ጋዜጠኛ፡- ‹‹የዓድዋ ጦርነት በማንና በማን መካከል የተካሄደ ጦርነት ነው?››
መላሽ፡- ‹‹በግብፅና በሐረር መካከል›› …
ጋዜጠኛ፡- ‹‹የውጫሌን ውል ከኢጣሊያ በኩል ሆኖ ሲያስፈፅም የነበረው ማን ነው?››
መላሽ፡- ‹‹ጋዳፊ›› …
ጋዜጠኛ፡- ‹‹ስለ ዓድዋ ጦርነት ድል የምታውቀውን ንገረኝ እስኪ?››
መላሽ፡- ‹‹ ስለዓድዋ ጦርነት ምንም አላውቅም›› …
ጋዜጠኛ፡- ‹‹የዓድዋ ድል የሚከበረው መቼ ነው?››
መላሽ፡- ‹‹ግንቦት 20›› …
ጋዜጠኛ፡- ‹‹ሚያዝያ 27 ቀን ተከብሮ የሚውለው ብሔራዊ በዓል ምን ይባላል?››
መላሽ፡- ‹‹መድኃኔዓለም››… ከላይ የተጠቀሱት ምልልሶች የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች በተለያዩ ጊዜያት በአዲስ አበባና በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ተዘዋውረው ለሕዝቡ ያቀረቧቸው ጥያቄዎችና ለጥያቄዎቹ የተሰጡ ምላሾች ናቸው፡፡ መቼም ለጥያቄዎቹ የተሰጡት ምላሾች ‹‹የመድኃኔዓለም ያለህ!›› የሚያስብሉ ናቸው፡፡ እንግዲህ እኛ እንዲህ ሆነናል … ስለ የካቲት 23 ስንጠየቅ ስለ ግንቦት 20 የምናወራ፣ ስለኮንት ፒየትሮ አንቶኒሊ ስንጠየቅ ስለ ጋዳፊ የምንመልስ … ብቻ እንዲህ ያለን ሆነናል!ምላሾቹን ከሰጡት መካከል አብዛኛዎቹ ሰዎች ወጣቶች መሆናቸው ከግምት ውስጥ ሲገባ ነገሩ በዝምታ መታለፍ የሚገባው እንዳልሆነና የሚያስጨንቅም፤ የሚያስፈራም እንደሆነ አመላካች ነው፡፡
ጥያቄው ‹‹ይህ ዓይነቱ ነገር ምን ያሳየናል? ምንስ ያስተምረናል?›› ነው፡ ፡ ለዚህ ‹‹ውርደት›› ብዙ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ቢችሉም ዋናው ግን ትውልዱ በቤተሰብ ክትትል ማጣትም ይሁን ተቋማዊ በሆነ ሴራና ጫና ታሪኩን እንዳያውቅ መደረጉ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ዓለም ያደነቀውንና ‹‹ልዩ/ብቸኛ›› ያስባለንን ዓድዋን ድል በደማቅ ቀለም ፃፉት፤ እኛ ግን ታሪኩን በጥቂቱ እንኳን ማወቅ ከበደን፡ ፡
‹‹… ስለዓድዋ ጦርነት ምንም አላውቅም›› ብሎ በኩራት መናገር ምንጩ ምን ይሆን?! በሰው ልጅ ታሪክ ከተፈፀሙት አሰቃቂ ቅጣቶች መካከል ስለሚመደበው፣ ከ82 ዓመታት በፊት አዲስ አበባ ላይ ስለተፈጸመውና ስለእናት አገር ሉዓላዊነት ሲባል ኢትዮጵያውያን ስለተቀበሉት የየካቲት 12 ጭፍጨፋ አምስት ገፅ ታሪክ እንኳን ለማገላበጥና ሰው ለመጠየቅ ለምን ሰነፍን?! ልጅ እንዲህ እስከሚሆን ድረስ ወላጅስ ምን ሥራ ይዞ ነበር?! መንግሥትስ ቢሆን ልማትና ዴሞክራሲ የሚባሉት ነገሮች ታሪኩንና ማንነቱን በማያውቅ ኅብረተሰብ ውስጥ ተንሰራፍተው ቢቀመጡ እንኳን ዘላቂነታቸው አስተማማኝ እንደማይሆን ጠፍቶት ነው? ታሪካቸውንና ማንነታቸውን ረስተው፤ ልማትና ብልፅግና ላይ ብቻ አተኩረው ሀብታም የሆኑ አገራት ዛሬ ‹‹ከሕዝብ ታሪክና መገለጫ (ባህል) ጋር ያልተጣጣመ ልማት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል›› ብለው ጉዟቸውን እየፈተሹ እንደሆነስ አልሰማንም? ጉዳዩን የበለጠ አስገራሚ የሚያደርገው ደግሞ፤ ጋዜጠኞችና በመገናኛ ብዙኃን ላይ ፕሮግራም የሚያቀርቡ ግለሰቦች በእነዚህ በዓላት ላይ የሚያቀርቧቸው መሰናዶዎች ከላይ ከተጠቀሱት ምላሾች ብዙም ያልራቁና ያልተሻሉ መሆናቸው ነው፡፡ እስኪ ጉዳዩን በምሳሌ እንመልከተው፤ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በየዓመቱ የካቲት 23 ቀን ሲከበር በዕለቱና በዚያው ሰሞን ተደጋገመው ከሚደመጡ አገላለጾች መካከል ‹‹በዓድዋ ጦርነት ወቅት ሁሉም የኢጣሊያ የጦር መሪዎች በኢትዮጵያውያን ተገድለዋል … ጦርነቱ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ተጠናቅቋል … ›› የሚሉት ሃሳቦች ይገኙበታል፡፡ እግረ መንገዴን ስህተታቸውን ጠቁሜ ልለፍ፤ ለግንዛቤ ማስጨበጫም ይሆናል ብዬ እገምታለሁ።
1ኛ. ከዋናዎቹ የኢጣሊያ ጦር አዛዦች መካከል ጀኔራል ጁሴፔ አሪሞንዲ እና ጀኔራል ቪቶሪዮ ዳቦርሚዳ በጦርነቱ ላይ የሞቱ ሲሆን፤ ጠቅላይ አዛዡ ጀኔራል ኦረስቴ ባራቲዬሪ ሸሽቶ አምልጧል፡፡ የመሐል ጦር አዛዡ ጀኔራል ማቴዮ አልቤርቶኒ ደግሞ በኢትዮጵያ ጦር ተማርኳል፡፡ 2ኛ. ጦርነቱ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ያለቀ ውጊያ አልነበረም፡፡ እንዲያውም የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም የተካሄደው የዓድዋ ጦርነት ሙሉ ቀን ሲካሄድ የዋለ የተጋጋለ ፍልሚያ እንደነበር የታሪክ ጸሐፍት መዝግበውታል፡፡ እንዲያው እኔ ለማሳያ ያህል እነዚህን ብቻ ጠቀስኩ እንጂ፤ ወጣቶቹ የሰጧቸው አስገራሚ/አስደንጋጭ ምላሾች፤ እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን ‹‹ባለሙያዎች›› የሚፈፅሟቸው ስህተቶች እነዚህ ብቻ አይደሉም፤ ብዙ ናቸው፡፡
የሕዝቡን (በተለይ የወጣቱን) ነገር እያየነው ነው፤ ጋዜጠኞቹ ከሕዝቡ የተሻሉ ሆነው ሕዝቡን ካላስተማሩና ስህተቱን ካላረሙ ጉዞው ከድጡ ወደ ማጡ ይሆናል፡፡ ሰሞኑን 73ኛ የልደት ቀናቸውን ያከበሩት ዝነኛውና አንጋፋው የፊልም ባለሙያ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ በአንድ ወቅት ‹‹… ትውልዱ ታሪኩን ቢያውቅ ኖሮ ይህን ሁሉ ስህተት አይሠራም ነበር …›› ብለው ነበር፡፡ ከዚህ ንግግር መገንዘብ የሚቻለው ታሪክ ማወቅ ‹‹ይህን ሠርቻለሁ›› እያሉ ለመኩራትና የበለጠ ስኬት ለማስመዝገብ፤ ለመነሳሳት ብቻ ሳይሆን ትናንት የተፈጸሙ ስህተቶችን ባለመድገምና ከስህተቶቹ በመማር ነገን የተሻለ ለማድረግ ዋስትና መሆኑን ነው።
እውቁ የፓን-አፍሪካኒዝም አቀንቃኙ ማርክስ ጋርቬይም ‹‹ታሪኩን የማያውቅ ሕዝብና ስር የሌለው ዛፍ አንድ ናቸው›› በማለት ታሪክን አለማወቅ ምን ያህል ከሰውነት ተራ ዝቅ እንደሚያደርግ አስገንዝቧል፡፡ በእርግጥ ከዓመታት በፊት ጀምሮ ትውልዱ በታሪክ ላይ ያለው ግንዛቤ ሲተችና ሲነቀፍ በተደጋጋሚ እንሰማለን፡፡
ትችቱና ነቀፋው ግን የሚፈለገውን ውጤት አምጥቷል የሚል እምነት የለኝም፡፡ እንዲያውም ፌስቡክ (Facebook) በስፋት መጠቀም ከተጀመረ ወዲህ የታሪክ ጉዳዮች ጥሩ የሚባል ሽፋን እያገኙ መምጣታቸውን መካድ አይቻልም፡፡ ይሁን እንጂ፤ ታሪክ እጅግ ተለዋዋጭና ለመቆጣጠር አስቸጋሪ በሆነው የፌስቡክ መድረክ ቀርቦ የትውልዱን ግንዛቤ ችግር ለመፍታት አስተማማኝ መፍትሄ ይሆናል ብሎ ማሰብ ታሪክ እንዳይታወቅና በሚገባ እንዳይመረመር ለማድረግ ሌላ ተጨማሪ አደጋ መጋበዝ ይሆናል።
ዛሬ የትናንት፤ ነገ ደግሞ የዛሬ ውጤቶች ናቸው። ታሪክ ማወቅ የሚያስፈልገው መልካም በሆነው የታሪክ ክስተት በመኩራት ለተሻለ ስኬት ለመነሳሳት ብቻ ሳይሆን፤ ከመጥፎው አጋጣሚ ትምህርት ለመውሰድና ያን መጥፎ አጋጣሚ ላለመድገምም ጭምር ነው፡፡ ትናንት በኢትዮጵያ ታሪክ የተፈፀሙትን ክስተቶች ብንወዳቸውም ብንጠላቸውም ከታሪክ አጋጣሚነታቸው/ክስተትነታቸው ልንፍቃቸው አንችልም። በተለያዩ ጊዜያት ለገባንባቸው ማኅበረኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች አንዱ ምክንያት ይኸው በታሪክ ላይ ያለን ደካማ ግንዛቤ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
በጎውን አጠንክሮ ማስቀጠሉ ይቅርና የትናንትናውን ስህተት ዛሬ እየደገምነው ከችግር አዙሪት መውጣት አቅቶናል፡፡ ‹‹ትናንት ይህ ስህተት እንደነበር አይተናል፤ ዛሬ መደገም የለበትም›› ያሉት ግን የትናንት ስህተታቸውን ባለመድገማቸው አቅጣጫቸው ወደፊት፤ ጉዟቸውም ወደተሻለ ደረጃ ሆኗል፡፡
ቀደምት ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጵያን ድንበር ለመድፈር ከሞከሩ ኃይሎች ጋር ተፋልመው፣ ዓድዋ ላይ ያን የመሰለ ትልቅና አኩሪ ድል አስመዝግበው፤ እንዲሁም ለአምስት ዓመታት ያህል በዱርና በበረሃ ታግለው ሉዓላዊነቷን ያስጠበቀች ነፃ አገር ያስረከቡን ለአገራቸውና ለክብራቸው ካላቸው የማይበገር ቀናኢነት በተጨማሪ፤ በወራሪ ኃይሎች በቅኝ ግዛት የተገዙ አገራት ሕዝቦች የተቀበሉት መከራ እንዳይገጥመንና እኛ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያዊነታችን ብቻ እንድንቆም ነበር፡፡ ዠግን ስለ ዓድዋ ጦርነትና ድል ስንጠየቅ/ሲጠይቁን ‹‹ስለ ዓድዋ ጦርነትና ድል ምንም አላውቅም›› ብለን ምላሽ ከሰጠን በቅኝ ግዛት ከተገዙትና ታሪካቸውንና ማንነታቸውን ከተነጠቁት አገራት ህዝቦች በምን ተሻልን?! (ማሳሰቢያ፡- በዚህ ጽሑፍ ‹‹ወጣቱ›› እያልኩ የወቀስኩበት ገለፃ በአገራቸው ታሪክ ላይ አሳሳቢ የሆነ የግንዛቤ ክፍተት ያለባቸውን በርካታ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን የመጠቆም ሙከራ እንጂ ሁሉንም ወጣት በአንድ ቅርጫት ውስጥ የማስቀመጥ ፍረጃ እንዳልሆነ ሊታወቅልኝ ይገባል!)
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2011
በአንተነህ ቸሬ