀነስ የሚያስችሉ እርምጃዎችን እንደሚወስዱ ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በሶማሊያና ኬንያ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት እንደ ምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ሊቀ መንበርነታቸው በቅርበት በመከታተል ወደ እርቅ የሚመጡበትን መላ እያፈላለጉ እንደነበር ተጠቅሷል።
የኬንያው ፕሬዚዳንት ኬንያታና የሶማሊያው አብዱላሂ መሐመድ ወደ ኢትዮጵያ ለይፋዊ ጉብኝት በዘለቁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከሁለቱም መሪዎች ጋር ባደረጉት ምክክር፤ ይህንን የኬንያና የሶማሊያ መሪዎች የፊት ለፊት ውይይት ለማመቻቸት ወስነው እንደነበር ጽህፈት ቤቱ አስታውሷል።
በተመሳሳይ ባለፈው ማክሰኞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከሶማሊያ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ ጋር በቀጣናው ሰላምና ደህንነት እንዲሁምበኢኮኖሚያዊ ትስስር ላይ ውይይት አድርገዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ከውይይቱ በኋላ እንደገለጹት፤ ሁለቱ መሪዎች በቀጣናው ሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂደዋል።
ከዚህ በፊት የተጀመሩ የሁለትዮሽና ቀጣናዊ ግንኙነቶችን ለማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም መክረዋል። ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ወደብ ማልማት መጠቀም በምትችልበትንና በአጠቃላይ በምጣኔ ሀብት ትስስር ዙሪያ መሪዎቹ ሰፊ ምክክር ማድረጋቸውን ገልጸዋል። እንዲሁም ከሶማሊላንድ አስተዳደር ጋር ባለው ግንኙነት ላይ ውይይትማካሄዳቸውን ተናግረዋል።
የቀጣናውን ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር ለማጎልበት የኢትዮጵያና የሶማሊያ ግንኙነት ወሳኝ እንደሆነ የገለጹት አቶ ንጉሱ፤ የሁለቱ አገሮችን መልካም ግንኙነት በማጎልበት የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ለማለፍ በጋራ ለመስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መሪዎቹ በሰፊው መምከራቸውን ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ቀን ጀምሮ ከኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ከኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂና ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ጋር በቀጣናው ሰላምና ደህንነት እንዲሁም የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸው ከኢዜአ የአገኘነው መረጃ ያመለክታል።
አዲስ ዘመን የካቲት 28/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር