አዲስ አበባ፡- ህገ መንግሥት የአንድ አገር የበላይ መተዳደሪያ፣ ሕዝብና መንግሥት በጋራ የሚመሩበት የጋራ ሰነድ በመሆኑ በሁሉም ዜጎች ዘንድ እኩል ቅቡልነት ሊኖረው እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን ይስማማሉ፡፡ይህን እንዴት መፍጠር ይቻላል? ከዚህ አኳያ አሁን በሥራ ላይ ያለው የኢፌዴሪህገ መንግሥት የተለያዩ አካላት ጎራ ከፍለው የሚከራከሩበትና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች እኩል የማይስማሙበት መሆኑ የቅቡልነት ችግር ያለበት መሆኑን በጉዳዩ ላይ የጻፉና ጥናት ያደረጉ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡
ከእነዚህ ምሁራን መካከል « ሪፎርም ወይስ አብዮት፡- ነጻነት፣ ፍትህ፣ ልማት» በሚል ርዕስ በተቋማትና በህገ መንግሥት ሪፎርም ላይ የሚያጠነጥን መጽሐፍ በ2009 ዓ.ም ለንባብ ያበቁት ጠበቃና የህግ አማካሪው አቶ ሞላ ዘገዬ ይገኙበታል፡፡
አቶ ሞላ «የህገ መንግሥት ሪፎርም ወቅታዊነት» በሚለው የመጽሐፋቸው ክፍል፤ «የዜጎችን መብት ለመጠበቅና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት የሚያግዙ በርካታ ድንጋጌዎች ቢኖሩትም ከብዙ አቅጣጫ ጥያቄ የሚነሳበትና የቅቡልነት ችግርያለበት ሰነድ መሆኑን መካድ አይቻልም» ይላሉ፡፡ እንደ ጸሐፊው ዕምነት ለዚህ የቅቡልነት ችግር መፈጠር ዋነኛው መንስኤ ሰነዱ የተዘጋጀበትና የጸደቀበት መንገድ ነው፡፡
ምክንያቱም የህገ መንግሥቱ ረቂቅ ሰነድ በተዘጋጀበት ወቅት ሕዝቡ አስተያየቱን አልሰጠበትም፤ በበቂ ሁኔታም አልመከረበትም፡፡ ያም ሆኖ በይዘት ረገድም ቢሆን ህገ መንግሥቱ የዜጎችን መብት ለመጠበቅና ዴሞክራ ሲያዊ ሥርዓትን በመገንባት በኩል በርካታ የሚደነቁ ድንጋጌዎች ቢኖሩትም ‹‹እንከን የለሽ›› የሚያስብል አለመሆኑንም አቶ ሞላ በመጽሐ ፋቸው ጠቁመዋል፡፡ የፖሊሲና የህገ መንግሥት አማካሪ እንዲሁም በህገ መንግሥት ዝግጅት ወቅት በአርቃቂነት የተሳተፉት ዶክተር ፋሲል ናሆም «እንከን የለሽ ሊባል የሚችል ህገ መንግሥት ከመለኮታዊ አካል የተሰጠ ካልሆነ በስተቀር ምድር ላይ ሊኖር አይችልም» ሲሉ ሃሳባቸውን ይሰነዝራሉ፡፡
ህገ መንግሥት በባህሪው በየዘመኑ ከሚኖረው የህብረተሰቡ የአስተሳሰብና አጠቃላይ የማህበረ ኢኮኖሚያዊ የዕድገት ደረጃ ጋር አብሮ እንዲጓዝ በሚያስችል ሁኔታ የሚቀረፅ መሆኑንም ነው ዶክተር ፋሲል ያመለከቱት፡፡ ከዚህ አኳያ የኢፌዴሪ ህገ መንግሥትም ይህን ጽንሰ ሃሳብ ይዞ የተቀረጸ በመሆኑ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ማሻሻያዎችን ለማድረግ የሚፈቅድ እንጂ ዝግ ሆኖ የተቀመጠ አይደለም፡፡ በይዘት በኩል እንደ ችግር ከሚነሱ ነጥቦች መካከልም በህዝቡ ውስጥ ክፍፍል የፈጠሩ፣ በፖለቲካ ልሂቃኑ መካከል በከፍተኛ ደረጃ የተራገቡና አጨቃጫቂ ሆነው የቀጠሉ የመሬትባለቤትነትና የብሔር ብሔረሰቦች መብት የመሳሰሉ አጀንዳዎች አሉ፡፡
ስለሆነም ህገ መንግሥቱ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተቀባይነት ያለውና ሁሉም አካላት የሚንከባከቡት የጋራ ቃል ኪዳን እንዲሆን ማሻሻል አማራጭ ይሆናል፡፡ለዚህም ሁሉንም አካላት በሂደቱ በማሳተፍና ኢትዮጵያውያን በበቂ ሁኔታ እንዲመክሩበት በማድረግ በጋራ እንዲፀድቅ ማድረግ ይገባል፡፡ ህገ መንግሥቱ ሲጸድቅ የህገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን አባል፣ የህገ መንግሥት ጉባዔ ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በበኩላቸው በአንዳንድ ወገኖች ‹‹ህገ መንግሥቱ የኢህአዴግ የፖለቲካ ማኒፌስቶ ግልባጭ ነው›› የሚለው አባባል ፍጹም ተሳሳተ ነው ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
«ምክንያቱም በህገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን አባልነት ከተመረጡ 29 ሰዎች ውስጥ ኢህአዴግን ወክለን የገባነው ሁለት ብቻ ነን፡- እኔና ዳዊት ዮሐንስ» ይላሉ፡፡ ቀሪዎቹ 27 አባላት በሽግግር ምክር ቤቱ ውስጥ ከተወከሉና ከሽግግር ምክር ቤቱ ውጭ ከነበሩ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ከተለያዩ የሙያ ማህበራት የተውጣጡ ናቸው፡፡ ይዘትን በተመለከተም ህገ መንግሥቱ ሲረቀቅ ጀምሮ እስካሁን ድረስ አጨቃጫቂ ሆነው የዘለቁ ጉዳዮች መኖራቸውን ዶክተር ነጋሶ አልደ በቁም፡፡
በህገ መንግሥቱ ውስጥ የአለመግባባት መንስኤ ሆነው ከቀጠሉ ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ የሪፐብሊኩን ሰንደቅ ዓላማ፣ የቋንቋና የማንነት ውክልና ጉዳዮች፣ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ፣ ህገ መንግሥትን የመተርጎም ስልጣን፣ የምርጫ ህግን የሚመለከቱት አንቀጾች ዋነኞቹ ናቸው፡ ፡ይህም ቢሆን ህገ መንግሥቱ በተዘጋጀበትናበጸደቀበት ወቅት በአንቀጾቹ ላይ ሰፊ ውይይትና ክርክር ተደርጎ በአብላጫ ድምፅ የጸደቀ መሆኑን የሚያስታውሱት ዶክተር ነጋሶ «ያም ሆኖ እነዚህ አንቀጾች ዛሬም ድረስ በህገ መንግሥቱ ላይ የጋራ መግባባት እንዳይኖር እንቅፋት ሆነው መቀጠላቸውን ያመላክታሉ፡፡
ስለሆነም የአለመግባባትና የልዩነት መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን የያዙ አንቀጾችን እንደገና ለህዝብ ውይይት ማቅረብና ህዝብ የፈለገውን እንዲመርጥ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ መወያየት ብቻ ሳይሆን ውሳኔ ህዝብ እንዲካሄድባቸው ማድረግም ይገባል፡፡ ይህም ህገ መንግሥቱ ሁሉም አካላት የሚያምኑትና እኩል የሚቀበሉት እንዲሆን ያስችላል በማለት መፍትሔውን ያስቀምጣሉ፡፡ ስለሆነም በአሁኑ ሰዓት የተፈጠረውን አገራዊ ለውጥ ተከትሎ በርካታ መልካም ውጤቶች እየታዩ ቢሆንም በሌላ በኩል እዚህም እዚያም የሚታዩ መንገራገጮች መከሰታቸው አልቀረም፡ ፡ ይህም አገሪቱ አጠቃላይ በከፍተኛ የለውጥ እንቅስቃሴ መሆኗን የሚያመላክት መሆኑን የሚገልጹት ዶክተር ፋሲል፣ «ስለሆነም ለውጡ በህገ መንግሥቱ ሊደገፍና ህገ መንግሥቱም አብዛኛው ህዝብ ያመነበትን ሃሳብ ሥራ ላይ የሚያውል እንዲሆን ያስፈልጋል» ይላሉ፡፡
ዶክተር ፋሲል፣ ይህን ለማድረግም ሦስት መሰረታዊ መንገዶች መኖራቸውን ይጠቁማሉ፡፡ እነዚህም ህዝቡ ምን ይፈልጋል? የሚለውን ማወቅ፤ የኢትዮጵያን ታሪክ በደንብ መመርመር ማጥናትና ማወቅ እንዲሁም የህዝቡን ራዕይ ምን እንደሆነ መረዳትና ዛሬ የት ላይ ነው ያለነው፣ ነገስ ወደየት መሄድ ነው የምንፈልገው? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ ያስፈልጋል ሲሉ ያብራራሉ፡፡ ከዚያም «ህገ መንግሥቱ መሻሻል ይገባዋል ወይ? ምንም የሚሻሻል ነገር የለውም፤ ወይንም ከነጭራሹ መለወጥ አለበት?» የሚለው በጥንቃቄ ከተጠና በኋላ ነው ወደ ህገ መንግሥት ማሻሻል ሥራ መገባት አለበት በማለት ያብራራሉ፡፡ ይህንን ሥራ መስራት የሚገባውን አካል በተመለከተም ራሱን የቻለ ህገ መንግሥት ኮሚሽን ማቋቋም የሚቻል መሆኑን ዶክተር ፋሲል ይመክራሉ፡፡
ዶክተር ነጋሶ ፣ የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ከመጽደቁ በፊት ህዝቡን ለማሳተፍ 73 ጥያቄዎች ተዘጋጅተው በመላ አገሪቱ በሚገኙ 23ሺ ቀበሌዎች መሰራጨታቸውንና ህዝብ እንዲወያይባቸው መደረጉን ያስታውሳሉ፡፡ ሆኖም በጥያቄዎች ላይ የተወያየው ህዝብ ብዛት ምን ያህል እንደሆነ በትክክል ስለማይታወቅ በረቂቁ ላይ ሃሳብ የሰጠው ህዝብ በቂ ላይሆን ይችላል የሚለው በተወሰነ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ሃሳብ መሆኑን ያመላክታሉ፡፡ ከህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም ጀምሮ የአገሪቱ የበላይ ህግ ሆኖ እያገለገለ የሚገኘው የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት በአንድ በኩል አድናቆትን በሌላ ወገን ደግሞ ተቃውሞን እያስተናገደ አሁን ላይ ደርሷል፡፡
ህገ መንግሥት የሁሉም ነገር መሰረት ነውና የጋራ እንዲሆን መስራት ያስፈልጋል፡፡ አሁን እየታየ ያለው ለውጥም መልካም ፍሬ አፍርቶ በአገሪቱ ሁሉንም ዜጎች እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ ፍትሐዊ ሥርዓት ዕውን ይሆን ዘንድ ሁሉም ዜጎች እኩል የሚቀበሉትና የሚጠበቁበት አንድ የጋራ የዜጎች የቃል ኪዳን ሰነድ መፍጠር ወቅቱን የሚዋጅ ያደርገዋል፡፡ በአገሪቱና በዜጎቿ መጻኢ ዕድል ላይ የሚኖረው አንድምታም ከሁሉም የላቀ ነው፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 28/2011
በይበል ካሳ