
የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) በየዓመቱ ከሚያከናውናቸው ስፖርታዊ ውድድሮች አንዱ የሠራተኞች ቀንን ምክንያት በማድረግ የሚካሄደው የሜይ ዴይ መታሰቢያ ውድድሮች ተጠቃሽ ናቸው። ሜይ ዴይ ዘንድሮ በኢትዮጵያ ለ50ኛ ጊዜ በዓለም ደግሞ ለ136ኛ ጊዜ በመጪው ሚያዝያ 23-2017 ዓም ይከበራል። ይህን የሠራተኛውን ቀን ለማክበር ከሚከናወኑ ተግባራት አንዱ ስፖርት ሲሆን፣ ለዚህም በተለያዩ ስፖርቶች የጥሎ ማለፍ ውድድሮች ሲካሄዱ ቆይተው የፍፃሜ ተፋላሚዎች ተለይተዋል።
የኢሰማኮ የውጪና የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ አቶ አያሌው አህመድ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ የዘንድሮው የሜይ ዴይ በዓል በሁለት መልኩ ይከበራል። አንዱ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ባሉባቸው ችግሮች ላይ የሚመክሩበትና ድምፃቸውን የሚያሰሙበት ነው። ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ የኢሰማኮ ሥራ አመራሮች፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የተለተያዩ ሀገር አቀፍ ተቋማት አዲስ አበባ ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ውይይት የሚያደርጉበት ነው። ሌላው ደግሞ በሠራተኞች መካከል የሚካሄደው ስፖርታዊ ውድድር ነው። ይህም ስፖርታዊ ውድድር በአዳማ ይካሄዳል።
በሠራተኛው መካከል የሚካሄዱት ስፖርታዊ ውድድሮች ለሜይ ዴይ ብቻ ሳይሆን የበጋ ወራት ውድድሮችና ሀገር አቀፍ ውድድሮች ተብለው ባለፉት ከሃምሳ ዓመታት በላይ ሲካሄዱ መቆየታቸውን ያስታወሱት አቶ አያሌው፣ ኢሰማኮ እነዚህን ውድድሮች በማስተባበርና በመምራት ሠራተኛው በስፖርት አማካኝነት የአካልና የአዕምሮ ዝግጁነት እንዲኖረው እየሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል። በዚህም በሥራው ላይ ንቁና ብቁ እንዲሆን ከማድረግ አኳያ ስፖርትን ከማንኛውም ተቋም በላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝ ገልፀዋል። በዚህም ስፖርት ለሠራተኛው የሚገናኝበት፣ የሚተዋወቅበትና ልምድ የሚለዋወጥበት መድረክ ነው ብለዋል።
አዳማ ላይ ለሚካሄደው የሠራተኛው የሜይ ዴይ መታሰቢያ የፍፃሜ ውድድር ለማለፍ በተለያዩ አካባቢዎች በተቋማት መካከል የጥሎ ማለፍ ውድድሮች ሲካሄዱ መቆየታቸውን የገለፁት አቶ አያሌው፣ በየስፖርት አይነቱ ከአዲስ አበባ የጥሎ ማለፍ አሸናፊ የሆኑ ተቋማት ሚያዝያ 23-2017 ዓ.ም አዳማ አካባቢ የጥሎ ማለፍ አሸናፊ ከሆኑ ተቋማት ጋር ለፍፃሜ ይጫወታሉ ብለዋል።
በዚህም መሠረት በሠራተኛው መካከል ከፍተኛ ፉክክር በሚታይበት እግር ኳስ ከትናንት በስቲያ በተካሄዱ ጨዋታዎች የሜይ ዴይ የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ ቡድኖች ተለይተዋል። መከላከያ ኮንስትራክሽን የኢትዮጵያ አየር መንገድን 2 ለ 1፣ አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 2ለ0 የረቱ ቡድኖች ናቸው። ሁለቱ ቡድኖች ሚያዝያ 20 በአዳማ በሚያደርጉት ጨዋታ አሸናፊ የሚሆነው በፍፃሜው ጨዋታ ከአዳማ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ አሸናፊ ከሚሆን ቡድን ጋር ለዋንጫ የሚፋለም ይሆናል።
በሌሎች የስፖርት አይነቶችም የፍፃሜ ተፋላሚ የሚሆኑ ቡድኖች ቀደም ብሎ የተለዩ ሲሆን፣ ማራኪ ፉክክር በሚደረግበት ቮሊቦል በወንዶች አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ከፋፋ ምግብ ጋር የፍፃሜ ጨዋታ ያደርጋሉ። ኢኮስኮና አዲስ አበባ የከተማ አውቶብስ ደግሞ ለደረጃ ይጫወታሉ። በተመሳሳይ በሴቶች ቮሊቦል አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ለፍፃሜው ጨዋታ የበቁ ቡድኖች ናቸው። ኢትዮ ቴሌኮምና መከላከያ ኮንስትራክሽን ደግሞ የደረጃው ተፋላሚ ሆነዋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክና ብርሃንና ሰላም ማተሚያ በወንዶች ጠረጴዛ ቴኒስ ለፍፃሜው ጨዋታ ሲበቁ፣ አዲስ አበባ የከተማ አውቶብስ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለደረጃ ይጫወታሉ። በሴቶች ደግሞ አዲስ አበባ የከተማ አውቶብስ ከኢትዮ ቴሌኮም ለዋንጫ ሲጫወቱ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከብርሃንና ሰላም ማተሚያ ለደረጃ ይፎካከራሉ።
በወንዶች የዳርት ውድድር መከላከያ ኮንስትራክሽን ከኢትዮ ቴሌኮም የዋንጫ ተፎካካሪ መሆናቸውን ሲያረጋግጡ፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ከፋፋ ምግብ ለደረጃ ይጫወታሉ። በተመሳሳይ በሴቶች አዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ ከብርሃንና ሰላም ማተሚያ ለዋንጫ፣ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ከኢትዮ ቴሌኮም ለደረጃ ይጫወታሉ።
በከረንቦላ ውድድር ኢኮስኮ ከብርሃንና ሰላም ለዋንጫ መጫወታቸውን ሲያረጋግጡ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ እንደፈጸመ አረጋግጧል። በዳማ የፍፃሜ ጨዋታ ደግሞ አዲስ አበባ የከተማ አውቶብስ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ይገናኛሉ። የደረጃው ጨዋታ ደግሞ ብርሃንና ሰላም ማተሚያን ከፋፋ ምግብ አገናኝቷል። አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ሦስተኛ ሆኖ ባጠናቀቀበት የቼስ ውድድር ኢትዮ ቴሌኮምና አዲስ አበባ የከተማ አውቶብስ የፍፃሜው ተፎካካሪ ናቸው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2017 ዓ.ም