ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት በኋላ ሁሉም የአውሮፓ አገሮች ኢኮኖሚ ተንኮታኩቶ ነበር:: በዚህም ምክንያት በሆላንድ አገር ሕፃናት ከረሃብ የተነሳ ምግብ ከቆሻሻ ገንዳ ላይ ይመገቡ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስታውሳሉ። በወቅቱ የአውሮፓ አገሮች የወይን ሐይቅና የቅቤ ተራራ የሚባሉ አገሮችም ነበሩ::
በጦርነቱ ምክንያት አስራ አምስት የአውሮፓ አገሮች ኢኮኖሚያቸው በከፍተኛ ሁኔታ የተንኮታኮተ ሲሆን ፤እነዚህም ውስጥ በአሁኑ ወቅት በኢኮኖሚ እድገታቸው በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት መካከል ጀርመን፣ እንግሊዝና ፈረንሳይ ይገኙበታል ::እነዚህ አገሮች ከኢኮኖሚ ውድቀቱ እንዲያገግሙ የአሜሪካ ድርሻ ከፍ ያለ ነበር::
የነዚህን አገሮች ኢኮኖሚ የታደጉ እውነታ በወቅቱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ የነበሩት ጆርጅ ማርሻል እ.ኤ.አ. ጁን 5 ቀን 1947 በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በመገኘት ባቀረቡት ሀሳብ መሠረት “ማርሻል ፕላን“ እየተባለ በሚጠራው መርሐ ግብር ተግባራዊ መሆን ጀመረ። እ.ኤ.አ. በ1948 ተግባራዊ በሆነው መልሶ ግንባታ አሜሪካ 15 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የገንዘብ እርዳታ አድርጋለች:: በዚህ የዕርዳታ መርሐ ግብር የምዕራብ አውሮፓ አገሮች የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲነቃቃ ተደርጓል::
የማርሻል ፕላን መርሐ ግብር ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት በኋላ ለምዕራብ አውሮፓ አገራት የኢኮኖሚ ዕድገት ሞተር መሆን ችሏል :: በመርሐ ግብሩ ኦስትሪያ፣ ቤልጂየም ፣ዴኒማርክ፣ ፈረንሳይ፣ ምዕራብ ጀርመን፣እንግሊዝ፣ ግሪክ ፣አይስላንድ ፣ጣሊያን፣ ሉክዘበርግ ፣ ኔዘርላንድስ ፣ ኖርዌይ ፣ስዊድን ፣ሲዊዘላንድ እና ቱርክ ተጠቃሚ ሆነዋል ::አገራቱ በመርሐ ግብሩ አማካኝነት ከአሜሪካ ያገኙትን እርዳታ በመጠቀም በጦርነቱ ምክንያት ከደረሰባቸው የኢኮኖሚ ውድቀት አገግመው ዛሬ በኢኮኖሚና በፖለቲካ ኃያል አገራት ተርታ መሰለፍ ችለዋል::
እኛስ አገራችንን እንዴት መልሰን መገንባትና ማልማት አለብን የአገራችን ኢኮኖሚ ከጦርነቱ በፊትም ቢሆን በሁለት እግሩ ያልቆመና ወደፊት ለመሄድ በመንገዳገድ ላይ እንደነበር ይታወሳል:: ተገደን የገባንበት ጦርነት “በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ’’ አይነት ሆኗል:: ደንባራ የነበረችው በቅሎ ቃጭል ሲጨመርባት ምን ልትሆን እንደምትችል ለመገመት አይከብድም:: ኢኮኖሚያችንም ቀድሞውንም ቢሆን ፉት ቢሉት ጭልጥ ዓይነት ነበር ::
መንግሥት የግብርናውን የኢኮኖሚ ዘርፍ ለማዘመን እያደረገ ያለው ከፍተኛ ጥረት ቢኖርም ፣ አገሪቱ ዛሬም በሞፈርና ቀንበር፤ በሰውና በእንስሳት ጉልበት እያረሰች መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ለመመገብ የማያስችል ደረጃ ላይ የምትገኝ ፤በኢንዱስትሪም ቢሆን ኋላቀር ከሚባሉት የአፍሪካ አገሮች ተርታ የምትሰለፍ ነች::
አብዛኛዎቹ የሰሜን ኢትዮጵያ ክፍሎችም ከጦርነቱ በፊት ረሃብና ቸነፈር የሚያጠቃቸው፤ በሴፍቲኔትና በሌሎች ፕሮግራሞች የታቀፉ ናቸው :: በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍሎችም ያለው እውነታ ከዚሁ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው ::
በተለይም በቆላማው አካባቢ የሚኖሩት አርብቶ አደሮች የዝናብ ወቅት ሳይዘንብ ከዘለላቸው እንስሳቶች ለእልቂት መዳረጋቸው የተለመደ ነው ። በአሁኑ ጊዜ ከተፈጥሮ አደጋ ባልተናነሰ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በጦርነት አማካይነት ሰላማዊ ሰዎች ከሰፈራቸው ተሰደው ችግር ላይ ወድቀው ይገኛሉ:: እንዲሁም በአንዳንድ ደቡባዊ የአገራችን ክፍል ለምሳሌ በቦረና ድርቅ ተከስቶ የአካባቢው ነዋሪዎች ችግር ውስጥ ይገኛሉ ::
የኢትዮጵያ ችግር በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ጦርነት የመጣ ድህነት ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ ኋላ ቀርነት ያመጣው ጣጣም ጭምር ነው:: ዋናው ጥያቄ ከዚህ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮ ያመጣውን የኢኮኖሚ ቀውስና ኋላቀርነት ለአንዴና ለመጨረሻ እንዴት እንወጣለን የሚለው ነው::ለዚህ ችግር መፍትሄ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን የመጀመሪያው ይሆናል::
ሰላምና መረጋጋት የሚመጣው በሁሉም ኢትዮጵያውያን መካከል መግባባትና መተማመን ሲኖር ብቻ እንደሆነ ይታመናል ::ሁለተኛው ቁርጠኛ የመንግሥት የኢኮኖሚ የለውጥ/ሪፎርም ፖሊሲ ድጋፍና የሕዝብ ተነሳሽነት ነው:: ይህ ደግሞ ፖለቲካዊ ሥራ ሲሆን ፖለቲካና ኢኮኖሚ መነጣጠል ስለማይችሉ ሁለቱንም ማጣጣምና አንድ ላይ ማስኬድ የመንግሥትና የሁላችንም ድርሻ ይሆናል::
የኢኮኖሚ መልሶ ግንባታና ልማት ሁለት መሠረታዊ ነገሮችን ይፈልጋል:: አንደኛው ገንዘብ ሲሆን ሁለተኛው የተገኘውን ገንዘብ በአግባቡ ኢኮኖሚን በሚቀይሩ የኢኮኖሚ መርሐግብሮችና ፕሮጀክቶች ላይ ስለ መዋላቸው እርግጠኛ መሆንን ይጠይቃል :: ገንዘቡ በሙሰኞች እጅ እንዳይገባ በመንግሥት ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ተደርጎበት ለታቀደለት ዓላማ ብቻ እንዲውል ማድረግ ያስፈልጋል:: ጦርነቱ ሊፈጥር በሚችለው ጫናዎች ምክንያትም ለመልሶ ግንባታ የሚሰበሰብ ገንዘብ ጮሌዎች እጅ እንዳይገባ ብርቱ ጥንቃቄ ማደረግ ይገባል ::
ለመልሶ ግንባታ የሚውለውን ገንዘብ አንድም የአገር ውስጥ የውዴታ ግዴታ መዋጮዎችን ከመጣል መሰብሰብ የሚቻል ሲሆን ፤ይኸውም መቶ ሚሊዮን ሕዝብ አስር አስር ብር ቢያዋጣ አንድ ቢሊዮን ብር ይኖረናል:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ግማሹ ብቻ በአማካይ አንድ አንድ ሺህ ብር ቢያዋጣ ሃምሳ ቢሊዮን ብር ይኖረናል:: እንዲሁም ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በትንሹ መቶ መቶ ዶላር ቢለግሱ በትንሹ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር መሰብሰብ ይቻላል::
ሌላው የገንዘብ ምንጭ ሊሆን የሚችለው ከሽብርተኛው የትህነግ መሪዎች ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ሽያጭ ሊገኝ የሚችለው ገቢ ነው:: ከዚህም ስሌት በተጨማሪ ወዳጅ አገሮችም ለኢኮኖሚ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች ድጋፍ ካደረጉልን ከችግር አፈትልከን የማንወጣበት ምንም ምክንያት አይኖርም::
የምናገኘውን የእርዳታ ገንዘብ ከወዲሁ ውጤታማ የሆኑ ፕሮጀክቶችን ቀርፀን ካልተንቀሳቀስን ለመልሶ ግንባታው በተለያየ መንገድ የሚሰበሰበውን ሀብት በዕለታዊ ሰብዓዊ የፍጆታ ቁሳቁስ ላይ አውለን ልንወጣው በማንችል የችግር የአዙሪት ውስጥ እንዳንገባ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል::
ለዚህም በቀላሉ መልማት የሚችሉ የኢኮኖሚ ዘርፎችን በመለየት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን በቅደም ተከተል ማልማት ይኖርብናል:: በተለይም በቀላሉ በምግብ እህል ራሳችንን በምንችልበት የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርገን ከሠራንና መንግሥትም በጀመረው የበጋ ስንዴ በመስኖ የማልማት ሥራ ከቀጠለ በመጀመሪያ በምግብ እህል ራሳችንን እንችላለን::ይህም ወደ ተቀናጀ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለመሸጋገር የምናደርገውን ጉዞ ቀላል ያደርግልናል ::
አንዳንድ ምዕራባውያን አገሮች በምግብ ራስን አለመቻላችንን በመገንዘብና ረሀባችንን መሠረት በማድረግ ኢኮኖሚያችንና ፖለቲካችንን ለመዘወር እጃቸውን እንዳያስገቡ ጥንቃቄ ማድረግ ፤ይህም ለሌላ ዙር ቀውስ ስለሚዳርገን በጥንቃቄ መራመድ ይኖርብናል::
ከመልሶ ግንባታና ልማት ጎን ለጎን መሠረታዊ የኢኮኖሚ ልማት ሥራዎችንም ማካሄድ አለብን:: በአገራችን ከፍተኛ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች አሉ:: ለእነዚህ ሥራ ፈላጊዎች በባለሙያ የታገዘ የዶሮ እርባታ፣ የበግ እርባታ፣ የወተት ላም እርባታ፣ የንብ እርባታ፣የእንስሳት መኖ ዝግጅት፤ የደን ልማት ወዘተ ፕሮጀክቶችን ቀርፆና በተግባር መተርጎም ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ወሳኝ ይሆናል::
እያንዳንዱ ፕሮጀክቶች ከገበያ ጋር የሚተሳሰሩበ ትንና የሚመጋገቡትን መንገድ ከወዲሁ አስቦ መንቀሳቀስ ወሳኝ ነው:: የሚቀርቡ የፕሮጀክት ሀሳቦች በዝርዝርና በጥልቀት መጠናት አለባቸው:: እያንዳንዱ የፕሮጀክት ሀሳብ በቴክኒክና በፋይናንስ አዋጭ ስለመሆኑም በቂ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል::
ቀደም ሲል መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት በጥቃቅና አነስተኛ ኢንቨስትመንት ላደራጃቸው ወጣቶች ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ በሚፈለገው ደረጃ ውጤት አላመጣም:: አንዳንድ ወጣቶች ለማምረቻ የተሰጣቸውን ቦታ በሽያጭ ወይም በኪራይ ወደ ሌላ በማዛወር ያገኙትን ገንዘብ ሲያባክኑ ይስተዋላል:: ለወጣቱ የኢንቨስትመንት ገንዘብ መስጠት የሚደገፍ ቢሆንም ገንዘብ መስጠት ብቻ በቂ እንዳልሆነም ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል ::
ዋናው ጉዳይ ወጣቶችን ማደራጀት፤ማሰልጠን ወደ ሥራ ማሰማራት፣ ለስኬታቸው መከታተል፤ መቆጣጠርና በባለሙያ የምክር ድጋፍ መስጠት ነው:: በዚህ በኩል የነበረውን ክፍተት በአግባቡ በማጥናት ክፍተቱን መዝጋት የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራትም በቂ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል::
የመኖሪያ ከተሞችና መንደሮችን መልሶ ግንባታና ልማት በጦርነት የወደሙ ከተሞችና መንደሮች አብዛኛዎቹ ማስተር ፕላን የሌላቸውና የተገነቡበትም የግንባታ ግብዓት አፈርና እንጨት እንደነበረ ይታወቃል:: አሁንም በነበሩበት ሁኔታ መገንባት ሳይሆን በባለሙያ ማስተር ፕላን ተዘጋጅቶላቸውና ፕላን ወጥቶላቸው በሲቪል ምሕንድስና ሙያ ተመርቀው ሥራ በመፈለግ ላይ ያሉትን ወጣቶች አደራጅቶ ከልዩ ኃይል ከሚሊሺያዎችና ከተጎጂ ኅብረተሰቡ የተውጣጡና የተሳተፉበት ቡድን ተቋቁሞ ቀንና ሌሊት በመሥራት ግንባታዎች በፍጥነት እየተከናወኑ ለነዋሪዎች እንዲተላለፉ ለማድረግ ከወዲሁ መዘጋጀት ያስፈልጋል::
ለዚህ የሚውሉ የግንባታ ግብዓቶችን በዘመቻ መልክ በማምረት በመልሶ ግንባታዎች ወቅት የግብዓት እጥረት እንዳያጋጥም ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል ። ሥራዎችን በጠንካራ ዲሲፕሊን መምራት የሚያስችል ቁርጠኝነትም ማዳበር ወሳኝ ነው ።
በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው በበረንዳ፣ በታዛና በድንኳን ተጠልለው ለሚገኙ ዜጎች ለሦስትና ለአራት ወራት በነበሩበት ሁኔታ ሰብዓዊ የምግብ ድጋፍ ማድረግን ጨምሮ ፣እነዚህ ዜጐች ያጋጠማቸው ችግር ለዘለቄታው እስኪፈታ ድረስ እንዲታገሱ ማድረግ የሚያስችል የማሳመን ሥራም በራሱ ተግዳሮት እንደሚሆን መዘንጋት አይገባም ::
ነገሮች “የነቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ” እንዳይሆንብን መታገስና ወደ ተሻለ የመኖሪያ ቤትና አካባቢ መቀየር የግድ ይለናል::ተመልሶ ወደ ተሻሻለ አዲስ ከተማ ፤ የመኖሪያ ቤትና አካባቢ መግባት እንዲችሉ ማድረግ ተፈናቃዮች የጦርነት ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ አለመሆናቸውን ስለሚያሳይ ከስነልቦና ተጎጅነት በቀላሉ ሊያገግሙ ያስችላቸዋል ::
ሹርሹራ ከአዲስ አበባ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 15/2014