በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያውያን በላይ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ምዕራባውያን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እና የህልውና ጦርነት እጃቸውን አስገብተዋል፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ትኩረታቸውን ሁሉ ኢትዮጵያ ላይ አድርገዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት አባላት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለበርካታ ጊዜያት ኢትዮጵያን አጀንዳ በማድረግ ስብሰባ ተቀምጠው ተወያይተዋል። የአውሮፓ ፓርላማ፣ የአሜሪካ የሕግ አውጪ ምክር ቤት ወዘተ… በኢትዮጵያ ላይ ፖለቲካዊ ጫና ለማድረግ እና ኢኮኖሚያዊ ማዕቀብ ለመጣል ብዙ ሞክረዋል፡፡ደክመዋል፡፡
ስለምን ይህን ያህል ስለ ኢትዮጵያውያን/ኢትዮጵያ ተጨነቁ? አሁን ላይ ያለው የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፀጥታ ሁኔታ ከኢትዮጵያውያን አቅም በላይ ነውን? የጎረቤት አገራት ማለትም የሶማሊያ፣ ሱዳን ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ ከኢትዮጵያ አንፃር እንዴት የምዕራባውያኑን የዜና አውታሮች ቀልብ መሳብ አቃተው? የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ትኩረት ለምን ተነፈገው? የሚሉ መሰል ጥያቄዎችን መጠየቅ ከአንድ ለእናት አገሩ ከሚያስብ ንቁ ዜጋ የሚጠበቅ ነው።
ስለእውነት እንነጋገር ከተባለ እነዚህ ምዕራባውያን አገራት በስንት ውጣ ውረድ በረሀውን እና ባህሩን አቋርጠው ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥገኝነትን ለሚጠይቁ ኢትዮጵያውያን/አፍሪቃውያን ይህን ያህል የሚንሰፈሰፍ አንጀት አላቸውን?
እንደእኔ እምነት እና ግንዛቤ መሠረት የትኛውም ምዕራባዊ አገር ስለ ጥቁር ሕዝብ ሕይወት እምብዛም ግድ የሚሰጠው አይደለም። ሰብአዊነት የወቅቱ የምዕራባውያን በሉአላዊ አገራት የውስጥ ፖለቲካ ጣልቃ ለመግባት የሚጠቀሙበት ዓይነተኛ መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
በምዕራቡ ዓለም አንድ የተለመደ አባባል አለ ‹‹There is no such thing as a free lunch›› ይላሉ። ይህ ማለት ያለ አንዳች ምክንያት የሚገኝ ጥቅም የለም እንደማለት ነው። ስለሆነም ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ ይህን ያህል ርብርብ የሚያደርጉት ከኢትዮጵያ ስለሚገኘው ጥቅም ታሳቢ በማድረግ ብቻ ነው።
ከኢትዮጵያ የሚገኘውን ጆኦ-ፖለቲካዊ ትርፍ ያለ ገደብ ለማግኘትና ለመጠቀም በምዕራባውያን ቁጥጥር ስር የሚዘወር ተላላኪ፣ ምስለኔና አድኀሪ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ማንገሥ ከሁሉ የቀደመ ተግባራቸው ነው። በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ ውስጥ ይህንን የምዕራባውያን እኩይ ዓላማ ሲፈፅም እና ሲያስፈፅም የከረመ ታማኝ ድርጅት ሕወሓት/ኢህአዴግ ስለነበር ማንኛውንም ዋጋ ከፍለው ዳግም አቧራውን አራግፈው ወደ መንበረ መንግሥቱ ለመመለስ ይፈልጋሉ።
ኢትዮጵያ አገራችን በታሪክ ለምዕራባውያን ቀኖና እና ዶግማዎች የማትመች አገር መሆኗ ይታወቃል። ለዚህም አድዋ ሕያው ምስክር ነው። አድዋ የነጮችን ትምክህት የሰበረ፣ ለመላው ጥቁር ሕዝብ የነፃነትን ብርሃን የፈነጠቀ፣ ኢትዮጵያኒዝም አብዮትን ለአፍሪቃ ያበረከተ ታላቅ የአሸናፊነት አርማ ነው።
ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ ላይ ተሞክሮ ስኬታማ የሆነ ዶግማ ሁሉ በቀላሉ በቀሪዎቹ አፍሪቃ አገራት ላይ ውጤታማ እንደሚሆን ጠንቅቀው ያውቃሉ። በመሆኑም አገራችን ኢትዮጵያን ለማዳከም በሁሉም ዘርፍ ያለ የሌለ አቅማቸውን ተጠቅመው የዓላማቸው ተጋሪ የሆነውን ሕወሓትን ከተበተነበት የተንቤን በረሃ ጉድጓድ ውስጥ አውጥተው የኢትዮጵያውያን ስጋት እንዲሆን እያደረጉት ይገኛሉ።
በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ እየተፋለመች ያለችው የእናት ጡት ነካሽ ከሆኑ ባንዳዎች ብቻ ጋር ሳይሆን ዘመናዊ ቅኝ ግዛትን ለማስፋፋት ከሚሹ የዘመኑ ኢምፔሪያሊስቶች ጋር ጭምር ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ያኔ እንደ ትናንቱ እንደ አባቶቻችን ፋሽዝምን በአርበኝነት ተጋድሎ ተዋግተው አሸንፈው የነፃነትን ችቦ እንደለኮሱ ሁሉ፤ እኛ የዚህ ዘመን ትውልድ የተቃጣብንን ሁሉን አቀፍ ወረራ መክተን እንደ አባቶቻችን ደማቅ ታሪክ በዓለም መድረክ ላይ መፃፍ ይኖርብናል።
ባለፉት ጥቂት ወራት ከአሸባሪው ሕወሓት መሪዎች በግልፅ ለመረዳት እንደቻልነው ከቻሉ የኢትዮጵያን ማዕከላዊ መንግሥት ቁልፍ የመሪነት ቦታዎችን በሽግግር መንግሥት ስም በድጋሚ በመቆጣጠር ትግራይን መልሶ ማልማት እና የሚፈለገውን ሀብት ከኢትዮጵያ በአግባቡ ከመዘበሩ በኋላ ቀሪውን የኢትዮጵያ ግዛት እንደአስፈላጊነቱ በትኖ የራስ አገር መመስረት እንደ ዋና ግብ አድርገው ተነስተዋል።
ኢትዮጵያ አገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ እንደተባለው ፤ ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት የዘረፉ፣ ያዋረዱ ነውረኖች በይቅርታ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የዘረፋችሁትን ሀብት እና ንብረት ይዛችው እየበላችሁ በሰላም ኑሩ ተብለው ቢተውም አሻፈረኝ ብለው የኢትዮጵያ ዋልታና ማገር የሆነውን የአገር መከላከያ ሰራዊት በእኩለ ሌሊት ጨፍጭፈውታል።
ፍፁም አረመኔያዊ በሆነ መንገድ ለሰላም ዘብ እና ዋስትና በሆነው ወታደር ላይ ግፍ ፈጽመዋል። ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይተውም እንደተባለው ያኔ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ አባታችን መለስ ዜናዊ በጅራፍ እየገረፈ ሲገዛችሁ ኖሯል ዛሬ እኛ የመለስን ራዕይ አስፈፃሚዎች በጊንጥ እየገረፍን እንገዛችኋለን እያሉን ነው።
ይሁንና በወረራ ይዘዋቸው በቆዩባቸው ቦታዎችና አካባቢዎች ንጹሐንን በጅምላ መግደል፣ ሴቶችን በመንጋ መድፈር፣ የእምነት ቦታዎችን ማርከስ፣ የደረሱ ሰብሎችን ማውደም/መዝረፍ፣ ፋብሪካዎችን፣ ጤና ጣቢያ/ ሆስፒታሎችን፣ የመንግሥት የተቋማትን፣ የንግድ ቤቶችን፣ ባንኮችን በመዝረፍ እና በማውደማቸው የፈፀሙት ተግባርም በአንፃሩ እንገዛዋለን ብለው ለሚያስቡት ሕዝብ አገር ምንም ደንታ እንደሌላቸው በግልጽ የሚመሰክር ነው፡፡
በአሁኑ ወቅትም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የአሸባሪው እኩይ አላማና የጋላቢዎቹ ፍላጎት ጠንቅቆ ገብቶታል፡፡ ‹‹ከዚህ በላይ ቀልድ እና ፌዝ በአገር እና በሕዝብ ላይ የለም። የማንንም አምባገነን ከርስ ለመሙላት እና ከሰብዓዊነት ዝቅ ብለን ለመኖር አንችልም›› በሚል ቆርጦ ተነስቷል፡፡ ከእኛ በላይ ስለኢትዮጵያ የምትጨነቁት ለራሳችሁ እንደሆነ ገብቶናል እያላቸው ይገኛል፡፡
ሁሉን ጠንቅቆ የአገር ጠላት የሆነውን የሽብር ቡድኑን የገባበት በመግባት ድባቅ እየመታው ይገኛል፡፡ ጣሊያኖችን እምብኝ በማለት አሳፍረን ወደመጡበት እንደሸኘናቸው ሁሉ፤ በእጅ አዙር የዘመናዊ ቀኝ ግዛት ፍላጎቶቻቸውን ሊጭኑበት ያሰፈሰፉትን ምዕራባውያን አሳፍሮ ወደመጡበት ለመሸኘት እየተፋለመ ነው፡፡
አፓርታይድን ከደቡብ አፍሪቃ፣ የናዚን አስተሳሰብ ከጀርመን ለማጥፋት እንደተሞከረው ሁሉ የሕወሓትን አስተሳሰብ ከኢትዮጵያ ማጥፋት የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። የሕወሓት አስተሳሰብ ተሸካሚ የሆነ ማንኛውም ግለሰብ፣ ድርጅት ወይም ተቋም በሕግ አግባብ እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል። ድር ቢያብር አንበሳ ያስር እንደተባለው ኢትዮጵያውያን በአንድነት በጋራ መቆም ያለብን ጊዜው አሁን ነው! ኢትዮጵያ ታሸንፋለች።
#ሰላም ለኢትዮጵያ!
የአባቶቻችን እና የእናቶቻችን አገር ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር።
ብሩክ ለማ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15 ቀን 2014 ዓ.ም